በህጋዊ መንገድ ነግደው ለማትረፍ የሚሠሩ ሐቀኛ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ በየአካባቢው ደግሞ በህገወጥነት ተጠምደው ህብረተሰቡን የሚያማርሩ አካላት መኖራቸውን በየጊዜው የምንታዘበው ጉዳይ ነው።በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ምርት በመደበቅ፤ ዋጋ በማናር እና ጥራት የሌለው ምርት በማቅረብ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ አካላት በተለያዩ ጊዜያት ነዋሪውን ለችግር ሲዳርጉ ይስተዋላል።
ችግሩን ለመቆጣጠርና የንግድ ስርዓቱን ለመምራት ደግሞ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊነቱን ወስዶ እየሠራ ይገኛል።እኛም በመዲናዋ ስላለው የንግድ ስርዓት፤ ስለሸማች ማህበራት እንቅስቃሴ፣ በምርት አቅርቦት እና ህገወጥነትን በመከላከል እንዲሁም ወቅትን ጠብቀው ስለሚወደዱ ምርቶች እና አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ ቁጥጥሮች በተመለከተ አንስተን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ ያለውን የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ምን ዓይነት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው?
አቶ መስፍን፦ እንደሀገር የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ታቅደው የሚከናወኑ ሥራዎች አሉ።የኑሮ ውድነቱ ችግር በመጀመሪያ ከአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ጋር የሚነሳ ነው።በሁለተኛነት የግብይት ስርዓታችን ለህገወጥነት የተጋለጠ በመሆኑ ነው።
በሦስተኛነት ደግሞ የገበያ መሰረተ ልማት በተለይ የዘመኑ የግብይት ማዕከላት የዘመኑ አለመሆናቸው ለህገወጥነት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።ይህም ምርቶች በሚፈለጉበት ቦታ እና ሰዓት እንዳይገኙም ተጽእኖ ስልሚያሳድር የኑሮ ውድነቱን በማባባስ ረገድ የእራሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል።እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በተለይ ከለውጡ በኋላ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ አቅርቦትን ለማሻሻል እና ምርትን ለማሳደግ እንዲሁም መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደሀገር የተከናወኑ ሥራዎች አሉ።
ለአብነት ስንዴ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሀገር ወጪ እናደርግ ነበር።የዓለም አቀፍ ገበያ እኛ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በዚህ ረገድ በሀገር ውስጥ በስፋት ተመርቷል።በከተማ ደረጃም ትኩረት ሰጥተን የሠራነው የምርት አቅርቦት አማራጮችን በማስፋት ላይ ነው።በተለያዩ የአዲስ አበባ አቅጣጫዎች ምርቶች በቀጥታ ከአምራቹ ወደገበያዎች እንዲገቡ ተደርጓል።በተጨማሪ ለቁጥጥር የማይመቹ የነበሩ የገበያ ቦታዎች ተሻሽለው እንዲገነቡ ተደርጓል።በዘመናዊ መልክ የተገነቡ የገበያ ማዕከላትም አሉ።ለአብነት በላፍቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከልን ማንሳት ይቻላል።
ቀድሞ ፒያሳ የነበረው የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ቦታ ለህገወጥነት የተጋለጠ እና የገበያ ዋጋ በአንድ ቦታ ተሰብስበው ውሳኔ የሚደረግበት ነበር።በጅምላ ዋጋ ይወሰናል፤ ከዚያም እዚያ አንድ ቦታ ላይ የተወሰነው ዋጋ በመላ ከተማው እንዲሰራጭ ይደረግ የነበረበት እና ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚዘውሩት የገበያ ስርዓት እንደነበር ይታወቃል።አሁን በሀገራችን የፕሮጀክት አፈጻጸም ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣው የላፍቶ ገበያ ማዕከል ግንባታ በ21 ቀን ውስጥ በማጠናቀቅ ለቁጥጥር የሚመች ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
በማዕከሉ ህጋዊ ነጋዴዎች ብቻ እንዲገቡ የተደርጎ እያንዳንዱ የሚያስገቡበት ዋጋ እና የሚሸጡበትን በመቆጣጠር በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶች ለህብረተረሰቡ እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል።ስለዚህ ዋጋ በመነጋገር የሚወሰንበትን መንገድ ያስቀረ ሥራ ተከናውኗል።ማዕከሉ በአንድ ቢሊዮን ብር የተገነባ እና የእራሱ መኪና ማቆምያ ስፍራ ያለው ዘመናዊ ገበያ ማዕከል ሲሆን፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ተጨባጭ ውጤት የታየበት ማዕከል ሆኗል።
በተጨማሪ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ በህገወጥ መንገድ ዋጋ በማናር የግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የነበሩ ደላሎች እና ሌሎች ግለሰቦች ከንግድ ስርዓት እንዲወጡ ተደርጓል።በሌላ በኩል በከተማችን አንዱ ችግር የሚታይበት ግብይት የቁም እንስሳት እና ስጋ ንግድ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ችግሩን ለማቃለል ሦስት የግብይት ማዕከላት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።ለአብነት የካራ የእንስሳት ገበያ ማዕከል ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደሥራ እንዲገባ ተደርጓል።የግብይት ማዕከላትን በማስፋፋት ምርት በተገቢው መንገድ እንዲቀርብ እና የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግበት በማድረግ የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመቀነስ እና የዋጋ ንረትን ለመከላከል ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡– ቀደም ሲል የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ገበያን እንዲያረጋጉ የሚል መነሻ ቢኖራቸውም፤ ትርፍን መሰረት በማድረጋቸው ህብረተሰቡን የማገልገል ሚናቸውን ተነጥቀዋል የሚል ስሞታ ይቀርብባቸዋል፤ እነዚህን አካላት ለመከታተልና ለመቆጣጠር ምን እየሠተራ ነው?
አቶ መስፍን፡– ህብረት ሥራ ማህበራት ትርፍ ማግኘት ሳይሆን ለህብረተሰቡ አማራጭ የገበያ ምንጭ መፍጠር ዋና አላማቸው እንደሆነ መታወቅ አለበት።በዋናነት ባለቤትነታቸው ለየአካባቢው ነዋሪ ሲሆን፤ በተጨማሪ ተጠቃሚ የሚያደርጉትም ውስጣቸው ተደራጅተው የሚያገለግሉትን ነው።
በዚህ አግባብ ካየነው የህብረት ሥራ ማህበራት ትርፍ የሚሰበስቡበት መንገድ አይኖርም።የተሻለ ዋጋ ያለው እና ጥራት ያለው ምርት ካላቀረቡ እና ማንኛውም ነጋዴ የሚያቀርበውን ዓይነት ዋጋ ካወጡ ደግሞ በገበያውም ተወዳዳሪ ሆነው መዝለቅ አይችሉም።በዋናነት እኛም ገበያው ላይ ካለው ዋጋ ያነሰ እንዲያቀርቡ ሥራቸው ላይ ክትትል እናደርጋለን።ለዚህም ነው በመንግሥትም ሰፊ ድጋፍ የሚደረግላቸው።
የህብረት ሥራ ማህበራት በገበያ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እንዲያድግ የሚያስችሉ ሥራዎችን አከናውነናል።አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች በስፋት የሚያስተናግዱ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ነው።በተለይ ከአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ምርቶችን ተረክበው ለመዲናዋ እንዲያቀርቡ እነሱም የሚሸምቱበት ገንዘብ በሰፊው ያስፈልጋቸዋል።ከዚህ አንጻር የከተማው አስተዳደር ካቢኔ በወሰነው መሰረት ግማሽ ቢሊዮን ብር ለህብረት ሥራ ማህበራት እንዲከፋፈል ተደርጓል።
የህብረት ሥራ ማህበራቱም ከልልሎች ጋር ትስስር ተፈጥሮ ቀጥታ ከአምራቹ እንዲረከቡ እና የግብይት ሰንሰለቱ ባጠረ መንገድ ምርት እንዲያቀርቡ ተደርጓል።በዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ ሰፊ ምርት ወደአዲስ አበባ አስገብተዋል።የጤፍ፣ የስንዴ ፣ የሽንኩት እና ሌሎችም ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ የተደረገው በዚህ አግባብ ነው።
ማህበራቱም ቀጥታ ከፋብሪካ እና ከአምራቹ ተረክበው የሚያቀርቡ በመሆኑ ያን ያክል የዋጋ ንረት ችግር አይስተዋልባቸውም።ማህበራቱ በመዲናችን ትልቁ የኑሮ ውድነት እና ዋጋ ንረት መንስኤ የሆነውን የአቅርቦት እጥረት በመፍታት ረገድ ትልቅ ጥረት እያደረጉ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ በድጎማ የሚቀርቡ እንደ ስኳር እና ዘይት ምርቶችም በተሻሻለ ሁኔታ ለመንግሥት ሠራተኞችም ሆነ ለህብረተሰቡ በየማዕከላት እንዲቀርብ ተደርጓል።ስለዚህ ሸማች ማህበራቱ ገበያው ዋጋ ይበልጥ እንዳይጨምር ወደታች ይይዛሉ፤ በተመሳሳይ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ በማዳረስ ገበያውን እያረጋገጉ ነው።እንደ ቢሮም ዋጋቸው ተመጣጣኝ እና ከነጋዴው አንጻር አነስተኛ እንዲሆን በየጊዜው ቁጥጥር እናደርጋለን።ማህበራቱ ደግሞ ባከናወኑት ሥራ የጤፍ እና ሌሎች ምርቶችን ዋጋ በማረጋጋት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነበር።
አዲስ ዘመን፦ በአዲስ አበባ በተለይ አንዳንድ ነጋዴዎች ሆን ብለው ሸቀጥ የመደበቅ፣ ዋጋ አላግባብ የማናር ሥራዎችን ሲሠሩ ይስተዋላል፤ ችግሩን ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው?
አቶ መስፍን፦ ምርቶችን በተለያየ አግባብ ማከማቸትና መደበቅ በከተማችን ላይ ከሚስተዋሉ ህገወጥነቶች መካከል አንዱ ችግር ነው።ይህም ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ ለመጨመር የሚደረግ ጥረት ነው።ከዚህ አንጻር ባደረግናቸው ክትትል ሰፊ ዕርምጃ ተወስዷል።
በግለሰቦች መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ዘይት ይዘን ለመንግሥት ገቢ አድርገናል፤ ምርቱም ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተከፋፍሏል።የሰብል እና የኢንዱስትሪ ውጤቶችንም ደብቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ላይ ሰፊ እርምጃ ተወስዷል።በዋናነት ምርቶች በህገወጥ መንገድ ተከማችተው ሲገኙ ይወረሳሉ፤ የደበቁትም በህግ እንዲጠየቁ ይደረጋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር በድግግሞሽ አከናውነናል።በከተማዋ የሚገኙ አንድ ሺህ አምስት መቶ መጋዘኖች ውስጥ ምን ዓይነት እቃ ተከማችቷል፤ ምን ያክል በህጋዊነት እይተሠራባቸው ነው የሚለውን በየጊዜው እያየን ነው።ለዚህም ከጸጥታ አካላት፤ ከገቢዎች ቢሮ እና ደንብ ማስከበር ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ተሠርቷል።
በተጨማሪ ዋጋ ያለአግባብ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ የምናደርገውን የዕለት ተዕለት ቁጥጥር አጠናክረናል።ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙትንም እስከማሸግ እና ፍርድ ቤት እስከማቅረብ የደረሰ ዕርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።በዚሁ ልክ ያለንግድ ፈቃድ የሚነግዱም ህገወጥ በመሆናቸው በህጋዊ መስመር ገብተው እንዲሠሩ ነው ጥረት የምናደርገው።
ፈቃድ እያለው ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽም ከሆነ የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው ደግሞ የባሰ የግብይት ስርዓትን ያልተከተለ እና ደረሰኝን ታሳቢ ያላደረገ ሥራ ስለሚያከናውን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ንረትን ያስከትላል።ስለዚህ ህገወጥነትን በመከላከል ረገድ በር ለበር ክትትል የተደረገበት እና ጠንካራ ዕርምጃ የተወሰደበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ በቅርቡ ሆን ተብሎ የምግብ ዘይት ከገበያ እንዲጠፋ ተደረገ፤ ቀጥሎ ስኳር፤ አሁን ደግሞ ወተት ፤ እነዚህ ችግሮች መነሻቸው ምንድነው ለመፍትሔውስ ምን ዓይነት አሠራር አስቀምጣችኋል?
አቶ መስፍን፦ የምግብ ዘይት ምርት ከውጭ አገራት ገበያ በብዛት ይመጣ ስለነበር በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በአቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት ከፍተኛ ችግር ይፈጠር ነበር።አሁን ምርቶቹን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ከግል ባለሀብቶች ጋር በመሆን ተከናውነዋል።
ለአዲስ አበባ በስፋት የምግብ ዘይት ምርት እያቀረቡ የሚገኙ ፊቤላ እና ሸሙ የተባሉ ሁለት የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች አሉ።ከሁለቱ ፋብሪካዎች በየወሩ አምስት ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እየቀረበ ነው።ከዚህ ቀደም በወር በአማካይ ሦስት ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከፊቤላ ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስ ለመዲናዋ ሲቀርብ ቆይቷል፤ ከዚህ ወር ጀምሮ ደግሞ በተጨማሪነት በሸሙ ማኔጅመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በኩል የተመረተ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ዘይት እየቀረበ ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ መንግሥት የምግብ ሸቀጦች አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የፍራንኮ ቫሎታ አሠራር ከውጭ ሀገራት ባለ የዶላር ገቢ ዘይት እንዲገባ ተፈቅዷል።በዚህ መንገድ በርካታ ነጋዴዎች የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ የስንዴ ዱቄት እና የሕፃናት ምግቦችን እያስገቡ ይገኛል።ይህም አቅርቦቱን ከማስፋት እና ገበያውን ከማረጋጋት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ከወተት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ሸማቾች ቅሬታ እያቀረቡ ነው።ወተት በባህሪው በፍጥነት ለገበያ ካልቀረበ የመበላሸት ዕድሉ ሰፊ ነው።ከዚህ ቀደም ወተት አቅራቢዎች የሚረከበን በማጣታችን በሺዎች የሚቆጠር ሊትር እየተበላሸ እንደሚደፋ ገልጸዋል፤ ችግሩም እንዳለ ማየት ይቻል ነበር።
በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብም ሆነ በሰፊው የገጠሩ ሀገራችን ክፍል ሰፊ የወተት ምርት ቢኖርም ከምርታማነት ጋር የሚነሱ ችግርች እንዳሉ ሆነው ወደከተማ አሊያም ወደፋብሪካ የሚገባው ግን በጣም ጥቂቱ ነው።በወተት ዘርፍ ያለው ገበያ ጉዳይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሰፊ ለውጥ ይመጣበታል ብለን እናስባለን።
ወተት ተረክበው ለከተማው ህዝብ የሚያቀርቡ ትላልቅ ፋብሪካዎች ወደሥራ እየገቡ ነው።የተለያዩ የህብረት ሥራ ማህበራትም የእራሳቸውን ወተት ማቆያ እያዘጋጁ ይገኛል።ይህም የተመረተው ወተት ጥራቱ ሳይጓደል ለረጅም ጊዜ ተጠብቆ እንዲቆይ ያግዛል፤ በገበያው ውስጥ ሰፊ አቅርቦት ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ትልቅ ድጋፍ ይሰጣል።በዚህ ሂደት ውስጥ የወተት ምርት አቅርቦት ችግር እየተፈታ ይሄዳል።
ከዋጋ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል።ወተት የሀገር ውስጥ ምርት እንደመሆኑ መጠን ለምን ዋጋው በየጊዜው ይጨምራል የሚለውን ማየት አለብን።ለዋጋው መጨመር ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው የሚለውን ካየን በመጀመሪያ የምርት ግብአት ዋጋ ጭማሬ ነው፤ በሌላ በኩል የፍላጎት መናር የሚያመጣው የዋና ጭማሬ አለ።በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ካየን የውጭ ሀገራት ገበያ ተጽእኖ የሚያመጣባቸው ምርቶች አሉ።
ለአብነት ለወተትም ምርት ማሸጊያ የሚውሉ ፕላስቲኮች ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ሲጨምር አሊያም የእኛ ብር የመግዛት አቅም ሲቀንስ በተመሳሳይ የመጨረሻ ምርቱ ላይ የሚደመር የዋጋ ጭማሪን ያስከትላል።የሠራተኛ ዋጋ መጨመር እና ሌሎችም የእራሳቸው ተጽእኖ አላቸውና ይህን ግን ማየት ያስፈልጋል።እንደመንግሥት ግን ሙሉ ለሙሉ እጅ አስገብቶ በዚህ ዋጋ ሽጥ ወይም አትሽጥ ማለት አይቻልም።መሆን ያለበት ግን የግብይት ሂደቱን ግልጽ እና ለቁጥጥር የሚመች ማድረግ ነው።
ወጪ ያላደረገበትን ዋጋ ሰዎች ላይ የሚጭን አካል ከሆነ ስርዓት እንዲይዝ የምናደርገው ምን ያክል አወጣ ምን ያክል ትርፍ ይዞ ገቢ አደረገ የሚለውን በመቆጣጠር ነው።ይህን እያከናወነ ይገኛል።በወተትም ሆነ በሌሎች ምርቶች ላይ ህገወጥ የዋጋ ጭማሪን የምናደርገው ቁጥጥር አጠናክረናል።አላግባብ ዋጋ መጨመራቸው በመረጃ እና በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ካሉ ዕርምጃ መውሰዳችን አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡– ወቅት ጠብቀው የሚወደዱ እና ዋጋቸው የሚለዋወጡ ምርቶች አሉ በተለይ በዓል ሲመጣ ዋጋቸው እንደሚንር የሚገመቱ ምርቶች አሉ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
አቶ መስፍን፡– በእኛ ሀገር ልምድ በዓላትን፣ የምርት መሰብሰቢያ እና መግቢያ ወቅቶችን ላይ ዋጋ የሚጨምርበት ዋጋ የሚቀንስበት ሁኔታ አለ።ይህን ዓይነት ችግር በዋናነት መፍታት የሚቻለው ትርፍ ምርት በማምረት ነው።ካለው ፍላጎት የበለጠ ምርት ሲመረት እና ወደገበያ ሲገባ ዋጋውም የተረጋጋ ይሆናል።
በበዓል ወቅት ለአብነት በአዘቦት ቀናት ከምንጠቀመው በእጅጉ በበለጠ ሁኔታ እንደዶሮ እና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦዎች ፍላጎታችን ይጨምራል።ከሌላው ጊዜ በበለጠ ሁሉም የበዓሉ አክባሪ በሚባል ደረጃ ሽንኩርት እና ዕንቁላል ለመግዛት ሊወጣ ይችላል።ይህ ገበያው ላይ ሰፊ ፍላጎት ይፈጥራል፤ ያንን ፍላጎት የሚያሟላ በቂ አቅርቦት ከሌለ ደግሞ የገበያ ውድድሩ የተሻለ ዋጋ ያቀረበ ሰው ብቻ ምርቶች ገዝቶ እንዲሄድ ያደርጋል።
በተለይ የግብርና ምርቶች ምርታማነት ማሳደግ እና በተገኘው ቦታ ሁሉ መሬት ጦሙን እንዳያድር የሚያስችል ሥራ ተከናውኗል።ከዚህ ባለፈ ደግሞ በየትኞቹ ወቅቶች ላይ የትኞቹ ምርት በብዛት ይፈለጋሉ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።በተጠና ደረጃ በስታስቲክስ ኤጀንሲ ደረጃ መሠራት አለበት።
በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሩ ደረጃ ዓመቱን ሙሉ የትኞቹ ምርቶች በምን ወቅት ፍላጎታቸው ይጨምራል የሚለውን የዳሰሰ እና ጥናትን መሰረት ያደረገ አቅርቦት እንዲኖር ተሠርቷል።የሸማች ማህበራት አቅርቦት ላይ ያለውን ክፍተት እንዲሞሉ አቅማቸው ከፍ እንዲል ድጋፍ ተደርጓል።
ከተማ አስተዳደሩ ባከናወነው ሥራ በተለይ በበዓል ወቅት በሰፊው አቅርቦት ወደከተማዋ እንዲገባ አድርጓል።ለአብነትም ያለፈውን የፋሲካ እና ረመዳን በዓላትን ማየት ቢቻል የሽንኩርት ገበያው በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ ከሰባት ብር ጀምሮ ከፍተኛ የተባለው እስከ አስራ ሦስት ብር በሚደርስ ዋጋ ነው ሲሸጥ የነበረው።
ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖርም አቅርቦቱም አስተማማኝ ስለነበር እንዲሁም ህገወጥ ዋጋ ጭማሪን መከላከል በመቻሉ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሽንኩርት ዋጋ ላይ ከ40 ብር በላይ በቀነሰ ሁኔታ ሲሸጥ ሰንብቷል።ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበዓል ወቅት ላይ 45 ብር እና 50 ብር ሲሸጥ የነበረው ሽንኩርት አሁን ላይ ከ500 በመቶ ባነሰ ዋጋ እነዲሸጥ ያደረገው አንድም አቅርቦት መሻሻሉ፤ በሌላ በኩልም ስርዓት ያለው ቁጥጥጥር በመደረጉ እንዲሁም የገበያ ሰንሰለቱ ባጠረ ሁኔታ ማህበራት ለሸማቾች ምርቱን እንዲያቀርቡ በመደረጉ ነው።
ይህም ጤናማ ውድድር በመፍጠሩ የገበያ ዋጋውን አረጋግቷል፤ ስለዚህ በበዓል ወቅትም ሆነ ሌሎች ወቅቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ተመሳሳይ አሠራሮችን መከተል ያስፈልጋል።በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች እንደተሠራው በሌሎች ምርቶችም ላይ ተመሳሳይ ሥራ እየተከናወነ ሲሄድ ወቅትን ሳይጠብቅ በተሻለ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት መገብየት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ በነፃ የገበያ ስርዓት ህግ የትርፍ ህዳግ የሚባል አለ፤ በኛ ሀገር ግን የነፃ ገበያ ስርዓት በሚል ሽፋን እንደፈለጉ ዋጋ የማናር ፍላጎት ይንጸባረቃል፤ የነፃ ገበያ ህግ እንደፈለጉ ዋጋ ማናርን ይፈቅዳል?
አቶ መስፍን፦ የምንከተለው የንግድ ስርዓቱ ነፃ ገበያ ቢሆንም ከአግባብ በላይ ትርፍ የሚያጋብስን አሠራር ግን አንፈቅድም።በአተረፈው ልክም ግብር እንዲከፍል ይደረጋል።100 ብር ያወጣበትን ምርት 110 ወይም 120 ብር ቢሸጥ ምንም አይደለም።ነገር ግን በዚያኑ ወጪ 200 ብር በመሸጥ እጥፍ ቢያተርፍ ግን አግባብ ነው አንልም፤ ስለዚህ ግብሩም በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል።
በትርፉ ልክ ግብር እንዲከፍል ከማድረግ ውጪ ደግሞ በዚያው ልክ ህጋዊ ዕርምጃዎችንም እንወስዳለን።በተለይ ከሸማች መብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ በተለይ የንግድ ውድድር እና በሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2011 መሰረት በተለይ ተስማምቶ በጋራ ዋጋ የመወሰን እና ህብረተሰብ ላይ ጫና የማድረግ ሁኔታ ካለ አስፈላጊው የህግ ዕርምጃ ይወሰዳል።የሸማቹን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድርግና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር በሀገራችን ለማስፈን ተመጣጣኝ ዋጋ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት በአዋጁ ተደንግጓል።
በዚህ አግባብ እስከእስር የደረሰ ዕርምጃ ይወሰዳል፤ ነገር ግን ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ያላቸው ጭማሪዎች እንደሚኖሩ መገንዘብ ይገባል።መረጃ የተያዘባቸው እና ወጪን መሰረት ያደረጉ እንዲሁም ሁላችንም ልንግባባቸው የሚችሉ ጭማሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ደግሞ ታሳቢ ይደረጋል።ከዚህ ባለፈ ግን የነፃ ገበያ ስርዓት የእራሱ አካሄድ እና ቁጥጥር ስርዓት ያለው በመሆኑ ማንም አያየኝም ብሎ የማይገባ ትርፍ የሚወስደውን ነጋዴ በህግ ሊጠየቅ እንደሚችል ማወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፦ በህገወጦች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ አስተማሪ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ከዚህ አንጻር እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ መስፍን፦ ከዚህ ቀደም የነበረውን እና ባለፉት ሦስት ዓመታት ያለውን ካየን የተለያየ ነው።ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ በዚህ ዓመት ህገወጦች ላይ አስተማሪ ዕርምጃዎች ናቸው እየተወሰዱ ያሉት።
አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ላይ በንግድ ቤቶች ላይ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ የማሸግ ሥራ ይከናወናል፤ ይህ በእራሱ የሚያመጣው ተጽእኖ አለ።አንድ ንግድ ተቋም ለ15 ቀን ሲታሸግ አገልግሎት አይሰጥም በዚያው ልክ የቤት ኪራይም እየተከፈለበትና ወጪ እያወጣ በመሆኑ ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው።ህግን መሰረት አድርገን ስንሠራ ግን ይህም እንደ ቅጣት መቅረቡ አስተማሪ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
እንደየጥፋታቸው ደረጃ በህግ ሂደት ላይ የሚገኙ፤ በገንዘብ የተቀጡሠም አሉ።ንግድ ፈቃዳቸው የተወሰኑ ወራትና ዓመታት እንዲታገዱ የተደረጉ እንዲሁም ፈቃዳቸው ተሰርዞ ሙሉ ለሙሉ ከንግድ ስርዓቱ እንዲወጡ የተደረጉም አሉ።ከዚህ በላይ ጠንከር ያለ ዕርምጃ ሊኖር አይችልም።
አንድ ሰው ሲያጠፋ በእስራት፣ በገንዘብ አሊያም በአስተዳደራዊ ዕርምጃ ነው የምትቀጣው ይህ ደግሞ ሌላውም ወደህገወጥነት እንዳይገባ አስተማሪ ነው።በተለያየ መንገድ ወንጀል ላይ የተሰማሩትን ባለንብረቶች ምርት እንወርሳለን።ለኤክስፖርት መቅረብ የነበረበት በርካታ ቶን ቡና እና የተለያዩ የምግብ እህሎችን ይዘናል።
ከዚህ ባለፈ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ደባልቀው ሲያቀርቡ የተገኙ አጥፊዎችን ከጸጥታ አካላት ጋር እና ከቁጥጥር ተቋማት ጋር በመሆን ክትትል ይደረጋል፡፡ በየጊዜው ተይዘው ለህግ ይቀርባሉ።ነገር ግን ህጉንም ሳይፈራ ወደህገወጥነት የሚገባ አካል ካለ ችግሩ የሚሆነው የእራሱ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የሃገራችን የንግድ ስርዓት ህግን የተከተለ ነው ለማለት ይቻላል?፤ በህግስ ይመራል ወይ የሚል ቅሬታ የሚያነሱ ሰዎች አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ምን ሃሳብ አለዎት?
አቶ መስፍን፦ በዚህ ደረጃ ጥያቄው መነሳቱ ይገርማል።ህግ ባለበት ሀገር ነን፤ በህግ ነው የምንተዳደረው።ንግዳችንም ሁላችንን በሚገዛ ህግ ነው የሚተዳደረው።ይብዛም ይነስም ክፍተት ኖሮበት ማሻሻያ ቢደረግበትም ላለፉት 60 እና ከዚህ በላይ ለሆኑ ዓመታት ሲያገለግል የኖረ የንግድ ህግ አለ።
ያ የንግድ ህግ ከነክፍተቱ ጠንካራ የነበረ ነው።ችግሩ የሚሆነው ምን ያክሎቻችን ያንን ህግ ተረድተን ለመፈጸም ዝግጁ ነን የሚለው ነው።በሁለተኛ ደረጃ ህጉን እንዲያስፈጽም የተመደበው አካል ምን ያክል ህጉን እያስፈጸመው ነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።ከዚህ አንጻር የሁላችን በሆነችው ሀገር ውስጥ ተስማምተን ያስቀመጥናቸው የጋራ ህጎች ላይ ተግባብተን መገዛት የማንችል ከሆነ ግን አስቸጋሪ ነው።
ለዚህም እኔ ምን ያክል ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ ብለን መጠየቅ ይገባል።ህጉን የሚያስፈጽመውም ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ዕርምጃ እያስተላለፈ እና ያለማንም አድልኦ ሁሉም አካላት ላይ ህጉን እያስፈጸመ የማይሄድ ከሆነ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።ከዚህ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን እንወስዳለን።
እንደማህበረሰብ ያሉትን ክፍተቶች ማስተካከል እነደሚገባ ሁሉ እንደተቋምም እኛ ጋር ያሉትን ክፍተቶች ማስተካከል ይኖርብናል።ችግሮቹን ለመፍታት የንግድ መዋቅሩን ሙሉ ለሙሉ የማሰልጠን እና አቅም የመገንባት ሥራ እያከናወንን እንገኛለን።ከህግ አግባብ የሚንቀሳቀሱ የእኛ መዋቅር አካላት ላይ ደግሞ ዕርምጃ እየወሰድን ነው።አስተዳደራዊ ብቻ የነበሩ ዕርምጃዎችን ወደህግ አካላት እየወሰድን እንዲታረሙ በማድረግ ጠንከር ያለ ዕርምጃ እየወሰድን መሆኑ መታወቅ አለበት።ስለዚህ የንግድ ስርዓቱ በህግ እና በህግ ብቻ እንዲመራ የምናደርገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በተጨማሪ ግን ከህግ አንጻር በሚኖሩ ክፍተቶች አማካኝነት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ህጎቹንም ማስተካከል ይጠበቅብናል።ለበርካታ ዓመታት ያገለገለውን የንግድ ህግ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እነዲጣጣም ተደርጎ በአዲስ መልክ ተዘጋጅቶ ወጥቷል።ህጉን ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅብናል።
በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅርም ህጉን ተገንዝቦ በአግባቡ እንዲተገብረው እነዲሁም ህጉም መሰረት ያደረገ ተጠያቂነት እንዲያሰፍን ሰፊ ሥራ ይጠበቃል።ከዚህ ባለፈ የህግ አፈጻጸም ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከል የህብረተሰቡ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ መታወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ጊዜና ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ መስግን፡– እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013