በተለመደው አካሄድ መሰረት ጥንዶች የሦስት ጉልቻ ምስረታን እንደየሀገሩ ባህልና የህግ አግባብ መሰረት እንደሚጀምሩት ይታወቃል። በሌላ በኩል ግን ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ጥንዶች በትዳር የተጋመዱት ባልና ሚስት የሚከውኑትን ሁሉ እያደረጉ ዓመታትን ይዘልቃሉ። በተለምዶ እነዚህን ጥንዶች ባለትዳር ናቸው ከማለት ይልቅ አብረው እየኖሩ ነው ሲባል ይሰማል ለመሆኑ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር፤ አንድምታዎቹ እና ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው? ስንል የህግ ባለሙያና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑትን አቶ አቤል ልዑል ሰገድን አናግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ አንቀፅ አንድ መሰረት ህጋዊ ጋብቻ በተለያዩ ሰነ-ስረዓቶች ሊፈፀም ይችላል። እነሱም በክብር መዝገብ ሹም ፊትና በሐይማኖት እና በባህል መሰረት የሚፈፀሙ የጋብቻ ዓይነቶች ናቸው። በተጨማሪም ጋብቻ ከላይ በተጠቀሱት በአንዳቸው ስነ-ስርዓቶች ቢፈፀም እንኳን ውጤቱም አንድ መሆኑን የዚሁ ህግ አንቀፅ አርባ ያትታል። ህጋዊ ጋብቻ በተጋቢዎቹ ላይ ሁለት ዓይነት ውጤት ይኖረዋል። የመጀመሪያው በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት ሲሆን፤ በስሩም የመከባበር፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ እና ቤተሰብን በጋራ የመስተዳደር እና በጋራ አንድ ላይ የመኖር ግዴታዎችን ያቅፋል። ሁለተኛው ውጤት ደግሞ ጋብቻ በተጋቢዎች ንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት ነው። ይህም ተጋቢዎች ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ጊዜ በግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ እና በስጦታ በየግላቸው ያገኟቸው ንብረቶች የግል ንበረታቸው ሆነው ሲቀሩ ከዚህ ውጪ ያሉ ንብረቶች በሙሉ የጋራ ንብረት ይሆናሉ።
ከጥንት ጀምሮ በወንዶችና በሴቶች መካከል ከነበሩ ማህበራዊ ግንኙነቶች መካከል ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር አንዱ ነው። የዚህ ዓይነት ግንኙነት ምንም እንኳን ለቤተሰብ መመስረት ምክንያት ቢሆንም በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ ማሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች ያላሟላ ስርዓት ነው። በሀገራችን እንደ ፍትሐ ነገስት ያለ ጥንታዊ የጋብቻ ህጎች ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖሩን ቢያወግዝም የፍትሐብሔር ህግ እና በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አስፈላጊነቱን በማመን ከለላ አድረግውለታል።
ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር አንድምታዎች
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 98 እንደሚያትተው ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ማለት አንድ ወንድ እና አንድ ሴት በህግ በሚፀና አኳኋን ጋብቻ ሳይፈፀሙ በትዳር መልክ የኖሩ ሲሆን ነው። የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት በህግ አግባብ ከሚደረጉ ጋብቻ ጋር ተቃራኒ ነው ተብሎ ሰለሚታሰብ እንደ “ፍተሐ ነገስት” ያሉ ጥንታዊ ህጎች እንደ ሐጥያት በመቁጠር ያወግዙት ነበር።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለማችን ከትዳር ውጪ የሚወለዱ ልጆችና የፍቺ መጠን ፍጥነት እየጨመረ ሲመጣ በተቃራኒው ደግሞ ከትዳር ውጪ አብሮ መኖር እየተለመደና እየበዛ መጥቷል። ይህም ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን ከለላ መስጠት አስፈላጊ እና የማይታለፍ መሆኑን ህጉ ተቀብሎታል:: እንደምክንያትነትም የኢትዮጵያ ህግ መንግሥት አንቀፅ 34 ለቤተሰብ የሚሰጠው ከለላ ይነሳል፤ ይህም ልክ በህግ እንደሚደረግ ጋብቻ ሁሉ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖርም ቤተሰብን ይመሰረታል።
ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ህጋዊ እንዲሆን ወይም ተገቢነት እንዲኖረው በህግ አግባብ የሚፈፀም ጋብቻ ማሟላት የሚገበውን ሁኔታዎች እና ስርዓቶች መፈፀም አይጠበቅበትም:: የዚህ ስርዓት ዋናው አስፈላጊ ነገር የሁለቱ ወገኖች ነፃ ፍቃድ እና ስምምነት ብቻ ነው።
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 99 ባስቀመጠው ማብራሪያ መሰረት፤ ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት አብረው ኖሩ ማለት ወንድየውና ሴትየዋ የሚያሳዩት ሁኔታ በህግ እንደተጋቡ ሰዎች ዓይነት መሆኑ አስፈላጊና በቂ ነው። በተጨማሪም ይህ ስርዓት ካሉት ልዩ ባህሪያት አንዱ ሁለቱ ወገኖች ለሦስተኛ ወገኖች እንደተጋቡ ሆነው መቅረብ አስፈላጊ አይደለም:: በሌላ በኩል አንድ ወንድና አንዲት ሴት በታወቀና በተደጋገመ ሁኔታ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መፈፀማቸው ብቻ በሁለቱ መካከል ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት ግንኙነት አላቸው ለማለት በቂ ምክንያት አይደለም።
ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብረው መኖር የሚያስገኘውን የህግ ከለላ ለማግኝት ለምን ያህል ጊዜ አብረው መቆየት አለባቸው የሚለው ነጠብ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው? ጊዜን በተመለከተ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ያስቀመጠው ገደብ የለም ነገር ግን በአንቀፅ 99 ንኡስ አንቀፅ 3 ስር ከላይ አንደጠቀስነው ተደጋጋሚ ሩካቤ ስጋ መፈፀም ብቻ ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት ግንኙነት አላቸው እንደማያስብል አይተናል:: ስለዚህ ከዚህ የምንረዳው የዚህን ስርዓት የህግ ከለላ ለማግኘት ከጊዜ ይልቅ በህግ አግባብ ጋብቻ እንደፈፀሙ ተጋቢዎች ዓይነት ባህሪ ማሳያት ነው። ለምሳሌ፡- መከባበርና መተጋገዝ ፣መደጋገፍ ፣ ቤተሰብን በጋራ መምራት ፣ መተማመን ወ.ዘ.ተ በመካከላቸው ካለ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት አለ ማለት ይቻላል::
ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር የሚያስከትላቸውን የህግ ውጤቶች።
የጋብቻ ዝምድናን አያስከትልም፡- ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በወንድየውና በሴቲቱ የስጋ ዘመዶች መካከል እንዲሁም በሴትየዋና በወንድየው የስጋ ዘመዶች መካከል አንዳችም የጋብቻ ዝምድናን አያስከትልም።
ነገር ግን የተሻሻለው ቤተሰብ ህግ አንቀፅ 100 ንዕስ አንቀፅ 2 ስር እንደተደነገገው “ሆኖም የጋብቻ ዝምድና ባለ ጊዜ፤ ጋብቻን የሚከለክሉ ድንጋጌዎች፣ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ባለ ጊዜም ተፈፃሚ ይሆናሉ” በማለት አትቷል። ይህም ማለት ምንም እንኳን ህግ ይህንን ስርዓት ለማስቀረት እና በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻን ለማበረታታት ሲል የጋብቻ ዝምድናን አይፈጥርም ቢልም በተገላቢጦሽ በሁለቱ ሰዎች ቤተሰቦች መካከል ጋብቻ እንዳይፈፀም ይከልክላል። በተጨማሪም ይህ የሚያመላክተው በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰቦች ላይ የጋብቻ ዝምድና እንደሚፈጠር ሁሉ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ ዘጠኝ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው ለሚኖሩ ሰዎችም ይሠራል ማለት ነው። ስለዚህ የጋብቻ ዝምድናን ያስከትላል።
የጋራ ወጪዎችን በጋራ መሸፈን፡- ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ኑሯቸውን ወጪ ለመሸፈን እያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው እና ችሎታቸው አስተዋፆ ማድረግ አለባቸው። ለዚህም የቤተሰብ ህጉ በአንቀፅ 101 ስር የጋራ ወጪዎችን በጋራ መሸፈን አለባቸው ሲል ያትታል።
ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ከሦስት ዓመት ላላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ፤ በግንኙነት ውስጥ እያሉ ያፈሯቸው ንብረቶች የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ። በተጨማሪም የሚገቧቸው እዳዎች አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ለጋራ ኑሯቸው ወይም ከግንኙነቱ የተወለዱ ልጆችን መሰረታዊ ፍለጎቶች ለማሟላት ሲባል የተገቡ ዕዳዎች ሲሆኑ ለዕዳዎቹ አከፋፈል ሁለቱም በአንድነትና በነጠላ ኃላፊዎች ይሆናሉ።
ጋብቻ ሳይፈፅም እንደ ባልና ሚስት አብረው ከሚኖሩ ወንድና ሴት የሚወለዱ ልጆችን ተወላጅነታቸው የሚረጋገጠው ልክ በትዳር ውስጥ እንደተወለዱ ልጆች “እውነት ነው ተብሎ በሚገመት” ሳይሆን ስለ መወለድ በሚባል አካሄድ ነው። ይህ አካሄድም በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ምዕራፍ ዘጠኝ ስር ተደንግጓል።
ግንኙነቱ የሚቋረጥባቸው መንገዶች እና ለግንኝነቱ መኖር እንደ ማስረጃ የሚቀርቡ ሁኔታዎችን ስንመለከት የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 105 ስር እንደደነገገው ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ወንድና ሴት በማንኛውም ጊዜ ግንኙነታቸውን ማቋረጥ ይችላሉ:: በተጨማሪም ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ያደረገው ወገን እንደ ዝሙት ያለ ጥፋት ካልፈፀመ በስተቀር ካሳ እንዲከፍል አይገደድም። ይህ የሚያመላክተው ወደ ግንኙነቱ ሲገባ ምንም ሁኔታዎች ማሟላት እንደማይጠበቅባቸው ሁሉ ግንኙነቱን ለማቋረጥም ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳያስፈልግ ማቆም ይችላሉ ማለት ነው።
በሌላ በኩል የግንኙነቱን መኖር ማስረጃ በተመለከተ አንድ ወንድና ሴት ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው ይኖራሉ የሚባለው ምንም እንኳን በህግ የተጋቡ ባይሆንም የተጋቡ ሰዎችን ሁኔታ ሲያሳዩና ቤተዘመዶቻቸውና ማህበረሰቡ እንደተጋቡ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው ብለው ሲገምቷቸው ነው። ይህም በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 106 ስር በግልፅ እንደተደነገገው “የግንኙነቱ ሁኔታ መኖሩን በማጋገጥ” ማስረዳት ይቻላል።
ተግዳሮቶች
ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ያሉበትን ተግዳሮቶች ለማየት ከህግ አግባብ ከሚፈፀም ህጋዊ ጋብቻ ጋር በማነፃፀር እንደሚከተለው እናያለን፡- በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ የትኛውንም ይዘት ቢይዝ በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚመዘገብ ሲሆን፤ በተቃራኒው ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ከነጭራሹም አይመዘገብም። ባለመመዝገቡም ለህጋዊ ጋብቻ በህጉ የሚሰጠውን መብቶች እና ከለላ አያገኝም ማለት ነው::
በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ፤ የጋብቻ ስነ-ስርዓት ወይም በተለምዶ አጠራር ሠርግ ሲኖረው ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ግን ምንም ዓይነት የአከባበር ስርዓት የለውም። በመሆኑም በማህበረሰቡ ዘንድ አዎንታ አያገኝም:: ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን ለማረጋገጥ አብሮ መኖር በጣም አስፈላጊና ዋንኛው ሁኔታ ሲሆን፤ በህግ አግባብ ለሚደረግ ጋብቻ ግን ዋነኛ ማረጋገጫ አይደለም። ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ውስጥ የጋራ ንብረት ለማፍራት ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ያክል አብረው መቆየት ይገባቸዋል። ከዚህ በተቃራኒ በህግ አግባብ በሚደረግ ጋብቻ ጊዜ የጋራ ንብረት ተብሎ መቁጠር የሚጀምረው ጋብቻው ከተፈፀመበት ዕለት አንስቶ ነው።
ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን በቀላሉ ያለምንም ምክንያት እና ቅድመ ሁኔታ ማቋረጥ ይቻላል። በተቃራኒው በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻን ለማፍረስ ግን ህጉ ያስቀመጣቸውን ሁኔታዎች ማሟላት ያስፈልጋል። በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት የጋብቻው ግንኙነት ፍሬ እንደሆኑ ሲገመት፤ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ውስጥ የሚገኙ ልጆች ግን ስለመወለድ የሚል አካሄድን በመከተል ነው ወላጆቻቸውን የሚያውቁት። መጨረሻም በህግ አግባብ የሚደረጉ ጋብቻን ለማረጋገጥ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ሲቀርብ፤ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን ለማረጋገጥ ግን የግንኙነት ሁኔታን በማስረዳት ብቻ ይሆናል።
ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ምንነት፤ አንድምታዎቹ እና ተግዳሮቶቹ ይህን ይመስላል። በመሆኑም በዚህ ዓይነት ግንኙነት ውስጥ ያሉ የማህበረሰባችን ክፍሎች ከህጋዊ ጋብቻ ይልቅ ይህንን ግንኙነት ለመምረጣቸው እንደ ምክንያትነት ከሚያስቀምጧቸው ነገሮች መካከል፤ በህግ ወይም በዕድሜ ጋብቻን ለመፈፀም አቅም ማጣት፣ ትዳር ውስጥ ከመግባት በፊት እንደሙከራ ለማደረግ፣ የሠርግ ወጪን ለመቀነስ ወ.ዘ.ተ ናቸው። ከላይ በተዘረዘሩት ፅንሰ ሃሳቦች መሰረት በማድረግ ምንም እንኳን ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሻሻለው ቤተሰብ ህግ ከለላ ቢደረገለትም፤ ዜጎች ግን በህግ አግባብ ከሚደረጉ ጋብቻዎች ከሦስቱ አንዱን ስርዓት በመምረጥ ቢፈፅሙ እና የተሟላ ቤተሰብ ቢመሰርቱ መልካም ነው በማለት የህግ በለሙያው አቶ አቤል ልዑል ሰገድ ያሳስባሉ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013