ብሔርን ወይም ሐይማኖትን ማዕከል በማድረግ የሚጸነስ የአክራሪነት መንፈስ የሰላም እንቅፋት እንደሚሆን አያጠያይቅም። እንደማሳያ ተደጋግመው የሚገለጹት ከስተቶች መካከል እኤአ በ1994ቱ የተከሰተው የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ አንዱ ነው። በዚህ አሰቃቂ ክስተት ወደ 800 ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉበት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። የዘር እልቂቱ ሁለት አስርት ዓመታት ቢያልፉትም አሁንም ድረስ ሩዋንዳውያን ከመራር ኀዘን ጋር ለመኖር የተገደዱ ሰዎች ቁጥር ትንሽ አይደለም። ቤተሰባቸውን በማጣትና አሰቃቂ ግድያዎችን በማየት አንዳንዶችም በደመነፍስ በድርጊቱ ውስጥ በመሳተፋቸው ከህሊና ፀፀት ጋር ህይወታቸውን በአሰልቺ መንገድ እንዲገፉት አድርጓል። ኢትዮጵያዊያንም ከሩዋንዳዊያን ብዙ መማር አለብን።
ነገሮች ሩቅ ቢመስሉም መቼ ቀርበው ደጃፋችን እንደሚደርሱ አይታወቅም። ዘር ወይም ሐይማኖትን ማዕከል አድርጎ ደግፎም ሆነ ተቃውሞ በውስጥ የጥላቻ መንፈስን መገንባት ለማንም አይበጅም። የአንድ ብሄር አባላትን በጭፍን መጥላትና ማጥላላት ሄዶ ሄዶ ወደ ግጭት ማምራቱ አይቀርም። በምክንያታዊነት ግልሰቦችን ከመንቀፍ፣ ከመደገፍና ከመቃወም ይልቅ የግለሰቦችን ሃሳብ በብሄር ላይ መለጠፍ የከፋ ውጤት ያስከትላል። ይህ አስተሳሳብ በየትኛውም ሰው ውስጥ ቢኖር እንኳ አስተሳሰቡ በእንጭጩ መቀጨት አለበት። አንድን ብሄር ወይንም ሐይማኖት መጥላት እና በእዚህ ላይ በክፋት መነሳሳት የሚጎዳው አንድ አካል ብቻ አይደለም። ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የሚደርሰው ድርጊቱን በሚፈፅሙት ግለሰቦችም ወይንም ቡድኖች ጭምር ነው።
እንዲሁም በአንድ ጊዜ በተወሰነ ቦታ የሚፈፀም ዘግናኝ ድርጊት ሊቀጣጠልና ሊስፋፋ እንደሚችልም መረዳት ያስፈልጋል። የማያቋርጥ ጥፋትና መራር ኀዘን በመላው አገሪቱ ሊያስከትልም ይችላል። ሐይማኖት ከሐይማኖት ብሄርን ከብሄር ለማጋጭት የሚደረጉ ሴራ ወለድ ጥረቶችን ማምከንና ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው መንግሥት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሲያበረክትም ነው። ለአገር መፍረስ መንስኤ ሆኖ መገኘት የታሪክ ተወቃሽነትን ከማስከተል አልፎ፤ በዚሁ ጥፋት የራስ ቤተሰብን እስከማጣትና ለዘላለም የራስንም ህይወት አደጋ ላይ እስከመጣል ሊያደርስ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል።
ሰው በህይወት ዘመኑ ቤተሰቡን፣ አገሩን እና ዓለምን ሊጠቅም ሲገባው በተቃራኒው በረባው ባረባው ምክንያት እየፈለገ ሰዎችን በማንነታቸው ወይም በሐይማኖታቸው ማጥቃት ኢሞራላዊ ነው። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ብሔርን ወይም ሐይማኖትን ማዕከል ያደረገ ጭፍጨፋ እንዲካሄድ፤ አገር እንድትበተን የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ነጋሪ አያሻም። የአገር የመበተን ፍላጎት ከጀርባው ምን እንደሆነም ይታወቃል። ዋነኛው መንስኤ የኢትዮጵያ ማደግ የእነርሱ ውድቀት መንስኤ ይሆናል ብለው የሚያምኑ አካላት የተፈጠረባቸውን ስጋት ነው። ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ አይጠፋም እንደሚባለው ሁሉ እነዚህ አካላት በሚጎነጉኑት ሴራ ተጠልፈው እና አንዳንዴም በተለያየ ጥቅም ተታለው የአገር ሰላምን ለማወክ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አሉ።
በአንጻሩ ደግሞ የአገርን ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ የሚተጉ ብዙ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊያ እንዳሉ ይታወቃል። በተለይ አክራሪ ብሄርተኝነት ያመጣውን ጣጣ ተከትሎ ተጠቃ በሚባለው ወገን በኩል ያሉ ከፍተኛም ሆነ መካከለኛ አመራሮች ‹‹አገር ይበልጣል›› ብለው በትዕግስት ማለፋቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። እርግጥ ነው ኃላፊነት ቦታ ላይ ካለ ሰው የሚጠበቀው ትዕግስትና አስተዋይነት ነው።
በእርግጥም በለው፣ ቁረጠውና ፍለጠው ማለት ማንንም አይጠቅምም። ስለዚህ የኢትዮጵያን ዕድገት ከማይፈልጉ የውጭ አገራት ትዕዛዝ በመቀበልና ራሳቸውም ትዕዛዝ በማስተላለፍ በአገሪቱ ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችንና ግለሰቦችን ሁሉም ለራሱ ሲል ከወዲሁ መከላከል አለበት። ምክንያቱም ግጭት የሚያስከትለው ጠባሳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በአጥቂውም ሆነ በተጠቂው በኩል የሚደርሰው ውድመትና ጦስ ብዙ ነው። ድህነትን ያስፋፋል። የሰዎችን ህይወት ይቀጥፋል። ንብረትን ያወድማል፤ የሰዎችን ኑሮ ያናጋል። በአጥቂው ጎራ የተሳተፉ ኃይሎች በጊዜያዊ ስሜት ተነሳስተው ባደረሱት ጉዳት ውለው አድረው ከፀፀት ሊድኑ አይችሉም።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚከፍለው ግብር የተማረው አካል፤ በአጉል የጥቅም ትስስርና በተዛባ አመለካከት ህዝቡን ለአደጋ ሊያጋልጠው የሚችል ተግባርን ከመፈፀም መቆጠብ አለበት። መንግሥት ብቻውን ሊያደርግ የሚችለው ነገር የለም። ህዝቡ ለራሱ ሲል የአገሩን ሰላም ማስጠበቅ አለበት። ጥርጣሬ ሲያድርበት ለጸጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት አለበት። አካባቢውን ተደራጅቶ መጠበቅ ይኖርበታል።
ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየው አክራሪ ብሄርተኝነትና የሐይማኖት ጸንፈኝነት በአንድ ጀንበር የተወለደ አይደለም። ላለፉት 27 ዓመታት ተኮትኩቶ ያደገ ነው። ለአብነት ያህል ከሁለት ዓሥርት ዓመታት በላይ ሆን ተብሎ አገሪቱን በዘር ከመከፋፈል ጀምሮ እስከ ግል መታወቂያ ካርድና የመኪና ሰሌዳ ቁጥሮች ድረስ የዘለቀው መለያ የሚፈጥረው ልዩነት ቀላል አይደለም።
ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ህዝባዊ አደረጃጀቶች ህዝቡን መከፋፈል አንድ በሚያደርጉን የጋራ አገራዊ እሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት አለባቸው። ሁሉንም እኩል የሚያሳትፍ የጋራ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠርም ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፉት ዘገባም ጥንቃቄ ያሻዋል። እንዲሁም አንድ ኢትዮጵያዊ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ወንድሙ እና እህቱ መሆናቸውን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም። ማንም ሰው ቢሆን በማንም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ማስከተል አይገባውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሐይማኖትና ብሄር ሳይለይ አብሮ የኖረ ፣በጋብቻ የተዛመደ ነው።
የጥላቻ ሃሳብ ለሚጠነስሱና አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ፤ ጥቃት እንዲፈጽም ለሚያነሳሱ እንዲሁም ለሚገፋፉን መንግሥት ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት ቢኖርበትም ህዝብም ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ችግር ፈጣሪዎቹን ሊያጋልጥ፣ አሳልፎ ሊሰጥ እና ሊመሰክርባቸው ይገባል።
በእርግጥ ከግጦሽ ጋር ተያይዞና በሌሎችም አንዳንድ ምክንያቶች ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ግጭቶች በአገር ሽማግሌዎች በዕርቅ እየተፈቱ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ዛሬም መሰል ግጭቶች እንዳይከሰቱ መከላከል ያስፈልጋል። ተከስተው ሲገኙ ደግሞ በቆየው የአገራችን ባህል በሽምግልና መፍታት ይገባል እንጂ የግጭት ነጋዴዎች ሰለባ መሆን አይገባም።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013