በኢትዮጵያ ባህል መሰረት ወዳጅ ማለት በደስታና በበጎ ቀናት ብቻ አብሮ የሚሆን አይደለም፤ በአስቸጋሪና በፈታኝ ወቅቶችም አብሮ የሚቆም ፣ አለሁ የሚል ፣ አብሮነቱ ከቋንቋና ከቃላት በላይ የሆነ ፤ ለችግሮች ራሱን የመፍትሔ አካል አድርጎ የሚያቀርብ ፣ የታላላቅ ሰብዓዊ እሴቶች ባለቤት የሆነ ማለትም ነው።
ኢትዮጵያውን ለወዳጆቻቸው ያላቸው አክብሮት ከነዚህ ትላልቅ ሰብዓዊ አሴቶች የመነጩና ከፍተኛም ናቸው፡፡ በቀደመው ሆነ በዚህም ዘመን ወዳጆቻቸውን የመዘከር ፣የማክበርና እውቅና የመስጠት ማህበራዊ እሰቶች ባለቤቶች ናቸው።
በተለይም አስቸጋሪ በሆኑ ወቅቶች ከጎናቸው የቆሙ እንደ ወርቅ በአሳት የተፈተኑ፣ የነጠሩ ወዳጆቻቸውን ከጉዳዩም በላይ አድርጎ በመውሰድ በታሪካቸው ውስጥ የጎላ ቦታ ይሰጣሉ። ትውልዶች ለሀገር ባለውለታዎች ከበሬታ እንዲኖራቸውም ከፍ ያለ ጥረት ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ከሚያጋጥሟቸው የመከዳት አጋጣሚዎች አንጻር እነዚህ ባለውለታዎች በያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የሚፈጠረው የመከዳት መንፈስ ሊፈጥር የሚችለውን ቁዘመና ተስፋ መቁረጥ በመግራት መታመን ከምንም በላይ የተሻለ መሆኑን እንዲያስቡ ጥሩ ዕድል ይፈጥራሉ።
አሁን ባለው የሀገሪቱ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ በተለይም ለውጡን ተከትሎ በሀገሪቱ የተጀመረውን የመሻገር ጉዞ ለማሰናከል እጅግ የበዙ፣ በሀገሪቱም ታሪክ ያልታዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ ናቸው። እነዚህ በውስጥና በውጭ ባሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ቅንጅትና መናበብ እየተፈጠሩ ያሉ ተግዳሮቶች ከፍተኛ የአሰላለፍ ለውጦች የታዩባቸውም ጭምር ናቸው።
ለዘመናት በወዳጅነት አብረውን የቆዩ፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተሻለ ወዳጅነት የሚያከብራቸው የአሜሪካ መሪዎች ሳይቀሩ የለውጡን ተስፋዎች አደጋ ውስጥ የሚከቱ ፍትሐዊነት የጎደላቸው የጫና ተግባራትን በአደባባይ ተግባራዊ ሲያደርጉ ይታያል።
በርግጥ በአሜሪካ ወደ ስልጣን የሚመጡ ገዥ ፓርቲዎች እና ግለሰቦች በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ላይ ያልተገቡ ውሳኔዎች በማሳለፍ ሀገራችንን ለከፍተኛ አደጋዎች ያጋለጡባቸው ጊዜያት ጥቂት ባይባሉም፣ የአሁኑ ግን በዓይነቱም በድርጊቱም ይለያል።
በኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ስልጣን ላይ የነበረው አምባገነናዊ ቡድን በህዝባችን ላይ ከፍ ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፣ የዴሞክራሲ መብት አፈናና የሀገር ሀብትና ንብረት ዘረፋ ሲያካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ቡድን በብዙ መስዋእትነት ላይመለስ የተወገደ ቢሆንም፣ የባይደን አስተዳደር ለእዚህ የአሻባሪው የህወሓት ቡድን ሕይወት ለመስጠት የሚያደርገው ጥረት የብዙ ኢትዮጵያውንን ልብ ሰበሯል።
በአንድ በኩል ስለ ሰብዓዊ መብት እና ስለ ዴሞክራሲ ጠበቃ ነኝ የሚለው በስልጣን ላይ ያለው የዴሞክራቶች መንግሥት ኢትዮጵያውያን ብዙ ተስፋ ያደረጉበትን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጅማሮ ከመደገፍ ይልቅ ፣ ይህን ሽብርተኛ ቡድን እንደ ዱቄት ከተበተነበት አየር ሰብስቦ ህይወት ሊሰጠው እየሄደበት ያለው መንገድ ኢትዮጵያውያን ከዴሞክራቱ ፓርቲና ከባይደን አስተዳደር ተስፋ ያደረጉትን እውነት አጨልሞታል።
የባይደን አስተዳደር በአደባባይ የሚታየውን የአሸባሪውን የህወሓት የትናንት እና የዛሬ እኩይ ድርጊት አይቶ እንዳላየ ፣ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኗል፤ በተገዙ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ በተቀጣሪ ሎቢስቶች እና መርህ አልባ በሆነ ግንኙነት የብድኑ የጡት አባት በሆን ከሀገሪቱ የቀድሞ ባለስልጣናት የሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ እየተላለፈ ያለው ውሳኔ አሜሪካን ከሚያህል ታላቅ ሀገር እና ከኢትዮጵያ ጋር በወዳጅነት ዘመናትን ካስቆጠረ መንግሥት የሚጠበቅ አልነበረም።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ጥቅሞች ላይ ሲያራምዱት ከነበረው የተዛባ ኣና ኢፍትሐዊ ከሆነው መንገድ ጋር አንጻጽረው የባይደን አስተዳደር በተሻለ ፍትሐዊነት ይመጣል የሚል እምነት ነበራቸው። በዚህም በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን እስከ መጨረሻው ለባይደን ድል ድጋፋቸውን ለግሰዋል። ከድሉ በኋላ በተጨባጭ እየተስተዋለ ያለው ግን የቀደመውን የተዛባ እና ኢፍትሐዊ መንገድ ማስቀጠል ሆኗል።
በባይደን አስተዳደር በኩል ያሉ እውነታዎች መላውን ህዝባችንን እያሳዘኑ ፤ ህዝባችን በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት ዳግም በአሜሪካ አስተደዳር የመከዳት መንፈስ እየተሰማው ባለበት ሁኔታ ፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ እውነትና ስለ ፍትህ ፤ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵውያን በመሞገት የክፉ ቀን ወዳጅነታቸውን በተግባር ያሳዩት ሴናተር ጂም ኢንሆፌ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ባለውለታ መሆን ችለዋል።
ሴናተር ጂም በአንድ በኩል የአሸባሪው ህወሓትን እውነተኛ ማንነት ለአሜሪካ ህዝብ እና ለመላው ዓለም ቡድኑን በሚመጥነው ስም በመጥራት በአደባባይ አስታውቀዋል፤ በተገዙ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፤ በተቀጣሪ ሎቢስቶች እና መርህ አልባ በሆነ ግንኙነት የብድኑ የየጡት አባት በሆኑ የቀድሞ ባለስልጣናት የሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች ትክክል እንዳልሆኑ በአደባባይ ሞግተዋል፤ አውግዘዋል።
ከዚያም በላይ ለእውነት ጆሮ ባለመስጠት የተዛቡ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ የባይደን አስተዳዳር በኢትዮጵያ ላይ እያደረገ ያለው ጫና እና ክልከላ ትክክል እንዳልሆም በመግለጽ የኢትዮጵያውያንን እውነት የሸፈነውን አቧራ በመጥረግ ሴናተር ጂም ኢንሆፌ ለሀገሪቱና ለህዝቦቿ የክፉ ቀን ወዳጅነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል።
ለእውነትና ለእውነት ብቻ ያላቸውን ተቆርቋሪነት በአደባባይ አሳይተዋል፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለጀመሩት የለውጥ ጉዞ ያላቸውን ከበሬታና አጋርነት በልበ ሙሉነት በመግለጽ የኢትዮጵያውያንን የነገ ተስፋዎች ተመልክተው ምስክር መሆን ችለዋል።
ኢትዮጵያውያን እውነት በራሱ አርነት እንደሚያወጣ ካላቸው ጠንካራ እምነት፤ ከሁሉም በላይ ሴናተር ጂም ኢንሆፌ ለእውነት ላላቸው ተቋርቋሪነት ከፍ ያለ ክብር ይሰጣሉ ። የሀገራችንንም የለውጥ ተስፋ በማየት ላሳዩት የተስፋ አጋርነታቸውም ያለን አክብሮት ከፍተኛ ነው።
ይህ የሴናተር ጂም ኢንሆፌ አጋርነት ለውጡ ለመጪው ትውልድ ይዟት ከመጣው ከፍያለ ተስፋ አኳያ ፤ በዚህ ትውልድም ሆነ በመጪዎቹም ትውልዶች ከፍ ያለ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡ በኢትዮጵያና በአሜሪካ ህዝቦች መካከል የቆየውን የወዳጅነትና የወንድማማችነት መንፈስ በማደስም በታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013