ከግንባታ ሥራ መሠረት ማውጣትና የማጠናቀቂያ ሥራ (ፊኒሺንግ)ጊዜ በመውሰድና በወጪም ከባድ እንደሆነ ይነገራል። በተለይም ለማጠናቀቂያ ለወለል ንጣፍ የሚውለው የሴራሚክ የግንባታ ግብአት በአብዛኛው ከውጭ የሚገባ በመሆኑ በገበያ ተለዋዋጭነት ወጨው በየጊዜው ከፍ እያለ ዘርፉን እየፈተነው እንደሆነ፣በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ጋር ተያይዞ የግብአቱ ዋጋ እየናረ መምጣቱ በገሀድ የሚታይ ሀቅ ነው። ለሴራሚክ የሚሆን የጥሬ ዕቃ ግብአት በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ ከመኖሩ በተጨማሪ ምርቱም በመመረት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ የጥሬ ዕቃ ሀብቱ ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑና ተመርቶ በመቅረብ ላይ ያለውም በጥራት መጓደል፣ በበቂ ሁኔታ አቅርቦት አለመኖሩ፣በዋጋም ቢሆን ከውጭ ከሚገባው ጋር ተቀራራቢ መሆኑ በቅሬታነት ሲነሳ ይደመጣል።
የሴራሚክ ዋጋን በገበያ ላይ ባደረግነው ምልከታ እንደየአካባቢው መጠነኛ ልዩነት ቢኖርም ተቀራራቢ ዋጋ ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። ሆቴልቤቶችና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎች ማጠናቀቂያ በስፋት የሚውለው ፖርስሊን (ለስላሳው) የተባለው የሀገር ውስጥ ምርት 60 በ60 ስፋት ያለው በካሬ 485ብር፣ሻካራው ደግሞ 380ብር፣40በ40 ስፋት ያለው 370ብር፣30በ30 ስፋት ያለው 360ብር በመሸጥ ላይ ነው።ከውጭ ከሚገባው ጋርም በንጽጽር በዋጋ በእጥፍ ይጨምራል። ለመፀዳጃና ለማብሰያ ቤት ግድግዳ ማሳመሪያ የሚውለው ሴራሚክም እንዲሁ በተለያየ ዋጋ በመቅረብ ላይ ነው። በዋጋ፣በአቅርቦት፣በሀገር ውስጥ ስላለው ለሴራሚክ የሚውል የጥሬ ዕቃ ሀብት ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎች በማነጋገር እንደሚከተለው ቃኝተናል።
የባማኮን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግርማ ገላው እንዳብራሩት በግንባታ መሰረት ማውጣትና የሴራሚክ ግብአት አቅርቦት የተለያዩ ቢሆኑም በሁለቱም ላይ የሚስተዋሉት ክፍተቶች በሁለት መንገድ ይገለጻል። የሕንፃ መሠረት የማውጣት ሥራ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም፣የሙያ ክህሎትና ጥሩ የሆነ አስተዳደር ይጠይቃል። በመሆኑም የተቋራጮች አቅምና ብቃት የሚለካው በቅድመ ግንባታ ወቅት የሚያደርገው ዝግጅት ወይንም በሚያወጣው ዕቅድ ነው። ቀድሞ ሳያቅዱ ሥራው ስለተገኘ ብቻ ለመሥራት መሞከር ጉዳቱ ያመዝናል። ሌላው በቂ የሆነ ግብአት አለመኖር ነው። በሲሚንቶ ግብአት አቅርቦት አለመኖር ድርጅታቸው የፕሮጀክቶች መጓተት አጋጥሞታል። በወለል ንጣፍ ሲራሚክም በኩል በተመሳሳይ የሕንፃ ሥራው ከመጀመሩ በፊት መታቀድ አለበት። በአንዳንዶች ያለው ተሞክሮ ሴራሚክ ሲፈልጉ ከባንክ ገንዘብ የመጠየቅ ሁኔታ ሲኖር፣ በአንዳንዶች ደግሞ ሊያጋጥም የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ቀድሞ በማቀድ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት ይደረጋል።
ምንም እንኳን ዕቅዱና የገበያው መለዋወጥ ላይጣጣም ቢችልም ቀድሞ አቅዶ መንቀሳቀሱ በመጠኑም ቢሆን ሊያጋጥም የሚችለውን ክፍተት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መቀነስ ይቻላል። አላስፈላጊ የሆነ ጥድፊያና ጭንቀት ውስጥ ከመግባት ያድናል።
በሀገር ውስጥ ተመርቶ እየቀረበ ስላለው የወለል ንጣፍ ሴራሚክም ኢንጂነር ግርማ እንደገለጹት፤ አሁን ባለው የግንባታ ሥራ በሀገር ውስጥ ተመርቶ በሚቀርበው ሴራሚክ እንደሀገር መሸፈን የሚቻልበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም። በጥራት በማቅረብ በኩልም ብዙ መሥራት ይጠይቃል። በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ ተመርተው የሚቀርቡ የሴራሚክ ግብአቶች በጣም ቅንጡ ለሚባሉ የግንባታ ሥራዎች የሚውሉ አይደሉም። ከውጭ በሚገቡ የሴራሚክ ግብአት ነው የሚሠራው። ወጪ ቆጣቢ ለሆኑ የግንባታ ዓይነቶች ግን የሀገር ውስጥ በስፋት እየዋለ ነው። ዕድገት ሲመጣ ጥራትም አብሮ ይፈለጋል። ዕድገት ሲመጣ ቀደም ሲል ከቻይናና ከህንድ ይገቡ የነበሩት ቀርተው የሌላ ሀገር ምርት ሊፈለግ ይችላል።በመሆኑም በሀገር ውስጥም የሚመረተው ምርት ሁሌም በተመሳሳይ እንዲሆን አይጠበቅም።ወቅቱን ማገናዘብ ይኖርበታል።
በሀገር ውስጥ በጥራትና በዋጋ የሚስተዋለው ክፍተት ሊቀረፍ የሚችለው በዘርፉ ብዙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተከፍተው በሥራ ላይ ሲሆኑና በመካከላቸው ውድድር ሲፈጠር እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጂነር ግርማ፤ የሀገር ውስጥ የሴራሚክ ምርት ከውጭ ከሚገባው ጋር ተቀራራቢ በሆነ ዋጋ መቅረቡንም ይቃወማሉ። በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ ተመርቶ የሚቀርበው የሴራሚክ ምርት በካሬ ከ10 እስከ 12 ዶላር ዋጋ እየተሸጠ መሆኑንም አስታውሰዋል። የአመራረት ሂደቱን ስለሚያውቁት አግባብ ባልሆነ ዋጋ ገበያ ላይ መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ። ችግሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና፣ተወዳዳሪ አለመኖር ሀገሪቱ የምትከተለው ነፃ የገበያ ሥርዓት ፋብሪካዎቹ አምራችም፣ ዋጋ ተማኝ፣ አከፋፋይ እንዲሆኑ መንገድ እንደከፈተላቸው አስረድተዋል። ‹‹በመንግሥት በኩል ዘርፉ እንዲበረታታ በማድረግ በውድድር ሥራዎች ቢሠሩ በተለይም በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ የገንዘብ ብድር ቢመቻች ለሴራሚክ ግዥ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል። በጥናት የታገዘ ሥራ ቢሠራ ደግሞ የበለጠ ውጤት ይመዘገባል›› ሲሉም አክለዋል።
ሌላው ሃሳባቸውን ያካፈሉን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግርማ ሀብተማርያም ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት ለግንባታ ማጠናቀቂያ የሚውለው የወለል ንጣፍ ሴራሚክ ምርት ሀገር ውስጥ ቢቀርብም በብዛትም ሆነ በጥራት ከውጭ ምርት ጋር ተወዳዳሪ ባለመሆኑ አብዛኛው የሕንፃ ተቋራጭ ከውጭ የሚገባውን ምርት መጠቀም ይመርጣል። እስከዛሬ ያለው ተሞክሮ ይሄ ቢሆንም፤ በኮቪድ 19 ቫይረስ ምክንያትና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ከውጭ የሚገባው የሴራሚክ ዋጋ ንሯል።ችግሩንም በሁለቱም መንገድ ይገልፃሉ።
ለእርሳቸው በሀገር ውስጥ ከሚመረተው ሴራሚክ ይልቅ ለቤት ወለል ንጣፍ የሚውለው ታይልስ የተባለው ግብአት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢንጂነር ግርማ መፍትሔ ይሆናል ያሉትንም ጠቁመዋል። አሁን ሀገሪቱ እየገጠማት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ግብአቱን ከውጭ በማስመጣት የግንባታውን ሥራ ለማከናወን በረጅም ጊዜ ችግር ሊያጋጥም ይችላል። የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ አለመገታትም ችግሩን ያባብሰዋል። በሀገር ውስጥ በስፋትና በጥራት እንዲመረት ማበረታታት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።
አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ግብአቱን ለማምረት የሚያስፈልጋቸው ማሽን ወይንም መሳሪያ በማሟላትና ሌሎች አስፈላጊ እገዛዎችንም ማድረግ ከመንግሥት ድጋፍ ይጠበቃል። በዚህ መልኩ በትኩረት ካልተሠራ በመንግሥትም ሆነ በግለሰቦች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ይስተጓጎላሉ። ሥራ ሲቆም ብዙ ጫና ያስከትላል። ጫናውም ኮትራክተሮች በገቡት ውል መሰረት ግንባታውን በወቅቱ አጠናቅቆ ባለማስረከብ፣ኮንትራክተሩ የሚጠይቀው የጊዜ ማስተካከያ ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋል። በተለያየ የግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከሥራ ውጪ ይሆናሉ። ይሄ ደግሞ ከግለሰብ አልፎ ሀገር ላይ ኪሳራ ያስከትላል።
ለሴራሚክ የሚውለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ምን ይመስላል? ሀብቱስ አለ ወይ? በሚለው ዙሪያም ባደረግነው ቅኝት ሰሞኑን በወዳጅነት ፓርከ ለሁለት ሳምነት በተካሄደው የኢትዮጵያ ሳምንት ፌስቲቫል ላይ የአካባቢያቸውን የተፈጥሮ ፀጋና እምቅ ሀብት ይዘው ከቀረቡት ክልሎች መካከል የአማራ ክልል አንዱ ነበር። ክልሉ ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ፣ለኢነርጂና ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ ሀብቶቹን ይዞ ነበር የቀረበው። ክልሉ ሀብቱን በማስተዋወቅ በዘርፉ ለመሰማርት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በክልሉ ምቹ ሁኔታ መኖሩን በመጋበዝ ነበር ሳምንቱን የተጠቀመበት።
በሙያቸው ጂኦሎጂስት የሆኑትና በክልሉ መአድን ኤጀንሲ ውስጥ የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዝናው አበበ፤ በክልሉ ስለሚገኘው ሀብት እንደገለጹልን ክልሉ በቅርቡ ጥናት አድርጎ ከለያቸው ሀብቶች አንዱ ግራናይት የሚባለው ጥሬ ሀብት ሲሆን፣ ከሁለት መቶ ስኩዌር በላይ በሆነ ስፋት ቦታ ላይ በምሥራቅ ጎጃም ጉዛመን ደብረኤሊያስ ወረዳ ጭምት ቀበሌ ውስጥ ከፍተኛ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። በምዕራብ ጎጃም ደግሞ ቡሬ ነቀምት መሥመር አባይ ጎርጅ በተባለው አካባቢና በአዊ ዞን በተመሳሳይ የግራናይት ክምችት መኖሩ በጥናት ተለይቷል። በጥናት የተለዩት ግብአቶችም ቡናማ፣ነጭና ቡላ ቀለም ያላቸው ውበት ያላቸው ናቸው። ግብአቱ ለመሬት ወለል ንጣፍ፣ለመፀዳጃና ለማብሰያ ቤቶችና ለሌሎችም ለግድግዳ ማስዋቢያ እንዲሁም ለጠረጴዛና ለእቃ ማጠቢያ እንደአስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ለሚውሉ ለግንባታ ማጠናቀቂያ የሴራሚክ ውጤት ይውላል። ክልሉ የተለያየ ቀለም ያለውን የግራናይት ግብአት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገባውን የሴራሚክ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከማዳን በተጨማሪ ለዜጎችም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነትን ለማሳደግም ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ እንደሆነም ከአቶ ዝናው ለመረዳት ችለናል።
ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት ተለይቶ የተገኘው ሀብት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ሆኖ ፍላጎት ያሳዩ ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባት ችለዋል። በዚሁ መሠረትም ባህርዳር ከተማ ላይ ባይካ የተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ቡሬ ላይ የተገኘውን ሀብት በመጠቀም የሴራሚክ ምርት ለማምረት ፋብሪካ አቋቁሞ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣የሙከራ ምርት በማምረት ሦስተኛ ወሩን ይዟል። አንዳንዶችም የማምረቻ ማሽን በመትከል ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ግብአቱ ከሚገኝበት ቦታ በቁፋሮ አውጥተው ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለሚያቀርቡና ለሚያመርቱ ከ30 በላይ ለሚሆኑ ድርጅቶች ከክልሉ ፈቃድ አግኝተዋል።
እንደ አቶ ዝናው ገለጻ የተገኘው ሀብት በጥናት የተለየ እንጂ ከፍተኛ እንደሆነ ይጠበቃል። የአዋጭነት ጥናት ያቀረቡ በግላቸው የሚንቀሳቀሱም በመኖራቸው ወደፊት ሰፊ ሀብት እንደሚገኝ ይጠበቃል። ለሲሚንቶ ግብአት የሚውሉ ላይምስቶን እና ጂብሰም የተባሉ ግብአቶችም ምሥራቅ ጎጃም ደጀን እና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ከፍተኛ ክምችት ይገኛል። በተለይም ላይምስቶን የተባለው ግብአት 80 በመቶ ለሲሚንቶ ይውላል።በመሆኑም አስፈላጊ ነው። የግብአቱን መኖር ተከትሎም በቁጥር አምስት የሚሆኑ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሥራ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ለግንባታ ዘርፉ ከሚውሉ ከእነዚህ ግብአቶች በተጨማሪ በተለይም ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለማምረቻ የሚጠቀሙበት የድንጋይ ከሰል ክልሉ የጥሬ ዕቃ ግብአትም አለው። ፋብሪካዎቹ ግብአቱን በስፋት ከሱዳንና ከደቡብ አፍሪካ ሀገሮች በማስመጣት የሚጠቀሙ በመሆናቸው በሀገር ውስጥ በመተካት ፋብሪካዎች በወጪና በውጣውረድ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው። የድንጋይ ከሰል አማራጭ የኃይል ምንጭ በክልሉ 10 ወረዳዎች ውስጥ በስፋት ለመሥራት ታቅዷል።
ከክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መካከል ለግንባታው ዘርፍ የሚውሉ ጥሬ ግብአቶችን ከመሬት ማውጣትና እሴት ጨምሮ ማምረት እንደሆነ የገለጹልን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይሄነው ዓለም፤በክልሉ በዘርፉ ከክልሉ አልፎ ሀገርንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እምቅ የሆነ ሀብት ቢኖርም በጥናት ያለውን ሀብት ለመለየት፤ የገንዘብ አቅምና እውቀት እንዲሁም ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ በሚፈለገው ያህል ጥቅም ላይ አለመዋሉን ያስረዳሉ።
የሀብቱን አጠቃላይ መጠንና ጥራት ለማወቅ ከፍተኛ አቅም ይጠይቃል። በክልሉ አቅም መሥራት በተቻለው የተወሰነ ሀብት ማግኘት ተችሏል። ክልሉ ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማጠናከርና ፍላጎት ያላቸውንም ባለሀብቶች ለመሳብ የኢትዮጵያ ሳምንት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። እውቀቱ፣ቴክኖሎጂው የገንዘብ ሀብቱ ያለው በዘርፉ እንዲሰማራም ጥሪ አቅርበዋል። ክልሉ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የማእድን ኤጀንሲ ቢሮ በማቋቋም ሀብቱ የሚገኝበትን ቦታ ከማሳየት ጀምሮ የሥራ ፈቃድ በመሰጠት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የግንባታ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ባለበት በዚህ ወቅት በራስ ሀብት አለመጠቀም ቁጭት ሊያሳድር ይገባል። በዘረፉ የተሰማሩትም ቢሆኑ ከጊዜያዊ ጥቅም ወጥተው በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዘርፉን በማገዝ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መልዕክታችን ነው። እንደ ሀገር እስከዛሬ በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ባልተገኘባቸው የማዕድን ሀብትና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ በትኩረት እየተሠራ በመሆኑ ወደፊት ተስፋ ሰጭ የሆነ ውጤት እንደሚገኝ ይጠበቃል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013