ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ተከታታይ ወራት ልታሳካ የወጠነቻቸው ሁለት ብርቱ ጉዳዮች አሏት-ምርጫና ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት። ይሁንና እነዚህን ሁለት ትልልቅ ክዋኔዎች ለመተግበር የማንንም ፈቃድና እገዛ ሳትጠይቅ እያከናወነች ትገኛለች። ባለመጠየቋና አቃተኝ ብላም ባለማቆሟ እድገቷን ለማይፈልጉ አንዳንድ ሃገራት አላስደሰታቸውም። በዚህ የተነሳ ከአሜሪካና ከአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ጫና እየደረሰባት ይገኛል።ነገር ግን ከጥንትም ጀምሮ ጥቃትን የማይወዱት ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን በማጠናከር ይህንን ጫና እየተቃወሙት ይገኛሉ። እኛም ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም አሜሪካ ከሰሞኑ ባወጣችው መግለጫ ላይ ተንተርሰን ለዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያን ወክለው በኒዮርክ ሲሰሩ ከነበሩት ከቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ጋር በተለይ ከዲፕሎማሲው አንጻር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘንላችሁ ቀርበናል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
አዲስ ዘመን፡– አፍሪካን በተመለከተ የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂ ምን ላይ የተመሰረተ ነው? የተመሰረተው መናጠቅ ላይ ወይስ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– አሜሪካንንም ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት አፍሪካን በተመለከተ ዲፕሎማሲ በጣም የተጠና እና የታሰበበት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አውጥተው በስራ ላይ የሚያውሉበት ጊዜ አነስተኛ ነው። ብዙ ጊዜ አስተውለሽ ከሆነ ምዕራባውያኑም ሆኑ በተለይ አሜሪካኖች በሚሰየሙበት ጊዜ የውጭ ጉዳዮቻቸውን በተመለከተ በአብዛኛው የሚያወሩት ስለአውሮፓ፣ ስለኢስያ፣ ስለላቲን አሜሪካ፣ ስለመካከለኛው ምስራቅና የመሳሰሉ አገሮች ላይ ነው። አፍሪካውያንን የሚያመጡት ምናልባት መጨረሻ አካባቢ ነው። በተለይ አሜሪካኖች ናቸው ይህን የሚያደርጉት።
ወደምዕራብ ስንሄድ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ለያይተን ማየቱ ጥሩ ነው። አውሮፓ ቅርባችን ነው። አፍሪካ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በአውሮፓ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያስከትላል። ለምሳሌ ከአፍሪካ የሚነሳው የሰው ፍልሰት የሚሄደው ወደ አውሮፓ ነው። ይህ ደግሞ በአገራቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስን የሚፈጥር ነው። ከዚህም የተነሳ የአፍሪካውያንን ጉዳይ አውሮፓውያን የሚመለከቱት በጣም በቅርበት ነው።
አሜሪካ ከዚህ አንጻር ትለያለች፤ አፍሪካውያንን በተለይ በአሁኑ ጊዜ ትንሽ በአሜሪካ እና በቻይና እንዲሁም መሰል አገሮች በመጠኑም ቢሆን ውድድር እየተነሳ ነው። እንዲህም ስል ውድድሩ የቀድሞው ቀዝቃዛ አይነት ጦርነት ባይሆንም በአገራቱ መካከል አፍሪካውያንን እያንዳንዱ ወደእርሱ ለመውሰድ ነው ጥረትና ውድድር የሚያደርጉት።
ቻይናውያኑ አፍሪካውያኑን በገንዘብ፣ በንግድ እንዲሁም በኢኮኖሚ በጣም እየሳቡ ነው። ሌሎቹ ግን በአሁኑ ወቅት ከመቼም ጊዜ የበለጠ በአፍሪካ አካባቢ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። የሚንቀሳቀሱት ግን ኢንቨስትመንት ይዘው መጥተው አሊያም ገንዘብ ደግፈው፣ ንግድ አስፋፍተው አይመስልም። ነገር ግን ያላቸውን ለስላሳ ኃይል ማለትም የሰው ኃይሉን፣ ሚዲያውን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና የመሳሰሉትን በመጠቀም አፍሪካ ወደእነዛ እንዳታዘነብል የማድረግ ሁኔታ ነው በአሁኑ ጊዜ እየተንጸባረቀ ያለው። ለዚህ ነገር ታጥቀውም ተነስተዋል። ምክንያቱም በቻይና እና በአሜሪካ የሚደረገው ውድድር ዓለማቀፋዊ ነው። እናም ይህ ዓለማቀፋዊ ውድድር በአፍሪካ ትንሽ ጠንከር ሳይል አይቀርም። ምክንያቱም ቻይና በኢንቨስትመንቱም ሆነ በሌላ በጣም ገፍታበታለች። በመሆኑም እነዛዎቹ ይህን አካሄድ ዝም ብለው ማየትን አይሹም።
አዲስ ዘመን፡– ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ስርዓት ወደየት እየሄደ ነው ማለት ይቻላል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– በአሁኑ ወቅት በሽግግር ላይ ነው። እኔ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ዓለም በመስቀለኛ መንገድ በሚል ርዕስ አንድ አርቲክል ጽፌ ነበር፤ ዛሬም የምደግመው ያንን ሐሳብ ነው። ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ በዓለም ላይ ሁለት ኃያላን ነበሩ። እነዚህም ራሽያና አሜሪካ ናቸው። እነዚህም የኒውክሌር ኃይል ነበራቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አገሮች የምዕራብ ተከታይ፤ የምስራቅ ተከታይ በሚል በእነዚህ በሁለቱ አገራት ተርታ የተሰለፉ ነበሩ።
በኋላ ላይ ሶቪዬት ህብረት በምትወድቅበት ጊዜ አንድ ኃይል ብቻ በዓለም ላይ እኤአ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ገኖ ወጣ።
ይህ ኃይል እስከአሁንም ድረስ ያለው አንድ ኃይል እኔ ነኝ እያለ ነው። ነገር የሆነው ነገር ሌሎቹ ሶቬዬት ህብረት ሲወድቅ ራሽያም ወድቃ አልቀረችም፤ ቻይና ደግሞ በጣም በጠነከረ ሁኔታ በሚሊታሪም፣ በኢኮኖሚም፣ በቴክኖሎጂም ሆነ በንግድ በአፍሪካ ላይ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ አሜሪካንን በሚያሰጋት ሁኔታ መውጣት ጀመረች። ስለዚህ አሁን ያለው ሁኔታ መልቲፖላር (ብዙ ኃይላት) እየወጡበት ያለ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ነው ያለው።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ አሜሪካ እያለች ቻይና የምትባል አገር አሜሪካንን ረግጣ ወደከፍታ በመውጣት የዓለም መሪ አትሆን ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል። ቻይና ደግሞ እኔ ከማንም ጋር አልወዳደርም፤ ነገር ግን የዓለምን ህዝብ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት አሳድጌ አብሬ ለማደግ ዝግጁ ነኝ። ከዚህ የሚያግደኝ የትኛውም ኃይል የለም ብላለች። ይህ ማለት በተለያየ ቋንቋ እኔ የራሴን አካሂዳለሁ አንቺ ደግሞ የራስሽን አካሂጂ ነው።
እነዚህ ሁለቱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች እየወጡ ያሉ ኃያላን አሉ። ለምሳሌ ራሽያ እንደገና አሁን እየመጣች ነው። ሌሎቹም ቢሆኑ በየቀጣናው ያሉ እንደቱርክ፣ ኢራን እና ሌሎቹም ተጠቃሾች ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ እንደድሮ አይነት መሪው እኔ ነኝ የሚል አይነት አካሄድ ወይም የታወቀ መሪ የለም። በሁሉ ዘንድ ተሰሚነት ያለውና ዓለምን የሚመራ ኃይል የለም፤ አሜሪካም ብትሆን። አሜሪካንንም ቢሆን ብዙዎቹ አገራት ዞር በይ በማለት ላይ ናቸው።
ምክንያቱም ዓለምን ለመምራት የሚችለው ኢኮኖሚ እንጂ ወታደራዊ ኃይል አይደለም። ለምሳሌ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ አውሮፓውያን በሙሉ ደቅቀው ነበር ማለት ይቻላል። አፍሪካ ደግሞ ገና እንጭጭ ነበረች። ገና ነጻነቷን በማግኘት ላይ ነበረች። በኢስያም ቢሆን ገና እነቻይና እና ህንድ ነጻነታቸውን አግኝተው አገር ለመሆን የሚውተረተሩበት ወቅት ነበር።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አሜሪካ በዚያን ወቅት የዓለም ኢኮኖሚን 60 በመቶ ትቆጣጠር ነበር። የዓለም ጂዲፒ 60 በመቶው የአሜሪካን ነበር። ሌሎች የዓለም አገራት ሁሉ ተደምረው 40 በመቶ ብቻ ነበራቸው። እናም የዚያኔው ሁኔታ በወቅቱ ለአሜሪካ ትልቅ ጡንቻ የፈጠረላት ስለሆነ አንተ በዚህ ሂድ፤ አንቺ ደግሞ በዚህ ግቢ የማለት ብቃትን አጎናጽፏት ቆይቷል።
ከዚያ በኋላ ግን የዓለም ኢኮኖሚ እያደገ በሚሄድበት ጊዜ የአሜሪካ ድርሻ እየቀነሰ መጣ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ 60 በመቶ የነበረው የአሜሪካ ኢኮኖሚ እኤአ 1980ዎቹ ገደማ ወደ 40 በመቶ ወረደ፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ይህ የሚያሳየው ሌሎቹ አገሮች በኢኮኖሚ እየጠነከሩ እንዲሁም ከአሜሪካ ትዕዛዝ ስር እያፈነገጡ መምጣቸውን ነው። በመሆኑም የአሜሪካን ኃይል ቀንሷል ማለት ነው። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ዓለም በአንድ ወይም በሁለት ኃይል ብቻ ነው ያለው የሚባል ነገር የለም ማለት ነው። በመሆኑም በየቀጣናው ብዙ አሉ፤ ሌሎችም እየወጡ ነው። እነ ቻይናን ብንመለከት ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተገፋፉ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ እየተስተዋለ ስለሆነ ዓለም አቀፉ ሁኔታ በጣም ዝብርቅርቅ ብሏል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ዲፕሎማሲው ራሱ ሸቀጥ ነው የሚሉ አሉ፤ የምዕራቡ የሎቢ ቡድን ዲፕሎማሲውን ሸቀጥ አላደረገውም ወይ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– ዲፕሎማሲው ሁልጊዜም ሸቀጥ ነበር። የቀድሞው የጋቦን ፕሬዚዳንት ኦማር ቦንጎ በጣም ሙሰኛ የሆኑ መሪ ነበሩ፤ ስልጣኑን ለልጃቸው አሳልፈው ነው የሞቱት። እኚህ መሪ ከቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከቡሽ ጋር ለመገናኘት ብለው ባለስልጣንን ለሚያግባቡ (Lobby) ለሚያደርጉ የሰጡት 20 ሚሊዮን ዶላር ነው። ፕሬዚዳንት ቦንጎ፣ ይህን ያደረጉት ቡሽን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን አሜሪካ የየአገራቱን መሪዎች የምትቀበልበት አቀባበል የቀይ ምንጣፍም ሆነ የምግብ ዝግጅቱ የተለያየ በመሆኑ ነው። አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ እየተባለ ሲሆን፣ የእኛ መሪዎች አጼ ኃይለስላሴን ጨምሮ ይህንን አግኝተው አያቁም። ከአፍሪካ የሚሄዱትን የምትቀበለው ዝቅ ባለ መልኩ ነው። ስለዚህም ቦንጎ ይህን አንደኛ ደረጃ አቀባበል በገንዘባቸው 20 ሚሊዮን ዶላር ከፍለው ማግኘት ችለዋል።
በእርግጥ እንዲህ አይነቱ አካሄድ አንዳንዴም ጠቃሚ ነው፤ እስራኤል አሜሪካንን እንዲህ የምታንቀሳቅሰው ባለስልጣንን የሚያግባቡ (Lobby) የሚያደርጉ አካላት ጠንካራ በመሆናቸው ነው። ሁሉ ነገር በርቀት ሲታይ ቅዱስ ስራ ይምሰል እንጂ ቀርበው ሲያስተውሉት ዘግናኝ እና ርኩሰቱ የበዛ ብዙ ነገር በውስጡ አለ።
አዲስ ዘመን፡- የሶስተኛው ዓለም አገራት ሰብዓዊ መብት በሚመስል ድለላ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ፤ ምዕራባውያን ራሳቸው በፈጠሩት ግጭት ሰው እያለቀ ሲሆን፣ በሰብዓዊ መብት ስም ግን ሲያስጨንቁ ይታያልና ይህ ከዲፕሎማሲ አንጻር እንዴት ይታያል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡- ይህ አይነት አካሄዳቸው አንዱ ስልት ነው። ምዕራባውያን የሶስተኛው ዓለም አገራትን አንገት ይዘው የሚጎትቱበት አንዱ ገመድ በሰብዓዊ መብት ስም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። ሰብዓዊ መብት የመጣበት ሁኔታ እና አሁን እየተሰራበት ያለው አካሄድ የተለያየ ነው። የመጣበት ሁኔታ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች (ጁሽ) ስለተገደሉ ሂትለር ስለጨፈጨፈ የዚህ አይነት ነገር ዳግም እንዳይፈጸም ህግ እናውጣ በሚል ነው የነበረው።
ህግ ሲወጣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳይን አስመልክቶ ነው። በኋላ ላይ ግን ተከፋፈሉ። በምዕራባውያኑ አካባቢ ኢኮኖሚው በግለሰብ እጅ ገባ፤ ይህም ምንም እንዳልሆነና ዋናው ነገር ፖለቲካው ነው የሚለውን ይዘው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን (ኤን.ጂ.ኦ) አከፋፈሉ፤ እነርሱ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና መገናኛ ብዙኃኑን አቀናጁ። በዚህም መሰረት የፈለጉትን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ ለምሳሌ ቢ.ቢ.ሲ ወይም ሲ.ኤን.ኤን የሚናገረውን እንጂ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች የሚናገሩትን የሚሰማ የለም።
እነ ሂዩማንራይትስዎች፣ እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚቀጥሩት የሰው ኃይል የአሜሪካ መንግስት ከሚቀጥረው በክፍያ ያነሰ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ሀብታሞች መንግስታቸው ብቻ ሳይሆን ስርዓቱም ይጠብቃቸዋል። ስርዓቱ እንዲጠብቃቸው ሲሉ ገንዘባቸውን ያፈሳሉ።
ከአገር አገር ለይተው ነው በሰብአዊ መብት ስም ያልተገባ ጥላቻ የሚያሳድሩት፤ ለምሳሌ ቻይናን የሚያደርጉትን ያህል ሳዑዲ አረቢያ ላይ አያደርጉም። ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ አሁንም ሰው ሰረቀ ተብሎ እጁን የሚቆረጥበት አገር ነው። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ አይነት ቅጣት ዛሬም ድረስ የሚፈጸምበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ይህን አይነቱን ቅጣት ሲያወግዙ አይሰሙም። ምክንያቱም ሳዑዲ አረቢያ የእነርሱ ወዳጅ ናት። እናም ይህ የሰብዓዊ መብት የኃይል መሳሪያ ሆኗል። በጣም ከፍተኛና ጠቃሚ መሳሪያው ሆኗል። ምክንያቱም ኤን.ጂ.ኦዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ገንዘብ ይበትናሉ። ኤን.ጂ.ኦ ነው ይባልና የሚፈልጉትን ያቋቁማሉ። ወደአፍሪካ ሲመጣ ደግሞ ድህነቱም ስላለ ተቀጣሪው ለእነሱ ጋሻጃግሬ ይሆናል። ቀስ በቀስ ደግሞ ወደፖለቲካ መድረክ ያመጡታል። ከዚያም እንደፈለጉት የሚያዙት ልጅ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– ታድያ የሶስተኛ ዓለም አገራት እጣ ፈንታቸው ምንድን ነው? በራሳቸው የሚወስኑትስ መቼ ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እጣፈንታቸውን በራሳቸው የሚወስኑበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብዬ አምናለሁ። እርግጥ ነው ለሁሉም ጊዜው ላይመጣ ይችላል። በመጀመሪያ ኢኮኖሚውን መገንባት ያስፈልጋል። ኢኮኖሚው ከተሽመደመደ ምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ቢኖር ከእነርሱ እጅ ማምለጥ አይቻልም።
በነገራችን ላይ እኔ የየትኛውም ፖለቲካ ተከታይ አይደለሁም፤ ነገር ግን ኢህአዴግን አልጠላውም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ኢኮኖሚውን እናስቀድም የሚሉት ነገር ነበራቸውና ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚውን ማሳደግ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሙስናን ማጥፋት ነው። ሙሰኛ መንግስት በምንም አይነት ሁኔታ ነጻ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ሌባ ስለሆነ እላዩ ላይ ያለው ቆሻሻ ይጋለጣል የሚል ስጋት አለውና ይፈራል። ሶስተኛው ደግሞ ህዝቡ ሊያምነው የተገባ መንግስት መሆን አለበት። እነዚህ ሶስት ነገሮች ተቀናጅተው የሚሄዱ ከሆነ ከየትኛውም አገር ጫና ነጻ መሆን ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ዓለም አቀፍ ጫና ከምን የመነጨ ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– አንዳንዱ ጂኦፖለቲክስ አለበት። አሁን እየደረሰብን ያለው ጫና በህወሃት ምክንያት ብቻ አይመስለኝም። አብዛኛውን ነገር የሚፈጥሩት እንደሚመስለኝ ግብጾች ናቸው። ግብጽ የመፈጸምም የማስፈጸምም አቅሟ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያውያኑ ዘንድ የማይካደው ነገር ወኔ መኖሩ ነው። የአገር ፍቅርም አለን። በዚህ ሁኔታ ተቋቋምናቸው እንጂ ሌላ የአፍሪካ አገር በኛ ቦታ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በዚህ መልኩ ሊዘልቅ አይችልም ነበር።
ምዕራባውያኑ ግብጽን መያዝ ይፈልጋሉ። ስለዚህ እኛን ልክ እንደመስዋዕት ላም ለግብጽ ወርውረው በምትኩ ከግብጽ ሌላ ነገር ማግኘት ነው የሚፈልጉት። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያደረጉት ይህን ነው። አሜሪካ ትኩረቷን ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ኢስያ አዘንብላ ነበር። በዚህ ውስጥ መካከለኛው ምስራቅ ሲረሳ ግብጽም ጭምር ተረስታ ነበር። ነገር ግን እንደ እድል እንበለው ወይም ደግሞ ፈጥረው ይሁን ባይታወቅም የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት ተፈጠረ። ይህ ሁኔታ አሜሪካንን ከኢስያ ወደመካከለኛው ምስራቅ ፊቷ መለስ እንዲል አደረገ። ይህ ደግሞ ግብፅን ፍለጋ እንድትሄድ አደረጋት።
ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለው ግጭት ሲነሳ ሁለቱን ሊያስታርቅ የሚችል በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ኃይል ግብጽ ብቻ ነች። ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ወደውጭ ውስጥ ለውስጥ መውጣት የሚችሉት በእስራኤል በኩል ወይም በግብጽ በኩል ነው። ስለዚህ ግብጽ በጋዛ ላይ ኃይል አላት።
ሁለተኛው ደግሞ ግብጽ ከእስራኤል ጋር ቁርኝት አላት፤ ከድሮ ጀምሮ የከረመ ጓደኝነት አላት። በደህንነቱም ጭምር መረጃ የሚለዋወጡ አገራት ናቸው። ስለዚህ ይህ ጦርነት በሚፈጠርበት ጊዜ ጦርነቱን እንዲያቆም ልትረዳ የምትችል ግብጽ ናት በሚል ፕሬዚዳንት ባይደን ዘለው የሄዱት ወደግብጽ ነው። በዚህ ሂደት ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የእኛ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ነው። ይህን ብታስቆሚ እኔ ደግሞ ይህን አደርጋለሁ በሚል በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው ያንን ያደረጉት። ዞሮ ዞሮ ግን ህወሃት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት ነው። የህወሃት ሰዎች በእኔ እድሜ ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው የዚህን አይነት ድርጊት ማድረጋቸው አሳዛኝ ነው የሚል አተያይ አለኝ። ይህ ሁኔታ በአካባቢው ያለውን ነገር ሁሉ ዝብርቅርቅ አድርጓል።
ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ብሞት ክእናንተ አልለይም ስትል የቆየችው ሱዳን እንኳ ለጊዜው መሽመድመዳችንን ስታይ ዘላ ከግብጽ ጀርባ ተለጥፋለች። ኢትዮጵያና ሱዳን ከድሮም ጀምሮ ቢሆን የወሰን ችግር እንዳለባቸው የሚታወቅ ነው። ይህን ችግር እምብዛም ዞር ብለው አያዩትም ነበር። ስንት ዓመት የቆየውን ችግር ዛሬ ክፍተት አገኘሁ ብላ ነው የመሰላትን እያደረገች ያለውና ይህም ያልፋልና ብዙ የሚያሰጋ አይሆንም። ሌሎች እንደሚያስቡት ተፍረክርከን የምንቀር አይደለንም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትናንት የተመሰረተች አገር አይደለችም፤ ብዙ ታሪክ ያላት፣ አገሩን የሚወድ ህዝብ ያላት፣ የመዋጋት ልምድ ያለው ወታደር ያላት እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ሌባ ያልሆነ መንግስትም ያላት አገር ናት።
አዲስ ዘመን፡– ትልልቅ ነን የሚሉ የዓለም መንግስታት በአፍሪካ ጠንካራ መንግስት እንዲመሰረት ብዙም አይፈልጉም፤ ስለዚህ በአፍሪካ ጠንካራ መንግስት መመስረት የሚቻለው እንዴት ነው?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– በአፍሪካ ጠንካራ መንግስት እንዲመሰረት ብዙ አገሮች አይፈልጉም የሚለው ጉዳይ ከድሮ በመጠኑም ቢሆን አሁን አሁን የተሻለ ሁኔታ አለ። ቀደም ብሎ አንዱ ከሌላው ጋር እንዲጋጭና አንደኛው ወገን አንዱን ሲደግፍ ሌላኛው ደግሞ ሌላውን ወገን የመደገፉ ነገር በብዛት ይስተዋል ነበር። በዚህም አካሄዳቸው አገሮቹ እንዳያድጉ የሚያደርጉበት ሁኔታ ነበር። ይህ በቀዝቃዛው ጦርነት አካባቢ ሲሆን፣ አሁን ግን የዚያን አይነት ነገር ብዙም አይደለም።
ሌላው ቀርቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኃያል አገር አሜሪካ ብቻ ናት የሚለው ነገር ራሱ በመለወጥ ላይ ነው። በአሁኑ ጊዜ አገሮች ፖሊሲያቸውን በደንብ አጥንተው እና አገናዝበው የሚሄዱና በዛ አንጻር ወዳጅ ሰብስበው ኢኮኖሚያቸውን የሚያሳድጉና ህልማቸውን የሚያሳኩ እንዲሁም በአገራቸው አንድነትና ፍቅር እንዲኖር የሚያደርጉ ከሆነ ትልቅ መንግስት መሆን ይቻላል። ደግሞም እየሆኑም ነው፤ ለምሳሌ እንደግብጽ ያሉ ከአህጉራችን ትልቅ እየሆኑ ነው። በኢኮኖሚም ሆነ በሚሊታሪ ተሰሚነታቸው እየጎላ ነው። ስለዚህም ይቻላል ባይ ነኝ፤ ነገር ግን ትግል ያስፈልጋል።
በእርግጥ እንደሚታወቀው ቻይናውያን ፖሊሲያቸው ከምዕራባውያን የተለየ ነው። እነርሱ እኤአ ከ1970ዎቹ ጀምሮ እያሉ ያሉት እኛ ታዳጊ አገር ነንና አብረን እናድጋለን ነው። አሁን ግን እነርሱ ከታዳጊ አገርነት ወጥተው ሀብታም አገር በመሆን ኃይል አገር ሆነዋል። ስለዚህ ከዛ አንጻር ድሮም ከእናንተ ጋር ነበርኩ አሁንም እረዳችኋለሁ፤ የኢኮኖሚ አቅማችሁንም አሳድጋለሁ፤ አብረን እንበለጽጋለን የሚል ፖሊሲ አላቸው። ይህን ሲያደርጉ የራሳቸውን ጥቅም አስጠብቀው ነው። ስለዚህ በምዕራባውያን እጅ ላይ ብቻ የነበርን አካላት ሌላ አማራጭ እየተገኘ ነው ማለት ነው። በመሆኑም ይህን አማራጭ በመጠቀም በአገር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ሊመረት የሚችልን ኢኮኖሚ በማሳደግ ከውጭ ተጽዕኖ በመላቀቅ በኢኮኖሚ ማደግ ይቻላል፤ በማደግም ላይ ናቸው።
ምዕራባውያኑ ድሮ አንዱን አገር ከሌላው ጋር ነበር ሲያጣሉ የነበረው፤ አሁን ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ያለውን አካል እርስ በእርሱ እንዲጋጭ እያደረጉ ነው። በዚህም ለማዳከም ሊሞክሩ ይችላሉ። ስለዚህ እንዲህ አይነቱን ቀዳዳ በመተባበር መድፈን ነው የሚጠበቅብን።
አዲስ ዘመን፡– አሜሪካና ኢትዮጵያ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት ይገለጻል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እርግጥ ግንኙነታቸው ወጣ ገባ ነበር። በዳውሮኛ ቋንቋ ሴትየዋ በየሄደችበት ቦታ ሁሉ ንጉስ ወንድም እንዳላት ትናገር እንጂ ንጉሱ ግን አንድም ቀን እህት አለችኝ ብሎ አያውቅም የሚል አባባል አለ፤ አሜሪካውያን የጠቀሙን ወቅት መኖሩ አይዘነጋም፤ ነገር ግን ደግሞ አብረውን መቆም ሲገባቸው ያልቆሙበትም ወቅት ነበር።
የእኛና የአሜሪካ ግንኙነት የተጀመረው በአጼ ምኒልክ ዘመን እኤአ ከ1903 ጀምሮ ነው። ትልቁ ግንኙነት የሚባለውና ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በውል የተቀራረበችው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። በዚያን ወቅት ፈረንሳይና ጣሊያን እንዲሁም ሌሎች አገሮች አብረው ወረዋል ለማለት ይቻላል። በወቅቱ ስንወረር የዓለም መንግስታት አባል አገር ሆነን ሳለ እኛን መርዳትና ጣሊያንን ማውገዝ ሲገባቸው ኢትዮጵያ ለነጻነት አልበቃችም፤ ባሪያ እየሸጠች ነው፤ አልሰለጠነችም በሚል ሰበብ አስባብ ለጣሊያን አሳልፈው ሰጥተውናል።
በወቅቱ እንደዛ ያደረጉት የአውሮፓ አገሮች ናቸው። አሜሪካውያኑ በዛ ሂደት ውስጥ ወረራውን ተቃውመዋል። ይህ በወቅቱ የግንኙነቱ መልካም ጅማሮ ነው ለማለት ይቻላል። በኋላ ላይ በጦርነቱ ወቅት በእርግጥ የአሜሪካ መንግስት እንኳ ባይሆን ጥቁሮቹ ንጉሱን ለመርዳትና ጣሊያን እንድትወገዝ ለማድረግ በአሜሪካ አገር በጣም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እነሱ ያደረጉት ጥረት በኢትዮጵያና በአሜሪካ ህዝብ መካከል በወቅቱ ጥሩ ጉድኝት መፍጠር ችሏል።
በጦርነቱ ጊዜ የአሜሪካ መንግስት በውል ኢትዮጵያን አልረዳትም። ከጣሊያን ነጻ ስንወጣ ግን በሁለቱም መካከል ፍላጎቱ ነበር። ምክንያት ቢባል እንግሊዞችም ሆኑ ፈረንሳዮቹ ኢትዮጵያን ሲጎነትሉ የነበሩና ለወረራ ሲዘጋጁ የነበሩ ናቸውና ንጉሱ ፍላጎታቸው በቅኝ ገዝቶ የማያውቅ፣ ሀብት ያለውና ገንዘቡ በጦርነት ያላደቀቀ አገር ዘንድ ብቀርብ ይሻላል በሚል ወደ አሜሪካ ጠጋ ለማለት በጣም ጥረት አድርገዋል። እናም እሱም ተሳክቶላቸዋል።
አሜሪካውያኑ ደግሞ ደግሞ በቅኝ ገዥ አገር ተይዞ የማያውቅ፤ የእንግሊዝም ሆነ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዥ ያልሆነች አገር ኢትዮጵያ ነችና ከእርሷ ጋር ብተባበር ይሻለኛል በማለቻው በሁለቱም ወገን ፍላጎት መኖሩን ማስተዋል ይቻላል። በተለይ የአስመራውን መቀመጫ መሰረት (ቤዝ) ካገኙ በኋላ ሚሊታሪያችንን እንደገና አደራጅተውልናል። ትምህርት እንዲስፋፋ የዓለማያ ዩኒቨርስቲን ከፍተውልናል። ይህም ማለት እስከ እኤአ እስከ 1960ዎቹ አካባቢ ረድተውናል ማለት ነው። እኤአ ከ1960ዎቹ በኋላ ግን የአስመራውን መቀመጫ (ቤዝ) አልፈለጉም። ሚሊታሪያችንን ለማደራጀት ገንዘብ ይሰጡን ነበር፤ በኋላ ላይ ግን እሱንም አቆሙ።
እኤአ በ1972 አካካቢ ንጉሱ ወደአሜሪካ ሄደው የሱማሊያ ወረራ ሊፈጸምብን ነው፤ ሱማሊያውያኑ በሶቬት ህብረት እስከአፍንጫቸው ድረስ መሳሪያ ታጥቀዋል፤ እናም እኛ ያለን መሳሪያ እነርሱ ካላቸው ጋር ሲነጻጸር በአራትና በአምስት እጥፍ ያነሰ ነው። በዚህ ሁኔታ ወረራ ቢፈጽሙ ልንቋቋም አንችልም። እናም እርዱን የሚል ነገር ነበር ያሰሙት። ነገር ግን አሜሪካውያኑ ያንን ለማድረግ አልወደዱም።
ያልፈለጉት በሁለት ምክንያት ነው፤ አንደኛው እነ ሳዑዲ አረቢያ መሳሪያ ሰጥታችሁ ኢትዮጵያ እንድትዋጋ የምታደርጉ ከሆነ ያላችሁ ግንኙነት ቅራኔ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ወይ እኛን አሊያም ኢትዮጵያን ምረጡ የሚል ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ለአሜሪካውያኑ አሰምተዋል። ስለዚህ አሜሪካውያኑ ሀብትና ገንዘብ ወዳለው ወግነው ለእኛ ጀርባቸውን ሰጡን።
ሁለተኛው ምክንያት የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት ድሮ ከጀርባችን አሜሪካውያን አሉ፤ ይረዱናል፤ መሳሪያም ይሰጡናል፤ የንጉሱ ወዳጅ ናቸው ብለው ሲያምኑ የነበሩ ሰራዊት ሲሆኑ፣ ንጉሱ ድጋፍ ፍለጋ እኤአ 1972 አካባቢ አሜሪካ ሄደው ባዶ እጃቸውን በመመለሳቸው ወታደሩ መክዳትና በንጉሱ ላይ ማመጽ ጀመረ። በዚህም ችግር ሆነ፤ አሜሪካውያኑ ለሱማሊያ አሳልፈው ሰጡን።
ከዛም በኋላ ደርግ መጣ፤ ፊቱንም ወደ ራሽያ አዞረ። ምክንያቱም በወቅቱ ሌላ አማራጭ አልነበረንም። ሁልጊዜ ደጋግሜ የምለው ነገር አለ፤ ራሽያውያኑ ባይደርሱልን ይህቺ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ልትኖር አትችልም ነው። በወቅቱ ራሽያውያኑና ኩባውያኑ ባይረዱን ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን ማሰብ ነው።ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ አሸባሪዎችን በመቋቋም እንዲሁም ግጭቶችን በማስወገድና ሰላም በማስጠበቅ በኩል የሚጫወተው ሚና የአፍሪካን የመሪነትና የሰብ ሰሃራ መሪነቱን በመያዛችን አሜሪካውያኑ አክብረውንና ደግፈውን እስካሁን ዘልቀናል።
አዲስ ዘመን፡– የቪዛ ክልከላው በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ወዴት ያደርሰዋል?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– የተጣለው ማዕቀብ መጥፎ ነው። አላስፈላጊም ነው። ማዕቀቡን በባለስልጣናቱ ላይ ጥለናል ነው ያሉት። በየትኞቹ ነው የሚለው ግን አይታወቅም። በእርግጥ የተጣለው ማዕቀብ በጅምላ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ አለመሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ ይህ የዚያን ያህል የከፋ ችግር ይፈጥራል ብዬ አልገምትም። በሂደትም የሚተውት ነው ብዬ አስባለሁ።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ ከማዕቀቡ በኋላ ከነጩ ቤተ መንግስት የወጣው መግለጫ ቀዝቅዞ ነው ያስተዋልኩት። እርግጥ አንዳንድ ቃላት እንደ ዘር ማጥፋት ጋር የተያያዘ አባባል ትንሽ ጠንከር ያለ ቢሆንም እያደረጉ ያሉት ግን በትግራይ አካባቢ ያለው ጉዳይ በቶሎ እንዲያልቅ ባለ በሌለ ኃይላችን እንጠቀም ይመስለኛል እንጂ ኢትዮጵያን እንበታትናት፤ አሳድደንም እንቅጣት የሚሉ አይመስለኝም። ምክንያቱም ያለኢትዮጵያ አካባቢውን መቆጣጠር ከባድ ነውና። በእርግጥ ደግሞ ኢትዮጵያን የሚተካ ሌላ እየፈለጉም ሊሆን ይችላል። እኛ ረጋ ባለ መንፈስና በሰከነ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ተጉዘን እነሱም ኢትዮጵያ በራሷ መንገድ እንጂ በሌላው ግፊት የማትወዛወዝ መሆኗ ብዙ ጊዜ የተነገራቸው ነውና ይህን በአግባቡ እንዲያውቁት ማድረግ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡– የተጣለው ማዕቀብ የአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያመጣው ጫና ይኖር ይሆን?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እነሱን አሁን ያስደነገጣቸው አንዱ ነገር ኢትዮጵያ ከተዳከመችና ብጥብጥ ከተነሳ የአፍሪካ ቀንድን የሚይዘው ማነው የሚለው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን ስትቆጣጠር ከማን ጋር ሆና ነው፤ እኛንስ ወዴት አድርጋ ነው የሚል ነው። ምናልባት ከዛ አንጻር ከኤርትራ ጋር ያደረግነው ግንኙነት በእነሱ በኩል ጥሩ እይታ ያለው አልመሰለኝም። ይህ የእኔ አስተያየት ነው። እሱ ምናልባት ኢትዮጵያን ወደሌላ አቅጣጫ ሊወስዳት ይችላል የሚል ፍርሃት አለ። የኤርትራ አቋም የታወቀ ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደዛ ካዘነበለች በአካባቢው የሚኖረው ሁኔታ በእኛ ቁጥጥር ስር አይሆንም የሚል ግምት ያለ ይመስላል። እንደሚታወቀው ዲፕሎማሲ የማይፈታው ችግር የለም። ዋናው ነገር በምንና እንዴት እንያዘው፤ መቼ ምን እንስራ፤ ከማን ጋር እንሁን የሚለውን ትንሽ በሰከነ ሁኔታ ማየቱ ነው የሚጠቅመው። ይህን ደግሞ መንግስታችን የሚያደርገው እንደሆነ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ?
አምባሳደር ጥሩነህ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2013