የአሜሪካ ኮንግሬስ በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈው ውሳኔና እሱን ተከትሎም የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የጣለው ማእቀብ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ ማስቆጣቱን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በሀገር ቤትም በውጭ ሀገርም ተቃውሟቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ይህን የአሜሪካ መንግስትንና የአንዳንድ ምእራባውያን ሀገሮች መንግስታትን ተመሳሳይ አቋም ሲቃወሙ የሰነበቱ ሲሆን፣ በሀገር ቤት ድምጻችን ይሰማ ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቁም የሚሉ መልዕክቶችን ኢትዮጵያውያን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች ይህንኑ አቋማቸውን ለማሰማት እየተንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በእንግሊዝ ኤምባሲ በመገኘት ደብዳቤ አስገብተዋል፤ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ባለው ጫና ዙሪያ ውይይትም አድርገዋል፡፡ ባለፉት ቀናት ደግሞ የባይደን አስተዳደር የሚቃወሙ ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ናቸው፡፡
አያሌ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ላይ እየተደረገ ያለው ጫና አሳስቧቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ማንም ሳይቀሰቅሳቸው ነው ሰላማዊ ሰልፍ እየወጡ ያሉት፡፡ በሀገር ውስጥም በውጪ ሀገርም የሚገኙት ኢትዮጵያውያን የባይደን አስተዳደር ያሳለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት መሆኑን በመግለጽ ተቃውመውታል፡፡ ውሳኔው ለአሸባሪው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባቱንና ለአሸባሪው ትህነግ ቡድን እውቅና መሰጠቱን በመቃወምም ነው ሰላማዊ ሰልፉን ያካሄዱት፡፡
በአዲስ አበባ ‹‹ድምጻችን ለነጸነታችንና ለሉአላዊነታችን›› በሚል መሪ ቃል የከተማዋ ወጣቶች ከትናንት በስቲያ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ወጣቶቹ ያካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ አንድነታቸውን ያሳዩበትና የውስጥና የውጭ ጠላቶች አንገታቸውን እንዲደፉ ያደረገ መሆኑንም በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያውያን አንድነት ሊቀጥል እንደሚገባም ነው የተገለጸው፡፡ ተመሳሳይ ሰልፎች በክልሎችና በተለያዩ የዓለም አገራት ተካሂደዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን ማእቀብ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ ሲሉ ተቀባብለውታል፡፡
በካናዳ ካልጋሪ፣ በኖርዌይ ኦስሎ እንዲሁም በጣልያን ሮም እንዲሁ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ መንግስት ማእቀብን በመቃወም ነው ሰላማዊ ሰልፉን ያካሄዱት፡፡ ኢትዮጵያውያውያኑ በሰሜን እዝ ላይ ክህደት በፈጸመውና የሀገርን ሉኣላዊነት ጭምር አሳልፎ በሰጠው ትህነግ ላይ መንግስት የወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ አድናቆት ሊቸረው ሲገባ የአሜሪካ መንግስት ይህን እውነታ ወደ ጎን በመተው በሀሰት በሀሰተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን የሚጎዳ እርምጃ ውስጥ መግባቱ እንዳሰዘናቸው አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ሀገራቸው በፈታኝ ወቅት ላይ መሆኗንም በመጥቀስም ወደ ሀገራቸው የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በመላክ የመንግስትን ዜጎችንና ሀገሪቱን ከድህነት የማውጣት ራእይ ለማሳካት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም የሃይማኖት፣ የብሔርና የፆታ ልዩነት በአንድነት በመቆም ድጋፉን ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት ሙሌቱ እንዲካሄድና ፕሮጄክቱም እንዲጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በባይደን አስተዳደር ውሳኔ እና ማእቀብ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ መግለጻቸው ጉዳዩን አለም አቀፉ ማህበረሰብ በአጽንኦት እንዲመለከተው ያስችላል፡፡ የባይደን አስተዳደርም ጭምር ጉዳዩን መልሶ እንዲያጤነው የሚረዳም ሊሆንም ይችላል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከአሸባሪውና ከከሀዲው ትህነግ ጋር የኢትዮጵያ መንግስት እንዲደራደር መወሰኑ አሜሪካ በሽብርተኝነት ላይ ስታራምድ የቆየችውን አቋም የማይገልጽና የኢትጵያን ድካምም መና ያስቀረ ነው፡፡ ከሽብርተኛ ቡድን ጋር ተደራደሩ ማለት ለሽብርተኛ እውቅና መስጠትና በያዝከው ጥፋት ቀጥል እንደማለት ነው፡፡ ይህን የአሜሪካ መንግስት አቋም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ለወዳጅ ሀገሮችና ለመላው ዓለም ለማድረስ የሰልፈኞቹ እርምጃ ተገቢና ወቅታዊ ነው፡፡
የውጭ ጣልቃገብነት የተቃወሙት የኢትዮጵያውያኑ ሰላማዊ ሰልፎች ጠንካራ መልእክት የተላለፈባቸው፣ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቁ፣ በአንድነት መቆም በሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ የተደረጉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያኑ ያካሄዷቸው ሰላማዊ ሰልፎች በሀገር ፍቅር ስሜት በራሳቸው ተነሳስተው ያደረጓቸው ሰልፎች ሲሆኑ፣ ጉዳዩ ውሎ የማያድር የአገር ጉዳይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በዚህ በኮረና ወቅት የተደረጉም መሆናቸው ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያውያን የተጋረጡብንን ፈተናዎች እስከምናልፋቸው ድረስ አንድነታችንን ማጠናከር የሚገባን ከመሆኑም አኳያ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም እየተካሄዱ የሚገኙ ሰልፎች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያሳደሩ አካላት ሁሉ ራሳቸውን ደግመው እንዲመለከቱ፣ ኢትዮጵያውያንም በዚህ የፈተና ወቅት አንድነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
ሰላማዊ ሰልፎቹን በተለይ በአዲስ አበባ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይዘውት ወጥተዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ መንግስት የተጣለባቸውን ማእቅብ ማውገዛቸውን እና ለውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማይንበረከኩ ለማስገንዘብ ይልቁንም አንድነታቸውን ለማጠናከር መነሳሳታቸውን ለማስገነዝብ አስችሏል፡፡
እስከ አሁን የተካሄዱት ድምጽ የማሰመቱ ዘመቻዎች ኢትዮጵያውያንን በማነቃነቅ ፣ በዚህ ፈታኝ ወቅት የአንድነታቸውን ፋይዳ በማስገንዘብ በኩል ብዙ ርቀት የተሄደባቸው ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የውጭ ሀይሎችን ጣልቃ ገብነት በማውገዝ እውነታውን ለማስገንዘብ ፋይዳው ከፍተኛ እንደመሆኑ፣ ይህን ዘመቻ በተለያዩ መንገዶችም ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም