
አዲስ አበባ፦ አሜሪካን የቪዛና ሌሎች እገዳዎችን የምታደርገው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን የእሷን ሃሳብ ተቀብለው አላቀነቅን ባሏት አገራት ላይ ሁሉ በመሆኑ ለጉዳዩ ብዙም መጨነቅ እንደማያስፈልግ በግብጽ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የነበሩት አቶ ግርማ ባልቻ አስታወቁ ።
አቶ ግርማ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ፣ አሁን ላይ በአሜሪካ የተወሰደው የቪዛ ማዕቀብ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድም ሲያስቡ የኖሩት ነገር ነው።
ከዚህ ቀደም የለውጡ መንግሥት ወደ ስልጣን ሳይመጣ እኤአ በ 2018 ተመሳሳይ እገዳን ለመጣል ሲያሴሩ ነበር፤ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን የእነሱን ሃሳብ ተቀብሎ አላቀነቅንም ባላቸው ማንኛውም አገር ላይ በመሆኑ ያን ያህል የሚገርምም የሚያስጨንቅም አይደለም ብለዋል።
ይህንንም አግዝፈን እንዳናየው፣ በሁለቱ አገሮች ላይ ያን ያህል የተጋነነ የጥቅም ግጭት የለም ያሉት አቶ ግርማ ፣ በእጅ አዙርም ቢሆን እኔ አውቅላችኋለው የሚለው ነገር ወደሻከረ ግንኙነት እንዳስገባን አመልክተዋል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ አገር አንድምታው ብዙ ነው ፣ እኛ ምንም እንኳን በኢኮኖሚም በሌላም የማንመጣጠን ብንሆንም እንደ አገር ግን አንዳችን ለአንዳችን ማስፈለጋችን አይቀርም ፣ አሁን እየሆነ ያለው ሁኔታ ግን ይህንን የሚያሻክር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እንደመሆኗ ለተወሰደው እርምጃም ጠንከር ያለ ምላሿን ሰጥታለች፤ ይህ መልካም ቢሆንም ዲፕሎማሲ ደግሞ የአገሮችን የሻከረ ግንኙነት ለማለዘብ የነበረውንም የማጠንከር ዓላማ ያለው በመሆኑ ከመግለጫው ጎን ለጎን ጠንከር ያለ ዲፕሎማሲያዊ ሥራን መሥራት ከመንግሥት የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ፣ እርምጃው በአገር ላይ የተቃጣና ጉዳቱም ለሁሉም የሚተርፍ በመሆኑ ህዝቡ በተቻለ መጠን ከመንግሥት ጎን መቆም ይጠበቅበታል። ልዩነትን አቻችሎ በአንድነት መቆም ከምንጊዜው በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው።
መንግሥትም ቢሆን አሁን ከኃያሏ አገር ጋር የገባንበትን ቅራኔ በተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለመፍታትና በተቻለ መጠን ግንኙነቱን ለማሻሻል የሚረዱ ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንደሚያስፈለግ አመልክተዋል፡፡
አሁን ላይ ከምዕራባውያኑ በተለይም ከአሜሪካን እየደረሰ ያለው ጫና ማየት ያለብን መጀመሪያ ከአገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንጻር ነው ያሉት አቶ ግርማ፣ ይህ ሲባልም የአገሮች ግንኙነት የተለያዩ ደረጃዎች እንዳላቸውም ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከዚህም መካከል ትብብር አንዱ ሲሆን ይህም በተለይም በሁለቱ አገሮች መካከል ላለፉት 30 ዓመታት ተጠናክሮ የመጣ ከዛም በላይ በኢኮኖሚ በጸጥታ በተለይም ሽብርተኝነትን ከመዋጋት አንጻር ተጠናክሮ የቆየ ትብብር መኖሩን ጠቁመዋል ።
ሌላው ውድድር ሲሆን ምናልባት እኛና አሜሪካን የማንመጣጠን አገሮች ከመሆናችን አንጻር ውድድር ያን ያህል የሚያስጨንቀን ባይሆንም አንዳችን ለአንዳችን ማስፈለጋችን አይቀርም ፤ በመሆኑም ይህንን ግንኙነት ለማሻሻል ጠንከር ያለ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ብቻ ሳይሆን ከመላ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም