
አዲስ አበባ፡- በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የቅድመና ድህረ ምርጫ ሂደቶች በተመለከተ ስልታዊ ክትትል እናደርጋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ አስታወቁ።
ኮሚሽኑ በምርጫ ወቅት ተፈጻሚ መሆን ያለባቸው ባለስድስት ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን ለፓርቲዎች ባስተዋወቀበት ወቅት ዶክተር ዳንኤል በቀለ እንዳስታወቁት፤ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ በምርጫው ሂደቶች ሰብአዊ መብቶች ስለመከበራቸው ስልታዊ ክትትል ያደርጋል። ክትትሉም ከምርጫ ታዛቢነት ስራ የተለየ እና የራሱ ስልታዊ አካሄድ ያለው መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ፤ ከድምጽ መስጫ ቀን በፊት፤ በእለቱ እንዲሁም ከድምጽ መስጫ ቀን በኋላ ባሉት ጊዜያቶች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ የሚደረግ ቁጥጥር አለ። የሰብአዊ መብቶች ተጥሰውም ከሆነ በፍጥነት እንዲታረሙ ጥረት ይደረጋል። በተለይ ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ የመደራጀት፤ ከአንድ ቦታ ወደሌላኛው የአገሪቷ ክፍል የመንቀሳቀስ መብት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንዳይደረጉ ስልታዊ ክትትሉ በሰፊው ይከናወናል።
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ በቦታው ተገኝቶ ከመዘገብ ባለፈ፤ ለመብት ጥሰት የተጋለጡ ጉዳዮችን ቀድሞ የማጥናት እና የመፍትሄ እርምጃዎችን የማፈላለግ ኃላፊነት አለብን ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ ለዚህም ከፍርሃት ውጪ በሆነ የስራ እምነት አቅም በፈቀደ መጠን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል። በምርጫው ሂደት ስልታዊ ክትትል ስራም ሙያዊ ስነምግባርን በተላበሰ መንገድ ሪፖርቶችን በማጠናቀር ይከናወናል።
ከፓርቲዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በምርጫ ወቅት ተፈጻሚ መሆን ያለባቸው ባለስድስት ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎች ማዘጋጀቱን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና እጩዎች ምርጫውን ካሸነፉ ሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የሚወስዷቸውን ተጨባጭ እርምጃዎች በተመለከተ በምርጫ ማኒፌስቷቸው ውስጥ በግልጽ እንዲያስቀምጡ የሚለው አንዱ ነጥብ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ በመንግስት ስልጣን የሚገኙም ሆነ ሌሎች እጩዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው በሰላማዊ እና በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ትኩረት ተደርጓል። በአባሎቻቸው የሚፈጸሙ የሰብአዓዊ መብት ጥሰቶችንም በመመርመር ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ግልጽ አሰራር ማስፈን እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
ዶክተር ዳንኤል እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ የአቅም፣ የገንዘብ እና የሰው ኃይል እጥረቶች ቢኖሩበትም የምርጫው ሂደቶች ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑ የሚያከ ናወናቸውን ስራዎች በተቻለው መጠን እያከናወነ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሚያከናውናቸው ስራዎች ላይ እምነት ጥለው መጓዝ ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እያደረገ የሚገኘውን ጥረት አድንቀው ቦርዱ ኮሚሽኑ ያወጣቸውን ባለ ስድስት ነጥብ አጀንዳዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይፋ ባደረገውና በምርጫ ወቅት ተፈጻሚ መሆን አለባቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ባለስድስት ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎች መካከል ከግጭት ቀስቃሽና የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃ መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን ያሳሰበበት ነጥብ አንዱ ነው። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ የሕግ፣ የፖሊሲና የአስተዳደር ጉዳዮችን ለመፈተሽ እና ማሻሻያ ለማድረግ በይፋ ቃል እንዲገቡም አሳስቧል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም