የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እ.ኤ.አ. በ2016 በትምህርት ቤቶች አካባቢ ስለሚፈፀም ጾታዊ ጥቃትና ተጽእኖውን የተመለከተ መረጃ አውጥቶ ነበር። በምዕራብ ሀገራት የሚገኙ ሴቶች በትምህርት ውጤታቸው ከወንዶች እየበለጡ ይገኛል። በዚህ ወቅት በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ሴቶች ከትምህርታቸው እንዲያቋርጡ የተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ያሉ ቢሆንም፤ በተለያዩ ደረጃ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች የራሳቸውን አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠሩ መሆኑ ተመልክቷል።
በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈፀም ጾታዊ ጥቃት አንዱና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ ችግር መሆኑም ይነገራል። የመረጃውን ጭራ ይዘን ወደ ሀገራችን ሁኔታ መመልከት ከቻልን በሀገራችን የትምህርት ተደራሽነቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሴቶችን ባሳተፈ መልኩ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ተችሏል። ሴቶችን ወደ ትህርት ቤት ከመላክ ትይዩ በትምህርታቸው እንዲገፉ በማድረግ ረገድ የነበሩ ጥረቶች ፍዝ እንደነበሩ አመላካች ነው። በዚህ ዙሪያ ፓንክረስትና ጓደኞቹ (እኤአ በ2016) በኢትዮጵያ የታዳጊዎች ደህንነት ዙሪያ አድርገውት የነበረን ጥናት መመልከት ያስፈልጋል።
በሀገራችን በትምህርት ቤቶች የሚፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚጠቁመው ጥናቱ፤ ከ50% እስከ 67% የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በእድሜያቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ጾታዊ ጥቃት ጾታ ተኮር ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑን ይፋ አድርጓል። በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ወሲባዊ ትንኮሳ እና አስገድዶ መድፈርን የሚያካትት ሲሆን፤ ጥቃቱ ከሚፈጸምባቸው አካባቢዎች መካከል ትምህርት ቤቶች ይገኙባቸዋል ይላል። ጥቃቱ መምህራን ተሳታፊ የሆኑበትና እየተስፋፋም የሚገኝ መሆኑን አሳይቷል።
የችግሩን አሳሳቢነት በተመለከተ በርካታ ጥናቶች በየጊዜው የሚወጡ ሲሆን ድርጊቱ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች፣ በሲኦሲ (የብቃት ማረጋገጫ ማዕከል)፣ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በስፋት የሚታይ መሆኑን ታውቋል።
በከተማም ሆነ በገጠር የሚፈጸሙት ድርጊቶቹ በገጠራማው አካባቢ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ችግሩ ገዝፎ እንደሚታይ፤ በከተማ ደረጃ በብቃት ማረጋገጫ ማዕከላት፣ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚፈጸም መሆኑ፤ በእነዚህ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እንደ መደበኛነት እስከመቆጠር እንደደረሱ ከጥናቶቹ ታዝበናል። በመንግስት በኩል በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ደረጃዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች መኖራቸውን ከማመን ባሻገር መፍትሄ ለመስጠት መንቀሳቀሱ ይታወቃል። 2006 ዓ.ም ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ቤቶች የሚፈፀም ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ረቂቅ መመሪያ በማዘጋጀት ችግሩን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ዋናው ነው። ሚኒስቴሩ መመሪያውን ለማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያትም እንደሚከተለው ነበር ያብራራው፤
በኢፌዴሪ ህገ መንግስትና በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችና ድንጋጌዎች የተረጋገጡትን የሰው ልጆች እኩልነት ክብርና ነፃነት በየትኛውም ቦታና ጊዜ ማክበርና ማስከበር ግዴታ በመሆኑና ማንኛውም ህጻን በነፃነት የመማር፤ መልካምና ምቹ የመማሪያ አካባቢ የማግኘት መብት አለው። ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል አንዱ ጾታዊ ጥቃት ሲሆን በተለይም
በትምህርት ቤቶች አካባቢ እየተፈፀመ ያለው የጾታዊ ጥቃት ተግባር ጤናማ የትምህርት ሂደት እንዳይኖር እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን መመሪያው ያመለክታል። ጾታዊ ጥቃት በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚፈፀም ተግባር ቢሆንም፣ በተለይ የችግሩ ተጋላጭ የሆኑት ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከወንዶች እኩል በመከታተል ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል፤ የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ ብቃትና ውጤታማነት የሚያቀጭጭ መሆኑን መገንዘብ መቻሉን አመልክቷል። በመሆኑም በቅድመ መደበኛ፣ በአንደኛ (1-8)ና ሁለተኛ ደረጃ (9-12) በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየተፈፀሙ ያሉ የጾታዊ ጥቃት ተግባራትን ለመከላከል፣ ለመቀነስና ብሎም በሂደት ለማጥፋት ከጾታዊ ጥቃት የጸዳ ምቹ አካባቢ በዘላቂነት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ስለዚህ የትምህርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 በተሰጠው ስልጣን መሰረት መመሪያውን ለማውጣት እንደተቻለ አስታውቋል።
በትምህርት ቤቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ከሰባት ዓመት በፊት ይህ መመሪያ ቢዘጋጅም፤ የችግሩን አሳሳቢነት መቀነስ ግን አልተቻለም። በተለይ ደግሞ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚደርሱት ፆታዊ ጥቃቶች የድብደባ፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በሲኦሲ ማዕከላት አካባቢ አይን እያወጡ መሆኑ መመሪያው የወረቀት ነብር ሆኖ መቅረቱ ይነግረናል። ከሰባት ዓመት በፊት ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው መመሪያ ውጤታማ አለመሆን አንዱና ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ ይቆጠራል። በተለይ ደግሞ ከአተገባበር ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መኖራቸው፣ ስለ መመሪያው በሚፈለገው ደረጃ ግንዛቤ ካለመፈጠሩ ጋር ተደማምሮ ውጤት ማምጣት እንዳይቻል ማድረጉ
ይታመናል። በሌላ በኩል የሚፈጸመው የድብደባ፣ ወሲባዊ ጥቃት ለመባባሱ ደካማ የህግ አተገባበር፣ የህግ ከለላ አለመኖር፣ የአስተዳደር ቁርጠኝነት ማጣት በመንስኤነት ይጠቀሳሉ። በመንግስት በኩል ከመመሪያው ጋር ተያይዞ ለተፈጠሩ ክፍተቶች መፍትሄ ለመስጠት ጥረት የሚደረግ መሆኑንም አስታውቆ ነበር። ይሄንኑ መሰረት በማድረግ ከሰሞኑ ትምህርት ሚኒስቴር ለሰባት አመት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረውን መመሪያ ተማሪዎችን መሰረት ያደረገ ፆታዊ ጥቃት መከላከል በሚያስችል መልኩ እየተሻሻለ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በሚኒስቴሩ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክተር ወ/ሮ የሺሃረግ ነጋሽ፤ ከዚህ በፊት በሥራ ላይ የነበረ መመሪያ ውጤታማ ቢሆንም በአተገባበር ዙሪያ አንዳንድ ውስንነቶች እንደነበሩበት አስታውቀዋል። መመሪያውን ለመከለስ የተፈለገበትም በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ከዘላቂ የልማት ግቦች፣ ከስድስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት መርሃ ግብር፣ ከትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ፣ ከኢትዮጵያ የትምህርት ሕግ፣ ከአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት ጋር በተጣጣመ መልኩ ለማዘጋጀት እንደሆነ ያመላከቱት ወ/ሮ የሺሃረግ፤ የፆታዊ ጥቃት አይነቶች፣ የሚወሰዱ የእርምጃ አይነቶች፣ የአቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሃሳብ አቅራቢ ኮሚቴ አወቃቀር፣ የውሳኔ ሃሳብ አቀራረብና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓትና የቅጣት ሪኮርድ መቆያ ጊዜ በድንጋጌዎች ከተካተቱት መካከል ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ለሰባት አመታ ሲተገበር የነበረውን መመሪያ የማሻሻል ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ በአራት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ሁሉም ክልሎች ወደ ራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀይሩት በማድረግ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013