ሀገርና ትውልድ አሻጋሪ የፈጠራ ሥራዎች

በተግባር ተደገፈ የፈጠራ ሥራ ተማሪዎች በንድፍ ሃሳብ ሲማሩ የቆዩትን ትምህርት በተጨባጭ የሚያረጋግጡበት ነው። ሥራው ተማሪዎቹን ወደፊት ከማሻገር አልፎ፤ የሕብረተሰቡን ችግር ይፈታል፤ ለትምህርት ጥራትም ሆነ ለአጠቃላይ ማህበረሰብ እና ሀገር ብልፅግና ጉልህ አስተዋጾ ያበረክታል። ከኢኮኖሚ አንፃር ለሥራ ፈጠራም ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።

መንግሥት ይሄን ከግንዛቤ በማስገባት ለፈጠራ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከጀመረ ሰነባብቷል። ሥራውን የሚያነቃቁ እና የሚያበረታቱ የተለያዩ ድጋፎችንም በየደረጃው እያደረገ ይገኛል። የፈጠራው ሥራው ምንጭ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ በወረዳ፤ በክፍለ ከተሞች፤ በክልሎች እንዲሁም በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደረጋቸው ያሉ የፈጠራ ሥራ ውድድሮች በማሳያነት ይጠቀሳሉ። በተለይ በትምህርት ቤት ደረጃ በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች በአውደ ርዕይ መልክ መቅረባቸው እየተለመደ መጥቷል። ዘንድሮም ባሳለፍነው ሳምንት በመዲናችን አዲስ አበባ በርካታ ተማሪዎች በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሕብረተሰቡን ችግር ፈቺ የፈጠራሥራዎቻቸውን ያቀረቡበት አውደ ርዕይ ለሦስት ቀናት በወዳጅነት ፓርክ ተከፍቶ ነበር፡፡

የ12ኛ ክፍሉ የቦሌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናታወርቅ መላኩ” በፈጠራ ሥራ የተካነ ትጉህ ትውልድ ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በተከፈተው አውደ ርዕይ ነው ያገኘነው። ተማሪው እንደነገረን ልብስ እና የተለያዩ ጥራጥሬ ማድረቅ የሚያስችል የማሽን ፈጠራ ሥራውን ያቀረበው በቦሌ ክፍለ ከተማ ካሉ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት መሠ

ረት በጣለለት የፊዚክስ ትምህርት በመወዳደር አንደኛ ወጥቶ ነው። በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀትም አግኝቷል፡፡

ክፍለ ከተማውን ወክሎ የተወዳደረበት ርቀት ቀላል እንዳልነበረም ያነሳል። ምክንያቱም በክፍለ ከተማው እጅግ በርካታ ጎበዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃታቸው የሚለካ ተማሪዎች ያሏቸው ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች አሉ። ከነዚህ ጋር መፎካከር ቀላል አልነበረም። በተለይ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ለሚደረገው ለዚህ አውደ ርዕይ የሚቀርበው ተማሪ አንድ አንደኛ የወጣ ብቻ ከመሆኑ አንፃር የሚያቀርበውን የፈጠራ ሥራ አሸናፊ ለማድረግ በተከታታይ ሁለት ቀኑን ሳይተኛ በሥራው ላይ አሳልፏል፡፡

ሥራውን ለመሥራት መነሻ የሆነው በልማት ምክንያት ከቤተሰቦቹ ጋር ተነስቶ ወደ የጋራ መኖሪያቤት መግባቱ ነው። ከመነሳታቸው በፊት በግቢያቸው ልብስ እንደ ልብ አጥበው፤ በርበሬ ደልዘው፤ ሽሮ አጥበው የፈለጉትን ዓይነት ጥራጥሬም እንደልብ የሚያሰጡበት ቦታ ሰፊ ነበር። ደህንነቱም ቢሆን ግቢያቸው የሚዘጋ በር ያለውና የግላቸው በመሆኑ አያሳስብም።

ወደ ጋራ መኖሪያ ቤቱ ሲገቡ ግን ካለው የቦታ ውሱንነት አንጻር ልብስ አጥበው ማድረቅ ስጥም እንደልባቸው ማስጣት አልቻሉም። ተማሪው ይሄ ችግር የብዙ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ችግር መሆኑን ለማረጋገጥ ራሱን የቻለ ጥናት አደረገ። መጠይቆችን በትኖ ባገኘው ምላሽም ብዙዎች ችግሩ ችግራቸው መሆኑን እና መፍትሄ እንደሚፈልጉም ገለፁለት። ጥናቱ ስለዋጋውም ስለኤሌክትሪክ ፍጆታውም ተጠቃሚውን ማእከል በማድረግ ዳስሷል። ከዚሁ ጎን ለጎን ሥራው ለእሱ ቋሚ የገቢ ምንጭ፤ ለሌሎች ተማሪዎችና ወጣቶች እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች ሥራ የሚፈጥርበትን ሁኔታም አካትቷል። ስያሜውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመስጠትም እንዴ እንደሚሰጥ መነሻ ሃሳብ ከማግኘት ጀምሮ የስያሜው ጉዳይ እስኪያልቅ ኢንተርኔት ላይ ሠርቼ በማድረግ ብዙ ጊዜ አሳልፏል። ይሄን መሠረተ አድርጎ ወደ ምርት ሂደት በመግባት በአውደ ርዕዩ የፈጠራ ሥራውን ማቅረብ መቻሉን ገልጾልናል ፡፡

በአውደ ርዕዩ በተፈጠረለት የገበያ ትስስር ሁለት ማድረቂያ ማሽኖች መሸጥ ችሏል። አምስት የይሰራልን ትዛዞችንም ተቀብሏል።

«የአንደኛ ደረጃ ተማሪም ሆኜ የምኖርበትን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በመወከል አንደኛ እወጣና የተለያዩ ሽልማቶችን አገኝ ነበር» የሚለው ተማሪው በተለይ የቦሌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ይሄንኑ ተሰጥኦውን የሚያውቁ የትምህርት ቤቱ አመራሮች የፈጠራ ክበብን እንዲመራ ካደረጉት በኋላ የራሱ ቢሮና ምቹ ሁኔታ በማግኘቱ ማሽኑን ሊሠራ መቻሉን ነግሮናል። ወደ ሥራው የገባው ወደ ኢኮኖሚ ነፃነት ሊያሻግረኝ ይችላል ብሎ መሆኑንም አንስቷል። ከእንግዲህ ወዲህ መፍትሄ በሚባል ድርጅት ሥር የፈጠራ ሥራው በሰፊው ለገበያ ቀርቦ የሕብረተሰቡን ችግር የሚፈታ ስለመሆኑም ተናግሯል።

ስያሜው ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ እንዲሆን ሰርች በማድረግ የተመራመርኩት ወደ ውጭ የመላክ ሃሳብ ስላለኝም ነው ብሏል። ተማሪው የሠራው የልብስና የተለያዩ እርጥበት ማድረቂያ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ያጠናውን ጥናት መሠረት አድርጎ እንደነገረን የኤሌክትሪክ ፍጆታው በኢትዮጵያ ቆጣሪ ሥርዓት መሠረት በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ብር ከአንድ ሳንቲም ነው ። ግፋ ቢል አምስት ቤተሰብ ያለውና በሳምንት አንዴ የሚጠቀም ነዋሪ የወር ኤሌክትሪክ ፍጆታው ከአራት ብር አይበልጥም። በልብስ ቁጥር ሲለካም አገልግሎቱ ልብሶቹ የህፃናት ከሆኑ በርካታ ልብሶችን ማድረቅ ያስችላል። የአዋቂ ከሆኑ እስከ 80 ልብሶችን ማድረቅ የሚያስችል አቅም እንዳለው ይናገራል።

ሥራው ከሌላው ገበያ ላይ ያለው የልብስ ማድረቂያ የሚለየው በትንሽ ቦታ እንደጌጥ ሳሎን ውስጥ መቀመጡ ነው። ግራና ቀኝ ለማድረቅ የሚያስችል ራሱን የቻለ ሶኬት አለው። እንደ ቤት ማሞቂያም ይጠቅማል። በዋጋ ደረጃም ከሰባት እስከ አሥር ሺህ ብር መሆኑን ያነሳል። መጠኑ ዝቅ ያለ ማሽንም ስላለ ዋጋው እንደ ተጠቃሚው አቅም ይወሰናል፡፡

በአውደ ርዕዩ በርካታ ሴት ተማሪዎች የፈጠራ ሥራቸውን አቅርበዋል። የሴቶቹንም የወንዶቹንም ሥራ የሚጎበኙ በርካታ ሴት ተማሪዎች በግልና በቡድን እንደ ትምህርት ቤት መጥተው ሲጎበኙም አስተውለናል።

“በፈጠራ ሥራዎች እሳተፋለሁ። የፈጠራ ሥራ አድናቂም ነኝ። ከትምህርት ቤት ተመርጠን ለጉብኝት የመጣነውም። በዚሁ ተሰጧችን ነው» የምትለው የግሪን ኒው ጀነሬሽን የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናታኒያ ክብሮምን አንዷ ናት። በቤተ ሙከራ ውስጥ አሲድ መሆንና አለመሆኑን የሚለይ አመልካች (ኢንዲኬተር) የፈጠራ ሥራ አይታለች። በተለይ የተማሪዎችንም ሆነ የሠራተኞችን ዐሻራና ፎቶ የሚወስደው የገቡበትን ሰዓት ጭምር መዝግቦ የሚያስቀረው የሰዓት መቆጣጠሪያ(አቴንዳንስ) ስቧታል። የሥእልና ሌሎች ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ሥራዎችም አይታለች፡፡

እንደ ተማሪዋ ይሄን ማየት የቻለችው የፈጠራ ሥራ ውድድር በከተማ ደረጃ በየዓመቱ በመደረጉ ነው። ይሄም አእምሯቸው ላይ ያለውን ማውጣት ያልቻሉ ተማሪዎች እንዲያወጡ ያደርጋል። ያበረታታና ለዘለቄታውም የሚጓዙበትን መደላድል ይፈጥራል ብላለች፡፡

አውደ ርዕዩ መስማት የተሳናቸውን በአጠቃላይም የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎችም አሳትፏል። በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዋ በኩል ያነጋገርኳት ገነት ሙላቱ በየካቲት ልዩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ናት። መስማት የተሳናት ስትሆን ከአፀደ ህፃናት ጀምሮ በፈጠራ ሥራ የመሳተፍ ፍላጎቱ ነበራት። ይሄን ፍላጎቷን ተከትላም በትምህርት ቤት በኩል በሚደረግ የተለያየ የፈጠራ ሥራ ስትወዳደር ቆይታለች። አሸንፋም ማበረታቻ ሽልማት ያገኘችበት ጊዜ አለ።

እስከ ሚያዝያ 18 በዘለቀው የሦስት ቀን አውደ ርዕይ ደግሞ ትምህርት ቤቷን ወክላ እና እናቷና የአካባቢው ማህበረሰብ በአቅራቢያው ተክሎ እንዲጠቀምበት አስባ በሠራቸው የእህል ወፍጮ መሳተፍ ችላለች። ወፍጮው ከሌሎቹ የሚለየው ቻርጅ በሚደረግ ባትሪ በተሻሻለ መንገድ ዘምኖ መሠራቱ ስለመሆኑም ነግራናለች። ሥራዋ በአውደ ርዕዩ ከተመረጠላት በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመወዳደር ዓላማም ሰንቃለች፡፡

መምህርት ጡሪ ታዬ

አዲስ ከተማ ከሚገኘው ገሊላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአፋን ኦሮሞ ትወና እና ጥበብ እንዲሁም የእጅ ሥራ መምህርት የሆነችው ጡሪ ታዬ ትምህርቱ በርካታ ተማሪዎች በትምህርት ቤትና በየሚኖሩበት አካባቢ በፈጠራ ሥራ እየተሳተፉ ራሳቸውንም ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ የማድረግ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ታነሳለች። ለአብነት ከክር ህፃናት የሚወዱትን የዳንቴል የህፃናት ጫማ፤ ቦርሳ እና ሌሎች የእጅ ሥራዎችን እየሠሩ ማቅረባቸውን ትገልጻለች። ህፃናት በብዛት ቤት ውስጥ ጫማ አያደርጉም ፤ በቦዶ እግራቸው ነው የሚሄዱት። ይሄ ደግሞ እግራቸው በወደቁ ስለታማ ነገሮች እንዲቆረጥ ደግሞም ለብርድ እና ለተለያየ የጤና ችግር እና አደጋ እንዲጋለጡ ሲያደርግ ይስተዋላል የምትለው መምህርቷ በአውደ ርዕዩ ችግሩን ለመፍታት በኪሮሽ የሚሠሩ የእጅ ሥራ ውጤቶች ይዛ መቅረቧንም ነግራናለች። ሥራውን ያቀረበችው በኪሮሽ የሚሠራ የእጅ ሥራ እንዳለ ወደ አውደ ርዕዩ የሚመጡ ተማሪዎች እንዲያውቁ ለማስተዋወቅ ጭምር መሆኑንም አንስታለች።

ከእቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪዎቹ ሂክራም መሐመድ እና ኤፍራታ አለማየሁ በጋራ በአይቲ ዘርፍ የፈጠራ ሥራ ነው ጉለሌ ክፍለ ከተማን ወክለው የተሳተፉት። አንድ አፈር ላይ ምን ዓይነት አዝርት እና ማዳበሪያ መጠቀም አለብን የሚለውን የሚመክር የአይቬዝድ ሥርዓት ነው የሠሩት። ከዚህ በፊት በትምህርት ቤቱ ከተሠሩ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሁም በቤታቸው ካገኙት ቁሳቁሶች ነው የሠሩት። ውስጥ ያለውን ሥርዓት እንዲደግፍላቸው የስልክ ቀፎ ፤ ጃንፐር ዋየሮች፤ አይዲኖ፤ ኤልሲዲ ዲስፕሌይ፤ ፒኤች ሴንሰርሪ መጠቀማቸውን ይናገራሉ። ኮድ ለማድረግ ኮምፒውተርም ተጠቅመዋል። ይሄን መሥራት ያስቻላቸውን ተሞክሮ እና ልምምድ እንዲያደርጉ ያስቻላቸው በፊዚክስ፤ በባዮሎጂ እና በኬሚስትሪ ዘርፍ የተደራጀው የትምህርት ቤታቸው ቤተ ሙከራ መገልገላቸው መሆኑን ይናገራሉ። እንዲሁም እአአ በ2024 በአርቲፊሻል ኢንተሌጀንስ የተዘጋጀውን ሥልጠና መውሰዳቸውም አግዟቸዋል። አሁን በፕሮጀክቱ ካለፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመወዳደርም አስበዋል። የፈጠራ ሥራው ለመሥራት ዓላማ አድርገው የተነሱት የሀገራቸውን የግብርና ዘርፍ ችግር ለመፍታት እና ምርታማነቱን ለማረጋገጥ ነው፡፡

ተማሪ ዳግማዊ መላኩ የገላን የወንዶች ትምህርት ቤትን የተቀላቀለው በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 98 ነጥብ ዘጠኝ እንዲሁም በመግቢያው ከ88 በላይ ነጥብ በማምጣት ነው። «ከዚህ ቀደም የፈጠራ ሥራዎች እሠራ ነበር» ያለው ተማሪው ትምህርት ቤቱ አዳሪ መሆኑ የፈጠራ ሥራዎቹን በስፋት ለመሥራት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለትም ይናገራል። በአውደ ርእዩ «ሳይቨር ሎክ አቴንዳንስ ሲስተም» የተሰኘ የፈጠራ ሥራ ይዞ ነው የቀረበው። የሚሠራው በጣት ዐሻራ፤ በፌት ገጽታ እና በአርኤፍ አይዲ ሲሆን አቴንዳንሱን ይመዘግባል። በኤግዚኤል ፋይል ላይም አደራጅቶ ያስቀምጣል። ሥራውን ለመሥራት የተጠቀምኩት «ፕሮግራሚንግ ላንጌጅ ፓይተን» ነው የሚለው ተማሪው «ሀርድ ዌር ኮንፖነንቶቹን ኮንትሮል» ለማድረግ «አርዲኖ» መጠቀሙን እና ይሄንም «በሲፕላስ ፕላስ» ፕሮግራም ማድረጉን ያስረዳል፡፡

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ «ስቲም ኢዲኬሽን» ተምሮ በሶስት ዙር ማለፉንም ነግሮናል። እዚህ ከሠራቸው መካከል መፀዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ ራሱ የሚያፀዳዳ ፤ ወርልድ ሮቦቲክስ ኦልምፒያል ላይ ሚል ሜት ሮቦት የተባለ ፕሮጀክት ይጠቀሳሉ። የሮበቱ ፕሮጀክት በተለይ ለህሙማን የኮረና ቫይረስ ዓይነት ተላላፊ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከሰዎች ተገልለው ኮማ ውስጥ ሲቀመጡ ምግብ ይዞላቸው የሚገባና የሚወጣና ሰው በሽታ እንዳይተላለፍበት ማድረግ የሚያስችል ነው። ይሄን ለማስቀረት በመስመር የምትሄደው ሮቦት ምግባቸውን አድርሳላቸው ተመልሳ እንድትመጣ ሠርቷል። ይሄም ከበሽተኞቹ ጋር ሊኖር የሚችለውን ንክኪ መቀነስ ያስችላል። በተጨማሪም በቡድን የተለያዩ ሥራዎችን ይዘው መቅረባቸውን ያነሳል። ይሄን ያሸነፈ ቡድን ኢትዮጵያን ወክሎ ቱርክ ሀገር የሚወዳደርበት አጋጣሚ የነበረ መሆኑን ያስታወሰው ተማሪው አውደርዕዩ ላይ ከጓደኞቹ ጋር 3ኛ መውጣት መቻላቸውን ነግሮናል። በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተካሄደው ውድድር ላይ የተለያዩ መጠጦችን የሚያደባልቅ የፈጠራ ሥራም ሠርቷል። ፕሮጀክቱ አንዱን ሲጫኑት ሻይን ከቡና ከወተት የሚደባልቅ ማኪያቶ የሚሠራ ነው።

በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት የተማሪዎችና የመምህራን የሥራ ፈጠራ ውጤቶች ይበል የሚያሰኝ ነው። በተግባር የተደገፈው የትምህርት አሰጣጥ ውጤት እያመጣ መሆኑን አንዱ አመላካች ነው።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You