ድሮ ባልተጻፈ ሕግ መመራት ሐጢያት አይደለም፤ እንደውም ያስመሰግናል። አሁን ላይ፣ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ግን ባልተጻፈ ሕገመንግሥትም ይሁን ሌሎች ሕግጋት መመራት የጤና አይደለም፤ በመሆኑም ጥልቅ ውይይት የሚያስፈልገው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። አሁን አሁን ጉዳዩ፣ የአሜሪካ ጫና ቅጥ እያጣ፣ ቅጣምባሩ እየጠፋ በመምጣቱና የአገራትን ሉአላዊነት እስከ ቀበሌ ድረስ ወርጄ ካልበጠበጥኩና ካላበጣበጥኩ በማለቱ እየተጋለጠ መጣ እንጂ መቼም ቢሆን ለተንቦረቀቀ ጥቅሟ (“ናሽናል ኢንተረስት” ለምትለው) ስትል ከሰው ትከሻ ላይ ወርዳ አታውቅም። የአሁኑ ዘመን ቅብዝብዝነቷ ግን ግራ ያጋባል፤ ላራስ ሳይሆን ለእሷ ለእራሷ፤ በራሷ ላይ ጠላት እያፈራች ላለችው እናስብላት ዘንድ ሁሉ ያስጨንቃል።
አሜሪካ እየሠራች ያለችው ሥራ ቢታወቅም አሁን ግን በሰው አገር እየገባች እስከ ቤተሰብ ድረስ ካላስተዳደርኩ፤ ካልሾምኩና ካልሻርኩ የማለቷ ጉዳይ ለብዙዎች ግራ ገብ ሆኗል። “ምን ነካት?” ከሚለው አልፎ “ምን ልትሆን ነው?” ወደ ማለት ሁሉ እያዘነበለ ይገኛል። አሜሪካ ሀብታም ነች፤ አሜሪካ ሃያል ነች። አሜሪካ የዓለም ሁሉ የበላይ ብቻ ሳትሆን የዓለም ፖሊስ ነች፤ አድራጊ ፈጣሪ፣ ሿሚና ሻሪ፤ አጉራሽና አልባሽ ወዘተ አድርጋ እራሷን አስቀድማ በመሾሟ ምክንያት ይሄው እውቅና በዓለም ተሰጥቷት ያሰበችውን ሁሉ ስትሆን ኖራለች። መሾምም ሆነ መሻር፣ ማግኘትም ሆነ ማጣት፤ መሞት ሁሉ ሳይቀር አሜሪካ ካልፈቀደች እንደማይሆን አድርጎ ዓለም ሁሉ ተቀበለ። ተቀብሎም የማይሻር ታሪክ፣ የማይገሰስ ማንነት አድርጎት አረፈው። ይህንን መልካም አጋጠሚ የተጠቀመችው አሜሪካም እነሆ፣ “ኧረ እንዳሻሽ ..” እንዳለው ዘፋኙ እንዳሻት ስትሆን ክፍለ ዘመናት ተፈራረቁ። 21ኛው ክፍለ ዘመን ባተ።
በእነዚህ በተፈራረቁ ክፍለ ዘመናት ውስጥ (ከሌላው የተሻለ ቢሆንም) እንዳሻት ከሆነችባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። (“እንዳሻት” የሚለውን ከሥሩ ለመገንዘብ የፍቅረ ስላሴን “እኛ እና አብዮቱ”ን ማንበብ)የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት እድሜው ዛሬ አይደለም፤ ትናንትም አይደለም፤ ከ120 ዓመታት የዘለለ ነው። በእነዚህ የረዥም ዓመታት የጊዜ ዥረት ውስጥ በእሷ የተሰራ አንድም ሆስፒታል ወይም ት/ቤት የለም። መንገድ ቅንጦት ነው፤ የውሃ ጉድጓድ እንኳን ታይቶ አይታወቅም። “… ጉራ ብቻ” እንደተባለው ስንዴ ብቻ በመላክ ነው “ወዳጅነታችን” እዚህ ዛሬ ድረስ የዘለቀው። (እርግጥ ነው በኋላ በዚህችው አገር አምባሳደር የምታደርጋቸውን አስቀድማ በፒስ ኮርፕስ ስም ልካች።) ምንም ሆነ ምን ሁለቱ አገራት መልኩን ሲቀያይር በኖረ የአገራት ግንኙነት ውስጥ አልፈው እዚህ ደርሰዋል። ብሎ ብሎ ቢያቅተው ደርግ በ24 ሰዓት ቢያስወጣትም (በዚሁ ባልተጻፈ ሕጓ ምክንያት) ያው ወቅቱን ጠብቃ ለመመለስ በቅታለች።
አሜሪካ ቀላል አይደለችም፤ ብሔራዊ ጥቅሜ (ናሽናል ኢንተረስት) በምትለው ሁሉ አጥፍታ ለመልማት ምን ጊዜም እራሷን አዘጋጅታ የምትኖር አገር ስትሆን ለዚህ ደግሞ ያልተጻፈ ሕጓን ሥራ ላይ ማዋል ብቻ ሳይሆን ይሉንታ የሚባል ነገር እንኳ ከነአካቴውም ያልተፈጠረባት መሆኗ ነው። ይሄንንም ወደ እራሳችን ስናመጣም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ንጉሥ ኃይለሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ያቀረቡትን (ዓለምን እስከ ዛሬ እያስደመመ ያለ) አቤቱታ ከምንም ባለመቁጠር ለፋሽስቱ ሥውር ድጋፍ ያደረገችበት አካሄድን እናገኛለን።
የሩሲያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሚያብራራው የሩሲያ መንግሥት ሰነድ ላይ እንደሰፈረው በዛን ወቅት ሃያላን ከሚባሉት አገራት መካከል ከኢትዮጵያ ጎን የቆመችው ሩሲያ ብቻ ነበረች። በወቅቱ አሜሪካ የወሰደችው አቋም የፋሽስት ጣሊያንን የሚያበረታታ እርምጃ ሲሆን እሱም “የገለልተኝነት አቋምን ነው የማራምደው” በማለት ለተበዳይ በመቆም ፋንታ ለበዳይ ሥውር ትብብር የሚያደርግ አካሄድን ነበር።
አሜሪካ ክብርና ኩራቷ በጊዜ ያካበተችው ገንዘቧና አስቀድማ የካበችው ማንነቷ ነው። “ቀድሞ መገኘት ነው” እንደሚባለው ዛሬ ላለችበት መንበር መነሻው የእሷ ቀድሞ መገኘት ብቻ ነው። በቃ – ከዛ ዓለምን በራሷ ልክ ማስፋትና ማጥበቡን ተያያዘችው። በእርግጥም ተሳክቶላት ኖራለች፤ በፈለገችው ሰዓት እየበረረችና ዋና ዋና ከተሞች እያረፈች ከፈለገች ትሽራለች፣ ከፈለገች ትሾማለች፤ ሁሉንም ካልፈለገች ደግሞ እንደነ ሳዳም ሁሴን … (ይህን ሁሉ የምታደርገው እንግዲግህ የተጻፈውን ሕግ ሠርዛ ያለትጻፈውን ተግባራዊ በማድረግ ነው።)
አሜሪካንን ከአቅሟ በላይ ሰማየ ሰማያት ያወጣት ከመሪዎቿ የማስተዋወቅና ቀድሞ የመገኘት አቅም በላይ የሌሎች አገራት እሷን የማምለክ ደረጃ ከፈጣሪያቸው በላይ መስፈንጠር ነው። ሁሉም አንድ ነገር ሲፈልግ እሷ እንድትደርስለት ነው የሚፈልገው፤ የሚማፀነውም እሷኑ። ወደ ሥልጣን ለመውጣት የአሜሪካ ዕርዳታ፤ ሥልጣን ላይ ያለውን ለመጣል የሲአይኤ ክትትልና ድጋፍ፤ ኮሽ ሲል ኤፍቢኢ ድረስልኝ ወዘተ ወዘተ እና የመሳሰሉት ተለማምጦዎችና ደጅ ጥናቶች፤ ከዛም ባለፊ የሚደረገው የማያቋርጥ የክጀላ እንቅስቃሴ ሁሉ ተዳምረውና ተደማምረው ነው ዩኤስኤ አሜሪካንን ዛሬ እዚህ እሰው አገር ቀበሌ ድረስ ካልገባሁና ማንነቴን ካላሳየኋችሁ ማለት ጥግ ድረስ እንድትንከባለል ያደረጋት። ቢሳካም ባይሳካ ደፍራናለች፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባልተጻፈ ሕግ ተደፍረናል።
አሜሪካ ዛሬ “የኢትዮጵያ መንግሥት …” ከሚለው መደበኛ የዲፕሎማሲና አስተዳደር ቋንቋ ወርዳ ክልሎቻችንን በስም እየጠራች ወደ ላይ፣ ወደ ታች፣ ወደ ጎን፣ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ እያለች በማዘዝ ስፖርት ልታሰራን እየፈለገች ነው፤ መፈለግ በቻ አይደለም ጀምራዋለች። የቀረው የኛ የመስጠትና አለመስጠት ጉዳይ ብቻ ነው።
አስቀድማ ለምን ልሩጥ ሳይሆን የት ድረስ ልሩጥ የሚሉና በሆዳቸው የተሰነጉ ባንዳዎችን አደራጅታለችና ከላይ የገለፅናቸውን ትእዛዛት ለማዘዝም ሆነ ትእዛዛቱን ለማስፈፀም መንገዱ ብዙም ኮረኮንች አልሆነባትም፤ አዋግታለች – ይህ በጣሊያን፣ በሱማሌና በሌሎችም ታይቷል፤ መንደር ለመንደር አደባድባናለች ሌላም ሌላም። መቸም ቢሆን የባንዳ ቁጥሩ ትንሽ ነውና በአገር ወዳዶችና አንድነት ሃይሎች መስዋዕትነት እዚህ ደርሰናል።
አሜሪካ ባልተጻፈ ዓለም አቀፍ ሕግ ያሻትን ስታደርግ ለመኖሯ ማረጋገጫችን ብዙ ነው። በሽብርተኝነት ላይ ዓለም አቀፍ ጦርነት (war on terror)ን አውጄአለሁ በማለት አገራት ከጎኗ እንዲሰለፉ ያደረገችውን ጥረት ወግድ ያሉ አገራትን “በጥቁር መዝገቤ አስፍሬአችኋለሁ” ካለች በኋላ የጦር መሣሪያ ግዥን ጨምሮ የተለያዩ እቀባዎችን ያደረገችባቸው ሲሆን ለዚህም ኩባ፣ ኢራን፣ ቬኑዙዌላ … አገራት ተጠቃሽ ናቸው። (በአፍሪካ አሻንጉሊት መሪዎችን ለመሾም በሄደችባቸው እርቀቶች አህጉሪቱን ምን ያህል እንዳጎሳቆለች ከዚህኛው ቅዳሜ በፊት በነበረው የ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ያሰፈሩትን ጽሑፍ ይመለከቷል።)
ከሩሲያና ቻይና ጋር በገባችው የአትጋፉኝ ፍጥጫ ምክንያት ካሁን አሁን ጦርነቱ ተጀመረ በሚል የዓለም ሕዝብ ዓይኑን አግጥጦ፣ ጆሮውን አቅንቶ እየተጠባበቀ ሲሆን የዚህ ሁሉ ሰበቡ የአሜሪካ ከኔ በላይ ላሳር ግትር አቋማና ለይስሙላ ከምታቀነቅነው “ውድድር” ይልቅ የያዙትን ይዞ መቆየት (ስታተስ ኮ)ን፤ የእስከ ዛሬውን የአሜሪካ የበላይነትንና ብቸኛ የዓለም ፖሊስነትን የማስቀጠል አባዜ ነው።
እራሷን ጨምሮ አገራት ተሰብስበው ያፀደቋቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች (ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር) በመደምሰስ፤ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ባዘጋጀው ስብሰባ (ሜይ 7) ላይ እንደተናገሩት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመሰረዝ፣ በዝግና ማንንም ባላሰተፈ ሁኔታ ባፀደቀቻቸው፣ አካታች ሳይሆን አግላይ የሆኑ ሕጎችን በማውጣትና እንደ ዓለም አቀፍ ሕግ በመቁጠር በሌሎች አገራት ላይ ጫና ለመፍጠር የምትሞክር አገር ነች አሜሪካ።
ላቭሮቭ እንዳሉትም ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብም ከዚሁ ከአጉል ጀብደኝነት፣ ማን አለብኝነትና እጅግ የከፋ ራስ ወዳድነት፤ እነዚህንም ሥራ ላይ ለማዋል ያልተጻፈ ሕጓን ከመጠቀም የመጣ ስለመሆኑ የአፍታም ጥርጣሬ አይኖርም።
በተለይ ከትራምፕ መመረጥና አሜሪካንን ዳግም ታላቅ የማድረግ እቅድ ከተዘረጋ በኋላ “ሁሉንም ኃይል ያስተካክለዋል” (might makes right) በሚለ መርህ የምትመራው አሜሪካ ድስቷን ያልጣደችበት አገር የለም። ትጣድ እንጂ ባብዛኛው ሲያር፣ ተሳካ ያለችውም በጥላቻ እንድትታይ ሲያደርጋትና ከወዳጅ ዘመዶቿ ሲነጥላት ነው የሚታየው።
ይህን የእሷን ከወዳጅ ዘመድ መነጠልና ጠላት እያበዙ የመሄድ ነገርን በተመለከተ አያሌ መረጃና ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚቻል ሲሆን፤ ከሁሉም በላይ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ላይ፤ እማያገባት ውስጥ በመግባት (የእርጎ ዝምብ በመሆን)፣ የጣለችው እገዳ ወይም ማዕቀብ ድርጊቷን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የለምና ማስረጃ ፍለጋ የትም መሄድ አያስፈልገንም።
ያለ ምንም ጥርጥር አሜሪካ ተሸውዳለች፤ ከኔ በላይ ትበል እንጂ ተበልጣለች። ሌላው ቢቀር ሎሬቱ “እጅ ስጥ አለኝ ፈረንጅ እጅ ተይዞ ሊወሰድ?” ያለበትን ሥራውንና ምክንያቱን አለማወቋ እራሱ ትዝብት ላይ የሚጥላት ብቻ ሳይሆን የ120 (የኢትዮ-አሜሪካ) መልካም ወዳጅነቷን የሚያሳጣት ፀረ-ዲፕሎማሲ ድርጊት ውስጥ ነው የከተታትና ስለ መሸወዷ ማስረጃ ነው።አሜሪካንን የእግር እሳት የሆነባት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እቅዷም ይሁን ፍላጎቷ ወደ ተገባር ሊሸጋገር፤ ወደ መሬት ሊወርድ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን አፍሪካ እንዴት ከእነ ቻይና ጋር ወዳጅነት ጀመረች፤ ተንሰራፋችም የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይነው።
ይህንን በስፋቱም ሆነ ወርዱ መዘርዘር ለጊዜው ፋይዳ የለውም። ባጭሩ የቻይና ወደ አፍሪካ መግባት የአፍሪካውያንን ዓይን ገልጧልና የሲኖ-አፍሪካ ግንኙነት በየትኛውም መስፈርት ይመሰገናል። በመሆኑም ግንኙነቱ አሜሪካንን የሚያበሳጭ ከሆነ ከማዘን በስተቀር (ከአሜሪካ አንድ ድልድይ እንኳን የማያውቀው ህዝብ) ሌላ ምንም ማድረግ አይችልም።
ሰሞኑን “የአፍሪካ ቀን” እየተከበረ መሆኑን ተከትሎ በርካታ አፍሪካንና ዓለም አቀፉን ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲቀርቡ ሰንብተዋል። ከእነዚህም መካከል የአፍሪካና የአሜሪካንን የእስከ ዛሬ ግንኙነት የመረመረ፤ አዲሱን የሲኖ-አፍሪካ ወዳጅነት የፈተሹ ይገኙበታል።
እንደ አስተያየቶቹና ፍተሻዎቹ ከሆነ አሜሪካ እስከ ዛሬ በአፍሪካ ላይ ስታላግጥና በአህጉሪቱ ድህነት ስትሳለቅ ከመኖሯም ባለፈ ከማይረባ እርዳታ ልገሳዋ ፈቀቅ ብላ ፊቷን ወደ አፍሪካን ማልማትና የጋራ ተጠቃሚነት አዙራ አታውቅም። በመሆኑም አፍሪካ ለዘመናት በጭለማና ረሃብ ውስጥ ኖራለች። ያ ዘመን አሁን የበቃ ይመስላል። በቻይና የረጅም ጊዜ ስትራተጂክ እቅድን መሰረት ባደረገ የቻይና-አፍሪካ ግንኙነት አህጉሪቱ ፊቷን ወደ ልማት አዙራለች። በዚህም ለውጦችን እያየች ነው።
አስተያየቶቹ ያስተናገዱት እነዚህን ብቻ አይደለም። ከመስተንግዷቸው መካከል ለአሜሪካ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችም ይገኙበታል። ከምክረ ሃሳቦቹም አንዱ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር በእስከዛሬው አይነት መንገድና ግንኙነት ልትቀጥል አትችልም። አዲስ ግንኙነት መመስረት ይቻላልና ያላት እድል እሱ ነው። ይህንን አዲስ ግንኙነት በመመስረት በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች። ተጠቃሚ ከምትሆንባቸው ዘርፎችም ዋናው “ለስላሳ ሃይል” (Soft power) ሲሆን ሙዚቃን፣ መዝናኛንና የመሳሰሉ ዘርፎች በአፍሪካ ገና ያልተነኩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ናቸውና በእነሱ ላይ በመሰማራት በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች የሚለው ሲሆን ሙሉ ሃሳቡን “Africa is greatest geopolitical opportunity. Do the US know it?” በሚል ርእስ ከቀረበው ጽሑፍ መረዳት ይቻላልና ቸር እንሰንብ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013