ርግጥ ነው ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የረጅም ዘመን የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት አገር ናትና ከአገራት ጋር በትብብርና በመደጋገፍ ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ ናት። ከዚህም በላይ ከሁሉም የዓለም አገራት በሚባል ደረጃ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅግ የሰመረና የተዋጣለት እንደሆነ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው ። የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ዲፕሎማሲ መርህ መከባበርና ሉዓላዊነትን ማክበር የሚል ነው። ስለሆነም በማንኛውም የታሪክ ሂደት ኢትዮጵያ የተከተለችው የዲፕሎማሲ መንገድ ይህንን መርህ በእጅጉ ያከበረና ያስከበረ ነው። ኢትዮጵያ በሌላ በማንም አገር የውስጥ ጉዳይ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት ሁሉ በራሷ ሉዓላዊነትና የውስጥ ጉዳይ ማንም ገብቶ እንዲፈተፍት ዕድል አትሰጥም።
ይህንን መርህ ልጣስ ያለ ማንኛውም አካል ሲነሳ ማንም ይሁን ማን ምላሿ አይቻልም፣ አይፈቀድም የሚል ብቻ ነው። ይህንን ደግሞ በታሪኳ ደጋግማ በማሳየት ለብዙዎች ምሳሌ ሆና ኖራለች፤ አሁን ምሳሌ ሆና ቀጥላለች። ከታሪክ መማር ያልቻሉ አንዳንድ አገራት ሀብትና ጉልበት አለን ብለው በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን በርቀት መቆጣጠሪያ ለመዘወር ቢያስቡም አንድ ጊዜም ተሳክቶላቸው ግን አያውቅም፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሉዓላዊነቷ ትልቅ ክብር የሚሰጡና የማይደራደሩ ኩሩ ዜጎች አገር መሆኗ ብቻ ነው።
እውነት ነው የተያያዝነው አገራዊ ለውጥና የልማት ጉዞ ዓለም አቀፍ ትብብርንና ድጋፍን ይሻል። ኢትዮጵያን በልማት ለማስቀደምና ለማበልጸግ በምናደርገው ጥረት ትብብርና ድጋፉ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አይካድም። ይሁንና ይህንን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ሉዓላዊነትን ለመድፈርና በውስጥ ጉዳይ ገብቼ ልፈትፍት የሚል ማንኛውም አገር ሲመጣ ግን ምላሹ ይህ ነገር በኢትዮጵያ በፍጹም አይቻልም የሚል ይሆናል ።
ይህን እንደመነሻ ለማንሳት የወደድነው ከሰሞኑ የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እያደረገ ያለውን የቀቢጸ ተስፋ ጫና በማስመልከት ነው ። የሰሞኑ የአሜሪካ ተግባር አንደኛ መነሻ የአሜሪካ አስተዳደር በዓባይ ወንዝ ላይ ከሚከተለው የተዛባ ፖሊሲ ጋር ተያይዞ በዚህ አቅጣጫ ያለአግባብ ለመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ ያለችውን ግብጽን ለማስደሰት ነው። የአሜሪካ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ሲልም በፕሬዚዳንት ትራምፕ የአስተዳደር ዘመን ለግብጽ ዓይን ያወጣ ውግንና በማድረግ ኢትዮጵያን ለመጫንና ለማስፈራራት ያደረገው የቀቢጸ ተስፋ ሙከራ ያተረፈለት ነገር ቢኖር ትዝብት ብቻ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር አሁንም የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ይህንን የተሳሳተ መንገድ መከተሉና ትርፍ በሌለው መንገድ መንጎዱ ነው።
የባይደን አስተዳደር ሀብትም ጉልበትም አለኝና በማንኛውም አገር ጉዳይ ገብቼ አለቃ እሆናለሁ የሚል ህሳቤን መሰረት አድርጎ የኢትዮጵያን ጥቅም በመጉዳት ኢ-ፍትሐዊዋን ግብጽን ለማስደሰት እየሰራ ቢሆንም ለአውነትና ለፍትሕ በጽናት የቆመችው ኢትዮጵያ ይህንን ዓይነት የእብሪተኝነት አካሄድ በፍጹም ልትቀበለው እንደማትችል ሊረዳው ይገባል። በሌላ አነጋገር በጫናና በማዕቀብ ጋጋታ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም፤ የለምም፤ ወደፊትም አይኖርም።
የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ በመክተት የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት አስተጓጉዬ ግብጽን አስደስታለሁ በሚል የማይጨበጥ ተስፋ ይህንን እያደረገ ቢሆነም ሊረዳው የሚገባው ትልቅ ቁምነገር ታላቁ የህዳሴ ግድብ በፍትሐዊነት መርህ በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት እየተገነባና ለፍሬ እየተቃረበ ያለ የመላ አፍሪካውያን ኩራት የሆነ ግድብ በመሆኑ ማስተጓጎል በፍጹም እንደማይቻል ነው ።
“ታሪክ የሌላቸው አገራት በገንዘባቸው አቅም ሊያዙን እንደማይችሉ፤ ኢትዮጵያውያን ያልተገዛንና የማንገዛ ያልተንበረከክንና የማንበረከክ መሆናችንን አልተገነዘቡም ። የእኛ ልማትም ጥፋትም በመሰረታዊነት የሚወሰነው በእኛ በኢትዮጵያውያን ብቻ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ያስተላለፉት መልዕክትም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ።
እውነት ነው የኢትዮጵያ ብልጽግና ዋነኛ ተስፋና ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ። የታላቁ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ ለዚህ ስኬት የበቃው መላ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለምንም የዕድሜ፣ የጾታ፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገደቡ ባደረጉት አኩሪ ርብርብ ነው ። ቀደም ሲል በአሜሪካ መሪነት የሚዘውሩት የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ኢትዮጵያ መብቷ ከሆነው የዓባይ ወንዝ ምንም እንዳትጠቀም ብድር በመከልከል ለማስቆም ሞክረው ነበር ። ክብር ለመላ ኢትዮጵያውያን ይሁንና ብድር በመንፈግ ኢትዮጵያን በሀብቷ ከመጠቀም የሚከለክላት ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ለማረጋገጥ ችለናል ።
እነዚህ ሁሉ ጫናዎችም ኢትዮጵያን አያንበረክኩም ።ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በውስጣዊ ጉዳዮቻቸው ማንም ጣልቃ ገብቶ እጃቸውን እንዲጠመዝዝ ፍላጎትም የጎደፈ ታሪክም የላቸውም ።ትላንት ‹‹ድምፃችን ለነፃነታችንና ሉዓላዊነታችን›› በሚል በአዲስ አበባ የተካሄደው የወጣቶች ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍም ለዚህ አንድ ማሳያ ነው ።
ኢትዮጵያውያን ለማንኛውም የውጭ ጫና እጃቸውን የማይሰጡ ስለመሆናቸውም ትላንት በአደባባይ ላይ በመውጣት አምባገነኖችንም እጃችሁን ከኛ ላይ አንሱ በሚል እምቢተኝነታቸውን አሳይተዋል ።ኢትዮጵያ ማለት ይቺ ናት ፡፡ እናም ሉዓላዊነታችንን በገንዘብ ለመግዛትም ሆነ በጫና ለመድፈር የሚሞከር ማንኛውም ኃይል ደጋግሞ ሊያስበውና ሊያጤነው የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ሉዓላዊነቷን በጫና የምታስደፍር ኢትዮጵያ የሌለችና መቼም የማትፈጠር መሆኗን ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013