ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ፈተናዎች አጋጥመዋታል ። ይሁን እንጂ ለነዚህ ዱላዎች ተንበርክካ እጅ የሰጠችበት የሽንፈት ታሪክ የላትም። ከውጭ ኃይሎች ቀጥተኛ ወረራ ጀምሮ በተዘዋዋሪ መንገድ አገሪቱን ለማዳከም የተሸረቡ ሴራዎችና አሻጥሮችም በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተደምድመዋል።
ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምዕራባውያን አፍሪካን በተቀራመቱበት ወቅት ፋሽስት ኢጣሊያም ኢትዮጵያን የግሏ ለማድረግ ቋምጣ ተነሳች። በወቅቱ ወራሪዎቹ ከነበራቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያና ከደረሱበት ስልጣኔ አንጸር ከዚህ ድርጊታቸው ሊያቆማቸው የሚችል አንዳችም ኃይል ይኖራል ብሎ የገመተ አልነበረም።በዚህ መሰረት ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረር የመጀመሪያውን ስህተት ፈጸመች።
እንዲህ አይነቱን ክብረነክ ተግባር ፈጽሞ የማይቀበሉት ኢትዮጵያውያን ይህንን ወረራ አሜን ብሎ የሚቀበል የሞራል ውድቀት አልገጠማቸውም። ይልቁንም ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት በመነሳት ይህንን ኃይል ለመመከት ያገዳቸው አንዳችም ኃይል አልነበረም። በወቅቱ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ጉልበት የሌለውም በፀሎቱ ለኢትዮጵያ ተፋልሟል።
በዚህ መሰረት በዓለም ላይ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅና ነጭ ወራሪዎችም ፈጽሞ ባልገመቱት ሁኔታ ወራሪው ኃይል እያንገፈገፈውም ቢሆን የሽንፈትን ጽዋ ተጎነጨ። ኢትዮጵያም በዓለም ላይ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ነጭ ወራሪ ኃይል ፊት ለፊት በመግጠም ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት አገር በመሆን ታሪክ አስመዘገበች። ይህ ታሪክ ደግሞ ከራሷም አልፎ ለሌሎች በግፍ አገራቸውን ለተቀሙና የሞራል ስብራት ለደረሰባቸው አፍሪካውያንና መላው የጥቁር ሕዝቦች ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆነ። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ የዓለም የነፃነት ፋና ወጊ ሆና ብዙዎች ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ አርአያ ሆናለች። በዚያው ልክም የወራሪ አስተሳሰብ በተጠናወታቸው አምባገነን ኃይሎች ጥርስ የተነከሰባት ሆና ኖራለች።
ከዚያ በኋላ ቅኝ ገዢዎች እንደቀደመው ጊዜ የሚፈልጉትን አገር በመውረር መግዛትና የተፈጥሮ ሃብታቸውን መመዝበር እንደማይችሉ ሲረዱ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ይልቁንም ስልታቸውን በመቀየር በእጅ አዙር የመግዛት ስትራቴጂን ተከትለው በርካታ አገራትን በቁጥጥራቸው ስር አድርገዋል። ለዚህ እጅ አዙር ስልት የተጠቀሙት ዋነኛው መንገድ ደግሞ በአንድ በኩል ኢኮኖሚ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው።
ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ፊት ለፊት በገጠመቻቸው ጦርነቶች ጠላቶቿን በማንበርከክ ታሪክ ብትሰራም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በገጠማት ደባና ሴራ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች። ከነዚህ ፈተናዎችም ውስጥ ከጎረቤት አገራት እና እርስ በርስ በሚደረጉ ግጭቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚሰሩ ደባዎችና ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያግዛትን የውጭ ካፒታል እንዳታገኝ የሚደረጉ ሴራዎች ይጠቀሳሉ።
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ በ1960ዎቹ መጨረሻ ከሶማሊያ ጋር ወደጦርነት እንድትገባና ብዙ ኪሳራ እንዲደርስባት ተደርጋለች፤ ከዚያም በኋላ በውስጥ የሚነሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችን በማስታጠቅና በመርዳት ኢትዮጵያ እንድትበታተን ለማድረግ ከፍተኛ ደባ ተሰርቷል። ኢትዮጵያም ከ30 ዓመታት በላይ በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ ተደርጓል።
ከኤርትራ ጋርም ቢሆን ለሃያ አመታት የዘለቀው ሞት አልባ ጦርነት የዚሁ የፖለቲካ ደባ ውጤት ነው። እነዚህ አገራት ከማንኛውም ጎረቤት አገራት የበለጠ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያላቸው አገራት መሆናቸው ይታወቃል። በጋራ ለማደግም በጋራ መስራታቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አገራት በጋራ እንዲሰሩ ከመደገፍ ይልቅ ሁለቱን አገራት በመለያየት አይንና ናጫ ሆነው እንዲኖሩ በማድረግ ሁለንተናዊ እድገት እንዳይመጣ ትልቅ እንቅፋት ፈጥረዋል ።
ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ወቅቶችም ቢሆን እነዚህ የኢትዮጵያን ውድቀት የማይፈልጉ ኃይሎች ተኝተው አያውቁም ። በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ለዘላለም አንድ እንዳይሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ የቤት ስራዎች በስፋት ሲሰሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣ በብሔርና በማንነት እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ በማድረግና ለወደፊቱም መተማመን እንዳይኖር የሚያደርጉ ሴራዎችን በመሸረብ አንድነታቸውን የመሸርሸር ስራ በስፋት ሲሰራ የቆየበት ወቅት ነበር ።
ሌላው በኢትዮጵያ ላይ የተሰራው ደባ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የተሰራው ሴራ ነው። እንደሚታወቀው 60 ከመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውን በጭለማ ውስጥ ይኖራሉ። አባይን የሚያክል በዓለም ትልቅ ወንዝ ያላት አገር ባለቤት ሆናም ሕዝቦቿን ከድህነት ማላቀቅ ያልቻለች አገር ናት ።
በአንፃሩ ከታችኛው ተፋሰሱ አገራት መካከል ግብጽና ሱዳንን ስንመለከት ከአባይ ወንዝ ተጠቃሚዎች ናቸው ። ግብጽ መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይልን ማዳረስ የቻለች ሃገር ናት። ዜጎቿም ከኢትዮጵያውያን የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ሱዳንም ብትሆን በርካታ የልማት ስራዎችን በማልማት በወንዙ ተጠቃሚ ናት ።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ ከዚህ ወንዝ ለመጠቀም ስትነሳ ይህንን ለማኮላሸት ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም ። ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንዳትገነባ ገንዘብ በመከልከል የተጀመረው የክፋት ሴራ አድጎ መስራት አቁሙ እስከማለት ዘልቋል። ከዚህም አልፎ በርካታ ማስፈራሪያዎችም እስከማድረግ ተደርሷል።
እነሆ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች በዚህ ብቻ የሚያበቁ አይደሉም። ውስጣዊ ሰላምን ለማረጋገጥና ዴሞክራሲዊ ምርጫ ለማድረግ ስትነሳም ይህንን ለማደናቀፍ ሙከራዎች ሲደርጉ ቆይተዋል ። ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዳይካሄድ የውስጥና የውጭ ቅጥረኞችን በማሰማራት በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖር ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል ። ይህ ሁሉ ኢትዮጵያን ማንበርከክ አለመቻሉን ሲገነዘቡ ደግሞ በትግራይ ክልል ስም የአሜሪካ ቪዛ እስከ መከልከል ተደርሷል።
በመሆኑም ከግራና ከቀኝ የተቃጣብንን አደጋዎች ለመቀልበስ፤ ቀልብሰንም የጀመርነውን የሥልጣኔ ጉዞ ለማሳለጥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነን በጋራ ልንቆም ይገባል። እጅ ለእጅ በመያያዝ የተቃጣብንን የጥፋት ዱላ እንመክት!
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም