የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ጥላሁን ተሊላ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ አስጎሪ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አስጎሪ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በአካባቢው በቅርብ ርቀት ሁለተኛ ደረጃ ባለመኖሩ ወደ አቃቂ በመምጣት አቃቂ ኮምፕሬንሲፍ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የቀድሞው ዲላ መምህራንና ጤና ኮሌጅ የአሁን ዲላ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነፅሁፍ ዘርፍ አግኝተዋል። የማስተርስ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በኢትዮጵያ ስነፅሁፍና ፎክሎር ላይ ሰርተዋል። ጋምቤላ የመምህራን ማሰጠልጠኛ እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥረው በሂውማኒቲስ፣ ቋንቋዎች ጥናትና ኮምዩኒኬሽን ኮሌጅ የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ክፍል ውስጥ ለሶስት ዓመታት በኃላፊነት ሰርተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በትምህርት ክፍሉ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ከእንግዳችን ጋር በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ትምህርት እድገት እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– በሃገሪቱ ከቋንቋ ትምህርት ጋር ተያይዞ የክህሎት ችግሮች እንዳሉ በስፋት ይነሳል፤ በተለይም ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ምን አይነት ስራዎች እንደሚቀሩ ይግለፁልንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ዶክተር ጥላሁን፡– በአጠቃላይ የቋንቋ ትምህርት ላይ የተጠኑ ጥናቶችም እንደሚያሳዩት የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ ስራ አለመሰራቱን ነው። በተለይም ደግሞ ለዚህ ግብዓት አበርክተዋል ከሚባሉት ነገሮች በራስ ቋንቋ መማር መቻሉ መልካም ነገር ሆኖ ሳለ ለውጭ ቋንቋዎች መዳከም እንደ አብይ ምክንያት ይነሳል። በሌላ በኩል የውጭ ቋንቋዎችን ለማሳደግ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ስርዓት ያለመዘርጋቱ እንደሆነ ይጠቀሳል። እነዚህ ሁለት ነገሮች በጥቅሉ የሚያሳዩን ነገሮች በቋንቋ የትምህርት መስክ የሚገባውን ያህል አለመስራታችንና ውጤት አለማምጣታችንን ነው። በእርግጥ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በርካታ ሞዶሌችንም አምጥቶ ለመተግበር ጥረት ተደርጓል። በተለይም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች ምን ያህል ወደተግባር መጥተዋል? የሚለው ነገር በራሱ ጥያቄ የሚፈጥር ሆኖ ነው የሚታየኝ።
በፕሮጀክት ደረጃ በሚደረጉ ጥናቶች ስርዓተ ትምህርቱን ለማሻሻል ሙከራ ተደርጓል። ለምሳሌ እንግሊዘኛ ቋንቋን ለማሻሻል መምህራኑን አስቀድሞ ማሰልጠን በሚል በመምህራን ላይ ያተኮረ ስልጠና ሲሰጥ ነበር። ከዚህ በተለየ ደግሞ ከይዘቱ ባሻገር ተግባራዊ ስልጠና ነው የሚያስፈልገው በሚል ከመማር ማስተማሩ ጋር አያይዞ የተለያዩ ስራዎች ሲከናውኑና ስርአተ ትምህርት እስከመቀየር የተደረሰበት ሁኔታ አለ።
እኔ በግሌ ያጠናሁት ጥናት ባይኖርም በተጨባጭ ከማየው ነገር ተነስቼ ለመታዘብ እንደሞከርኩት መማሪያ መፅሃፎቹ የይዘት ዝምድናቸው ብዙ ተጠንቶባቸው የተዘጋጁ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። በተለይም ቋንቋውን እንደአንድ የትምህርት አይነት ብቻ ወስዶ ከማስተማር ባለፈ የጎንዮሽ ዝምድና በመፍጠር በየትምህርት አይነቱ ቋንቋውን ለማበልፀግ የተሄደበት ርቀት እምብዛም አጥጋቢ አይደለም። አሁንም ቢሆን ይህ ጉዳይ በጥናትም ያልታየ ክፍተት ነው። ይህንን አብነት አድርጎ መጥቀስ የሚቻለው በ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ላይ ሲሆን እነዚህ ክፍሎች ላይ የይዘት መጣረስ ሁኔታ ይታያል።
በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም ለእንግዝኛ ትምህርት አለማደግ እንደዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ከትምህርት ቤቶቹ ውጭ የማንጠቀምበት በመሆኑ ነው። አንድ ተማሪ በትምህርት ቤት ውስጥ የተማረውን ነገር በቤትና በመኖሪያ አካባቢው ሊጠቀምበትና ሊያዳብርበት የሚችልበትን ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። ለምሳሌ በድምፅና ተንቀሳቃሽ ምስል የታገዘ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ብንጠቀም ቋንቋውን የበለጠ ለማሳደግ ያግዘናል። ይሁንና ይህንን የሚደግፍ የትምህርት ስርዓትና መፅሃፍ ከግል ትምህርት ቤቶች ውጭ እምብዛም አይስተዋሉም።
አዲስ ዘመን፡– በቋንቋም ሆነ በሌሎች የትምህርት ዘርፎች በግልና በመንግስት ተቋማት ያለውን ልዩነት በምን መልኩ ነው ማጥበብ የሚቻለው?
ዶክተር ጥላሁን፡– በግልና በመንግስት የትምህርት ተቋማት ላይ ሰፊ ልዩነት አለ። ሁለቱም ጋር ‹‹የእኔ ይሻላል›› የሚሉትን ሃሳብ ማጣመር ቢችሉ ግን የተሻለ ውጤት ማምጣት እንችላለን ብዬ አምናለሁ። ማጣመር ሲባል ለምሳሌ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የአካባቢ ሳይንስ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚሰጡትን ያህል በአማርኛ የሚሰጡ አሉ። ሁለቱም ይዘቱ ተመሳሳይነት ያለው ሆነው ግን ደግሞ ሁለቱንም ቋንቋ እኩል ያሳድጉታል። ይህ ተሞክሮ በመንግስት ተቋምም ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ በግሌ አይታየኝም።
በሌላ በኩል በመንግስት ትምህርት ቤቶች ምን አልባት የአቅም ጉዳይ ሊፈትን ቢችልም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ብቻውን ለማስተማር ከመጣር ይልቅ አማራጭ አሰራሮችን ለመዘርጋት ቢያንስ በሃሳብ ደረጃ ሊነሳ ይገባል። ለምሳሌ በግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው spokene English እንደአንድ የትምህርት አይነት በመንግስት ትምህርት ቤቶች ሊሰጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻት ይገባል።
አሁን ላይ እንዳውም በዘርፉ በየዓመቱ በርካታ የሰው ሃይል እየተመረቁ ግን ደግሞ ስራአጥ ሆነው የተቀመጡ በመኖራቸው ይህንን አሰራር በመንግስት ትምህርት ቤቶች ማምጣት ከቻልን በተዘዋዋሪ መንገድ የስራ እድል እንፈጥራለን ማለት ነው። ስለዚህ ተማሪዎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከገቡ በኋላ spokene English ለብቻው ከመስጠት ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ብናስገባው የተሻለና ውጤታማ የሆነ ተማሪን ለማፍራት ያስችላል ብዬ አምናለሁ። በአጠቃላይ በመንግስት ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች ላይ የሚታዩ መልካም ተሞክሮችን ቀምሮ ስራ ላይ ማዋል ይገባል የሚል እይታ ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ባለፉት 27 ዓመታት ሁሉም ዜጋ በቋንቋው የመማር እድል መሰጠቱ መልካም ሆኖ ሳለ በፌደራል ተቋማት ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ይነሳል። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር ጥላሁን፡– እንደተባለው የተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተካተው ስራ ላይ ማዋል መቻሉ ያመጣው ጥሩ ነገር አለ። እኔ እንደአንድ የዘርፉ ምሁር የማምነው ቋንቋውን የሚጠቀም አካል እስካለ ድረስ ለዚህ አካል ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ማቅረብ ይገባል የሚል ነው። በሌላ በኩል በአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ መማሩ ከሌላው አካባቢ ተማሪ ጋር ለመወዳደር አዳጋች ሊሆንበት እንደሚችል እሙን ነው። በመሆኑ እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ሳንሸሻቸው ምንያታዊ የሆነ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል።
እነዚህን ፅንፍ የያዙ አመለካከቶችን በምን መልኩ ልናቀራረባቸው እንደምንችል ማሰብና መፍትሄ ማግኘት ያሻናል። ይሁንና ልዩነቶቻን የሚያሰፉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ አይገባንም። ለምሳሌ ‹‹አማርኛ ቋንቋ ሌሎቹን ቋንቋዎች ተጭኗል›› ተብሎ ይነሳል፤ እንዴትና ለምን ተጫነ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመርምራቸው ካልንና ዋና ካደረግናቸው ለወደፊት ባለንበት ፍጥነት ለመራመድ ይገቱናል።
ይልቁንም የአማርኛን ያህል ያላደጉ ቋንቋዎችን ማሳደግ እና ሊያድጉ የሚችሉበትን መንገድ መቀየሱ ወሳኝ ነው ብዬ አምናሁ። ያለፈውን ነገር ብቻ እያነሳን የምንሄድ ከሆነ ወደኋላ ከመመለስ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም ባይ ነኝ።
ይህንን ስንል እርግጥ ነው የቋንቋዎቹ አመጣጥና ታሪካዊ ሂደት መጠናት የለበትም ማለቴ አይደለም። ግን እይታችን ወይም ካሜራችን ከየት ቢጀምር ጥሩ ነው? የሚለውን ነገር ትኩረት ቢያገኝ ጥሩ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ በቋንቋዎች ላይ የሚነሱ ክርክሮችን ወደ ማስታረቁ ነው መምጣት መቻል ያለብን። ለምሳሌ እኔ እንደአንድ በመስኩ እንዳለ ሰው ዛሬ ላይ ቆመን የማደግ እድሉን ያገኛም ሆነ ያላገኘው ቋንቋ ወደኋላ ተመልሰን እንዴት መጣ ? እንዴት ሊያድግ ቻለ ብለን የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርገን ትኩረት ባናደርገው እመርጣለሁ። ትኩረት ልናደርግበት የሚገባና መነሻ ሊሆነን የሚገባው ዛሬ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ነው። እርግጥ ነው ያሉንን ቋንቋዎች በሙሉ በአንድ ጊዜ ማሳደግ እንችላለን ወይ የሚለው ነገር መሰረታዊ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ይህንን ማድረግ ብንችል እንኳ እርስበርስ የመግባባታችን ጉዳይ ምን ይሆናል? የሚለውም ነገር ሊታሰብበት ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ቋንቋ ሃብት ነው፤ ልናሳድገው ይገባል›› የሚል አካል አለ። ለምሳሌ ቻይና በአሁኑ ወቅት እንግሊዘኛ ቋንቋን እያስፋፋች ነው። ለምንድን ነው ወደዚህ የመጣው የሚለውን መፈተሽና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ራሳችንን መቃኘት ይገባናል። በመሰረታዊ ልዩነቶቻችን ላይ ከተነጋገርን መፍትሄ ማምጣት እንችላለን። የግድ አንድ ፅንፍ መያዝ አለብን ብዬ አላምንም ገዢ ሃሳቡን መርጠን ልንሄድበት እንችላለን። እኔ በሁለቱም አስተሳሰቦች ፈላጊ እስካላቸው ድረስ ገበያው ላይ ይቅረቡ፤ ገዢው ይግዛ። ገዢው ለመግዛት ደግሞ እነዚህን ነገሮች ለገዢው በሚስማማ መልኩ በመስኩ ያሉና የሚመለከታቸው ተቋማት ሊነጋገሩበት፤ ሊሰሩበት ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– በሌላ በኩል ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ በራሱ አንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ከሌላው ጋር ከማቀራረብ ይልቅ የሚለያይበትን ሁኔታ ፈጥሯል ብለው የሚከራከሩ አሉ። እርሶ ይህንን ሃሳብ ይጋሩታል?
ዶክተር ጥላሁን፡– በመሰረቱ እኔ ቋንቋ በዜጎች መካከል ልዩነት ይፈጥራል ብዬ አላምንም። ነገር ግን በተጨባች የልዩነት ምክንያት አድርገው የተጠቀሙባት መኖራቸው አያጠያይቅም። ከዚህ አንፃር እኔ ከቋንቋዎች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች በዚህ አገር ለቋንቋዎቹ ትኩረት ካለመስጠት የሚመነጭ ይመስለኛል። ምንም እንኳን ቋንቋዎች በራሳቸው በሰዎች መካከል ልዩነት ወይም አለመግባባት ባይፈጥሩም አንድ አንድ ግለሰቦች ለልዩነትና ለፖለቲካ ፍጆታ ሲያውሉት ይስተዋላል።
በተለይም የአገራችን ፖለቲከኞች ቋንቋን እንደአንድ መሳሪያ ተጠቅመውበታል። እርግጥ ነው እነዚህ ፖለቲከኞች ከቋንቋ ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። ይህም ሆኖ የሚባውን ያህል ልዩነት ፈጥሯል የተባለው ቋንቋ በራሱ በአግባቡ ይዘነዋል ወይም የሚገባውን ያህል አሳድገነዋል ብዬ አላምንም። ቋንቋ በራሱ ችግር ፈጥሮም ከሆነ ፤ ጠቅሞም ከሆነ የሚገባውን ያህል ትኩረት ተሰጥቶታል ብዬ አላምንም። ይህንን ስል ደግሞ ለምሳሌ በፌደራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ ቋንቋን የሚመለከት የሚያጠና የተለየ ክፍል የለም። ምንአልባት በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ነው ተካቶ ልናገኘው የምንችለው። በእኔ እምነት አይደለም ራሱን የቻለ ክፍል ብቻ ሳይሆን በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ብናደራጀው ጥቅሙ የጎላ ነው።
‹‹ቋንቋ አገር አፈረሰ ወይም ገነባ›› የሚለው ክርክር ዋና መሰረታዊ ጉዳያችን ከሆነ ለምንድነው በዚያ ልክ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትኩረት ያልሰጠነው? በጀት መድበን ያላጠናነው? ያሉትንስ ችግሮች ለምን መለየት ተሳነን? ስሙን የምንጠራውን ያህል ለእድገቱ አልሰራንለትም። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ይህ ዘርፍ ከሌላ ዘርፍ ጋር ደባል ሆኖ እንዲሰራ ነው የተደረገው። ይህም ሳይንሱ በሚለው መሰረት ዘርፉን ለማሳደግ እንዳንችል አድርጎናል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በመሆኑም ዘርፉ አሴት ሊፈጥርልን በሚችል መልኩ መደገፍ ይገባናል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንዶች ግን የበዛ ትኩረት መሰጠቱ ነው ሁሉም የራሱን ቋንቋ ብቻ ከፍ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት መቃቃሮች የመጡት ብለው የሚከራከሩ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ ?
ዶክተር ጥላሁን፡– እኔ ትኩረት አልተሰጠውም ስል መፍትሄ ለማምጣትም ሆነ ለአገራዊ ጥቅም ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ ማለቴ እንደሆነ እንድትገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ። እንደተባለው ከህገመንግስቱ ጀምሮ ቋንቋዎችን ማበልፀግ የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል። በክልል ደረጃ ሁሉም የየራሱን ቋንቋ ማሳዳግም ሆነ ማስተማር እንዲችሉ ተደርጓል። የስራ ቋንቋ አድርገው እየተጠቀሙም ነው ያሉት። እኔ እያልኩት ያለው ይህንን አይደለም። ይሄ በራሱ ያለው በክልሎችና በብሄረሰቦች ደረጃ ነው። ይህንን ከታች በዚህ አይነት መልኩ እየበቀለ የመጣውን ነገር ፌደራል ላይ ስትመጪ አታይውም።
በመሰረቱ የቋንቋዎቻችን እድገት በክልሎች ደረጃ ከቀረ እኔና አንቺ ተመሳሳይ ነገር እያወራን ላንግባባ እንችላን። ስለዚህ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል አሰራር መዘርጋት አለብን። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ሞዴል ተሞክሮችን ማምጣት መቻል አለብን። ለምሳሌ አንዱ ሞዴል የጋራ መግባባት የሚፈጥርና ልንጋራ የምንችላቸውን ጉዳዮች ማምጣት መቻል ነው። ከዚህ አንፃር ይህንን ነገር ጉዳዬ ብሎ የሚሰራ አካል አለ ብዬ አላምንም። እኔ እንደመምህር ክፍል ውስጥ አስተምራለሁ። እኔ የማስተምረው በተሰጠኝ ይዘትና ስርዓተ ትምህርቱ መሰረት ነው፤ ሌላው በተመሳሳይ መልኩ በተናጠል ይሰራል። ነገር ግን ሁሉንም በሚያግባባ መልኩ የሚሰራ መንግስታዊ ተቋምና አደረጃጀት የለም። አሉ የሚባሉትም ቢሆኑ ጉልህ የሆነ ስራ ሰርተዋል ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– ቋንቋ ለኢኮኖሚ እድገት ምንአይነት ፋይዳ አለው? በዚህ ደረጃ የተጠቀሙ አገራትን ለአብነት መጥቀስ እንችላለን?
ዶክተር ጥላሁን፡– በተደጋጋሚ እንደሚባለው ቋንቋ መግባቢያ ነው። ከመግባቢያነቱ ባለፈ ግን በርካታ አገሮች ለአገር እድገት ወሳኝ መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል። ቅድም ካልኩት አንፃር ቋንቋ ሃብት ነው ስንልም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ጭምር ነው። ምንም እንኳ በገበያ ላይ በቀጥታ የምንሸጠው እና ገቢ የምናገኝበት ነገር ባይሆንም ቋንቋዎቻችንን ባስፋፋን ቁጥር ከአገራት ጋር ያለንን የኢኮኖሚ ትስስር የበለጠ ለማሳደግ እድል ይፈጥርልናል።
ለምሳሌ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመላው አለም የመስፋቱን ያህል የእነሱን ምርቶች በቀላሉ ለማወቅም ሆነ ለመግዛት እድል ፈጥሯል። የዚያኑ ያህል እኛም ቋንቋዎቻችንን መሸጥ መቻል አለብን። ይህንንም ለምሳሌ በቴክሎጂና በፈጠራ ስራዎች አማካኝነት መሸጥ እንችላለን። ለዚህም የሰው ሃይል ማፍራት፣ መሰረተ ልማት መዘርጋት ይፈልጋል። ወደዚያ መሄዳችንም የግድ ነው። ሉአላዊነት እየተገፋን ነው። ለዚህ ድግሞ የቋንቋ ፖሊሲ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በተመሳሳይ ‹‹ያሉንን አገር በቀል እሴቶች ለአገራዊ አንድነት ልንጠቀምበት ይገባል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ካለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ አሁን ያለው ትውልድ ሊቀበለው ስለማይችል አይጠቅምም›› የሚሉ ሁለት ፅንፍ የያዙ ክርክሮች አሉ። በእርሶ እምነት እነዚህ ሃሳቦች እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?
ዶክተር ጥላሁን፡– እኔ አገር በቀል እሴቶቻችን መጠቀማችን ጠቃሚ ነው ብዬ ነው የማስበው። እነዚህ ነገሮች በየአውዳቸውና በየቦታቸው መተግበራቸው ጥሩ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል። ለምሳሌ በተለያዩ ብሄረሰቦች ያሉ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ብዙ ተፅፈዋል። ከማስተርስ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ተቋማትና ግለሰቦች ደረጃ ጥናት ተደርጎባቸዋል። የመጠንና የጥልቀት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በየቦታው አሉ። ለምሳሌ የጆካ የተባለውን የጉራጌን የግጭት አፈታት ባህላዊ ዘዴን መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን ትኩረት ያላደረግንበትና ያላጠናነው ብዬ የማስበው የቱ ጋር የባህል ልዩነት እንዳለ፣ ምን የጋራ ጉዳዮች አሉ? የሚለውን ነገር ላይ ነው።
በተለይም በባህል ዙሪያ ንፅፅራዊ ጥናት ትኩረት አግኝቷል ብዬ አላምንም። በመስኩ እንዳለ አንድ ሰው ይህንን ጉዳይ ትኩረት ያለመስጠት የጋራ እሴቶችን ማበልፀግ አንችልም። ከመናገር ባለፈ የተቆጠረ ነገር ልናስቀምጥ አንችልም። ለምሳሌ ግጭት የሚፈጠርባቸው አካባቢዎች መቼና ምን ሲሆን ነው ግጭቶች የሚነሱት? የሚለውን ነገር የሚመልስ ጥናት እምብዛም ነው። ስለዚህ የልዩነት መፍጠሪያ ሳይሆን የጋራ ጉዳዮቻችን ለይቶ ጥቅም ላይ ማዋል የምንችልበት ሁኔታ መፈጠር መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ። በዚህ መልኩ በግልፅ መነጋገር ካልቻልን አሁንም ልዩነቱ መፈጠሩ አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ጥናት ማጥናቱም ሆነ ችግሮችን መለየት መቻሉ በራሱ ልዩነቶችን ያስቀራል?
ዶክተር ጥላሁን፡– ይህንን ስልሽ ይሄ ብቻ ነው አማራጩ እያልኩሽ አይደለም። ዋናው ቁምነገሩ ግን መፍትሄ ከውስጥ ይመጣል የሚለው ነገር በደንብ አምነንበታል ወይ? የሚለው ነው። ይህንንስ አምኖ ወደተግባር የሄደ አካል አለ ወይ? ለእኔ ልዩነቶችን ለማስቀረት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያቀረበ አካል እስከአሁን አላየሁም። ለምሳሌ በየተቋማቱ ጥናት እንዲያጠኑ የተቋቋሙ በርካታ የሥራ ከፍሎች አሉ፤ ግን ምን እየሰሩ እንደሆነ በውል አይታወቅም። በየአመቱ በርካታ ተማሪ ጥናት አጥንቶ እየተመረቀ ነው ። እነዚህ ጥናቶች ምንድን ናቸው? ምንስ ተሰራ? ምን ውጤት ተገኘ? ከዚህ የተገኘው ግብዓት ደግሞ ወደተግባር ለመመንዘር የሚያስችል አደረጃጀትና እዛ ላይ ትኩረት ያደረገ አካል አላየሁም። ለእኔ ይሄ አንድ ክፍተት ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ በውጭ ሃይሎች እየተደረገ ላለው ጫና ዋነኛ ምክንያት የውስጥ አለመግባባት ማየሉ እንደሆነ አንዳንድ ምሁራን ያምናሉ። እርሶ ይህ ሃሳብ ምን ያህል አሳማኝ ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ጥላሁን፡– እንግዲህ በዚህ ሃሳብ ላይ እንደባለሙያ ሳይሆን እንደአንድ ዜጋ ነው አስተያየት ልሰጥ የምችለው። እንደተባለው ሁላችንም ህብረት ቢኖረን ወይም አንድነት ቢኖረን ኖሮ የውጭ ሃይሎች ሊያጠቁን እንደማይችሉ እኔም አምናለሁ። ትክክልም ነው። በታሪክም ውስጣዊ ጥንካሬያችን ሲሳሳ ነው የውጭ ሃይል ክንዱን የሚያበረታብን። አሁን ላይ ውስጣዊ መከፋፋል ሊፈጠር አይገባም ነበር። ትልቅ ወዳጆቻችን ናቸው የምንላቸውና ረጅም ጊዜ እሴት የገነባንባቸው ሀገራት በዚህ አጭር ጊዜ በዚህ ደረጃ ወደጠላትነት መሸጋገራችን ያሳዝናል።
ለውጭ ጫና ያጋለጠን ደግሞ አብሮነታችን መሳሳት ነው። የሃሳብ ልዩነት መፈጠሩ እንዳለ ሆኖ ጉልህ በሆነ መልኩ መቃቃር ውስጥ መግባት አልነበረብንም ባይ ነኝ። ከመቃቃር አልፎ በክፉ እስከመፈላለግ የሚያደርስ ሁኔታ ውስጥ መግባታችን ይህንን ክፍተት ፈጥሯል። ስለዚህ እኔ እንደአንድ ግለሰብ ልናገር የምችለው ይህንን የውስጥ ጥንካሬያችንን መመለስና ማጠናከር ይገባናል የሚል ነው።
ምንአልባት ደግሞ መጠበቅ ያለብን ከዚህም በላይ ገፍተው ሊመጡ ይችላሉ። አሁንም ወደ መስማማትና ህብረት መምጣት ካልቻልን ጫናው ገፍቶ ሊመጣ ይችላል። በመሆኑም ያለው ብቸኛ መፍትሄ አሁንም ቢሆን አብሮነታችንን ወደቦታው ለመመለስ የሚያስችል መድረክ መፍጠር ነው። ያ ካልሆነ ግን ከጠላቶቻችን ጎን የሚሰለፉ ባንዳዎች መበራከታቸው አይቀርም። ይህ ሲሆን ደግሞ ችግሩ የከፋ ሊሆን ስለሚችል የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ሊያስቡበትና ወደ ስራ ሊገቡበት ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ለልዩነቶች መስፋት በአገሪቱ ያሉ ልሂቃንና ፖለቲከኞች ዋነኛ ድርሻ ይነሳል። በዚህ ረገድ ከእነዚህ አካላት ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ዶክተር ጥላሁን፡– እኔ በመጀመሪያ ደረጃ ለዚህች አገር ህዝብ ልዩነትና መቃቃር መበራከት ምሁራን ወይም ሊሂቃን ሚና ነበራቸው ብዬ አላምንም። ምሁራን ግጭት ያባብሳሉ የሚል እሳቤም የለኝም። እኔን እንደ አንድ ምሁር ከወሰድሽኝ ባለኝ የትምህርት ደረጃ አንፃር ነው በዚህች አገር ላይ ሚናዬን ልጫወት የምችለው። በሌላ በኩል እኔ የማህበረሰቡ፣ የትምህርቱም፣ የሳይንሱም ውጤት ነኝ። እኔ ጋር ያለው ሃሳብ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ይቅርታ ላቋርጦትና አሁን እርሶ እንደሚሉት ማንኛውም ምሁር ወይም ሊሂቅ የማህብረሰቡ ወይም የሳይንሱ ውጤት እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም በተማሩት ልክና ሁኔታ በአገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳይ ላይ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ጥላሁን፡– ይሄውልሽ በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲከኛ የሆኑ ምሁርን ማለቴ እንዳልሆነ እንድትገነዘቢልኝ እወዳለሁ። የፖለቲካ አቋም የያዙ ምሁራን ሙያቸው ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩት ለእኔ ይለያሉ። በያዙት አቋም መሰረት ያላቸውን እውቀት ለፖለቲካ ስራቸው እየተጠቀሙበት ስለሆነ በጥቅሉ ካሉት የተለዩ ናቸው ብዬ ነው የማምነው። ለእኔ አንድ ትክክለኛ ምሁር ሃሳቦችን ወደ መድረክ ማምጣት እንጂ አቋም ይዞ ይህና ያ መሆን አለበት ማለት አይገባውም። ገዢ የሆኑ ሃሳቦችን በማቅረብ የሚመስለውን ነገር መግለፅ ይጠበቅበታል ። አንድ ሊሂቅ ምክረ ሃሳብ ነው እንጂ ሊሰጥ የሚችለው አስገዳጅ የሆነ ሃሳብ ሊሰጥ አይችልም።
ለምሳሌ የሃይማኖት ውግንና የያዙ ምሁራን መጠሪያው ምሁር ብቻ ሊሆን አይችልም የሃይማኖት ሰውም ጭምር እንጂ! ። የፖለቲካ አቋም የያዘውም ምሁር በተመሳሳይ መንገድ ፖለቲከኛ ነው ልንለው የምንችለው። በአጠቃላይ እነዚህ ሰዎች ሚናቸውን ያለዩ ምሁራን ናቸው ብንል የሚያስማማን ይመስለኛል። ከዚህ አንፃር በጥቅሉ ምሁራን ለልዩነቶቻችን መስፋትም ሆነ ለግጭቶች መበራከት አስተዋፅኦ ነበራቸው ካልን እስካሁን የገነባናቸውን መልካም እሴቶችና የምናከብራቸውን ምሁራንን ስሜት ጭምር እንጎዳለን።
እያንዳንዳችን በምሁራን ምድብ ውስጥ ያለን ሚናችንን መለየት ብንችል የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። ሃሳብ መስጠት ያለብን ያንን ሚና በለየ መልኩ መሆን ነው ያለበት። ወደ ወቅታዊው የፖለቲካ ጉዳይ ስንመጣ እኔ እያየሁ ያለሁት ነገር ብዙም የሚያጓጓ ሆኖ አላገኘሁትም። የአየር ጊዜ ተሰጥቷቸው እየተከራከሩ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግሌ የተለየ ሃሳብ ይዘው ቀርበዋል ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡– ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር ጥላሁን፡– ምርጫው ተካሂዶ ነጭና ጥቁር የሚፈጥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ብዬ አላስብም። ይህም ማለት የጎላ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አላምንም። ይህንን ስልም ርዕዮተ-ዓለምን መሰረት ያደረገ አዲስ ፖሊሲ ይዞ የቀረበ እስካሁን አላየሁም። እርግጥ ነው በእኔ ሃሳብ ላትስማሚ ትችያለሽ። ግን እኔ አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡– ግን ከመቼውም ጊዜ በተለየ በርካታ ፓርቲዎች የተሳተፉበት እንዲሁም ሰፊ ዝግጅት አድርገው የቀረቡ ፓርቲዎች ባሉበት በደምሳሳው ይህን ማለትዎ አሳማኝ ነው ብለው ያምናሉ? ደግሞስ አለም ላይ ካለው የተለየ ርዕዮተ–ዓለም ከወዴት ሊያመጡ ይችላሉ? ከሁሉስ በላይ ይህችን አገር ማዳን አይቀድምም?
ዶክተር ጥላሁን፡– አገር ማዳን የሚለው ነገር በተደጋጋሚ ሲነሳ አዳምጣለሁ። በነገራችን ላይ አገሪቷ ምንም አትሆንም ባይ ነኝ። ምንም አትሆንም ማለት የሃሳብ ፍጭቶች ግጭቶች መጠንከራቸው ይህችን አገር ከነጭራሹ ያጠፋታል ብዬ አላምንም። አሁን ላይ እኮ በእኛ አገር ግጭቶች የተለመዱ የዕለት ተዕለት ክስተታችን ሆኗል። ብሔር ተኮር ግጭቶች በፊትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም በነበረው ግጭት የተጋጩት የህብረተሰብ ክፍሎች መልሰው ይታረቃሉ፤ አሁን እየጎላ የመጣው ነገር ምንአልባት የፖለቲካ ተቋማትና በዚህ መልኩ የተደራጁ ሆነው መምጣታቸው ያሳስባል።
ይህንን ሃሳብ ለማንሸራሸር ነፃ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ አይነት መልኩ ለፉክክር መቅረባቸው፣ መድረኩ መፈጠሩ ጥሩ ነው። ግን አሁን ያሉትን ስናይ ከምንፈራው ችግርና ስጋት ይታደጉናል ብዬ አላምንባቸውም። አብዛኞቹ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም ነው ይዘው የቀረቡት። ይህ የእኔ የግሌ እይታ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ግን ለመለየት ብቻ ሲባል የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ጭምር መለየት አለባቸው ብለው ያምናሉ? ይሄስ ሄዶ የሚጎዳው ህዝቡንና ሀገሪቱን አይሆንም?
ዶክተር ጥላሁን፡– ምክንያት ስጋቴ ተመሳሳይ ስለሆኑብኝ ነው። ተመሳሳይ መሆናቸው ችግሮቻችንን ሊቀርፉልን አይችሉም የሚል ጥርጣሬም ስላለኝ ነው፤ ይህንን በድፍረት የምናገረው ነው። ችግሮቻችንን ቢቀርፉልን እኔም ሆንኩኝ ሌላው ሰው የሚጠላው አይመስለኝም። የመራጩን ሀሳብ በጉልህ መልኩ ሊያስተናግዱ የሚችሉ ሆነው አላገኘኋቸውም ። አብዛኞቹም ሊያመጡ ይችላሉ ብዬ የማምነው ጥገናዊ ለውጥ ነው። ይህም አስታራቂ ሃሳብ ያመጣል ብዬ ለማናገር አልደፍርም። ከዚህም ባሻገር በመድረክ ላይ ከሚያቀርቧቸው ጥሩ ጥሩ ሃሳቦች ባሻገር የተጨበጠ ለውጥ አያመጡም የሚል ስጋት አለኝ። እኔ በግሌ የምጠብቀውን ያህል አልሆነልኝም።
አዲስ ዘመን፡– በአጠቃላይ ኢትዮጵያን እንደ ሶሪያና የመን ለመበታተን ሲባል በውጭ አካላት የሚደረግብንን ጫና ከመመከት አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ጥላሁን፡– እኔ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ እንደሶሪያና ሌሎች ሀገራት ልትበታተን ትችላለች የሚለውን ሃሳብ አልወደውም። ማሳያ ምሳሌዎቹ ራሳቸው ጥሩ አይደሉም ባይ ነኝ። ለምንድን ነው አገራችንን ከፈረሱት አገራት ጋር የምናስተያየው እርግጥ ነው አሁን ላይ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎብናል፤ ግን ደግሞ እስካሁን ብዙ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሀገራት አሉ። እሺ እነሱን ምሳሌ ማድረግ እንችላለን። ሊቢያን ምሳሌ ስናደርግ ስነልቦናችን ሊጠነክር አይችልም። ይልቁንም እንደእነሱ እንዳንሆን ብለን ስንወራጭ የበለጠ ጉዳት ላይ እንወድቃለን የሚል እምነት ነው ያለኝ።
የተወራጨ ሰው የሌለ ጉልበት ያወጣል፤ የማይሆን ቦታ ሊመታ ይችላል፤ ራሱንም ሊጎዳ ይችላል። ስለዚህ እንደእገሌ እንዳንሆን የሚለው ነገር ሃይል አሰባስበን፤ ተጠናክረን የሚል ትርጉም ነው ለእኔ የሚሰጠኝ። ስለዚህ ማዕቀብ የተጣለባቸው ብዙ ሀገራት አሉ። እኔ ይህ አባባል የሚፈጥረው ስሜት ነው የማይመቸኝ። የወደቀን ሀገር ምሳሌ ስናደርግ መልካም የሆነ አስተሳሰብ ይፈጥራል ብዬ አላምንም። ምሳሌ የምናደርጋቸው ነገሮች አዎንታዊ መሆን ቢችሉ የተሻለ ነው።
ከዚያ ይልቅም ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነገር ግን ተቋቁመው ጉዳቱን መቀነስ የቻሉ ሀገራትን ምሳሌ ብናደርግ የተሻለ ነው ባይ ነኝ። ያም ሆኖ ግን አስቀድመን እንዳልነው ለዚህ ሁሉ የዳረገን የውስጣዊ ግንኙነታችን መላላት ነው። በነገራችን ላይ በደርግ ዘመንም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የኢትዮ-ሱማሌ ጦርነት የሚታወስ ነው። በዚያ ወቅት ተመሳሳይ የሆኑ የውስጥና የውጭ ጫናዎች ነበሩ። ግን ያንን ችግር እንዴት አለፍነው የሚለው ነገር እንደ አንድ ምሳሌ ልንወስደው ብንችል የተሻለ ነው።
ምንአልባት ማዕቀቡ ባለበት ካልቆመና ከቀጠለ ውስጣዊ ጥንካሬያችንን የበለጠ ማጠናከር ነው የሚገባን። ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በአንድ መድረክ ተሰባስበው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ መግባባት ቢፈጠር የተሻለ ነው። ከሁሉ በፊት ግን የውይይት መድረክ መፍጠሩ በራሱ ትልቅ እምርታ ነው። ከዚህም ባሻገር ለለውጥ ሁላችንም ዝግጁ መሆን አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ጥላሁን፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013