የአንድ አገር ሕዝብ የአገሩ ሁለንተናዊ ጉዳይ ባለቤት ነው። ስለአገሩ ከሱና ከሱ በላይ ሊያስብ የሚችል አይኖርም። ለማሰብ መሞከርም ከሞራል አንጻር ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችል ከፍያለ ጉዳይ /አጀንዳ/ ነው። በተለይም እንደኛ ላሉ ጥንታዊና የብዙ ሺ ዘመን ታሪክ ላላቸው ሕዝቦች ጉዳዩ ከዚህም በላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል።
ለእነዚህ ሕዝቦች አገር ማለት የዘመናት የትውልዶች ውጣውረድ፤ የብዙ ተጋድሎና መስዋእትናት ፍሬ እንዲሁም የብዙ ትውልዶች አሻራ ነው፡፡ የብዙ ትውልዶች የማንነት ቅብብሎሽ ድምር ምስል፣ ከዚህም በላይ የመጪው ትውልድ መንፈሳዊና ቁሳዊ እሳቤ መሠረትና የማንነት ግንባታ መዋቅር ጭምር ነው።
በዚህ ተጨባጭ እውነታ ተገዝተው ነው ቀደምት አባቶቻችን፣ እናቶቻችንና አያት ቅድመ አያቶቻችን ስለአገር በየዘመኑ ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱት፤ እየከፈሉም ያለፉት፡፡ እኛም በትውልዶች የመስዋእትነት ቅብብሎች እዚህ የደረስነው፣ ባለሀገርም የሆነውም በዚሁ ተጨባጭ እውነታ ተገዝተን ነው። ለዚህም ነው አሁን ያለችን አገር የብዙ ትውልዶች የተጋድሎ ታሪክ ድምር ውጤት ናት የሚባለው፤ ታሪክም በዚሁ መልኩ የሚዘክራት።
በቀደሙት ዘመናት የነበሩ አባቶቻችንና አያቶቻችን በተቃርኖ ውስጥ በሆኑባቸው የትኛዎቹም ወቅቶች የአገር ጉዳይ ሲመጣ አንድ አድርጎ እያስተሳሰራቸው የኖረው ይህ በትውልዶች መካከል በየዘመኑ ስለአገር የተከፈሉ ትላልቅ መስዋእትነቶች በተሰራንባቸው ውስጣዊ ማንነቶች ላይ ያላቸው የገዘፈ ስፍራ ነው።
ስለ አገር የሚፈጠር መነሳሳት፤ በፉከራና ቀረርቶ የሚገለጸው የታመቀ የአትንኩኝ ባይነት መንፈስና ለመስዋእትነት የመዘጋጀት ቁርጠኝነት ከተራ ስሜትና መንፈስ የሚቃዳ ሳይሆን፣ በታላቅ መስዋእትነት ከተፈጠረ ማንነት የሚመነጭ ከገዘፈ ስብእና የሚፈልቅ ነው።
አባቶቻችን አገራዊ ክብርን ላለማስደፈር በተዋደቁባቸው የተጋድሎ ውሎዎች የታየውም፣ ዓለምንም ያስደመመው እውነታም ይሄው ነው። ኢትዮጵያውያን የትኛውም ዓይነት ልዩነት ቢኖራቸው፣ ልዩነታቸውን ትተው ስለአገራቸው ክብርና ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ በአገርም በታሪክም ፊት በክብር አልፈዋል።
ያ በመስዋእትነት የተገነባ ክብር በየዘመኑ ለአገር በክብር ላይ ክብር በመሆን ዜጎችን እኛን ጨምሮ የዚህ ክብር ባለቤት አድርጎን በዚህ ክብር ቀና ብለን እንድሄድ አስችሎናል። የሚቀጥለው ትውልድ ደግሞ ከዚህ ከፍ ባለ ክብርና ሞገስ መሄድ እንዲችል ለማድረግ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል።
ይህ የታሪክ ምዕራፍ ያለንን በማጽናት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የጎደለንን በመሙላት የቀደሙት አባቶቻችንን የነፃነት ተጋድሎና ከዚህ የተገኘውን ክብር ሙሉ የሚያደርግ፤ መጪውን ትውልድ የሚያሳርፍ የመልማት እና የመበልጸግ መሻትን የሚያጸና አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው ፡፡
ይህም እንደ አገር ሙሉ የሚያደርገን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ቀና ብለን ያለመሸማቀቅ መሄድ የሚያስችለን፤ ከአድርጉ አታድርጉ ባለጊዜዎች ነፃ የሚያወጣንና የራሳችንን ዕጣ ፈንታ በራሳችን የምንወስንበት ፍጥረታዊ ማንነታችንን በትክክለኛ መሠረት ላይ የምናዋቅርበት ታሪካዊ ወቅት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
ታሪካዊ ምዕራፉ እንዲሁ በቀላሉ የሚጻፍና የሚገለጥ አይደለም። ለነፃነት ከከፈልነው መስዋእትነት ባልተናነሰ ከፍያለ መስዋእትነትን ይጠይቃል፤ ለዚህም የሚሆን ዝግጁነትን ይፈልጋል። የነፃነት ትግሉ እልህ አስጨራሽ እንደነበረ ሁሉ ይህም ከዚያ የባሰ እልህ አስጨራሽ ነው። ከራስ መሸሽን ሳይሆን ከራስ ጋር መታረቅን ይፈልጋል። የዛሬን ብቻ ሳይሆን ትናንት ከፍያለ መስዋእትነት ከፍሎ ያለፈውን ትውልድ፣ ነገ የሚመጣውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ማሰብን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ የባላደራ ትውልድ ጥልቁ ኃላፊነት ነው።
የቀደሙት አባቶቻችን ልጆቻቸው፣ የልጅ ልጆቻቸው፤ ትውልዳቸው በባርነት ከሚኖር ብለው ስለሚመጣው ትውልድ የከፈሉት መስዋእትት እኛን የነፃነት ባለቤቶች አድርጎናል። የተጋድሎ ታሪካቸውም በባርነት ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች የተስፋ ሰንደቅ፤ የትግል ስንቅ ሆኗል።
ዛሬ ለመበልጸግ እና ለመልማት የጀመርነውና በተግዳሮት የተሞላው መነሳሳታችን የነገ ሙሉ አገራዊ ክብር መጎናጸፊያ የመጨረሻው የታሪካችን ምዕራፍ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው። ይህንን ታሪካዊ ምዕራፍ በድል ተወጥተን ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር በመገንባት የትውልድ ባላደራነታችንን በስኬት ለመወጣት እንደቀደመው ዘመን አንድነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል።
ብዙ የተሻለ ነገር ነበራቸው የተባሉ ጠላቶቻችንን ቅዥት በሚመስልና ለወሬ ነጋሪ በማይመች መልኩ ድል ያደረግንበት የትናንቱ ታሪካችን ትልቁ ምስጢር በአንድነት መቆማችን ነው። ዛሬም በአገራችን በተስፋ መንገዳችን ላይ የቆመው ተግዳሮት የቱንም ያህል ብርቱ ቢመስል አንድነታችን ውስጥ ያለውን ኃይል ሊገዳደር አይችልም !አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013