ወጣትነት ለውጥ ናፋቂነት ነው፡፡ የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው ባላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው።
በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላለፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። አገርን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ነው።
አገር በአንድና በሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣ የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና የሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው። ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው። በሌላ በኩል ወጣቱ ሥራ ፈጣሪ በመሆን ለራሱና ለአገሩ የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንዳለበት ይታመናል፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ስለ ሥራ ፈጣሪነት የተወሰኑ ነገሮችን እንመልከት፡፡ ሥራ ፈጣሪዎች በውስጣቸው ከፍተኛ የሚንቀለቀል የመሻት ኃይል አላቸው፡፡ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪዎች ስለሚሠሩት ሥራ ውስጣቸው የሚንቀለቀል ‹‹እሳት›› ያላቸው ናቸው። ስለሚያመርቱት ምርት ወይም ስለሚሰጡት አገልግሎት፣ ወይም ተያይዞ ስለምንፈጥረው ተፅዕኖ በቀላሉ የማይበርድ ውስጣዊ ትኩሳት ሊኖር ያስፈልጋል። ይህ ስሜት ከሌለ ሥራው ሲሳካ የሚፈጥረውን ስሜት በማሰብ ራስን መቆስቆስ ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጥር የሚችለው እንዴት ያለ የሥራ መስክ ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።
በቢዝነስ ጉዞ ውስጥ ብዙ ውጣ ውረድ ሊገጥም ስለሚችል፣ እንዲህ ያለ ውስጣዊ ኃይል እንደ ነዳጅ ሆኖ ውጣ ውረዱን ለመወጣት ኃይል የሚሰጥ ይሆናል። ስለወደፊቱ ማሰብ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪዎች ከዛሬው እንቅፋት፣ ውጣ ውረድ ወይም ጊዚያዊ ድል ይልቅ የወደፊቱ ጊዜና የሚደርሱበት ከፍታ የሚታያቸው ናቸው። ሁልጊዜም ከወራት፣ ከዓመታት በኋላ ሥራቸው የት እንደሚደርስ በማሰብ መቃኘት ይኖርባቸዋል። ራዕይና ዓላማቸውን ሲያስቡ የወደፊት ግብ መላልሰው የሚያስቡ ሲሆን፤ ዛሬ የሚገጥመውን እንቅፋቶችም ሆነ ‹‹ማታለያዎች›› ለማለፍ አቅም ይኖራቸዋል።
ነገሮችን የማቀናጀት ክህሎት አዲስ ሥራ ሲጀመር፣ እየሰሩም ከሆነ ሥራውን ለማስፋት ስያስቡ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። ያለን ገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ ትስስር ወዘተ…በሚፈለገው ‹‹ሃሳባዊ›› ልክ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው። ስለዚህ ያሉትን ነገሮች ቅደም ተከተል በማስያዝና በሁነኛ መንገድ በማቀናጀት መሥራት መቻል ይገባል። እንዲህ ማድረግ እንዲቻል ደግሞ ነገሮችን የማቀናጀትና ውጤት የማምጣት ክህሎትን ማዳበር ያስፈልጋል።
ከገንዘብ ይልቅ እሴትን ዋጋ መስጠት በእርግጥ አንድ ቢዝነስ ህልውናው ሊቀጥል የሚችለው አትራፊ ከሆነ፣ በሌላ አባባል ከወጪው ይልቅ ገቢው ከበለጠ ነው። የዚህ ዋናው መለኪያ ደግሞ የተስተካከለ የገንዘብ ፍሰት ነው። ይሁን እንጂ፣ አንድ ቢዝነስ ትርፋማ ለመሆንና ላለመክሰር መጠንቀቅ ያለበትን ያህል ዋና ግቡን እንዲያው ዝም ብሎ ገንዘብ ማጋበስ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ስለዚህም፣ ‹‹በፍጥነት›› ከምንሰበስበው ገንዘብ ይልቅ፣ በምርታችን ወይም በአገልግሎታችን ለምንጨምረው እሴት ዋጋ መስጠት ይኖርብናል። ለጥራት፣ ለአገልግሎት እርካታና ለመሳሰሉት እሴቶች ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጥ ከሆነ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተዓማኒነታችን ከፍ እያለና ትርፋችን እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነው። ስለ ሥራ ፈጣነት እንዲህ ከተመለከትን ከሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ድረ ገፅ ያገኘነውን ሥራ ፈጣሪ ወጣት ኃብተስላሴ ገብረክርስቶስ ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ወጣት ኃብተስላሴ ገብረክርስቶስ የተወለደው በአዲስ አበባ ቦሌ ማተሚያ ቤት አካባቢ ነው። ሥራ ፈጣሪው ወጣት አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በነጻነት ብርሃን ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ነጥብ አገኘ። ሆኖም በትምህርት ዘርፍ ምርጫ ወቅት በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጠው አፕላይድ ማቲማቲክስ ዘርፍ ስለተመደበና የትምህርት ዘርፉ እሱ ከሚያስበው የሕይወት አቅጣጫ ጋር ስላልሄደለት ብዙም ሳይገፋ አቋርጦ ወጣ። ከዚያም በአድማስ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መማር ጀምሮ በሥራ ጫና ምክንያት ሣይገፋበት መቅረቱን ይናገራል።
ኃብተስላሴ መጀመሪያ ሥራ ሲጀምር ‹‹ኤ3›› በሚባል የቅርብ ዘመዶቹ በሚያስተዳድሩት የማስታወቂያና የህትመት ድርጅት ውስጥ በግራፊክስ ዲዛይነርነት ነበር። ጊዜውን ሲያስታውስ ‹‹እዚያ ለዓመት ከመንፈቅ ከሰራሁ በኋላ በገበያው ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የዲዛይን ባለሙያዎች እጥረትና የክህሎት ክፍተት አስተዋልኩ።
የግራፊክስ ባለሙያዎች ማስተማሪያና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መክፈት አስብ ነበር። ግን በቂ የገንዘብ ዝግጅት ስላልነበረኝ ለጊዜው ሃሳቡን አቆየሁት። ሃሳቡ ግን እንቅልፍ ይነሳኝ ስለነበር ለስቱዲዮ የመቀረጫ ወጪ ላለማውጣት ቤቴ ውስጥ በራሴ ላፕቶፕ የሰው እንቅስቃሴና ድምጽ በማይኖርበት ሌሊት በዘጠኝ ሰዓት እየቀረፅኩ ወጪ በማይጠይቅ መልኩ እገዛን ለማድረግ የማስተማሪያ ሲዲን በአማርኛ አዘጋጀሁ›› ይላል።
ማተሚያ ቤት ውስጥ በሚሰራበት ወቅት በዘርፉ ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች በደንብ ማስተዋል ቻለ። በተለይ በጨርቅና በልብስ ላይ የሚታተሙ ህትመቶች የሚያስወጡትን ከፍተኛ ወጪ ሲመለከት መፍትሄ ማበጀት እንዳለበት አሰበ። የማተሚያ ዋጋው ከጨርቁ ወይም ከቲሸርቱ ዋጋ በጣም ይበልጥ ስለነበር ‹‹ሂት ትራንስፈር ፔፐር›› የተባለውን ለሥራው ግብዓት የሚሆን ወረቀት በተመጣጣኝ ዋጋ በአገር ውስጥ በጥራትና በብዛት ማምረት የሚቻልበትን መንገድ ማጥናት መጀመሩን ይናገራል፡፡
በጊዜውም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ያረፉበት ወቅት ስለነበር ለቲሸርት ህትመት ይህ ሂት ትራንስፈር ፕሪንቲንግ ወረቀት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነት ነበረው። ለድርጅቱ መሠረት የሚሆን የፋይናንስ ብርታት ያገኘውም በዚህ ወቅት ነበር። በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ ገባ። ከመጀመሪያዎቹ አምራቾች መካከል በመሆኑ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘቱን ይጠቅሳል፡፡
‹‹በ2003 ዓ.ም በቴሌቭዥን በሚተላለፈው የንግድ ሥራ ተሰጥኦ ውድድር ይህንኑ ሃሳብ አቅርቤ ከ40ዎቹ አሸናፊዎች መካከል ስለነበርኩ በጃክሮስ አካባቢ 80 ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታ በጣም ትንሽ በሚባል ገንዘብ እንደሽልማት ተሰጥቶኝ ሥራዬን አጠናክሬ መሥራት ጀመርኩ። ከዚያም በፊት 40 ሺህ ብር ተከራይቼ ስለነበር የምሰራው ሽልማቱ ጫናውን አቃልሎልኛል›› በማለት ሥራ በጀመረበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
ነገር ግን ለሕትመት የሚሆነውን ወረቀት በብዛት ቢያመርትም የሚታተምበትን ጨርቅ ግን በፈለገው አቅርቦት መጠን ማግኘት ያልቻለው ኃብተስላሴ፤ ጨርቁን ለማምረት ወሰነ። ሆኖም በወቅቱ በልብስ ስፌት ሥራ ላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሊሰጥ የሚችል ማሰልጠኛ ስላልነበረ አብረውት ከሚሰሩት ባልደረቦቹ ጋር በራሳቸው ሙከራ ጀመሩ።
እገዛ እንዲያገኙ በማሰብ ከነሱ በፊት በሥራው ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለማማከር ሲሄዱ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋቸው እንደነበር ይናገራል። ‹‹እውቀቱ ያላቸው ሰዎች ሥራቸውን የምንወስድባቸው መስሏቸው በምንም መልኩ ሊረዱን አልፈለጉም። ስለዚህ ልምድ ያላቸው ሰዎችን ቀጥረን በ2005 ዓ.ም የስፌት ሥራና ህትመትን ቀላቅለን መሥራት ጀመርን።›› ይላል፡፡
ድርጅቱም ኃብቴ ጋርመንት የተባለው በዚህ ወቅት ነበር። በአዲስ መልክ ሥራ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በብዛት ለማምረት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት አጋጥሞት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ እንደመፍትሄ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከውጪ ማስመጣትና መሥራት ቀጠለ። በዚህም እየተጠናከረ፣ ድርጅቱ እያደገ፣ ሥራውንም እየለመዱት መጡ።
በአሁኑ ወቅት በድርጅቱ ውስጥ 110 ሰራተኞች አሉ። ሥራቸውን የበለጠ ለማስፋት በማሰብ ባደረጉት የገበያ ዳሰሳ ምቾት ያለው፣ ለጨዋታ የሚሆን የቤት ልብስ እጥረት መኖሩን ስለተመለከቱ ‹‹ኩርታ›› የተባለ የልጆች አልባሳት ዲዛይን ምርትና ሽያጭ ጀመሩ። መገናኛ፣ ገርጂና ስቴዲየም አካባቢ ሱቆች ከፍተው እየሸጡ ይገኛሉ። ከአራስ እስከ 14 ዓመት ለሆኑ ልጆች ከ70 እስከ 80 ዓይነት ስታይል ያላቸው ልብሶችን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ። ጥሩ ተቀባይነትም ማግኘታቸውን ያስረዳል፡፡
‹‹ሥራ ፈጣሪው ያሰበው ነገር ለየት ያለ ሲሆን፤ ማህበረሰቡ ላይረዳው ይችላል። እንዲያውም ራዕዩን ሳይረዱለት በሚናገሩት ነገር በራስ መተማመኑ ሊሸረሸር ይችላል። በተጨማሪም የግብዓት እጥረት፣ ፍቃድ ለማግኘት ረዥም ጊዜ መውሰዱ ከግዢ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከነዚህም ሁሉ በላይ ደግሞ ከዚህ በፊት በዚህ ሥራ ላይ ልምድ የለህም ተብሎ ዕድሎችን መነፈግ እነኚህ ሁሉ ወደኋላ ይጎትታሉ። እኔን ካጋጠሙኝ ነገሮች ተነስቼ የምመክረው አንድ ነገር ስኬት እንዳለ ሁሉ ውድቀትም ሊኖርም ይችላል። ስለዚህ ጫናን ለመቋቋም ጫንቃን ማደንደን ያስፈልጋል።›› በማለት ምክሩን ለሌሎች ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ለሚፈልጉ ወጣቶች ይናገራል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ድርጅታቸውን በማስፋፋት ብዙ ሥራዎችን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበሩ። እንዲህ ባሉ ጊዜያት ሥራ ፈጣሪዎች ይፈተናሉ። ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመትና ችግሮች እንደሚመጡ ቀድሞ የነገሮችን አዝማሚያ እያዩ በቂ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል። ለምሣሌ እነሱ ባላቸው ማሽን ‹‹ምን ዓይነት ምርት ማምረት እንችላለን›› ብለው በማሰባቸው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) በማምረት ይህም ጊዜ የራሱ ፈተናዎች ቢኖሩትም ነገር ግን ብዙ ዕድሎችም ይዞ እንደሚመጣ በማመን ወደ ሥራ መግባታቸውን ይጠቁማል።
የኃብቴ ድርጅት ሞዴል በመሆን በመልካም ሥራ አፈጻፀም ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝነት ስላደገ ከከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የዕውቅና ምሥክር ወረቀት ተሰጥቶታል።
‹‹ሥራ ፈጠራ በትምህርት ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም። በቀለም ትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን የራስ ሥራ ለመጀመር አይበቃም። ጥንካሬና ራዕይ፣ በራስ መተማመንና ለፈተናዎች ሁሉ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። ሥራ መፍጠር ለየት ያለ አተያይ ይፈልጋል። በትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን ሥራ ፈጣሪ ለመሆን አይበቃም። የማህበረሰቡን ችግር ለየት ባለ መረዳት ማየት ያስፈልጋል›› በማለት ሀሳቡን ይገልፃል፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም