ወንበዴ የሚለው ቃል ለማህበረሰቡ አዲስ አይደለም። ይልቁንም በተለምዶ ጉልበተኛ ሆኖ ሠላም እየነሳ ለሚያስቸግር ሽፍታ እና ቀማኛ የባህሪ መገለጫ አድርጎ ሲጠቀምበት ኖሯል። ምንም እንኳን ህብረተሰቡ ውንብድናን ከጉልበተኝነት ጋር አያይዞ የሚጠቀምበት መሆኑ በጥቂቱም ቢሆን በህጉ ለውንብድና ከተሰጠው ትርጓሜ ጋር ቢያመሳስለውም የቃሉ ተለምዷዊ አጠቃቀም ከወንጀል ህጉ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።
ውንብድና በወንጀል ህጉ ስድስተኛ መፅሀፍ በምዕራፍ ሁለት ከተመለከቱት በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የወንጀሉ ምንነት በወንጀል ህጉ አንቀፅ 670 በዝርዝር ተቀምጧል። ይኸውም ማንኛውም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው የሆነውን ተንቀሳቃሽ እቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት ሲል በሌላ ሰው ላይ የሀይል ድርጊት ወይም ከባድ የሆነ የማንገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ ከፈፀመ እንዲሁም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው መከላከል እንዳይችል ያደረገ እንደሆነ የውንብድና ወንጀል መፈፀም መሆኑን ደንግጓል። እዚህ ላይ በተለምዶ እይታ የሚያይ ሰው ውንብድና እና ስርቆት በምን ይለያል? የሚል ጥያቄ ሊያነሳ እንደሚችል እሙን ነው።
በውንብድና እና በስርቆት ወንጀሎች መካከል መመሳሰል መኖሩ የማይካድ ቢሆንም ውንብድና ከስርቆት በተለየ መልኩ የሀይል ድርጊት የቀላቀለ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ምንም ዓይነት ሀይል ሳይጠቀም የሌላ ሰውን ተንቀሳቃሽ ንብረት ከወሰደ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 665 መሠረት የስርቆት ወንጀል ይባላል። በአንፃሩ የሌላ ሰው የሆነን ተንቀሳቃሽ ንብረት ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ ለመከላከል በሚሞክር ሰው ላይ የሀይል ድርጊት፣ ማንገላታት ወይም ከባድ ዛቻ የተፈፀመ እንደሆነ ድርጊቱ የውንብድና ወንጀል ይሆናል ማለት ነው።
ሌላው በማህበረሰቡ አለፍ ሲልም በምርመራ መዛግብት ላይ ጭምር የውንብድና ወንጀልን ዘረፋ ወይም በጦር መሳሪያ ዘረፋ በሚል ሲገልፁት መስማት የተለመደ ነው። እውን ውንብድና እና ዘረፋ ተመሳሳይ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ሲታይ በአጭሩ መልሱ አይደለም ነው። ይኸውም ዘረፋ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 672 የተመለከተ ሲሆን፤ በሚወሰዱት እቃዎች እንዲሁም በአፈፃፀሙ ሁኔታ ከውንብድና የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። የዘረፋ ወንጀል ተፈፀመ የሚባለው የተወሰዱት እቃዎች ለህዝብ ህይወት፣ ለአገር ኢኮኖሚ ወይም እድገት ጥቅም በሚሰጡ ምግቦች፣ ስንቆች፣ በሚታደሉ እቃዎች መሣሪያዎች ወይም ሌሎች ንብረቶች ሲሆኑ ወይም ደግሞ ድርጊቱ የተፈፀመው በመሬት፣ በባህር፣ ወይም በአየር በሚመጣ መጓጓዣ ላይ የሚከሰቱ እንደ መኪና አደጋ ወይም የአውሮፕላን ድንገተኛ ተገዶ ማረፍ ወይም እንደ መርከብ መስጠም የመሳሰሉ አደጋዎችን ምክንያት በማድረግ የተፈፀመ እንደሆነ ከድንጋጌው መረዳት ይቻላል። ስለዚህ የውንብድና እና የዘረፋ ወንጀሎች የተለያዩ ወንጀሎች በመሆናቸው ማደበላለቅ አይገባም።
የውንብድና ወንጀል የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት
ውንብድና በወንጀል ህጋችን በወንጀልነት የተደነገገ እንደመሆኑ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትልና በእሥራት ቅጣት የሚያስቀጣ ነው። የሚጣለው ቅጣትም እንደ ወንጀሉ አፈጻፀም ሁኔታ የሚለያይ ነው። በአንቀፅ 670 መሠረት ማንኛውም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው የሆነውን ተንቀሳቃሽ እቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት ሲል በሌላ ሰው ላይ የሀይል ድርጊት ወይም ከባድ የሆነ የማንገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ የፈፀመ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው የመከላከል እንዳይችል ያደረገ እንደሆነ ከአስራ (15) በማይበልጥ ፅኑ እሥራት የሚቀጣ ይሆናል።
ሆኖም የውንብድና ወንጀል የሚፈፅም ሰው የሚፈፅመው የሀይል ድርጊት ከማስፈራራት እና ከማንገላታት አልፎ በሚከላከለው ሰው ላይ የአካል ጉዳት ባስ ሲልም ሞት ሊያስከትል እንደሚችል በተግባር የታየ ነው። ይህ ዓይነቱ ጉዳት መከሰትም የወንጀሉን አፈፃፀም የሚያከብድና ቅጣቱንም ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ህጉም ይህንን ድርጊት ከባድ ውንብድና በሚል ሥያሜ ሰጥቶ ከባድ የሚያሰኙ የአፈጻፀም ሁኔታዎቹን በአንቀፅ 671 በዝርዝር ደንግጓል።
በአንቀፅ 671(1) መሠረት ወንጀል ፈፃሚው ወንጀሉን የፈፀመው በሰዎች ወይም በንብረት ላይ የሀይል ድርጊት ለመፈፀም በተቋቋመ የወንበዴ ቡድን አባል በመሆን ከሆነ፣ ተበዳዩን እገድልሀለሁ ብሎ እርግጠኛ የሞት አደጋ ሊያደርስ በሚችል መልኩ በጦር መሣሪያ ወይም በተለይ አደገኛ በሆነ ሌላ ዓይነት መሣሪያ በማስፈራራት ወይም ሥቃይ በሚያደርስ ሁኔታ በማንገላታት ወይም ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ ከሆነ ወይም በተለይ አደገኛነቱን በሚያሳይ በማናቸውም ሌላ ሁኔታ ከሆነ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣ ነው።
በአንቀፅ 671(2) ሥር እንደተገለፀው ደግሞ እስካሁን ከተገለፁት በከባድ ሁኔታ የተፈፀመ ድርጊትን የሚያሳይና ከፍተኛ ቅጣትም የሚያስቀጣ ነው። ይኸውም ወንጀል ፈፃሚው ወንጀሉን የፈፀመው ከተደራጀ ቡድን ጋር በመሆን ወይም የጦር መሣሪያ ወይም ሌላ አደገኛ መሣሪያ በመያዝ፣ የሕዝብ ፀጥታን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የተለየ ጨካኝነትን የሚያሳይ ዘዴን የተጠቀመ ወይም የተፈፀመው የሀይል ድርጊት ዘላቂ የአካል ጉዳት ወይም ሞትን ያስከተለ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የእድሜ ልክ እሥራት ወይም ወንጀሉ እጅግ ከባድ ከሆነ የሞት ቅጣት ሊወስን እንደሚችል ደንግጓል።
እዚህ ላይ “የወንበዴ ቡድን አባል በመሆን እና የጦር መሣሪያ ወይም በተለይ አደገኛ የሆነ ሌላ ዓይነት መሣሪያ በመያዝ” የሚሉት ሁኔታዎች የተለያየ ቅጣት ባስቀመጡት በሁለቱም ንኡስ አንቀፆች ሥር መካተቱ ጥያቄ ሊያጭር እንደሚችል ይታመናል። ይኸውም አንድ ተጠርጣሪ የወንበዴ ቡድን አባል ሆኖ ወይም የጦር መሣሪያ ወይም ሌላ አደገኛ መሣሪያ ይዞ የውንብድና ወንጀል በመፈፀም ቢጠረጠር በየትኛው ድንጋጌ ነው የሚጠየቀው የሚል ነው። እርግጥ ነው ህግ በተለያዩ ባለሙያዎች በተለያየ እይታ ሊተረጎም እንደሚችል ባይካድም ይህ ግን የወንጀል ጉዳይ እንደመሆኑ ለድንጋጌዎች የሚሰጠው ትርጓሜ እና አፈጻፀም ወጥነት ያለው እንዲሆን የግድ ነው።
በመሆኑም በንኡስ አንቀፅ ሁለት ሥር የተቀመጠው ድንጋጌ የወንበዴ ቡድን አባል መሆንን ወይም ጦር መሣሪያ አሊያም ሌላ አደገኛ መሣሪያ መያዝን ብቻ ሳይሆን የድርጊቱ አፈጻፀም የሕዝብ ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል መሆን፣ የተለየ ጨካኝነትን የሚያሳይ ዘዴ መጠቀምን አለፍ ሲልም ድርጊቱ ሞት ወይም ዘላቂ የአካል ጉዳት ያስከተለ መሆን ከሚሉት መመዘኛዎች ጋር ተመዝኖ ተፈፃሚ የሚሆን መሆኑን መረዳት ይገባል ማለት ነው።
በአጠቃላይ የውንብድና ወንጀል በህጉ ላይ የተሰጠው ትርጓሜ ህብረተሰቡ በተለምዶ ካለው አረዳድ የተለየ እና ከዘረፋ ወንጀልም የተለየ ሲሆን፤ ለህብረተሰቡም ሥጋት እየሆነ ያለ ወንጀል ነው። በሌላ በኩል ከላይ እንደተመለከተው ድርጊቱ ከፍተኛ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ወንጀል ከመሆኑ አንፃር በወንጀል ፈፃሚዎቹ እና በቤተሠቦቻቸው ላይ የሥነልቦና ጉዳት ጭምር የሚያስከትል ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ ወንጀሉን በመከላከልም ሆነ ተፈፅሞ ሲገኝ ለፍትህ አካላት ተባባሪ በመሆን የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል።
ምንጭ፡- ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም