የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ነን ይላሉ። ለዓለም የሰብዓዊ መብት መከበር አበክረው እንሰራለን ብለው ይመጻደቃሉ። በእነሱ እሳቤና ጥቅማዊ አተያይ እምብዛም አይጠቅሙንም፤ አያስፈልጉንምና የጥቅማችን ተጻራሪ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን አገራት ሰብዓዊ መብት አላከበሩም እያሉ ውሃ ቀጠነ በሚል ሰበብ ሲያሻቸው የኢኮኖሚ፤ ሲፈልጉ የቪዛ ክልከላ ማዕቀብ ይጥላሉ። በአንጻሩ ከእነርሱ ጋር የጥቅም ትስስር ያላቸው አገራት ያሻቸውን ሰብዓዊ መብት ቢጥሱ፣ ባያከብሩና ሰቅጣጭ ድርጊት ቢፈጸሙ ዓይናቸው እያየ እንዳላየ ሰምተው እንዳልሰሙ ያልፏቸዋል። ድንቄም የሰብዓዊ መብት ጠበቃ!
ለአብነት ያህል የግብጽ መንግስት የሰብዓዊ መብትን ከሚጥሱ የአገራት መንግስታት አንዱ እንደሆነ ብዙ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያመላክታሉ። በግብጽ ውስጥ በርካታ ሰዎች በተለያዩ እሥር ቤቶች ታጉረው ኢሰብአዊ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል። በፕሬዚዳንት አብድልፈታህ አልሲሲ አገዛዝ የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት እና የመብት አቀንቃኞች እስራት እና የደረሱበት እስከማይታወቅ ድረስ በፀጥታ አካላት እንዲሰወሩ ይደረጋል። የአሜሪካ መንግስት ግን ግብጽን በሚመለከት የዓለም አቀፍ የመገኛኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ የሚያወጡትን ዘገባዎችና ሪፖርቶች ከግብጽ መንግስት ጋር ያላቸውን የጥቅም ትስስር በማጤን ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ ያልፈዋል።
አሁን በቅርቡ በእሥራኤልና በሀማስ መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ብዙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ሲቪሎች፣ ህጻናትና አረጋዊያን በጥቃቱ ሰለባ ሲሆኑ፤ የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ነኝ እያለ የሚመፃደቀው የአሜሪካ አስተዳደር ጉዳዩን እንዳላየ አልፎታል። የአሜሪካ መንግስት ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም። ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስታውስ፤ በአፍጋኒስታንና በኢራቅ ጦርነት ወቅት ላይ የአሜሪካ ወታደሮች የፈጸሙት ኢሰብአዊ ድርጊት ተዘርዝሮ አያልቅም። ይህን አሳፋሪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የአሜሪካ ህዝብና ታዋቂ ሰዎች ሳይቀር በአደባባይ ወጥተው ሲያወግዙት መንግስቱ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ሲያስተባብል እንደነበር የሚታወስ ነው።
በዓለም ላይ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር መታገል የሚያስመሰግን፤ ማንኛውም የዓለም አገራትን የሚያስማማ ዓለም አቀፋዊ ህግ ቢሆንም በሰብዓዊ መብት ይከበርና በሌሎች ጉዳዮች በሚል ሰበብ የሚጠቅማቸውን አገር ሰብዓዊ መብት እየጣሰ በዝምታ ማለፍ በተቃራኒው የማይፈልጉት አገር ደግሞ በሰብዓዊ መብት ይከበር በሚል ሰብብ ማውገዝና ማዕቀብ መጣል ኢ-ፍትሀዊ አካሄድ ነው። ምክንያቱም ሰብዓዊነት ለይቶ ማልቀስና ጫና ማሳደር አይደለም። ሰብዓዊነት ፍትሀዊ፣ ሚዛናዊና ገለልተኛነት ይጠይቃል። የዴሞክራሲ ጠበቃ መሆን በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባትና የሌሎችን አገሮች ሉዓላዊነት ያለማክበር አይደለም። በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትም ተቀባይነትም፤ ህጋዊም አይደለም።
ሰብዓዊ መብት ጠበቃ ነኝ እያለ የሚያላዝነው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ‹‹እጄን አስገብቼ ካልፈተፈትኩ›› እያለ ጫና መፍጠሩ በሚዛናዊ፣ በፍትሀዊና በዴሞክራሲያዊ መርህ እንደማያምን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው። ለዚህ ተጨማሪ ማሳያ የሚሆነን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ነኝ እያለ የሚደሰኩረው የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብቼ ካልፈተፈትኩ እያለ መፎከር ከጀመረ ቆይቷል። በትግራይ ህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ በአገር ኩራት በሆነው ሰራዊታችን ድል የሽንፈት ካባ የተከናነበው አሸባሪው ህወሓትና የእሱ ጥቅም ተጋሪዎች በሚነዙት የሀሰት ዘገባ መነሻ አድርጎ የአሜሪካ መንግስት ሰሞኑን በመንግስት ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ ማዕቀብ ጥሏል። ይህ ለኢትዮጵያ ያለው አመለካከት የተዛባ መሆኑን ያሳያል።
የአሜሪካ መንግስት በባለስልጣናት ላይ የጣለው ቪዛ ክልከላ ማዕቀብ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብተን ካልፈተፈትን የሚል አንድምታ ቢኖረውም ዋና ድብቅ ሴራ ግን ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለችውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ያለመ ነው። ይህ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ካላችበት ስር የሰደደ ድህነት የምትላቀቀው በውጭ ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ስታለማ ነው።
በተለይ የኤሌክትሪክ ሀይል ደግሞ በከተሞች እየተስፋፉ ለመጡት ኢንዱስትሪዎች የሀይል አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ፣ በኩበትና በቅጠል ጭስ ለተቸገሩት የገጠር እናቶች የሀይል አማራጭና ብርሃን እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ይህ ደግሞ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ዘላቂ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ስለዚህ የአሁኑ የአሜሪካ መንግስት ከግብጽ ጋር ባለው የጥቅም ቁርኝት ምክንያት በሰብዓዊ መብትና የኢትዮጵያ መንግስትን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ ከተሰየመ ድርጅት ጋር ተደራደሩ በሚል ተገቢ ያልሆነና አሳፋሪ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና እያደረገ መሆኑ ዓብይ ማሳያ ነው።
ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ በማውጣት በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ ከመጠን በላይ ጫና ማሳደር አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው። የአሜሪካ መንግስት ሽብርተኝነትን ለማጥፋት በሌሎች አገሮች የሉዓላዊ ወሰንን ጭምር ተላልፎ ጥቃት እየፈጸመ የኢትዮጵያን መንግስት ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ተደራደር ማለት ኢሞራላዊ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረርና የሚደፍር ተግባር ነው።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የምታካሂደው ከአባይ ወንዝ ፍትሀዊ ተጠቃሚ ለመሆን ነው። ህዝቦቿን በብርሃን ለማድመቅ፣ ከድህነት ለመውጣት ነው። ይህ ግድብ የሚገነባው ከውጭ በሚገኝ ብድርና ዕርዳታ ሳይሆን በዜጎቿ አንጡራ ሀብት ነው። ስለሆነም ዓይናችሁን ጨፍናችሁ ላሞኛችሁ የሚለውን የግብጽ የአባይን ወንዝ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ፈሊጥ አሜሪካ ከግብጽ የምታገኘውን ጥቅም ለማካካስ የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ላይ የምትፈጥረው ጫና በማር የተለወሰ መርዝ መሆኑ መታወቅ አለበት።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በመጪው ሀምሌ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ አድርጓል። ይህን ተከትሎ ግብጽ በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር በአገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመደገፍ ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። እነዚህ ሁሉ ሊሳኩላትና ያሰበችውን ዓለማ ሊያሳኩላት ስላልቻሉ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የጥቅም ትስስር ተጠቅማ በእጅ አዙር በአሜሪካ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየጣረች መሆኑ የቪዛ ክልከላ ማዕቀቡ አንዱ ማሳያ ነው።
አሜሪካም ሆነች ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም፣ አሜሪካ በባለስልጣናት ላይ የጉዞ ዕገዳ ማዕቀብ ብትጥልምና ሌሎች ጫናዎችን ብትፈጥርም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሁሉንም ችግሮችና እንቅፋቶች አልፈው ብልፅግና ማረጋገጣቸው አይቀርም። ኢትዮጵያ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም ብዙ ጫናዎች ደርሰውባታል። እነዚህን ሁሉ ተቋቁማ በህዝቦቿ አንድነትና ፅናት ነጻነቷን አስጠብቃ እስካሁን ቆይታለች። ዛሬም ሆነ ወደፊት በህዝቧቿ አንድነትና ፅናት የውጭ ተፅዕኖን ተቋቁማ ታልፋለች። ዕድገትና ልማቷን ታረጋግጣለች። ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው የህዝቦቿ ኑሮ የሚሻሻልበትና የምትበለፅግበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም