አንድን ትልቅ ሀገርና ህዝብ የሚወክል መንግስት፣ ከዚህም በላይ የዓለም ፖሊስ ለመሆን የሚሻና ይህንኑ መሻቱን እውን ለማድረግ የሚንቀሳቀስ መንግስት ከሁሉም በላይ ለዓለም አቀፍ ሕግጋት ተገዥ ሊሆን ይገባል። ከዚህም በላይ ጉዳዮችን የሚያይበትና የሚዳኝበት መርሁ ፍትሀዊነትን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል።
የሀገራትን ሉአላዊነት ከማክበር ጀምሮ በሀገራት ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትን ፣ የሀገራት ሕዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የሚፈቱበትን መንገድ ከማመቻቸትና ከመደገፍ ባለፈ ባለጉዳይ ሆኖ መገኘት ነውር እንደሆነ፣ ይህ ነውር የሚወክለውን ህዝብ የሚያሳንስ እንደሆነም በአግባቡ ሊያጤነው ይገባል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ ከደረሰበት የንቃተ ህሊና ከፍታ አንጻር በዚህ ዘመን ሞግዚት የሚፈልጉ ህዝቦች እንደማይኖሩ፣ ሃገራት ሞግዚት ከመፈለግ አልፈው ራሳቸውን በመሆን የተሻለ ቁመና ለመላበስ አዲስ በሆነ መነቃቃት ላይ እንደሆኑ መረዳትም ይፈልጋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ላለፉት ዘመናት ተተግብረው ስኬታማ ተደርገው የሚወሰዱ አለም አቀፍ የሴራ ፖለቲካ አካሄዶች በዚህ ዘመን አዋጭ እንዳልሆኑ፣ ዘመኑ በመተማመንና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ከሁሉም በላይ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማጤንም ተገቢ ነው።
ዘመኑ እንደቀደሙት ዘመናት ራሳቸውን አሸንፈው ለመውጣት የሚፈልጉ የዓለም ሀገራት የህዝቦችን ተስፋ በተወሳሰበ ሴራና የጉልበት መንገድ ማደናቀፍና ተስፋቸውን ጥለው በግራ መጋባት ውስጥ እንዲዳክሩ ማድረግ የሚቻልበት ዘመን አይደለም። በዚህም መንገድ የሚመጣ የዓለም ሰላምና መረጋጋት እንደማይኖርም ያለፉት 100 አመታት የሆነው ነገር ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ዘመኑ ከእንትና እንትና ይሻለኛል በሚል አንዱን የመስዋእት በግ ሌላውን በተሰዋው በግ ደም መዋጀት የሚቻልበት አይደለም። የእንትና ወዳጅነት ከእንትና ጠላትነት ይሻላል እያልን የምናሰላበትም የፖለቲካ ምህዳር ጊዜ ያለፈበትና የቀደመው ዘመን የአስተሳሰብ ጥላ ነው። በዚህ ደረጃ የወረደ የፖለቲካ ንግድም አዋጭ አይደለም። ሊያስከፍል የሚችለውም ዋጋ ከፍ ያለ እንደሚሆን ይታመናል።
ይህ ዘመን በጉልበትና በማን አለብኝነት መንፈስ ብዙ እርምጃ መራመድ የሚቻልበትም አይደለም። የጉልበትና የማን አለብኝነት መንገድ ቀደም ባለው ጊዜ ዓለምን የቱን ያህል ከፍያለ ዋጋ እንዳስከፈለ ኢራቅን ፣ ሶሪያን፣ ሊቢያንና የመንን ማየቱ ብቻ በቂ ነው። ፍርድና ፍትህ ባለቤት ስላላቸው በነዚህ ሀገራት ህዝቦች መከራና ስቃይ የተገኘ የፖለቲካ ትርፍ ይቆይ እንጂ የችግሩን ተዋንያን ከፍያለ ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው።
በዚህ በኩል የአሜሪካ አስተዳደር ቀደም ባሉት አመታት የአሜሪካንን ተደማጭነትና ተቀባይነት ችግር ውስጥ የከተቱ ያልተገቡና ዓለምን ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈሉ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም በፕሬዚዳንት ትራምፕ ዘመን የአሜሪካንን ጥቅሞች አደጋ ውስጥ የ ከተቱ የአሜሪካንን ህዝብ የማይመጥኑ ተግባራት በአደባባይ ሲከወኑ ታይተዋል፣ ተደምጠዋልም።
ይህም ለፕሬዚዳቱ ውድቀት ትልቁ ጉዳይ ሆኖ አልፏል። በሳቸው እግር ወደ ስልጣን የመጣው የባይደን አስተዳደር ቀደም ሲል በትራምፕ መስመር የሳተውን የሀገሪቱን የውጪ ፖሊሲ በማስተካከል የተሻለ ቁመና እንዲላበስ ያደርጉታል የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር። በተለይም ባይደን የወከሉት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ከመሆኑ አንጻር ፤ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ለሚጥሩ ሀገራትና ህዝቦች የተሻለ ዕድል ይዞ መጥቷል የሚል ከፍያለ ግምት ነበር።
ይህ ሁኔታ ግን በብዙ መልኩ የታሰበውንና የተጠበቀውን ያህል እየሆነ አይደለም። በተለይም ኢትዮጵያ አሜሪካ ትራምፕ የስልጣን ዘመን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘችው ያልተገባና ፍትሀዊነት የጎደለው የማን አለብኝነት አካሄድ ወደ ትክክለኛው መንገድ ይመጣል የሚል ተስፋ ነበራት።
በተጨባጭ በባይደን አስተዳደር የሚስተዋለው ግን ከትራምፕ አስተዳደር በከፋ መልኩ ኢፍትሀዊ ከመሆንም ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል ከምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረውን ግንኙነት የማይመጥን ፣ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን የሚያሳንስ ተግባር ነው።
የባይደን አስተዳደር በተለይም በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ሽፋን በማድረግ ሀገሪቱ የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከዛም ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያራምዳቸው አቋሞች የኢትዮጵያን ህዝብ ሉአላዊ መብቶች የሚጋፉና ፍጹም ጣልቃ ገብነት የሚስተዋልባቸው ናቸው።
በተለይም የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያ ሕዝብ በተወካዮች ምክር ቤት በኩል አሸባሪ ያለውን የህወሓት ቡድን ከተቀበረበት ጉድጓድ አውጥቶ ሕይወት ለመዝራት የሚያደርገው ጥረት፤ ከዚህም በላይ መንግስትን ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር በማስተካከል ለድርድር እንዲቀመጥ መጠየቁ ለህዝባችን ያለውን ከፍ ያለ ንቀት ያሳየ ነው።
የውሳኔ ሃሳቡ በአሸባሪ ቡድን የሽብር ሴራ ለሞቱ ፣ ለቆሰሉ ፣ እስከ ዛሬድረስ ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ህይወታቸውን ለመምራት ለተገደዱ ዜጎቻችን ርህራሄ ትኩረት አለመስጠቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ይህ ደግሞ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነኝ ከሚል አስተዳደር የሚጠበቅ አይደለም። ይህ አሸባሪ ቡድን የትግራይን ህዝብ ለመጠበቅ ለሁለት አስርት በምሽግ በቆየው የመከላከያ ኃይል ላይ የፈጸመውን ከፍተኛ ወንጀል ባለቤት ከማሳጣት ባለፈ ለህዝባችን ደህንነትና ሉአላዊነት ደንታ ቢስ መሆን ነው።
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያም የባይደን አስተዳደር አሁንም ፍትሃዊና አለም አቀፍ ህግን መሰረት ያደረገ ገለልተኛ አቋም አለመያዙ ከዛ ይልቅ በመካከለኛው ምስራቅ ለተፈጠረው አሁነኛ ችግር የመደራደሪያ አቅም አድርጎ ለማቅረብ እየሄደበት ያለው ያልተገባ መንገድ የሀገራቱን ግንኙነት ከፍያለ አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ለመረዳት አይከብድም።
በአጠቃላይ ይህ ተግባር በዴሞክራሲና በዴሞክራሲ እሴቶች ላይ ቆሜ እራመዳለሁ ለሚለውና ዴሞክራቶችን ለሚወክለው አስተዳደር የሞራል ጥያቄ ከማስነሳቱም በላይ ከአሜሪካን ህዝብ የሞራል እሴቶች ያፈነገጠና በአሜሪካን ቀጣይ ጥቅሞች ላይ ተግዳሮት ሊሆን የሚችል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም