ልብ ከሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ውስጥ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ እውቅና የተሰጣት አባል አካል ናት ማለት ይቻላል። ከ20 ሺህ ዓመታት በፊት በዋሻዎች ውስጥ በሚገኙ ስዕሎች ውስጥ ሳይቀር የልብ ስዕል ይገኛል። ጥንታውያን ግሪኮች ደግሞ የአንድ ሰው ብልህነት በልብ ላይ ይገኛል ብለው ያምኑ ነበር። አብዛኞቻችን ደግሞ ልባችንን የነብሳችን ወይም የስሜታችን መገኛ ቦታ አድርገን እናቀርባለን።
በዕለት ተዕለት ቋንቋችን ውስጥም መከፋታችንን ለመግለፅ ልቤ ተሰብሯል፤ ማፍቀራችንን ለመግለፅ ደግሞ ልቤ ተማርኳል እንላለን። የልብ ሥራ ደምን ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ከማዳረስም በላይ ነው። ልብ ሰውነት ለሚፈልገው የኦክስጅን ፍላጎት ፈጣን ምላሽ መስጠት አለበት። ልባችን በእንቅልፍ ሰዓት፣ ወይም በከፍተኛ የአካል እንቅስቃሴ ጊዜያትና የአደጋ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምላሽ የምትሰጥበት መንገድ ይለያያል።
የልብን ድምፅ ሲመታ የምንሰማው ጡንቻዎቹ ሲኮማተሩና ሲፍታቱ ሳይሆን የልብ ክፍልፋዮች ባልቦላ የደም ፍሰትን ለመፍቀድና ለመግታት ሲከፈትና ሲዘጋ ነው። የሰው ልጅ ልብ አራት ክፍልፋዮች ያሉት ሲሆን እነኝህ ክፍልፋዮች በኦክስጅን የበለፀገ ደም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍል በግፊት የሚያሰራጩና የተቃጠለ አየርና ውጋጅ ቆሻሻዎችን የያዘ ደም ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ለተሃድሶ ወደ ሳንባ እንዲሄድ የሚያስችሉ ክፍሎች ናቸው። ሁኔታውን ለመረዳት ጥቂት ስለ ደም ዝውውር ሥርዓት ማየት ተገቢ ነው።
የልብ ምት መጠን
የአንድ አዋቂ ሰው ልብ በእረፍት በሚገኝበት ሁኔታ ውስጥ በደቂቃ ወደ 72 አካባቢ ትመታለች። ነገር ግን ልብ የዚህን ሦስት እጥፍ ፍጥነት መምታት ትችላለች፤ ማለትም ልብ በደቂቃ እስከ 200 ጊዜ ልትመታ ትችላለች፤ በተለይ በከፍተኛ እንቅስቃሴዎችና በድንጋጤ ወቅት የልብ ምት ከፍተኛ ይሆናል። የሕፃናት ልብ ደግሞ በጤነኛ ጊዜ እስከ 120 ምት በደቂቃ ሊሆን ይችላል። የአትሌቶች ልብ ደግሞ በደቂቃ ከ40-60 ሊሆን ይችላል፤ በአትሌቶች ላይ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ልብ በነዚህ ምቶች ብቻ በቂ የሆነ የደም መጠን ገፍታ መርጨት ስለምትችል ነው።
በልብ ላይ የሚያጋጥሙ በሽታዎች
የልብ በሽታ የሚባለው ማንኛውም በጤነኛ የልብ አሠራር ላይ ጣልቃ በመግባት አሠራሩን የሚያዛንፍ ሁኔታ ነው። ይኸውም፡- በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰተው፣ በልብ ጋኖች ባልቦላ ላይ የሚያጋጥመው፤ በልብ ጡንቻዎች ላይ የሚያጋጥመው እና በልብ ምት ላይ የሚፈጠረው መዛባት እና በልብ ላይ በሚያጋጥም ኢንፌክሽን ከወሊድ በፊት የሚለክፍ የቅርፅ ችግር (በሚወለዱ ሕፃናት ላይ የሚያጋጥም) ሊሆን ይችላል። ከነዚህ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በሰዎች ላይ የሚያጋጥመው ከልብ ደም ቧንቧዎች መጥበብ ጋር የሚያያዘው ነው።
በልብ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ በደም ቧንቧዎች መጥበብ ምክንያት ደም እንደልቡ ለልብ ጡንቻዎች እንዳይደርስ በማድረግ ነው። በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ የሚከሰተው በተለያዩ ምርመራዎች መኖሩ ሊረጋገጥ ይችላል፤ የታማሚውን የጤና ታሪክ በመገምገም እንዲሁም በተለያዩ የውስጥ አካላትን በሚያሳዩ መመርመሪያ መሣሪያዎች ሊታወቅ ይችላል። በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ ለሚከሰተው በሽታ የተለያዩ ሕክምናዎች እንደ አስከፊነት ደረጃቸው ሊሰጥ ይችላል።
የልብ ጤና ችግር ምክንያቶች
የልብ ጤና ችግር ምክንያቶች ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በዋነኝነት ግን በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ የሚያጋጥም መጥበብ ነው። ይህ መጥበብ የሚያጋጥመው ደግሞ በደም ቧንቧ ግድግዳዎች ውስጥ በሚከሰት የቅባት መጋገር ነው። የልብ በሽታ በተለይ እንደ አሜሪካ ባሉ አደጉ በሚባሉ አገሮች በስፋት ይታያል፤ ለምሳሌ በአሜሪካ በዓመት 710,000 የሚደርሱ ሰዎች በልብ በሽታ ምክንያት ይሞታሉ።
በልብ ላይ ከሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ደግሞ በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ የሚያጋጥመው በሽታ ነው። ይህ በሽታ የሚከሰተው ለልብ ኦክስጅንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ይመግቡ የነበሩ ደም ወሳጅ ቱቦዎች በመጥበብ የልብ ጡንቻዎች በቂ የሆነ ደም ፍሰት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው። ነገር ግን ሌሎች ብዙ ተጨማሪ ምክንያቶችም የልብን የጤንነት ሁኔታ ሊያጓድሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ከወሊድ ጋር አብሮ የተፈጠረ የልብ ችግር ሊጠቀስ ይችላል። ይህ ሁኔታ በተለይ በሕፃናት ላይ በብዛት ያጋጥማል።
ሌሎች ማለትም የልብ ክፍልፋዮች ባልቦላ በተገቢው ሁኔታ አለመስራትና የተዛባ የልብ ምት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ማንኛውም በልብ ላይ የሚፈጠር አንድ እክል ልብ በተገቢው እንዳይሰራ በማድረግ መላ አካልን ያዳክማል። ሁኔታው ሲባባስና ልብ በተገቢው ሳይሰራ ሲቀር ደም ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች እንዳይደርስ ስለሚያደርግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት ሊያበቃ ይችላል።
የልብ ድካም
የልብ ድካም የሚባለው የልብ ምት ሥራ ማቆምን አያመለክትም፤ ነገር ግን ልብ በተገቢው ሁኔታ እየሰራች እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልብ እየሰራች ቢሆንም በቂ ደምና ኦክስጅን ግን የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን እንደሚፈልጉት እየደረሳቸው አይደለም። ይህ ሁኔታ ቶሎ ሕክምና ካላገኘ ወደ ባሰ ሁኔታ በመሸጋገር ሕይወትን የሚያሳጣ ነው።
የልብ ምት መዛባት
ይህ ሁኔታ የሚከሰተው የልብ ምት የተዛባ ሲሆን ነው፤ በሽታው ልብ በዝግታ ሁኔታ (በደቂቃ ከ60 በታች) ስትመታ ወይም በፍጥነት (በደቂቃ ከ100 በላይ) ስትመታ ወይም ቅኝቷን ሳትጠብቅ በተዘበራረቀ ጊዜ ስትመታ የሚከሰት ነው። ይህ የጤና ችግር በልብ ላይ የተዛባ ሁኔታ በመፍጠር ከባድ ችግር ሊያስከትልብን ይችላል።
በልብ ላይ የሚያጋጥም ድንገተኛ ጥቃት
ይህ ሁኔታ የሚፈጠረው በደም ቱቦ ውስጥ ተጋግሮ የሚገኝ ክምችት በሚፈረከስበት ወቅት ወይም የደም ቱቦ ጠቦ በሚደፈንበት ወቅት የሚፈጠር የደም መስመር መዘጋት ነው። በዚህ አጋጣሚ ምክንያት በኦክስጅን የበለፀገ ደም የማይደርሰው የልብ ጡንቻ ክፍል እየሞተ ይመጣል፤ በጊዜ ሳይደረስበት ከቀረም ለሞት ያበቃል።
የልብ ጋኖች ባልቦላ በተገቢው ሁኔታ አለመስራት
የልብ ጋን ባልቦላዎች በበቂ ሁኔታ ሳይከፈቱና ደም እንደልቡ ማለፍ ሳይችል ሲቀር ወይም ደግሞ የልብ ጋን ባልቦላዎች ተከፍተው ደም ካሳለፉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሳይከደኑ ሲቀሩ የልብ ጤና ችግር ያጋጥማል። በመሆኑም ባልቦላዎች በደንብ ሳይከፈቱ ቀርተው ደም አላሳልፍ ሲሉ ደም በበቂ ሁኔታ ለሰውነት ስለማይደርስ የጤና ችግር ይሆናል፤ እንዲሁም ባልቦላዎች ተከፍተው ደም ካሳለፉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሳይከደኑ ሲቀሩ ደም ወደ መጣበት የመመለስ ሁኔታ ስለሚያጋጥም የጤና ችግር ይሆናል። እነዚህ ሁለት ሁኔታዎች በልብ ጋኖች ባልቦላ ላይ የሚያገጥሙ የጤና ችግሮች ናቸው።
ለልብ በሽታ እንደመንስኤ የሚታዩ ምክንያቶች
በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ የሚፈጠር ችግር ለድንገተኛ ልብ ሥራ ማቆም ሊዳርግ ይችላል። ይህ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው የጠበቡ የልብ ደም ቧንቧዎች በሚገኙበት አካባቢ አንዳች ቋጠሮ ሲፈጠርና የደም ፍሰትን በከፊል ወይም በሙሉ ሲዘጋ ነው። ችግሩ ኦክስጅን ወደ ልብ እንዳይደርስ ስለሚያደርግ የልብ ጡንቻዎች እንዲሞቱ ያደርጋል። በልብ ጡንቻዎች ውስጥ የኦክስጅን እጥረት ሲፈጠር በደረት አካባቢ ከፍተኛ የማቃሰት ወይም ትንፋሽ የማጠር ስሜት ይፈጠራል፤ ይህንን ሁኔታ ቶሎ እንደአደገኛ ምልክት መውሰድ ያስፈልጋል።
ሌሎች ምልክቶች ማለትም ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና የላብ መብዛት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በድንገተኛ የልብ ሥራ መስተጓጎል ከሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሞት አደጋ ያጋጥማቸዋል። ነገር ግን የመጀመሪያ ፍንጭ ምልክቶችን አይተው ቶሎ ወደ ሕክምና ማዕከል ሄደው የሚታከሙ ሰዎች የመሻልና፣ የማገገም ሁኔታቸው ከፍተኛ ነው።
የልብ ጤና ችግር ሲያጋጥመን የሚታዩ ምልክቶች
በልብ ቧንቧዎች ላይ በሚያጋጥም መጥበብ የሚፈጠር የጤና ችግር ከሚታዩ ምልክቶች ውስጥ ከደረት ጀምሮ ወደ አንገት፣ አገጭ፣ ጀርባና የግራ እጅ የሚሰራጭ የሰውነት መዛል ነው። በዚህ ሁኔታ የሚፈጠር የልብ ችግር ደረትንና አንገትን ቀስቶ የሚይዘው በስፋት የሚታይ ነው። ይህ ምልክት በቂ ደም ወደ ልብ ጡንቻዎች እየደረሰ እንዳልሆነ የሚጠቁም ሲሆን ሕመሙም የሚፈጠረው ልብ በዚህ ምክንያት ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት ስለሚኖርባት ነው።
ቀስቶ የሚይዝ የደረት አካባቢ ሕመም አብዛኛውን ጊዜ የሚነሳው ችግሩ ያለበት ሰው በድንገት ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ሲጀምር ወይም ደግሞ ጠንካራ የሆነ የስሜት መጎዳት ሲኖር ነው።
ሕክምና
በልብ ደም ቧንቧዎች ላይ የሚያጋጥም መጥበብ ሊድን የሚችል የጤና ችግር አይደለም። ነገር ግን የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከልና መድኃኒቶችን በአንድነት በመጠቀም መቆጣጠር ይቻላል። በመሆኑም በችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ከማጨስ መቆጠብ፣ በመደበኛነት መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግና የቅባት መጠኑ በጣም ያነሰ ምግብ መመገብ አለባቸው።
የደም ኮሌስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር ሐኪም በማማከር መድኃኒቶችን መውሰድ ያስፈልጋል። እንደ ቅድመ ጥንቃቄ በሐኪም በየቀኑ የሚወሰድ አስፕሪን ሊታዘዝ ይችላል። ይህ እርምጃ ድንገተኛ የልብ ሥራ ማቆምን ሊከላከል ይችላል፤ ምክንያቱም አስፕሪን በደም ውስጥ በሚገኘው ፕሌትሌት ላይ ተፅእኖ መፍጠር ይችላል። ፕሌትሌት ማለት ከደም መርጋት ጋር ቁርኝት ያለው የደም ህዋስ ነው። ችግሩ ሲፀና የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል፤ ይህ ሁኔታ ልብን በሌላ ልብ እስከመተካት ሊሆን ይችላል።
ምንጭ፦ከሰርቫይቫል 101/Survival 101
በዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013