የአንድ አገር መንግሥት በፍጥረቱ ሉአላዊ ነው። ሙሉ በሆነ ክብሩ የሚወክለውን ሕዝብ ሁለንተናዊ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ የሕግም የሞራልም ኃላፊነት አለበት። የመንግሥት ጥንካሬ በአንድም ይሁን በሌላ የዚያች አገር ጥንካሬ፤ ድክመቱም የዚያች አገር ድክመት ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ በዘመናት መካከል የነበረና ያለ ዘመን ተሻጋሪ እውነት ነው። በቀጣይም ገዥ እውነትነቱን ይዞ የመቀጠሉ ሁኔታ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ከዚህ ጋር የተያያዘው ሌላው ትልቁ ጉዳይ የአንድ አገር እና ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከዚሁ ተጨባጭ እውነታ የሚመነጭ መሆኑ ነው።
በአንድም ይሁን በሌላ በዘመናት ውስጥ ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት የቻሉ አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን በማስከበርና የተጠቃሚነታቸውን አድማስ በማስፋት የተገቡ ብቻ ሳይሆኑ ያልተገቡ ጥቅሞች ባለቤት ሆነዋል። በሚያገኟቸው ጥቅሞች የበለጠ እየፈረጠሙ የዓለሙ ገዥ ሕግ ጉልበት የሆነበት ዓለም አቀፍ ሥርዓት ውስጥ ገብተናል።
እነዚህ በተገባም ይሁን ባልተገባ መልኩ ጉልበታቸውን አፈርጥመው ራሳቸውን የዓለም ፖሊስ አድርገው እስከ ማየት የደረሱ መንግሥታት በአንድ በኩል ራሳቸውን የበለጠ ጉልበተኛና የዓለም አቀፍ ኃይል ሚዛን ባለቤት ለማድረግ የሚሄዱበት የሴራ መንገድ የብዙ ሕዝቦችን ተስፋ የሚነጠቅ ሆኗል።
ከዚያም በላይ እነዚህ መንግሥታት ሌሎች የዓለም ሕዝቦች ጥቅማቸውን የሚያስከብርላቸው ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት የሚያደርጉትን ጥረት በማሰናከል ደካማ፣ በራሱ መወሰን የማይችል ከዚያም በላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለነሱ ጥቅም የተገዛ / ያደረ/ መንግሥት በማስቀመጥ የሕዝቦችን ጥንካሬና የጥንካሬ መንፈስን ሲሰብሩ ቆይተዋል፣ አሁንም እየሰበሩ ይገኛሉ።
በነዚህ መንግሥታት ምክንያት ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መንገድ ከፍትሀዊነትና ሰጥቶ ከመቀበል ወጥቶ በጉልበት ወደ መናጠቅ የለየለት አምባገነናዊ መንገድ ከገባም ውሎ አድሯል፣ በዚህም ከፍ ያለ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱ የሶሪያ፣ የኢራቅ፣ የየመን አገራት ሕዝቦችን መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህም ባለፈ ዲፕሎማሲው በራሱ የገበያ ሸቀጥ ሆኖ ለሎቢስቶች ከፍ ያለ ገንዘብ በመክፈልና ባለመክፈል መካከል ያለ እውነታ ሆኗል። በዚህም የተነሳ ዕውነታቸውን ተነጥቀው በገበያ መረጃ በበደላቸው ላይ ተጨማሪ የገበያ በደል የተቀበሉና እየተቀበሉ ያሉ አገራት ሕዝቦች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። የዛሬው የእኛ ፈተናም አንዱ የዚህ እውነት ተጨባጭ ማሳያ ነው።
በተለይም አፍሪካውያን ትልቅ ህልም አልመው ከፍ ያለ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው የነፃነታቸው ባለቤት ከሆኑ ማግስት ጀምሮ ራሳቸውንና ህልማቸውን የሚመስል ጠንካራ መንግሥት ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ከፍ ያለ ዋጋ ቢያስከፍላቸውም እውን ማድረግ አልቻሉም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚነታቸውን የሚያጸና ጠንካራ መንግሥት ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ገና ከጅምሩ ውስብስብ በሆኑ ሴራዎች መክነው እስከ ዛሬ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ መድረክ ፍትሀዊ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን አቅም አጥተው ከጠባቂነት መውጣት ሳይችሉ ቀርተዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያንም ብንሆን የረጅም ዘመን የመንግሥት ታሪክ ባለቤት የሆነውን ያህል፤ ለነፃነታችን ካለን ቀናዊነት ብዙ ዋጋ ከፍለን ነፃነታችንን አስከብረን ዘመናትን መሻገር ብንችልም ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት ያደረግናቸው ጥረቶች ግን በምንፈልገው ደረጃ ስኬታማ ሆኖ ማየት አልቻልንም።
በአንድ በኩል የማህበረሰባችንን እሴቶች መሠረት ያላደረጉ የተውሶ አስተሳሰቦችን በሥልጣን ለመቆየት የሚቃርሙ፣ ከዚያም በላይ ከአገርና ከሕዝብ ተጠቃሚነት ይልቅ በቡድን ተጠቃሚነት ሁለመናቸው የተያዙ ቡድኖች ወደ ሥልጣን መምጣታቸው ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት ያደረግነውን ጥረት አምክኖታል።
ቡድኖቹ በአንድም ይሁን በሌላ የሄዱበት መንገድ ጠንካራ መንግሥት ፈጥረን ብሔራዊ ጥቅማችን ማስጠበቅ እንዳንችል ሌት ተቀን በሚሰሩ ኃይሎች ሴራ ተጠልፎ የሥልጣን ዘመናቸውን በሕዝብ ጥቅም ዋጅተው መጥተው፤ ሄደዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ይህንን እውነታ ለመቀልበስ በሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። የጠንካራ መንግሥት ግንባታ የነገ ተስፋችን አልፋና ኦሜጋ መሆኑን በአግባቡ ተገንዝበን ጠንካራ መንግሥት በመመስረት ሂደት ውስጥ እንገኛለን።
የጠንካራ መንግሥት ግንባታ ከጠባቂነትና ከመጣንበት የጉስቁልናና የልመና ሕይወት እንደሚዋጀን አምነን ከዚያም በላይ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ጠንካራ መንግሥት መስርተው የሄዱበት መንገድ ታላቅ አገር መፍጠር እንዳስቻላቸው ከራሳችን የትናንት ታሪክ መረዳት ችለናል።
ከትናንት ታሪካችን በመነሳትም ዕጣፈንታችን በራሳችን መቅረጽ እንደምንችል በተጨባጭ ተረድተናል። ይህንን መረዳታችንን ሊወስድብን የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ አቅም እንደማይኖር ለተስፋችን ካለን ቁርጠኝነት እርግጠኛ ሆነናል። ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ተነስተን ነው እጃችሁን ከሉዓላዊነታችንና ከውስጥ ጉዳያችን ላይ አንሱ የምንለው።
እጃችሁን አንሱ የምንለው እንደ አገርና እንደ ሕዝብ እጃችሁ በምንም ዋጋ በማንደራደርበት የእኛና ከእኛም በላይ የመጪው ትውልድ ተስፋ ላይ የተጫነ በመሆኑ ነው። ጫናችሁ የቱንም ያህል አቅም የሚፈታተን ቢሆን፤ ካየነው ብርሃንና ብርሃኑ ከፈጠረልን ተስፋ ሊበልጥ አይችልም። ከጀመርነውን ራሳችንን የመሆን መንገድም አያስቆመንም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013