በዘመነ ደርግ በ1960ዎቹ መገባደጃ አብዮቱ በተፋፋመበት ጊዜ ከውስጥ አብዮቱን ቦርቧሪ የተባሉት የደርግ ተቃራኒ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ከውጭ ደግሞ የሶማሊያ ወራሪ፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም (በደርግ አጠራር) ወዘተ… ደርግን በተፈታተኑበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት ነጋዴዎች በአገሪቱ የበርበሬ ዕጥረት እንዲፈጠር በመጋዘን በማከማቸትና በመሰወር ህብረተሰቡን ለችግር ዳርገው መንግሥትን መኮነን በመጀመራቸው በነጋዴዎች መጋዘን ውስጥ አሰሳ ተካሂዶ ደብቀው የተገኙ የመርካቶ ነጋዴዎች አሻጥረኛ ተብለው አፋጣኝ አብዮታዊ እርምጃ ተወሰደባቸውና መቀጣጫ ሆኑ፡፡ በዚያን ጊዜ አብዮታዊ እርምጃ ማለት የሞት ብይን ማለት ነው፡፡
በዚያው በደርግ ዘመን ሽሮሜዳ አካባቢ የሚገኝ አንድ ዳቦ ቤት የተባይ ማጥፊያ ዲዲቲ ከዳቦ ዱቄት ጋር በመቀላቀል ዳቦ ተጋግሮ ለተጠቃሚዎች በመሸጡ ጠዋት ዳቦ ቤት ደጃፍ ተሰልፈው ገዝተው የተመገቡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፍተኛ ህመም ተዳርገው በየካቲት 12 እና በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል በህክምና ክትትል ውስጥ እንደነበሩና የዳቦ ቤቱ ባለቤትና ሠራተኞቹ በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ይህ ድርጊታቸው «አሻጥር » ተብሎ ነበር፡፡
«አሻጥር» /Sabotage/ ማለት ተንኮል፣ ሸር፣ ደባ ማለት ሲሆን፤ ለመጉዳት የሚፈለግን አካል ዕቅድ ለማሰናከል የሚከናወን መሰሪ ተግባር ነው፡፡ ይህንን ትርጉም ከያዝን በጥልቀት ወደ ውስብስቡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሻጥር ሳንዘልቅ እንዲያው ላይ ላዩን እንመልከተው፡፡
ኢትዮጵያ በየትኛውም የመንግሥት አስተዳደርዋ ውስጥ ይብዛም ይነስም ለሕዝቡ ይበጃል የተባሉ የኢኮኖሚ መስክ እንቅስቃሴዎች ለመግታት ሳይታክቱ የሚሰሩ ነጋዴዎችና የተወሰኑ የመንግሥት አመራሮች ያልተከሰቱበት ጊዜ የለም፡፡
የውጭና የአገር ውስጥ ገንዘብን ዝውውር ማገድ፣ ወደ ከተማ የሚገቡ ምርቶችን ማገድ፣ በርበሬን ከሸክላ እንዲሁም ከቀይ ሥር ጋር፣ ጤፍን ከአፈርና ከብጣሪ፣ ከጄሶና ከእንጨት ፍቅፋቂ /ሰጋቱራ/፣ የምግብ ዘይትን ከአደገኛ ዕፅዋት፣ ቅቤን ከሙዝና ከከብት ሞራ፣ የታሸጉ ጭማቂ መጠጦችን ከውድቅዳቂና ከበሰበሱ አትክልቶች፣ ቤንዚንን ከናፍጣ ጋር በማቀላቀል፤ ለዚሁ መጥፎ ድርጊታቸው ሠራተኞችን በመቅጠር፣ ስውር የሥራ ቦታ በማዘጋጀትና ለሽያጭ በማቅረብ በወገኖቻቸው ጉዳት፣ ህመምና ሞት ኑሮአቸውን ሲያደላድሉ የነበሩ አሻጥረኛ ነጋዴዎች ተከታዮቻቸውን እያፈሩና በእነርሱ እኩይ ተግባር ታንፀው አድገውና አቅማቸውን አፈርጥመው ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡
የራሳቸውን ወገኖች ከምንም ሳይቆጥሩ ለግል ጥቅማቸው ብቻ የሚያስቡ ነጋዴዎች ህዝቡን ለከፋ ችግርና ፍዳ አብቅተው ሕዝቡ መንግሥትን በቅሬታ ዓይን እንዲመለከትና በዓይነ ቁራኛ እንዲተያዩ ማድረግ ዓላማቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ መንግሥትና ሕዝብን ለማቃቃር ሲባል በኢኮኖሚ ላይ የሚፈፀም አሻጥር ማለት፡፡
ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ባልተከተለ ሁኔታ መበልፀግን ዓላማ አድርገው የተነሱ ነጋዴዎችና ረዳቶቻቸው ይህን እኩይ ተግባር የሚፈፅሙት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማቀጨጭ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማሰብ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያማረር ማድረግ ሲሆን፣ ላቅ ሲልም ህዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው በማድረግ ወደአልተገባ ግጭትና እልቂት ለመውሰድ ያለመ ነው፡፡
አሻጥረኞቹ ሸቀጦችን ደብቆ ህዝቡ በሚፈልገው ጊዜ እንዳያገኝ በማድረግ ህዝቡን ላልተፈለገ ወጪ በመዳረግ በመንግሥት ላይ ማነሳሳት፣ ህገወጥ የሆነ የገበያ ሥርዓትን ባለመከተል መንግሥት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ማሳጣትና የአገሪቱን እድገት ወደኋላ መጎተት ዓላማቸው ነው፡፡
ይህ የኢኮኖሚ አሻጥር አንድ መልክ ሲሆን፣ የፖለቲካ አሻጥር ደግሞ ሌላው የከፋው ገፅታ ነው፡፡ ይህ የከፋ የተባለው የፖለቲካ አሻጥር ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች ቢኖሩትም የአሻጥሩ መጨረሻ ግቡን የሚመታ ከሆነ ውጤቱ እርስ በርስ መበላላት እንጂ አሸናፊና ተሸናፊ ሊኖር የማይችልበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
ከፖለቲካ አሻጥሮች መካከል ተቀናቃኞችን ለማጥፋት፣ ለማጣላት፣ ለመበታተን የሚሸረብ ደባ፣ ተቃራኒ ቅስቀሳ ማድረግ፣ በፓርቲ አመራሮች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ ማድረግ፣ ምስጢርን መሰለል፣ ስብሰባዎችን ማስተጓጎል፣ ተቃራኒን ለማጥፋት ነፍሰ ገዳይ መቅጠርና ማሰማራት፣ ባንዳ ሆኖ ማገልገል፣ በህዝቦች መካከል ጊዜ ጠብቆ ሊነሳ የሚችል ቅራኔን አዳፍኖ ማስቀመጥ፣ አገርንና ህዝብን የሚጎዳ ድብቅ ስምምነት ማድረግ፣ ነባር ታሪክን ለማጥፋት አቅዶ መነሳት ወዘተ… በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የሚታዩና ተባብሰው የቀጠሉ የኢኮኖሚም ሆኑ የፖለቲካ አሻጥሮች ህብረተሰቡ በከፍተኛ ተጋድሎ ሊያስወግዳቸው ካልቻለና በቸልታ የሚያልፋቸው ከሆነ ለዘመናት በመልካም የታሪክ ሁነቶች ዳብሮ የቆየው አብሮነታችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጋረጠብን ትልቅ ፈተና አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ይሆናል፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት እየተጓዝንበት ያለው የዴሞክራሲ ጎዳና፣ ለብዙ ዓመታት ለመራራቃችን ምክንያት የሆነው ድባብ የተገፈፈበት የመስዋዕትነት ፍሬ እንዲከስም ሊያደርጉ የሚችሉ ነጻነትንና ሥርዓት አልበኝነትን ባለመለየት የሚከናወኑ፣ ሕግና ሥርዓትን የጣሱ እንቅስቃሴዎች ሊገቱ ይገባል።
በቅርቡ ያስተናገድናቸው የሥርዓተ አልበኝነት ውጤት የሆኑ የጅምላ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ንብረት ማውደምና ዝርፊያ እርስ በርሳችን ቂም የሚያያይዙና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈታተኑ ናቸው። በህግ የበላይነት የማይመራ ህብረተሰብና አገር ዕጣ ፋንታው የሰላም ኑሮው ተናግቶ ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተስፋፍቶ፣ ግጭት፤ መጠፋፋትና በስተመጨረሻም መበታተን ይሆናል፡፡ ስለዚህም የአሻጥርኞች ሴራ በህግ የበላይነት ሊሸነፍ ይገባዋል፡፡