
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ11 ወራት 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በ2017 ዓ.ም 11 ወራት 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የፍራፍሬ ምርቶች ለገበያ ቀርበዋል፤ ከእነዚህም ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የሙዝና የአቮካዶ ፍራፍሬ ምርት ነው ብለዋል።
በክልሉ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ ተክል የተሸፈነ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ ከ80 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በሙዝ ተክል እንደተሸፈነ እና ይህም ከመስኖ ሥራ ውጭ የሚለማ እንደሆነ አስረድተዋል።
በክልሉ ያለው እምቅ አቅም የአቮካዶ ምርት እንደሆነና በዚህም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አቶ አሸናፊ አስረድተዋል። በተለይም ምርጥ ዘር ከመለየት እና በዘመናዊ መንገድ ከማምረት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አንድ አርሶ አደር ዘመናዊ ባልሆነ መንገድ አቮካዶ እያመረተ እስከ ሦስት መቶ ኩንታል ምርት ድረስ ወደ ገበያ አውጥቶ ይሸጣል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ይህ በዘመናዊ መንገድ ቢታገዝ የምርት መጠኑ እጅግ በጣም ይጨምራል፤ በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይኖረዋል ሲሉ አመልክተዋል።
ምርትን ከማዘመን እና ከማሳደግ አንጻር በክልሉ በ25 ወረዳዎች ፌዴራል መንግሥት በአቮካዶ ምርት ላይ ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የአቮካዶ ተክል የማሳ ሽፋን 30ሺህ ሄክታር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ክልሉ ካለው አቅም አንጻር በጣም ትንሽ የሚባል እንደሆነና የማሳ ሽፋኑን በአምስት ዓመት 150 ሺህ ሄክታር መሬት ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በክልሉ የሚመረተው የአቮካዶ ምርት በዘመናዊ መንገድ ባለመመረቱ ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችል በቂ መረጃ የተሟላለት እንዳልሆነም ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር በስፋት እየቀረበ ያለው ለሀገር ውስጥ ዘይት ፋብሪካዎች መሆኑን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ በቀጣይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማብዛት እና በዘመናዊ መንገድ በማምረት ለውጭ ገበያ የመላክ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በክልሉ ከደጋ ፍራፍሬዎች ውጭ ሁሉም የፍራፍሬ አይነቶች በስፋት እንደሚመረቱ ገልጸው፤ በ11 ወራት ለገበያ ከቀረቡት ፍራፍሬዎች ሙዝ፣ አቮካዶ፣ፓፓያ፤ አናናስ እና ሌሎች የፍራፍሬ አይነቶች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም