ተማሪዎች የክረምቱን ጊዜ ከትምህርት ዝግጅት ባሻገር ተሰጧቸውን ለማዳበር እንዲጠቀሙበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡-ተማሪዎች የክረምቱን ጊዜ ለቀጣዩ ክፍል ዝግጅት ከማድረግ ባሻገር ተሰጧቸውን ለማዳበር እንዲጠቀሙበት የወላጅ፣ ተማሪ ፣ መምህር ህብረት (ወተመ)አባል ምክር ሰጡ።

የራዕይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የወተመ ፀሐፊ አቶ ተመስገን ሰይፉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የክረምት ወራት ትንሽ ቢመስልም ተማሪዎች ከሠሩበት ሊጠቀሙበትና እውቀታቸውን ማዳበር የሚያስችላቸው ነው። ተማሪዎች ክረምቱን ተሰጧቸውን በማዳበር እና በቀጣዩ የትምህርት ክፍል ላይ ዝግጅት በማድረግ እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመሥራት ቢያሳልፉ በርካታ ጠቀሜታዎችን ያገኛሉ ብለዋል።

እንደ አቶ ተመስገን፤ ተማሪዎች የ2017 ዓ.ም ውጤታቸውን በመመልከት፤ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡበትን ለቀጣይ ጥሩ ውጤት ለማምጣት፤ ጥሩ ውጤት ያመጡበትንም ይበልጥ ለደረጃ ለመወዳደር የክረምቱ ወራት ከወዲሁ ዝግጅት ለማድረግ የሚረዳ ወርቃማ ጊዜ ነው ሲሉ አመላክተዋል።

ወላጆችም የልጆቻቸውን ተሰጥኦና ዝንባሌ በትኩረት መገንዘብ እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ ውጤታቸውን በመመልከት ይበልጥ እገዛ በሚያስፈልግበት የትምህርት ዓይነት ላይ ማገዝ እንዲሁም ልጆች ሳይጨነቁ ዕውቀት እንዲይዙ እና ውጤት ማምጣት እንዲችሉ መንከባከብ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

ዕረፍት ተገኘ ተብሎ የልጆችን አዋዋል እና የጊዜ አጠቃቀም ቸል ማለት ልጆችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመራቸው እንደሚችል ጠቅሰው፤ ወላጆች ቁጥጥር ቸል በሚሉበት ጊዜ ልጆች መስመራቸውን ስተው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመሩ ቁጥጥር ወሳኝ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

መስከረም ላይ ለትምህርት ዝግጁ የሆነ አዕምሮ እና ውጤታማ ልጅ ለማግኘት ክረምቱን ዕውቀትና መጠነኛ የአካል ጥቅም ያለው ጨዋታ ለልጆች ያስፈልጋል ብለዋል።

በየትምህርት ቤቱ ለግማሽ ቀን የሚሰጥ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ለቀጣይ ክፍል እንዲዘጋጁ እጅግ የሚጠቅም እና የልጆች አእምሮ ትምህርት ላይ እንዲያተኩር የሚያግዝ እንደሆነም ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ የ7ኛ እና የ5ኛ ክፍል ተማሪዎች ናታን አንተነህ እና ብሩክ አስናቀ በበኩላቸው፤ የክረምቱን ጊዜ ለቀጣይ የትምህርት ዘመን የተወሰነ ዝግጅት በማድረግ እንዲሁም በአካል ብቃት ስፖርት ለማሳለፍ  ማሰባቸውን በመጥቀስ፤ በዋናነት ከወላጆቻቸው ጋር የመንፈሳዊ መዝሙር ለመማር ማሰባቸውን ተናግረዋል።

በኮከበ ፅባሕ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ተስፋ ሰለሞን በበኩሉ፤ በ2017 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን ገልፆ፤ ለዚህም ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ትምህርቱን ይከታተል እንደነበር  እና በአግባቡ ትምህርት መከታተሉ ውጤማ እንዳደረገው ተናግሯል።

ተማሪው፤ ለክረምት ወራት ፕሮግራም ማውጣቱን በመግለፅ ለቀጣይ ክፍል የሚሆን የክረምት ትምህርት በመማር እና በጣም የሚወደውን የእግር ኳስ ስፖርት ጊዜ ሰጥቶ በመጫወት እንዲሁም ከቤተሰቦቹ ጋር ጥሩ የእረፍት ጊዜ ለማሳለፍ ማቀዱን ገልጿል።

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You