
አዲስ አበባ፡- ጫና በማሳደር ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ቅኝ ሊገዙና ሊያስተዳድሩ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችን እቅድ ማክሸፍ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባዋ ከ900ሺ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የቱሉ ጎዶ ሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ትናንት መርቀው በከፈቱበት ወቅት ፣ ‹‹የተፈጥሮ ሀብታችንን እንዳንጠቀም ሁልጊዜም የውጭ ሃይሎች በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ ለማሳደር ጥረት ያደርጋሉ፣ በእጅ አዙር ቅኝ ሊያስተዳድሩንና ቅኝ ሊገዙን ይፈልጋሉ›› ብለዋል፡፡
የውጭ ኃይሎቹ ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳረፍ አገራዊ እቅድን ለማደናቀፍና ኢትዮጵያውያንን ለማሳነስ እርብርብ እያደረጉ ናቸው ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች፤ ሕዝቡ ውስጣዊ ልዩነቶችን በመተው አንድነትን ማጠናከር፣ መደማመጥና ከመንግስት ጎን በመቆም ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የጥቃት እቅድ ማክሸፍ እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡
ለአባቶቻችን የኢትዮጵያን ነጻነት ማስጠበቅ ከባድ ዕንዳልነበር ያመለከቱት ምክትል ከንቲባ አዳነች ፤ ኢትዮጵያ ተደፈረች ሲባል ኢትዮጵያዊያን የነበራቸውን ልዩነት ወደ ጎን ትተው በጋራ ለነጻነት መሰለፋቸውንም አስታውሰዋል። የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን ፈለግ በመከተል በአንድነት ለኢትዮጵያ ነጻነት በጋራ በመቆም ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሰሪ ትውልድ መሆን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
በ2013 በጀት ዓመት ከተማ አስተዳደሩ አንድ ሺ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ማድረጉን አስታውሰው፤ ይህም የከተማውን አማካይ ፕሮጀክት አፈጻጸም ከሁለት እጥፍ በላይ ያሳደገ ነው ብለዋል፡፡ የቱሉ ጉዶ ሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚህ አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በቀን 100ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመጨመር ታቅዶ እንደነበር አመልክተው፤ እስካሁን ድረስ በቀን 90ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማልማት መቻሉን የገለጹት ምክትል ከንቲባ አዳነች፣ ቀሪው 10ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀጣይ ወራት ለአገልግሎት እንደሚበቃም አስታውቀዋል፡፡ ውሃን በአግባቡ በመጠቀም ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
የቱሉ ጉዶ ሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ሲሆን ፣የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዕለታዊ የውሃ ማምረት አቅምን ከ574 ሺህ ሜትር ኪዩብ ወደ 664 ሺህ ሜትር ኪዩብ መሳደጉም በመቅቱ ተነግሯል፡፡
ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት ሲገባ በአቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ፕሮጀክቱ በተገነባበት አካባቢ የሚገኙ 900 ሺ የሚገመቱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም