አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የእርሻ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በአነስተኛ መሬት ላይ ነው። ከዚህም አልፎ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተለይም ትራክተር እና የተለያዩ ጊዜ እና ጉልበት የሚቆጥቡ ማሽነሪዎችን የሚጠቀሙትም ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ ነው። በሆርቲካልቸር ዘርፉም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ የተሰማሩ አልሚዎች ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ የተለያዩ የአሠራር ችግሮች እንዳሉባቸው እሙን ነው። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በየዓመቱ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት ጉዳይ ነው።
በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ የተቋቋመው የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ ግብአት በማቅረብ፣ የተሻሻሉ የአስተራረስ ዘዴዎችን እና ዘመናዊ አሠራሮችን በማስተዋወቅ ረገድ በዋናነት ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ይገኛል። እኛም ከግብርናው በተለይም ከሆርቲካልቸር ዘርፉ ጋር ተያይዞ የተከናወኑ ሥራዎች፣ ለአርሶአደሩ የቀረቡ ግብአቶች እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በተከናወኑ ሥራዎች ዙሪያ የግብርና ሚኒስቴር የሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ከሆኑት አቶ ወንዳለ ሃብታሙ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– የዘንድሮው የመኸር እና በልግ እርሻ ሥራዎች በምን ደረጃ ላይ ናቸው?
አቶ ወንዳለ፡– የዘንድሮው መኸር እርሻ አርሶአደሮችን እና ከፊል አርሶ አደሮችን ብቻ ሳይሆን አርብቶ አደሮችን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራበት ነው። ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና እና ሆርቲካልቸር ልማት ሥራ ምቹ ነበር።
እርጥበት መገኘቱ መሬቱን ለማረስ ብቻ ሳይሆን ለመስኖ ልማት የሚያስፈልጉ የውሃ አካላትንም አቅም ጨምሯል። ስለዚህ ዝናቡ በመስኖም ሆነ በመኸር ልማት ሥራችንን እንድናከናውን እየረዳን ይገኛል። በተለይ እኔ የምመራው የሆርቲካልቸር ዘርፉ ደግሞ በመስኖ ውሃም ሆነ በመኸር የሚለማ እንደመሆኑ መጠን የተሻለ ለማምረት የሚያስችል ሥራ ተከናውኖበታል።
በደጋፊ መስኖ፣ በበልግ፣ በመኸርና በበጋ መስኖ በአጠቃላይ በሆርቲካልቸር ዘርፉ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም አበባ ምርት ረገድ ጥሩ ምርት ተገኝቷል። የመኸሩ ዝናብ እንደወጣ የተወሰነ እርጥበት ይኖራል፤ ያንን ደግሞ ለማልማት ጥቂት የመስኖ ውሃ ነው የሚፈልገው። በመሆኑም ከመኸር ዝናቡ የተገኘውን ውሃ ከወንዞች አሊያም ከተለያዩ ወራጆች ጠልፎ ወደእርሻ መሬት በማስገባት የምናለማበት መንገድ ነው «ስፔት ኢሪጌሽን» ወይም ደጋፊ መስኖ የምንለው። በነዚህ የተለያዩ የግብርና አማራጮች በርካታ አትክልቶች ለምተዋል።
ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አንድም ማሳ ጦሙን ማደር የለበትም በሚል ኮቪድን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተገኘው ክፍት ቦታ ሁሉ የግብርና ሥራ እንዲከናወን አነሳስተዋል። ከዚህ በመነሳት እንደአገርም በግለሰቦች ደረጃም ቢሆን የግብርና ውጤቶችን በሰፊው እንዲመረቱ ስንሰራ ቆይተናል።
አዲስ ዘመን፡– ከግብርና ሥራዎች ጋር በተያያዘ በተከናወኑ ሥራዎች ምን ያክል ውጤት ተገኘ፤ በተለይም ከእቅዶቻችሁ ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸማችሁ ምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ወንዳለ፡– በደጋፊ መስኖ ልማት በ2013 በጀት ዓመት 358 ሺህ ሄክታር መሬት እናለማለን ብለን ነበር ያቀድነው። ይህ ውጥን እንግዲህ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የግብርና ዘርፉን ሥራ እንዳያስተጓጉል በሚል የጥንቃቄ እርምጃዎችንም ታሳቢ አድርገን የተዘጋጀ ነበር።
አሁን ባለው አፈጻጸም ግን በሆርቲካልቸር ዘርፉ በ10 ወራት ውስጥ ብቻ በደጋፊ መስኖ ሥራ 385 ነጥብ 5 ሺህ ሄክታር መሬት አልምተናል። ይህም ከእቅዱ አንጻር 107 በመቶውን ማሳካት እንደተቻለ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ በበልግ ዝናብ አማካኝነት 382 ነጥብ 8 ሺህ ሄክታር መሬት በሆርቲካልቸር ዘርፍ ለማልማት አቅደን፤ 387 ሺህ መሬት ነው ያለማነው ይህም ከእቅዱ አንጻር 101 በመቶ ነው። ዝናብ በተገኘበት አጋጣሚ ሁሉ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የአትክልት ምርቶችን በማምረት ለአካባቢ ገበያ እና ለአርሶአደሩም ለእራሱ የምግብ ግብአት የሚጠቀምበት ዕድል ተፈጥሯል።
ከደጋፊ መስኖ እና በልግ ዝናብ ባለፈ በመኸር እርሻ ሌሎች ሰብሎች እንደሚዘሩት ሁሉ በክረምት ወቅት ሽንኩርት፤ ቲማቲም እና ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮችን የሚጠቀሙ በርካታ አርሶአደሮች አሉ። በሆርቲካልቸር ዘርፉ ዘንድሮ 603 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደን በ10 ወራት ውስጥ ብቻ 639 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት ችለናል።
በሆርቲካልቸር ዘርፍ በዋናነት በመስኖ ውሃ ብቻ ተጠቅመን 577 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደን ነበር፤ በ10 ወራት ውስጥ 766 ሺህ ሄክታር መሬት ነው ያለማነው። የመስኖ ልማቱ በተለየ መልኩ 132 በመቶ አፈጻጸም የታየበት ነው። ከደጋፊ መስኖ 47 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ይገኛል ብለን ውጥን ይዘን የነበረ ቢሆንም እስካሁን 50 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ከፍተኛ ምርት ተገኝቷል።
በበልግ ወቅት ደግሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ ዝናቡ ጥሩ ስለነበር አርሶአደሩ ለሆርቲካልቸር ልማት የሚውሉ በርካታ መሬቶችን አርሷል። በዚህም 70 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል፤ ይህም ውጤታማ ነበር። በመኸር ደግሞ 63 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል እናገኛለን ብለን አቅደን 58 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል አግኝተናል፤ ይህም ከእቅዱ 92 በመቶ ነው።
የመኸር ምርቱ ከሌላው በተለየ ከእቅዱ ያነሰበት መሠረታዊ ምክንያት ምርቱ እስከ ሰኔ ወር ድረስም የሚቀጥል በመሆኑ ያልተሰበሰቡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችም በመኖራቸው ነው። ማሳ ላይ ያለው የመኸር ምርት ሲሰበሰብ እና የሁለት ወር ሪፖርት ሲጠናቀር ከእቅዱ በላይ ውጤት እንደሚገኝ ይታመናል።
አዲስ ዘመን፡– እንደአገር ከሚመረተው የአትክልትና ፍራፍሬ መካከል ምን ያክሉ ለአገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል?
አቶ ወንዳለ፡– በአብዛኛው በኢትዮጵያ የሚመረተው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ነው የሚውለው። በአገር ውስጥ ከሚመረተው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት 97 በመቶ የሚሆነው ለአገር ውስጥ ፍጆታ ይቀርባል።
ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት አገር እንደመሆኑ መጠን በርካታ የአትክልትና ፍራፍሬ ፍጆታ እንደሚያስፈልገን ማወቅ ያስፈልጋል። ወደውጭ አገራት የሚላከው የሆርቲካልቸር ምርት ሦስት በመቶው ብቻ ነው፤ ከዚህ ውስጥም አራት አምስተኛውን እጅ የሚይዘው የአበባ ምርት ነው። በዚህ ምክንያት ሰፊውን የሆርቲካልቸር ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገባው የአበባ ምርት ነው። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው በርካታ ሕዝብ የአገር ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ አብዛኛው ምርት ወደውጭ አገራት የሚላክ ይመስለዋል።
የአበባ ምርትም በጥሩ ሁኔታ ከተዘጋጀ በዓለም ላይ ጥሩ ገበያ ይገኛል። እንደዚያም ሆኖ ግን አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአበባ ማምረቻ ከ1 ሺህ 30 ሄክታር በላይ አይደለም። አበባ እርሻ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ መሬት የያዘ ሊመስለን ይችላል፤ ይሁንና በዚህች አነስተኛ መሬት ላይ ጥራት ያለው አበባ አምርተን በመላክ ነው ከአፍሪካ ሁለተኛ ከዓለም ደግሞ ከኢኳዶር፣ ኔዘርላንድ እና ኬንያ ቀጥለን በአራተኛ ደረጃ የያዝነው።
በአበባ እርሻዋ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ባለፈም ደግሞ ለ200 ሺህ ወጣቶች ሥራ ተፈጥሯል። ሥራውም ከዘር ዝግጅት አንስቶ እስከ ምርት ለቀማ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ከዘርፉ ከሚገኘው ምርት አብዛኛው ለአገር ውስጥ መቅረቡ ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥ ዜጎች ዘላቂ ሥራ በመስጠት ረገድ ትልቅ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– የኮቪድን የእንቅስቃሴ ገደብ ተጽእኖ በመቋቋም የግብርና ምርት በተለይም በሆርቲካልቸር ምርቶች የወጪ ንግድ ላይ ምን ሰራችሁ፤ ከዘርፉስ ምን ያክል ገቢ ተገኘ?
አቶ ወንዳለ፡– በኤክስፖርት ሥራችን ከአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ወደውጭ አገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል። ኮቪድ-19 በሽታ ዓለምን እየናጠ ባለበት ወቅት በርካታ አገራት በራቸውን ዝግ አድርገው መቀመጣቸው ይታወቃል፤ የጥንቃቄ እርምጃዎቹም የወጪ ንግድ እንዲስፋፋ የሚያበረታቱ አይደሉም፤ ይህ ሁሉ እያለ ግን ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ጥሩ እየሰራች ነው።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ባለን መልካም ግንኙነት በጋራ እየሰራን ይገኛል። አየር መንገዱም ለሆርቲካልቸር ምርቶች በተለይ የአየር ጭነት አገልግሎት ዋጋ ላይ ማስተካከያ አድርጎ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች በመላው ዓለም በማድረስ ላይ ይገኛል። በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ባለፉት 10 ወራት ብቻ 433 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
ይህ ቀላል ውጤት ተደርጎ የሚቆጠር አይደለም። ምክንያቱም በከፍተኛ ሁኔታ ምርቶቻችንን የሚቀበሉ አገራት በኮቪድ በሽታ ክፉኛ ተጠቅተው ነበር። ስፔን፣ ኔዘርላንድ ፣ እንግሊዝ እና ስካንዴኔቪያን አገራትን ጨምሮ የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንቅስቃሴ እስከመገደብ ያደረሰ ክልከላን ተጠቅመው ነበር።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ምርት በብዛት የሚቀበሉ እንደተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ሌሎች የአረብ አገራት ላይ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ችግሮች ነበሩ። ኢትዮጵያ ግን የአየር መንገዷ የጭነት አገልግሎት ጥሩ ስለነበር ችግሮችን ተቋቁሞ የሆርቲካልቸር ምርቶችን በብዛት ለመላክ ጥረት ተደርጓል። በቀጣይ ሁለት ወራት የሚገኘው ገቢ ሲጨመርበት ደግሞ ከዚህም በላይ በዓመቱ መጨረሻ እንደሚገኝ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡– የቋሚ ተክሎች ችግኝ ማፍላት እና አጠቃላይ የዝግጅት ሥራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ወንዳለ፡– በኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከሚሰጡት ጥቅም ባለፈ የገቢ ምንጭ የሚሆኑ ተክሎችንም በብዛት ማልማት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ጋር ተያይዞ ባለፈው 10 ወራት ብቻ 60 ሚሊዮን ቋሚ ተከሎች ማለትም የአቮካዶ፣ ማንጎ ፣ ፓፓያ እና ሌሎችም ችግኞች ተተክለዋል።
በቀጣይ የክረምት ወቅት ከዚህ ባለፈ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቋሚ ምርት የሚሰጡ ተክሎች በየክልሎቹ እንዲተከሉ ይደረጋል። ለዚህም የሚሆን የችግኝ ዝግጅት ሥራ በአራቱም አቅጣጫ እየተከናወነ ይገኛል። የችግኞቹ ቁጥር በርካታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ቁጥራቸውን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው። በኢትዮጵያ ተራራዎች እና የማይታረሱ ቦታዎች ላይ የሚተከሉ ችግኞች በብዛት የፍራፍሬ ምርት የሚሰጡ እንዲሆኑ ታስቦ እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያ ከዛሬ 60 እና 70 ዓመት በፊት ከቆዳ ሽፋኗ 40 በመቶ የሚደርስ ደን ነበራት። ብዙ ደን መኖር ብቻ ግን ሃብታም አያደርግም። ዋጋ የሚያስገኝ እና ዘላቂ ገቢ የሚያመነጭ ተክል ሲኖር ነው ደንም የበለጠ ጥቅም የሚሰጠው የሚል እምነት አለ። በገበያ ላይ ዋጋ ያላቸው እንደ ብርቱካን፣ አፕል፣ ፓፓያ እና የመሳሰሉትን የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ተክሎች ደኖቻችን ውስጥ በቋሚነት ማልማት ስንችል አገራችንም አረንጓዴ እያደረግን በተመሳሳይ ተራሮቻችንን የገቢ እንዲሁም የምግብ ምንጭ እንደርጋቸዋለን።
በዚህ ጉዳይ በንቃት እየሰራን ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በአግባቡ የሆርቲካልቸር ሥራው ከተሰራ በአረንጓዴ አሻራ ልማት ሀብት የማንፈጥርበት ምክንያት አይኖርም። አንዳንዶቹ ቋሚ ተክሎች ውጤታቸው ከሦስትና አራት ዓመታት በኋላ የሚታይ ነው፤ በዚያ ጊዜ የተከልናቸው ፍሬ መስጠት ሲጀምሩ አገራችንም በዓለም ገበያ ላይ የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ እንዲሁም ለአገር ውስጥ ፍጆታ የተሻለ ምርት የሚገኝባቸው እንደሚሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– ከግብርና ግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የጸጥታ ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች በምን መልኩ አስፈላጊ ግብአቶችን እያደረሳችሁ ነው?
አቶ ወንዳለ፡– አሁን ባለው ሁኔታ የጸጥታ ችግሩ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይኖራል። እንደሚታወቀው ግን የጸጥታ ችግር የሚፈጥሩ አካላት አንድ ቀበሌ ወይም ወረዳ ተቆጣጥረው አይደለም የሚገኙት፤ እራሳቸውን ደብቀው ነው ጥቃት የሚፈጽሙት።
በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግሮች ቢያጋጥሙም የግብርና ግብአት እንዳናደርስ ግን ያስተጓጎለን አጋጣሚ አልነበረም። አስፈላጊ የጸጥታ ጥበቃ ተደርጎ ግብአቶችን ማድረስ ችለናል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ትግራይ ክልልም ጭምር የተጠየቀውም የማዳበሪያም ሆነ ሌሎች የግብርና ግብአቶችን በሙሉ አድርሰናል።
እንደአጠቃላይ የጸጥታ ችግር በአገሪቷ የለም ማለት ሳይሆን፤ ያን ያክል ሥራችን ላይ እክል ፈጥሯን ብለን የምናነሳው ዓይነት የጸጥታ ሁኔታ ግን የለም። ያለውን ችግር ተቋቁመነውም ቢሆን በየቦታው ያሉ የግብርና መዋቅሮቻችን ሥራቸውን በማከወን ላይ ናቸው።
የሆርቲካልቸር ልማት ሲያድግ እና ምርት ሲጨምር በዚያው ልክ የግብአት አቅርቦቱም ጨምሯል። ባለፉት 10 ወራት 730 ሺህ 293 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር ተጠቅመናል። ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ደግሞ ማዳበሪያ ተጠቅመናል። አሁን ባለው ሁኔታ ለሰው ጤና ጎጂ አለመሆናቸው የተረጋገጡ 206 ሺህ ሊትር የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል እንዲሁም በዱቄት መልክ የሚረጭ 145 ሺህ ኪሎግራም ኬሚካል ተጠቅመናል።
ይህም ምርቶች በተባይና በበሽታ ተጠቅተው እንዳይበላሹ የእራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። በተመሳሳይ በሁሉም አካባቢዎች የግብርና ግብአት ለጠየቀ ሁሉ በተገቢው ሁኔታ እያቀረብን ይገኛል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎችም የተገኘውን እርጥበት በመጠቀም የግብርና ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ የኬሚካል እና ሌሎች ግብአቶች ያለምንም እክል በተገቢው ቦታ ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይ ክልል አርሶአደሩ እንዳያርስ ችግር እየተፈጠረበት ነው የሚል ቅሬታ የሚያነሱ አካላት አሉ፤ በአካባቢው የጸጥታ ችግር እንዳለ ሆኖ አርሶ አደሩ በምን ሁኔታ ነው የግብርና ሥራ ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው?
አቶ ወንዳለ፡– በትግራይ ክልል አርሶአደሩ እንዳያርስ ችግር እየተፈጠረበት ነው በሚል የሚነዛው ወሬ ውሸት ነው። ይህን የሚሉ ትልቅ የፖለቲካ ጨዋታ ላይ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል። የትግራይ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ በሚገኙ በሁሉም ክልሎች የግብርና ግብዓቶችን በወቅቱና በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከሁሉም ክልሎች በተሰበሰበው ፍላጎት 18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ማወቅ ተችሏል። ከዚህም ውስጥ ትግራይ ክልል 800 ሺህ ኩንታል ያስፈልገኛል ብሎ ባቀረበው ፍላጎት መሠረት ሁሉም ደርሷል። ይህ የቀረበው እንዲታረስ እንጂ እንዳይታረስ አይደለም።
ስለዚህ ትግራይን በተመለከተ ግብርና ግብአት ላይም ሆነ የእርሻ ሥራ ላይ የሚነሳው ወሬ ፈጽሞ ውሸት ነው። አንፃራዊ መረጋጋት ባለባቸው አካባቢዎች አርሶአደሮች ግብርና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚረዱ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። አርሶአደሩም ሕይወቱ የሆነውን እርሻውን አይተወውም።
አዲስ ዘመን፡– የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ላይ ያለው ሂደት በተለይ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ላይ የተሻለ ነው፤ ይህን ተሞክሮ ወደሌሎችም ለማስፋት ምን እየተሰራ ይገኛል?
አቶ ወንዳለ፡– አገራችን ላይ ያለውን የዘመናዊ ግብርና መሣሪያዎች እጥረት ለመቀነስ ከለውጡ በኋላ ግብርና ሚኒስቴር የወሰነው ትልቁ ውሳኔ ሜካናይዜሽን ላይ የወሰነው ውሳኔ ነው። እኛ አገር ባር እና ሬስቶራንቶች ውስጥ የሚገኙ መጠጦች አሊያም ግብአታቸው በአብዛኛው ከውጭ አገራት በዶላር ተገዝተው የሚገቡ ናቸው።
የትኛውም ቦታ ላይ ብንመለከት ግን የዶላር እጥረት ባለበት እንኳን የውስኪ እጥረት ግን በከተሞች አይታይም። ብዙ ገጠራማ ቦታዎች መግባት ቢቻል የአልኮል መጠጥ እጥረት የለም። በአንጻሩ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የግብርና መሣሪያዎች ግን እጥረት አለ። የሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን ማየት ቢቻል ግን ከሁለት ዓመት በፊት ታክስ ይቆረጥባቸው ነበር።
ከለውጡ መንግሥት በኋላ ግን በተለይ ያለፉት ሁለት ዓመታት በተላለፈው ትልቅ ውሳኔ መሠረት በኢትዮጵያ 600 የሚሆኑ የተለያዩ የግብርና ዘመናዊ መሣሪያዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ ነው። አሁን ማንኛውም አርሶአደር ትራክተር አሊያም መለዋወጫውን ላስገባ ቢል ከቀረጥ ነፃ ነው የሚያስገባው። በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ሜካናይዜሽን የመጠቀም ሁኔታ መነቃቃት አሳይቷል።
ክልሎች ደግሞ በእራሳቸው መንገድ አስተባብረው ለአርሶአደሮቻቸው በብድር የግብርና መሣሪያዎችን ያቀርባሉ። ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ላይ ትራክተር ሲያቀርቡ አርሶአደሮቹ ገንዘብ ከፍለው ይወስዳሉ እንጂ በነፃ አያቀርቡም። ክልሎች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር ከካፒታል በጀት፣ ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር እንዲሁም ሌላ የፋይናንስ ምንጭ ተጠቅመው ትራክተር ሊያቀርቡ ይችላሉ።
በዚህ አካሄድ ኦሮሚያ በጣም ከጠነከረ ወይም አፋር ክልል ከጠነከረ ብዙ ትራክተሮችን ሊያሰራጭ ይችላል። አሁን ክልሎች እያሰራጩ የሚገኘው ትራክተርም ሆነ ሌላ የግብርና ሜካናይዜሽን ግብአት በክልሎቹ በእራሳቸው ጥንካሬ የተገኘ እንጂ ከፌዴራል መንግሥት ወይም ከግብርና ሚኒስቴር በሚቀርብ የገንዘብ ድጋፍ ብቻ አይደለም። ለአንዱ ክልል የተለየ ድጋፍ ለሌላው የተለየ አይደረግም።
እኛ እንደግብርና ሚኒስቴር ግን እንደማንኛውም ዕቃ ሱቅ ሄደው እንደሚገዙት ከታክስ ነፃ በሆነ መንገድ ቴክኖሎጂውን እንዲያገኙ ዕድሉን አመቻችተናል። በዚህ ልክ በየክልሎቹ፣ በኅብረት ሥራ ማህበራት እና አርሶአደሮች ዘንድ የሜካናይዜሽንን ልምድ እንዲወስዱ እና የሜካናይዜሽን ጥቅምን እንዲረዱ እናደርጋለን።
የፋይናንስ አካታችነት ሥርዓትን በተለይ የብድር እና የሊዝ ፋይናንስ ሥርዓቶች በባንኮች እንዲፈቀድ የማድረግ ሥራ እያከናወንን ነው። ይህንን ዕድል የመጠቀም ፈንታው ግን የክልሎች ነው። ሁሉም ክልሎች ተጠናክረው የሜካናይዜሽን ምርቶችን ለአርሶአደሮቻቸው በብዛት ሲያቀርቡ እንደአገር ያለው የግብርና ምርቶች የዘመናዊ ቴክኖሎጂ እጥረት ይቃለላል። ግብርናውም በተሻለ መንገድ ይዘምናል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም ጥሩ ምርት ያገኙ አርሶአደሮችን በመሸለም ሌሎች አርሶአደሮችንም ለማነሳሳት ጥረት ይደረጋል። አሁንስ በተመሳሳይ መልኩ የተሻለ የሰሩ አርሶአደሮች ለመሸለም እቅድ አላችሁ?
አቶ ወንዳለ፡– አርሶአደሮችን መሸለም አንድም ለሥራቸው እውቅና መስጠት ነው። በቀጣይም የተሻለ ገቢ አግኝተው የሚሰሩበትን መንገድ ያሳድጋል። በግብርና ሚኒስቴርም ሆነ በመሪዎች ደረጃ በርካታ አርሶአደሮች በሞዴል አርሶአደርነት ተሸልመዋል።
በዚህም ሌሎች አርሶአደሮች እኔም ለዚህ ክብር እበቃለሁ ብለው እንዲነሳሱ ያግዛል። ስለዚህ መሸለም እና እውቅና መስጠት አንድም ባለቤቱን በተለይ ተመልካቹን ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነውና ጥቅም አለው። በቀጣይ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የእውቅና መርሃ ግብሮች ሊኖሩ ይችላሉ።
ሽልማት በባህሪው ድንገቴ (ሰርፕራይዝ) ስለሆነ አሁን ላይ ይህን እናደርጋለን ብለን መናገር ይከብዳል። በይፋ ባይነገርም አርሶአደሮቻችንን የምናበረታታበት ሥርዓት ይኖረናል። በቀጣይ አምራች አርሶአደርም ሆነ ከፊል አርሶአደሮች የበለጠ ሀብት እንዲያካብቱ የሚያበረታታ አሠራር ይኖረናል።
አዲስ ዘመን፡– የግብርና ባለሙያዎች ከክፍያ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ክፍያ ነው የምናገኘው በሚል ቅሬታቸውን ያሰማሉ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ምን ታስቧል?
አቶ ወንዳለ፡– ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ነበሩ፤ ለክልሎችም ቀርቦ በሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር በኩል ማስተካከያዎችም ተደርገዋል። ከማስተካከያ እርምጃዎችም በኋላ ቢሆን ግን ተመሳሳይ ጥያቄዎች አሉ። በግብርና ብቻ ሳይሆን በጤናውም ዘርፍ ሆነ በትምህርት እና በሌሎች ዘርፎችም የእኛ ክፍያ አንሷል፤ አይበቃንም የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ።
የአገሪቷ የመክፈል አቅም በሚፈቅደው ሁኔታ የግብርና ባለሙያውን ክፍያ ከሌላው ዘርፍ ጋር ተቀራራቢ ክፍያ እንዲኖረው የሚያስችሉ ማስተካከያዎች በተለይ በዚህ ዓመት ተወስደዋል። ይህም ሆኖ ግን በአንዳንድ ዘርፎች በተለይም በግብርናው ስር ያሉ እንደ እንስሳት ዘርፍ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች የሥራ ምዘና ሲወሰድ አንሶብናል የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ የማይለወጥ አቋም የለንም፤ ቅሬታውን ለማየት ዕድል እንሰጣለን።
ይህ አገር ሰፊ ነው፤ ተቋሞቻችንም ብዙ በመሆናቸው እስከ ቀበሌ ድረስ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ነው ያሉን። ሁሉም ቦታዎች ላይ ያሉ ሥራዎች ደግሞ እንከን የለባቸውም ብለን አንወስድምና ባለን አቅምና እውቀት ልክ ችግሮቹን እየፈታን ነው። ከክፍያው ጋር የሚነሱ ቀሪ ጥያቄዎችንም እያጠናን ለመፍታት ዝግጁ ነን። ሠራተኛው ደስተኛ ሆኖ ካልሰራ፣ እንደአገርም ምርትና ምርታማነት ላይ እክል ያመጣል።
ከአርሶአደሩ፣ ከፊል አርሶአደሩ እና አርብቶ አደሩ ባለፈ የግብርና መሪውም ሆነ ሠራተኛው በፍላጎት ካልሰራ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያመጣል ብለን ነው የምናስበው። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ ሠራተኞቻችንን ለማበረታታት ዝግጅት እናደርጋለን።
በግብርና ሚኒስቴር ረገድ በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ እቅድ ውስጥ አካተን ሠራተኛውን በምን መልኩ እንጥቀም የሚለውን እየሰራንበት ነው። በቀጣይም ሠራተኛው በምን ዓይነት መልክ ይበረታታ የሚል ጥናቶች ተደርገው በሥራ ላይ ይውላሉ፤ ይህንን ጊዜው ሲደርስ ይፋ የምናደርገው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– የአትክልትና ፍራፍሬ ሀብት በስፋት ለማልማት የሚያስችሉ የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ዎችን ከማዘጋጀት አኳያ ምን ያክል ትኩረት ሰጥታችሁ እየሰራችሁ ነው?
አቶ ወንዳለ፡– የሆርቲካልቸር ዘርፍ የኢትዮጵያ የወደፊቱ ተስፋ ነው። እንደነኔዘርላንድ እና ጀርመን እንዲሁም እስራኤል ያደጉበትን መንገድ መመልከት ቢቻል የሆርቲካልቸር ዘርፉ አንዱ የኢኮኖሚያቸው መሠረት መሆኑን ማየት ይቻላል። ሆርቲካልቸር በአንድ በኩል የሕክምና ዘርፍ ነው፤ በሌላ በኩልም ገቢ የሚያስገኝ የምግብ አማራጭ ነው።
ሆርቲካልቸር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ እንደአጠቃላይ መንግሥት ዘርፉን በማክሮ ደረጃ እየመራው ይገኛል። ዘርፉ ከውጭ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ገቢ በሚያስገኝበት ወቅት በአንድ በኩል የባንክ ሴክተሩንም ያነቃቃል፤ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ገበያውም የሆቴል፣ የቱሪዝም፣ የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ያለው ሥራ ይነቃቃል። የአግሮ ፕሮሰሲንግ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ሥራቸውም በተሻለ ሁኔታ ይሄዳል።
የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ኢትዮጵያ በሰፊው እየሰራችበት ለሚገኘው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ግብአትነት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራውም ቢሆን ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል። በአንዳንድ የሥራ ዘርፎች ላይ መመልከት ቢቻል የሚፈጠረው የሥራ ዘርፍ ጊዜያዊ ሊሆን ይችላል፤ ሆርቲካልቸር ዘርፍ ግን ተከታታይነት ያለው እና ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ዘርፍ ነው። በአጠቃላይ ዘርፉ ትርጉም ባለው ደረጃ በአገራችን እየተሰራበት ይገኛል። ይህ ጅምር ከአረንጓዴ ልማቱ ጋር ተገናኝቶ እንዲሄድ በክረምቱም ወራት በሰፊው ይሰራበታል።
የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ ዘርፉ የእራሱ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲኖረው ከመስከረም ወር አንስቶ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሰርተናል። ይህም በመሆኑ የሆርቲካልቸር ዘርፉ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም ፍኖተ ካርታ የሚመራባቸው ሦስት ሰነዶች በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ የመጀመሪያው የማርቀቅ ደረጃ ላይ ደርሰናል።
አሁን ላይ አጋር አካላት በተሳተፉበት መንገድ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አካላት እየገመገሙ ይገኛል። የውጭ ኢንቨስትሮች እና የአገር ውስጥ ባለሀብት፣ አርሶአደሩ እና አርብቶ አደሩ እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሩ በሚሳተፍበት መንገድ ይበልጥ ሊያሰራ የሚችል የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነን።
አርሶ አደሩ በርካታ መሬት በሆርቲካልቸር ዘርፍ ለማልማትም የተለያዩ አማራጮችን በማየቱ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል። የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ገበያው ላይ የተሻለ ገቢ እያስገኙ ነው፤ በገበያም ተፈላጊነታቸው ጨምሯል፤ ከዚህ ባለፈ አትክልትን የመመገብ ባህሉ በከተማም ይሁን በገጠሩ አካባቢዎች ላይ እየዳበረ ነው።
በዚህ ምክንያት አርሶ አደሩም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በሰፊው ለማምረት ያለው ፍላጎት ጨምሯል። በአጠቃላይም በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ዜጎች አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ እየተሳተፉ ይገኛል። እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ሌሎች ቋሚ የፍራፍሬ ተክሎችን ጨምሮ በርካታ ምርቶች በሆርቲካልቸር ዘርፉ እየለሙ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ ወንዳለ፡– እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013