በአንድ ወቅት በአስከፊ የድህነት ታሪኳ ትታወሳለች፡፡ በዚሁ ድህነቷ ምክንያት በግዜው ከእርሷ በእድገት የላቁ አገራት የእርዳታ እጆቻቸውን ቢዘረጉላትም የእናንተ እርዳታ በአፍንጫዬ ይውጣ ብላ የድህነትን አስከፊነት በተረዱ ታታሪ ሕዝቦቿና መሪዎቿ ትግል ታሪኳን ቀይራለች፡፡ ዛሬ ላይ ከአስከፊው ድህነት ተላቃ ከምንግዜም ተቀናቃኟ አሜሪካን ቀጥሎ የዓለማችን ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ቁንጮ ባለቤት ለመሆንም በቅታለች- ሀገረ ቻይና፡፡
ዛሬ ቻይና የሕዝቦቿን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል አልፋ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በምታከናውናቸው ግዙፍ የግንባታ ኢንቨስትመንቶች ከራሷ አልፋ የብዙ ሰዎችን ሕይወት መለወጥ ችላለች፡፡ ኢኮኖሚዋንም በእጅጉ አሻሽላ ከአሜሪካን የማይተናነስ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ወደ ውጪ አገራትም በርካታ ምርቶችን በመላክ ወደር ያልተገኘላት ቻይና ምርቶቿ በሁሉም የአለም ዳርቻ አይገኙም ማለት ዘበት ነው፡፡
የበርካታ ሀገራት ኢኮኖሚ በኮቪድ 19 ተፅእኖ ሲሽመደመድም የእርሷ ንቅንቅ አላለም፡፡ ቫይረሱ ሊያሳድር የሚችለውን ሁለንተናዊ ተፅእኖ አስቀድማ መከላከል በመቻሏ ኢኮኖሚዋን ከውደቀት ታድጋለች፡፡ አሁን ግን በምጣኔ ሀብታዊ እድገቷ ላይ በተለይ ደግሞ በአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችል አንዳች ነገር ተከስቷል- የሕዝቧ ብዛት፡፡
የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር አጠቃላይ አገራዊ ምርትን ለዜጎች እኩል ማቋደስ የማይቻል ከመሆኑ አኳያ የዜጎች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ እንደሚቀንስ የታወቀ ጉዳይ ቢሆንም የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለቻይና ያን ያህል ስጋት አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለቻይና ስጋት የሆነው እየጨመረ የመጣው ያረጁ ሰዎች ቁጥር ነው ሲል ቢዝነስ ስታንዳርድ ከሰሞኑ ፅፏል፡፡
በዘገባው በቀጣዮቹ ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ አንድ ሶስተኛ ያህሉ የቻይና ሕዝብ ጡረተኛ እንደሚሆንና ለነዚህ ጡረተኞች ኑሮ መደጎሚያና ጤና እንክብካቤ የሚወጣው ወጪ አንድ አራተኛ የሚሆነውን የአገሪቱን አጠቃላይ ምርት እንደሚወስድ አረጋግጧል፡፡ በተለይ ደግሞ ሰባተኛው የቻይና ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ እድሜው የገፋ የአገሪቱ ሕዝብ ለሁሉም ሕዝብ ቀጣይነት ያለው ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ለአዛውንቶች እንክብካቤ ዋጋ የሚጠይቅ የፖሊሲ ፈተና እንደፈጠረም አሳይቷል፡፡
የቻይና ዘመናዊ የሕዝብ ቆጠራ እ.ኤ.አ በ1953 መካሄድ ከጀመረበት ግዜ ወዲህ ባለፉት አስርት ዓመታት አጠቃላይ የቻይና የሕዝብ እድገት አዝጋሚ እንደነበር በዘገባው የታወሰ ሲሆን ‹‹የ ዋን ቻይልድ›› ፖሊሲ እ.ኤ.አ በ2016 ተሰርዞም የሕዝብ ቁጥር እድገቱ ቀርፋፋ እንደነበርም ተመላክቷል፡፡
እንደ ሀገሪቱ የብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ከሆነ ደግሞ በቀጣዮቹ በሃያ አምስት አመታት ውስጥ አንድ ሶስተኛ ያህሉ የቻይና ሕዝብ ጡረተኛ እንደሚሆንና ለነዚህ ጡረተኞች ኑሮ መደጎሚያና ጤና እንክብካቤ የሚወጣው ወጪ አንድ አራተኛ የሚሆነውን የሀገሪቱን አጠቃላይ የተጣራ ምርት እንደሚወስድ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም የቻይና አረጋውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣት የሰራተኛ አቅርቦትን እንደሚቀንስና በቤተሰቦች አረጋውያን እንክብካቤ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ከፍ ሲል ደግሞ በመሰረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ተጨማሪ ጫና እንደሚያሳድርም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ የቻይና አረጋውያን ቁጥር ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱንና በቀጣዩ ዘመን የማያቋርጥ የረጅም ጊዜ ያልተመጣጠነ የሕዝብ እድገት ግፊት እንደሚያጋጥመው የአገሪቱ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ኒንግ ቲጁአ ከዚህ ወር ቀደም ብለው መናገራቸውም ተነግሯል፡፡
በቻይና ሜትሮፖሊስ የተለቀቀው የሕዝብ ዳታ ቤጂንግና ሻንጋይን በመሳሰሉ የሀገሪቱ ዋና ከተሞች በእድሜ ስብጥር ከፍተኛ መጠን ያለው ልዩነት ማሳየቱንና በብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ደግሞ የቻይና ሜትሮፖሊስ ከተሞች በእድሜ በገፉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸውና ይህም ከሀገሪቱ ብሔራዊ አማካይ እድሜ በላይ መሆኑንም ዘገባው አትቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት የቤጂንግ ማዘጋጃ ቤት መንግሥት 60 እና ከዛ በላይ እድሜ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር 4 ነጥብ 29 ከመቶ መሆኑንና ይህም ከብሔራዊ አማካይ እድሜ በዜሮ ነጥብ 9 ከመቶ መብለጡን ማስታወቁም ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ከተካሄደው ስድስተኛው ብሔራዊ የሕዝብ ቆጠራ ዳታ ጋር ሲወዳደር በእድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር በ7 ነጥብ 1 ከመቶ መጨመሩም በዘገባው ተብራክቷል፡፡
የ 2020ን የሕዝብ ቆጠራ መረጃ ከለቀቀች በኋላ ቻይና ከ2011 እስከ 2019 ያለውን የውልደት መጠን መረጃዋን እያስተካከለች መሆኗን ሪፖርት ማድረጓንም ዘገባው ተጠቅሶ መረጃው የተጠናከረው ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት በተወሰደ አነስተኛ ናሙና መሆኑን መናገሯን አስታውቋል፡፡
ቻይና ከዚህ በፊት ባሉት አስርተ ዓመታት ውስጥ ወደ ላይ ከፍ ያለውን አብዛኛውን የሥነ-ሕዝብ መረጃ መከለስ መጀመሯንና በሕዝብ ቁጥር መቀነስ ስታትስቲክሳዊ መረጃ ተአማኒነት ላይ ሀሳብ እየተነሳ መሆኑንም ዘገባው ተናግሯል፡፡ የቻይና የሕዝብ ቁጥር እድገት በ5 ነጥብ 38 ከመቶ እንደጨመረና ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ 1 ነጥብ 41 ቢሊዮን ስለመድረሱ ሪፖርት ማድረጓንም አያይዞ ጠቅሷል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013