
አዲስ አበባ፡- ከተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መስህቦች ተጠቃሚ ለመሆን የሀገር ሰላምን ማስጠበቅ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ አስታወቁ።
‹‹ቱሪዝም ለሰላም፣ ሰላም ለቱሪዝም›› በሚል መሪ ሃሳብ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራዎች ማሰልጠኛ ተቋም ባካሄደው ስምንተኛው የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም ላይ ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለጹት፤ ልማትና ዕድገት የተያያዙ በመሆናቸው ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የቱሪዝም ሀብትን መጠቀም ይገባል።
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም መስህብ ባለቤት ናት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባህላዊ፣ ተፍጥሯዊና ታሪካዊ ሀብትን ወደ ቱሪዝም መስህብነት በመቀየር ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ለመሸጋገር በቅድሚያ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ አመልክተዋል።
መስህቦችን ወደ ሀብትነት ለመቀየር እውቀትን መሰረት ማድረግ ይገባል። የውስጥና የውጭ ጐብኝዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ በማስቻል የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ማስቻል ያስፈልጋል። ቱሪዝምን ከእርሻና ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር በማቆራኘት ትልቅ መስህብ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በውስጧ ወርቅን ጨምሮ በርካታ የብረት ማዕድንና የከበሩ ጌጣጌጦች አሏት ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በባህላዊ መንገድ እንዴት እንደሚመረቱ ማሳየትና ጐብኝዎችን በማቆየት ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የሀገርን ኢኮኖሚ መደጎም እንደሚቻል አመልክተዋል።
ጊዜው የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ የቱሪዝም መስህቦችን በማስተዋወቅ ጎብኝዎች እንዲመጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፣ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ሕብረት መስራችና መቀመጫ፣ የአፍሪካ የፖለቲካና የዓለም ዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የቱሪዝም ገቢን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
‹‹ቱሪዝም ለሰላም፣ ሰላም ለቱሪዝም›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ማዘንጊያ ሽመልስ በበኩላቸው፤ ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ሰላምንና የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከርን ይሻል ብለዋል። ሰላም ካልሰፈነ የቱሪዝም መስህቦችን ወደገቢ ማስገኛነት መለወጥ እንደማይቻልም አመልክተዋል።
ጐብኝዎች እንዲመጡና የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ በቅድሚያ ሰላምን መጠበቅ ያስፈልጋል። ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ይጐዳል። ቱሪዝም የሰዎችን ግንኙነት በማጠናከር የባህል ልውውጥን በማሳደግ፣ ድህነትን በመቀነስ፣ የሥራ ዕድልን በመፍጠርና የአንድን ህብረተሰብ ግንዛቤ በማሳደግ ለሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የቱሪዝም መስህቦችን ተጠቅሞ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና ዘላቂ ልማትን ማስፈን ይገባል ብለዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም