የአፍሪካ ቀንድ ለረጅም ዓመታት መረጋጋት የራቀው፤ የግጭት ቀጣና ነው። ከዚህም የተነሳ የአካባቢው አገራት ሕዝቦች ተነግሮ ለማያልቅ መከራና ስቃይ ተዳርገዋል። አካባቢው ለሰላም ባዕድ ከመሆኑም የተነሳ የልማት ጉዳይም የሚታሰብ አይደለም።
ወደ ልማት የገቡ የአካባቢው አገራት ሕዝቦችም ቢሆኑ ልማታቸውን በሚፈልጉት መልኩ ለማከናወን ባለመቻላቸው ድህነትን አሸንፎ ለመውጣት ያደረጓቸው ጥረቶች የተፈለገውን ያህል ውጤት ሊያስገኙ አልቻሉም። ሕዝባቸውን በአግባቡ መመገብ ሳይችሉ ቀርተውም የዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ የምጽዋት እጅ ለመጠበቅም ተገደዋል።
መመጽወቱም ቢሆን በብዙ የፖለቲካ ሴራዎች የተጎነጎነ በመሆኑ የአካባቢው አገራት ሕዝቦች የራሳቸው ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም አጥተው ዘመናት ባስቆጠረ ድህነትና ከዚህ ከሚመነጨው ጠባቂነት፤ ጠባቂነት በፈጠረው ግራ መጋባት ነገዎቻቸውን ለማየት የሚያስችል አቅም አጥተው ቆይተዋል።
«በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» እንዲሉ በአካባቢው ባለው ጠባቂነትና ግራ መጋባት ተጠቃሚ ለመሆን የሚጥሩ አክራሪ ኃይሎች በአካባቢው ላይ ዓይናቸውን ካሳረፉ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንደ አልቃይዳና አልሸባብ ያሉ አሸባሪ ቡድኖች መመሸጊያና መፈልፈያ ጎሬም ሆነዋል።
በተለይም የአንድነትና የጠንካራ መንግሥት ክፍተት ባለባት ሶማሊያ ያለው እውነታ የአፍሪካ ቀንድ አገራትና ሕዝቦች የስጋት ምንጭ እንደሆነ ያለፉት 20 እና 30 ዓመታት በተጨባጭ ያሳዩት ነው። በአገሪቱ የመሸጉ አሸባሪ ቡድኖች በሶማሊያ ሕዝብ ላይ ካደረሱት የከፋ ግፍና በደል በተጨማሪ በአካባቢው አገራት ሕዝቦች ላይ ያደረሱት ጥፋትም ቀላል የሚባል አይደለም።
ኢትዮጵያ እንደ አገር የሕዝቦቿን ደህንነት ለማስጠበቅ በነዚሁ ዓመታት የሄደችበት መንገድ ከራሷ አልፋ በአካባቢው ላሉ አገራት የተሻለ ሰላም እና አካባቢያዊ መረጋጋት እንዲሰፍን አስችሏል። ብዙ ዋጋ በመክፈልም በአንድ በኩል የአሸባሪ ቡድኖችን የሽብር ተግባር በማክሸፍ ለዜጎቿ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ፈጥራለች።
በሌላ በኩል በአካባቢው (በቀጣናው) መረጋጋት ለመፍጠር ድንበር ተሻግራ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ አድማሳቸውን እንዳያሰፉ፤ የመሸጉባቸው ሕዝቦችም የተሻለ ሰላም እንዲያገኙ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጋር በመሆን ከፍ ያለ ዋጋ ከፍላለች። በዚህም አካባቢው በአንጻራዊነት የተሻለ ሰላም እንዲኖረው ትልቁን ኃላፊነት ተወጥታለች።
ከዚህም በላይ በጎረቤት አገራት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ የመሪውን ስፍራ በመውሰድ ግጭቶች እና አለመግባባቶች የአገራቱን ሕዝቦች ዋጋ እንዳያስከፍሉ ሰርታለች። የሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራትም የጎረቤት አገራት ሕዝቦች በተሻለ ሰላም ውስጥ እንዲኖሩ አድርጋለች፤ እያደረገችም ነው።
ኢትዮጵያ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ይሄን ያህል ማድረግ የቻለችው የተሻለ የፖለቲካ መረጋጋትና ከዚህ የሚመነጭ አቅም መፍጠር በመቻሏ ነው። ይህ አቅሟ ከራሷ ባለፈ ለአካባቢው አገራት ጭምር መተማመኛ የሆነ ነው። አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት ተደማጭነትና ተደማጭነቱ የተፈጠረበት እውነታ በአገሪቱ የነበረው ሰላምና መረጋጋት እንደሆነ ግልጽ ነው።
አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ይህን አቅሟን በሁለንተናዊ መልኩ ማሳደግ በሚያስችል የለውጥ ሂደት ውስጥ ነች። ለውጡ ይዞት የመጣው ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ አብሮ የማደግ ጠንካራ አስተሳሰብ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተጨባጭ የሚታይ እውነታ ነው።
በአንድ ወቅት በከፋ ጠላትነት ከሚተያዩ የጎረቤት አገራት ጋር የፈጠረችው ሰላም ፣ ሰላሙን ተከትሎ በቀጣናው የነበረው የጠላትነት መንፈስ በትብብር የማደግ መንፈስ ተለውጦ አገራት ከጸጥታና ደህንነት ባለፈ በጋራ የሚያድጉበትን መንገድ እንዲያሰሉ አድርጓል። ይህም በአገሪቱ የተከሰተው ለውጥ ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ለውጡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አገራት መካከል የነበረውን የጠላትነትና የጥርጣሬ መንፈስ በማስወገድ የመተማመንና ዕጣ ፈንታን የማስተሳሰብ አዲስ የፖለቲካ አሳቤን ይዞ መጥቷል። በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በሶማሊያ መንግሥታት መካከል በሰላምና ደህንነት ጉዳይ የተደረሰው ስምምነት ፣ ከዚያም በላይ አገራቱ በጋራ ለማደግ የደረሱባቸው መግባባቶች ተጠቃሽ ናቸው።
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የነበረችበት ቁመና በለውጡ አዲስ አስተሳሰብ ተገርቶ ለአካባቢው አገራት የተሻለ አቅም እየሆነች ባለበት ታሪካዊ ምዕራፍ፤ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከግጭትና ካለመረጋጋት ወጥቶ በአዲስ ሰላምና መረጋጋት፣ ከዚያም በላይ በጋራ የመልማት መነቃቃት ውስጥ ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰራው ሴራ አካባቢውን የከፋ የግጭትና ያአለመረጋጋት ቀጣና የማድረግ ሙከራ ያህል ነው።
ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት፤ ለሕዝቦቻቸው ልማት እና ዕድገት እናስባለን የሚሉ ኃይሎች ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከዚያም በላይ ልማት ስትራቴጂክ አቅም በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የጀመሩት ዘመቻ አካባቢውን ከዚህ ቀደም ወደ ነበረበት የግጭት ማዕከል መመለስ እንደሆነ በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል።
አገሪቱ ያላትን ጥንካሬና ከጀመረችው የለውጥ ጎዳና ለማስወጣት የሚደረገው የተጠናከረ ርብርብ በአካባቢው ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖር የማድረግ ሴራ አካል ነው። ይህ ሴራ ደግሞ የአካባቢው አገራት ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዳይወስኑ ለዘመናት ሲደረግ የነበረው ሴራ ቀጣይ ምዕራፍ ነው።
የአካባቢው አገራት ሕዝቦች በአንድ በኩል ባልተገባ ትምክህትና እብሪት ባበጡ መሪዎች በሌላ በኩል ሰላማቸውን እና ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ባልቻሉ ደካማ መንግሥታት ምክንያት ላለፉት 50 እና 60 ዓመታት ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለዋል። ዜጎቻቸው ለሞትና ለስደት ብሎም ከፍ ላለ መፈናቀል ተዳርገዋል።
ይህንን እውነታ ለማስቆምና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን የጀመሩት መንገድ አብቦ ፍሬ እንዲያፈራ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሊደግፋቸውና አቅም ሊሆናቸው በሚገባበት በዚህ ወቅት የነዚህን አገራት ሕዝቦች የተስፋ መንገድ ለማጨለም እየተሄደበት ያለው መንገድ ከቀደሙ ታሪኮች ያለመማር ውጤት ነው።
ኢትዮጵያውያን የትኛውም ዓይነት ጫና ቢደረግባቸው በለውጡ መንፈስ ውስጥ ያዩትን አዲስ ተስፋ ለመውረስ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁነታቸው ከፍ ያለ ነው። የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን የሚከፍሉት ዋጋ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን ላልቻሉ ሕዝቦች አዲስ ተስፋ ፈንጣቂና ጎህ ቀዳጅ መሆኑም አይጠረጠርም !
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013