
አዲስ አበባ:- በትንሽ ካፒታል ተነስቶ ውጤታማ የሚሆኑ እንደ ሲንቄ ባንክ ያሉ በርካታ የልማት ምሰሶዎችን ማጎልበት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
በአነስተኛ ካፒታል በ1987 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ‹‹ሲንቄ ባንክ›› በሚል ስያሜ ወደ ባንክ አደገ፡፡
በምስረታው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት አቶ ሽመልስ እንዳስታወቁት፤ ቁጠባ ተቋሙ እስከ ታችኛው የገጠሩ ማህበረሰብ በመድረስ ባደረገው ብርቱ ጥረት ህዝቡ የቁጠባና የሥራ ባህል እንዲዳብር አስችሏል፡፡
በሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል የሲንቄ ባንክ መመስረት መቻሉ በቁርጠኝነት ከተሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ሲንቄ ባንክ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የቀድሞ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት እና የባንኩ የቦርድ አባል ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው፣ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ከተፈለገ ሁሉም በየተሰማራበት የሙያ ዘርፍ ጠንክሮ መሥራት ብቻ ሳይሆን የቁጠባ ልምድ ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በወቅቱ የብድርና ቁጠባ ተቋሙን ለማቋቋም የተፈለገውም ህዝቡን ከልመናና ከድህነት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሸጋገር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
የሲንቄ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ዘውዴ ተፈራ፣ ባንኩ ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት እንዳለው አስታውቀዋል። በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከአፍሪካ ተመራጭ ባንኮች መካከል እንዲመደብ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል፡፡
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም