በመልካም ወዳጅነት፣ መከባበርና ትብብር ላይ የተመሰረተው የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊና ተምሳሌታዊ ግንኙነት ስለመሆኑ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ሁለቱ አገራት በልማት፣ በሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና አሸባሪነትን በመዋጋት ረገድ እስካሁን ድረስ ያላቸው መልካም ግንኙነት ለብዙዎች ምሳሌ የሚሆን ነው።
በዚህ መልካም ግንኙነት ውስጥ ከሰሞኑ በአሜሪካ የጸደቀው በባስልጣናት ላይ የጉዞ ክልከላ ሲታይ በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ያላገናዘበ፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ዝንባሌ የታየበትና በአጠቃላይ ለረጅም ዘመን በሁለቱ አገራት መካከል የዘለቀውን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት ለዚህ ውሳኔ መነሻ ያደረገው በወንጀለኛውና አሻባሪው ህወሓት ቅሪቶች የቀረበለትን የሀሰት መረጃ መሆኑ ደግሞ ውሳኔውን እጅግ የተሳሳተና ተገቢነት የሌለው ያደርገዋል። በሀገሪቱ ለ27 አመታት የዘለቀውን የትህነግ አገዛዝ ለማስወገድ ሰፊና ብዙ መስዋዕትነት የጠየቀ ትግል ጠይቋል። በዚህ ትግል ብዙ ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፣አካላቸውን አጥተዋል፣ ከሀገር ተሰደው አስከፊ የስደት ኑሮ ለመኖር የተዳረጉም ጥቂት አይደሉም ።
ቡድኑ በረሃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ይከተለው የነበረው ሕዝብንና አገርን አማራጭ የማሳጣት የፖለቲካ አስተሳሰብ ፣ ከዛም በላይ ይከተለው የነበረው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቃርኖ አስተሳሰብ አገርና ሕዝብን በብዙ መልክ ዋጋ አስከፍሏል። በስልጣን ለመቆየት ሲል ቡድኑ ያራምደው የነበረው ጠርዝ ያጣ የልዩነት ፖለቲካ በአገሪቱ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን የአንድነት መንፈስ በመሸርሸር አለመተማመንንና እርስ በርስ መጠራጠርን ፈጥሯል ።
የጥፋት ትርክቶችን በመፍጠር፣ የታሪክ ጠበሳዎች በማከክና በማሳከክ የሕዝባችንን አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴቶች አደጋ ውስጥ ጨምሯል። እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ሳይቀር ችግር ውስጥ የሚከቱ ሴራዎችን በመጎንጎን በሴራ ተልዕኮ ላይ ተጠም ዶም ቆይቷል። ከአገር ውስጥ ባለፈም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር የአካባቢው ሕዝቦች ተረጋግተው ወደ ልማት እንዳይሄዱና ለዘለቄታው ልማታቸው ማስተማመኛ እንዳያገኙ ሲያደርግ ቆይቷል ።
ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የመገናኛ ብዙሃን ጋር በፈጠረው መርህ አልባ ግንኙነት በሚያገኘው ድጋፍም ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከማሳሳት አልፎ ረጅም ዓመታትን በሥልጣን እንዲቆይ ዕድል ፈጥሮለታል ። መርህ አልባ በሆነው ግንኙነቱ ያፈራቸው የሚዲያ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙ ግለሰቦችና የአገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር ቡድኑ በአገር ውስጥም ሆነ በአካባቢው አገራት ላይ የሚያደርገውን ያልተገቡ ተግባራት አይቶ እንዳላየ በመሆን የልብ ልብ ሠጥተውት እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ይህ ቡድን አገራዊ ለውጡን በሚቻለው አቅሙ ሁሉ ለማፈን የሄደበት መንገድ አገርና ሕዝብን ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈለ መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ነው። የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ በሚከት መልኩ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃትም የአጠቃላይ እብሪቱ የመጨረሻ መገለጫ እንደነበር ይታወሳል ። በኃይል ዳግም ወደ ሥልጣን ለመምጣት ያደረገው ጥረት በአንድ በኩል ለራሱ ሲሰጥ ከነበረው የተሳሳተ ግምት የመነጨና በሥልጣን በነበረበት ዘመን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የመገናኛ ብዙሀን ጋር የፈጠረው መርህ አልባ ግንኙነት የፈጠረው ያልተገባ ድፍረት አካል ጭምር ነው ።
ከዚህ ክፉ ባህሪው አንጻር ስለዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ተቆርቋሪ ነን የሚሉት አንዳንድ አገራት በተለይም ደግሞ የአሜሪካ አስተዳደር ሞቶ ለተቀበረው የትህነግ ቡድን ትንሳኤ ለመስጠት እየሄደበት ያለው መንገድ በአንድ ሉዓላዊ መንግሥት የውስጥ ጉዳይ ላይ ከመግባት ባለፈ የሞራልም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ዛሬ አገርና ሕዝብን በሚያሻግር በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ባለንበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት በአገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት በአሻባሪነት ለተፈረጀው ለዚህ ወንጀለኛ ቡድን ህይወት ለመስጠት እየሄደበት ያለው መንገድ ፍጹም የተሳሳተ ነው።
በተገዙ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች ፤ በገንዘብ ተገዝተው መረጃዎችን እያጣመሙ በሚያሰራጩ ሎቢስቶችና በቡድኑ የቀደመ መርህ አልባ ግንኙነት ተጠቃሚ በሆኑ ግለሰቦች በሚፈጥሩት ጫና የአሜሪካ መንግሥት መወሰድ የለበትም። የሚጨበጡ መረጃዎች አደባባይ በሞሉበት ሁኔታ በሀሰት መረጃ በመታመን የጀመርነውን ለውጥ ከሚያደናቅፉ ተግባራትም ሊቆጠብ ይገባል።
የአገራችንን የሕዝባችን ጉዳይ ከኛ በላይ ሆኖ ማሰብ ከሕግም ሆነ ከሞራልም አንጻር የሚያስኬድ አይደለም። ይህ አካሄድ በቅኝ ግዛት ዋዜማ የነበረውን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ለቅኝ ግዛት ሴራቸው ሲያራምዱት የነበረውን የሞግዚትነት አስተዳደር እንድናስታውስ ያስገድደናል። ይህ የሞግዚትነት አስተዳደር መላውን አፍሪካ ለከፋ ባርነት የዳረገ ፤ የአህጉሪቱን ሕዝቦች ተነግሮ ለማያልቅ እስከዛሬም ላላበቃ መከራና ስቃይ የዳረገ መሆኑም አይዘነጋም።
የአሜሪካ መንግስት የለውጥ ንቅናቄዎችን በአግባቡ በመደገፍ ለስኬት እንዲበቁ የመርዳት የሞራል ግዴታ አለበት ። ይህ ግዴታው ስለ ዴሞክራሲ ካለው እምነትና ከዚያም ለመርህ ከመገዛት ትልቅ እሴቱ የሚመነጭ ነው ። በአጠቃላይ በተሳሳተ መረጃ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ መግባቱ ለረጅም ዘመን የቆየውን የኢትዮ- አሜሪካን ወዳጅነትን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ ታውቆ በአፋጣኝ ሊስተካከል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013