
አዲስ አበባ:- በብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በመንግሥት በኩል እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች በተሻለ መልኩ ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ እንዲካሄድ በር እንደሚከፍቱ የዶንጋ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ገለፀ፡፡
የዶንጋ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለገሰ ለመንጎ በተለይ ለአዲስ ዘመን አንዳስታወቁት፤ በተካሄዱት ባለፉት አምስት ምርጫዎች ተሳትፌያለሁ፡፡ ምርጫዎቹ ለገዢው መደብ የወገኑና ሰፊ ዕድሎችን የሚሰጡትም ነበሩ፡፡ በተቃራኒውም ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹና ነፃ ያልሆኑ አሠራሮችና ጫናዎች የነበሩባቸው ናቸው፡፡
የዘንድሮ አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ግን ምንም እንኳን የውጭና የውስጥ ተጽዕኖ እያለ የሚካሄድ ቢሆንም፤ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃና እኩል የመወዳደር ዕድሎችና አሰራሮች እየታዩበት ይገኛል፡፡ በመሆኑም ምርጫው ህዝባዊ፤ ዲሞክራሲ የሚረጋግጥበትና የሚጀምርበት የመሆን ዕድል እድሉ ሰፊ ነው። ‹‹በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን፣ ለህዝባችን ጥቅም መከበርም እንሠራለን›› ያሉት አቶ ለገሰ፤ የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና አካታች ሂደቶች እየታዩበት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ድርጅታቸው ሰላማዊ ትግል የሚካሄድበት ሰላማዊ ምርጫ እንዲሆን እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡
ለውጡ ፓርቲዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የምርጫ ዘመቻ እንዲያካሂዱ፣ የሬድዮና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በተሰጣቸው የአየር ሰዓት በመጠቀም ፖሊሲዎቻቸውን እንዲያስተዋወቁ አስችሏል፡፡ ትግበራውም ባለፉት ምርጫዎች ያልነበረና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሚና ያለው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በነፃነት ሃሳባችንን እየገለፅን የምርጫ ቅስቀሳዎችን እያደረግን እንገኛለን፤ ይህም አንዱ የዲሞክራሲያዊነት ማሳያ ነው ባጠቃላይም ምርጫው ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡
አቶ ለገሰ ጨምረው እንዳብራሩት የዶንጋ ህዝብ በደቡብ ክልል በከምባታ ጠምባሮ ዞን ሃደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ የሚገኝ ነው፡፡ የአካባቢው ህብረሰብ የመንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ የመንገድ፣ የጤናና ሌሎች የመሰረተ ልማት ውስንነቶች አሉበት። ሲና የሚባል የጊቤ ወንዝ ገባርና ቃጤ የሚባሉ ወንዞች ያሉት ቢሆንም ከመልካም አስተዳደር ችግር የተነሳ ለመስኖ ሥራ ሳይውሉና ህዝቡንም ሳይጠቅሙ ቆይተዋል።
ድርጅታቸው እስካሁን የዶንጋን ህዝብ የማንነት፣ የአስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለረዥም ጊዜ ሲታገል መቆየቱን በማስታወስ አሁንም የህዝብ ጥያቄዎች እስኪመለሱ ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጠሉ ተናግረዋል፡፡
ሙላቱ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም