የአማራና የትግራይ ህዝቦች የግጭት ነጋዴዎች ያስጣሏቸውን የቀደመውን የወንድማማችነት ፍቅር ሊያስቡ ይገባል !
በአንድ ሀገር ህዝቦች መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች በመሰረታዊ ምንጫቸው አንድም በተለያየ መልኩ የሚገለጹ የግጭት ነጋዴዎች አልያም ከህብረተሰቡ ባህልና ወግ ከዚህ ከሚመነጨው አስተሳሰብ ባፈነገጡ የሳቱ “ልሂቃን “ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንደሚሆንና እንደሆነ የዓለም ታሪክ በስፋት የሚተርከው ነው።
ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ፣ ከኢስያ እስከ አፍሪካ በታሪክ ምእራፍ ውስጥ ተከስተው ያለፉ የማህበረሰብ ግጭቶች በአንድም ይሁን በሌላ ከግጭቶች እናተርፋለን ብለው ከሚያስብና የአፈንጋጭ/ አክራሪ / አስተሳሰብ ባለቤት በሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች አነሳሽነት የተከናወኑ ናቸው።
ግጭቶቹ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ከተፈጠሩ በኋላ ግን ከፍ ያለውን ዋጋ ለመክፈል የተገደደውና በተጨባጭም ዋጋ የከፈለው የግጭቱ ባለቤት ያልሆነው የሀገራቱ ንጹሃን ህዝቦች ናቸው ። እነዚህ ህዝቦች ከግጭቱ ጀርባ የነበረውን ሴራ እና ሤራው የተሸከመውን ሞት፣ ስደት እና የንብረት ውድመት ማየት ባለመቻላቸው ፣ ላላዩት ግን በስማቸው ለተከሰቱ ግጭቶች የከፈሉት ዋጋ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ትልቁን ጥቁር ምእራፍ ይዞ አልፏል።
የየትኞቹም ግጭቶቹ ባለቤት ሕዝብ ካለመሆኑ የተነሳ ህዝቦች ለግጭቶች ከፍ ያለ ዋጋ በከፈሉ ማግስት ወደ አለፈው ማህበራዊ ትስስራቸው ለመመለስ ብዙም አስቸጋሪ አይሆንባቸውም ቀድሞ የሆነው ነገር ያልተፈጠረ እስኪመስል ወደ ቀድሞው መስተጋብራቸው በመመለስ ሕይወት ወደ ቀድሞ ስፍራዋ ትመለሳለች ።
እንድ ህዝብ ከሌላው ጋር በተጋመደበት በሚታይ ሆነ በማይታይ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ መስተጋብር ተሳስቦ እንደገና ህይወትን በጋራ መጓዝ ይጀምራል። መስተጋብሩ በአዲሱ ትውልድ እዲስ እና ያደገ ማህበራዊና መንፈሳዊ መስተጋብር እየተጋመደ አንዱ ለአንዱ ሕይወት ፣ ውበት እና አቅም ይሆናል።
ባለንበት ዘመን በህዝባች መካከል በተፈጠረው ጠንካራ መስተጋብር ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተቀየረች ትገኛለች። የቀደሙ መንደርተኝነት አስተሳሰቦች ዓለም አቀፋዊ በሆኑ እሴቶች እየተዋጡም ይገኛል።
አሳዛኙ ነገር ግን በዘመነ ግሎባላይዜሽን የግጭት ነጋዴዎች በማህበረሰብ ደረጃ ግጭትን የማትረፊያ መንገድ አድርገው መውሰድ አለማቆማቸው ፤ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉ የሴራ ጉንጎናዎችን ሲጎነጉኑ ውለው ማደራቸው ነው።
የቡድኖችና የግለሰቦች መረን የወጣ የተጠቃሚነት መሻት ዓለሙን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለ ሁሉ በሀገራችንም ይኸው ችግር በየዘመኑ መላው ህዝባችንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ከዚህ የችግር አዙሪት መውጣት ባለመቻላችንም ዛሬም ለግለሰቦች እና ቡድኖች ያልተገራ የተጠቃሚነት መሻት ከፍ ያለ ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን ።
የቀደመውን የሀገራችንን ታሪክ ትተን ባለፉት 27 ዓመታት የትህነግ ቡድን ወደ ስልጣን ለመምጣት ሆነ ከዚያም ቦኋላ በስልጣን ላይ ለመቆየት በተጠናና በተደራጀ መልኩ የጎነጎናቸው ሴራዎች በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ተቻችሎና ተከባብሮ፣ ተፋቅሮና ተዋህዶ የመኖር እሴቶችን በመሸርሸር ቀናቶቻችን በዚሁ የክፋት ጭጋግ እንዲያዙ አድርጓል ።
በተለይም ቡድኑ ለዘመናት አብረው በኖሩ በተጋቡ በተዋለዱ የአማራና በትግራይ ህዝቦች መካከል የዘራው አረም በህዝቦቹ መካከል አለመተማመን ከመፍጠር ባለፈ አንዱ አንዱን በነጻ የወንድምነት ፍቅር እንዳይቀበለው ፣ እንዲጠራጠረው ፤ በተለይ አዲሱ ትውልድ ከዚህም እልፍ ብሎ በጠላትነት እንዲተያይ ሠፊ ስራዎችን ሰርቷል ። የስራውን ያህል ባይሆንም ዘሩ ፍሬ ያፈራበትም ሁኔታ ያለንበት እውነታ አካል ሆኗል ።
እነዚህ ህዝቦች በባህል በሃይማኖት አንዳቸው ከአንዳቸው ከሚለያዩበት ይልቅ የሚቀራረቡበት ፤ ከተለያዩበት ይልቅ የተጋመዱበት ከፍ ያሉ የጋራ ማህበራዊ እሴቶች ባለቤት ናቸው። ከዚህም በላይ ዕጣ ፈንታቸው አንድ የሆኑ በተስፋና ስጋታቸው ሳይቀር የሚጋሩ ናቸው።
እነዚህን ህዝቦች በልዩነት ትርክቶች በመከፋፈል አንዳቸው ለአንዳቸው ተስፋ፣ አንዳቸው ለአንዳቸው ውበት ፣ አንዳቸው ለአንዳቸው አቅምና መተማመኛ ፣ ከዛም በላይ የሀገር ተስፋ፣ ውበት እና አቅም እንዳይሆኑ ተደርገዋል። በዘመናት የተጋመዱበት የማህበራዊ አሴት ጥንካሬ እንጂ ሁኔታው ሊያስከፍላቸው ይችል የነበረው ዋጋ ከፍ ያለ ነበር።
በህዝቦቹ መካከል የቆየውን የመንድማማችነት ፣የመተማመንና አብሮ የመኖር ታሪካዊ እውነታ ለመመለስ በመንግስት በኩል የተጀመረው ጥረት ከፍ ያለ እውቅና ሊሰጠው ይገባል። ወደ ቀደመው ስፍራችን የመመለሳችን እውነታ ዕጣ ፋንታቸው ከመተሳሰሩ አንጻር ነገዎቻቸውን ብሩህ ለማድረግ አልፋና ኦሜጋ ነው ።
የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የክልል ልዩነት ከመፈጠሩ በፊት የኖሯቸውን ዘመናት አሁን ቆም ብለው በሰከነ አእምሮና መንፈስ ሊያጤኑት ይገባል ። በነዚህ ዘመናት ውስጥ የነበራቸውን መስተጋብር፤ መስተጋብሩ የፈጠረውን የወንድማማችነት መንፈስ ፤ በዚህ መንፈስ ያሳለፏቸውን ክፉና ደግ ዘመናት ሊያሰላስሏቸው ይገባል።
በዘመናት ውስጥ በመካከላቸው የተፈጠሩ ግጭቶች ከህዝቦቹ መሻት የፈለቁ ሳይሆኑ የግለሰቦችና የቡድኖች የተጠቃሚነት መረን ያጡ መሻቶች የፈጠሯቸው እንደሆኑ በአግባቡ ለመገንዘብ አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው። እነዚህ ህዝቦች ከየትኛውም የግጭት መድረክ እንደ ህዝብ የተጠቀሙት አንዳች ነገር የለም ።
በቀደሙትም ሆነ አሁን በተፈጠሩ ግጭቶች ልጆቻችው ፣ ተስፋቸውንና ፣ ነገዎቻቸውን ከመገበር ያለፈ ጠብ ያለላቸው ነገር አልነበረም ፤ ወደፊትም ሊኖር አይችልም ። ይህንን እውነት በአግባቡ ሊረዱትና ሊገነዘቡት ይገባል።
እነዚህ ህዝቦች ህይወታቸው የተጋመደ እጣ ፈንታቸው የተሳሰረ ነው ። ተስፋቸውን በተጨባጭ ለመጨበጥና የተስፋቸው ባለቤት ለመሆን እራሳቸውን ከግጭት ነጋዴዎችና ከሳቱ “ሊሂቃን” ሊጠብቁ ይገባል ።”ጠላትህን እንደራስህ ውደድ” የሚል ህያው ቃል የተቀበሉ እነዚህ ወንድማማች ህዝቦች ልባቸውን በአግባቡ ሊመረምሩ የግጭት ነጋዴዎች ያስጣሏቸውን ፍቅራቸውን መልሰው ሊጨብጡ ለዚህም ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል ።