ልጆች እንዴት ናችሁ? ሁሉም ሠላም ነው? ትምህርታችሁን በአግባቡ እየተከታተላችሁ ነው? ጎበዝ ሁኑ እሺ።
ልጆቼ፣ ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅና ቆንጆ ሀገር ልጆች ስለሆናችሁ ታድላችኋል። ይህች ቆንጆ ሀገር ግን አንዳንዴ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሟታል። ያንን ችግሯን የሚቀርፍላት ጎበዝ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ያስፈልጋታል። እናንተ ደግሞ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ ትውልድ አባላት ናችሁ።
ልጆች የነገ ሀገር ተረካቢዎች መሆናችሁን ታውቃላችሁ አይደል? አዎ ተረካቢዎቹ እናንተ ስለሆነናችሁ የቀጣዩ ዘመን ጠንካራና ብቁ ዜጎች እንድትሆኑ የሚመለከተው ሁሉ የበኩሉን ጥረት የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ሁሉም እናንተ በጥሩ ሥነ ምግባር ታንፃችሁ እንድታድጉ ሲጥሩ እናንተ ደግሞ ጥሩ ተማሪዎች ሆናችሁ የተለያዩ የሕይወት ክሂሎቶችን መቅሰም ይኖርባችኋል።
የአሁኑ ልጆች የነገ ሀገር ተረካቢዎች (አባባ ተስፋዬ “ልጆች የዛሬ አበባዎች፣ የነገ ፍሬዎች” ይሉ እንደነበረው ማለቴ ነው) ብቃት ባለው ትምህርት መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በቅድሚያ ልጆች ለትምህርት ጠንካራ ፍላጎት እንዲኖራችሁ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ለሁሉም ነገር (መልካም ሰብዕና) መሠረት በመሆኑ ነው፡፡ በተቻላችሁ መጠን የተለያዩ መንገዶችን እየፈጠራችሁ ማንበብ፣ መፃፍና ትምህርትን በሚገባ መውደድ አለባችሁ።
ትምህርት ቤት ከገባችሁ ጥናት ወሣኝ ጉዳይ ነው። የጥናትን ጥቅም በሚገባ ካወቃችሁ በኋላ የአጠናን ዘዴን ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢ ነው። ልጆች በተፈጥሮ የተሰጣችሁ ችሎታ እንዳለ ሆኖ መልካም የአጠናን ዘዴን መከተል ለላቀ ውጤት ያበቃችኋል። በዘመናዊና ሣይንሳዊ የአጠናን ዘዴ ሂደት ዋናው ጉዳይ የጊዜ አጠቃቀም ነው፡፡ በአንድ ቀን ውስጥ (24 ሰዓት) ያሉትን ሰዓቶች በሚገባ ከፋፍሎ መጠቀም ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም እንዲኖራችሁ ያደርጋልና ይህንን አድርጉ።
ስለሆነም ጊዜን (ከእሁድ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ ያሉት ቀናት) እንደየባህርይና ልምዳችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር በመተጋገዝ የጊዜ አጠቃቀም ሠሌዳ ለማዘጋጀት ጥረት አድርጉ፡፡ የጥናት ሠሌዳ ስታዘጋጁም አጥኚዎች ለጥናት የሚገለገሉባቸውን ቁሶችና ንቁ የሚሆኑባቸው ሰዓታት በምሣሌነት በመውሰድ መምረጥና መጠቀም ይጠበቅባችኋል፡፡ በተቻለው መጠን የሚመቸውን ቦታ መርጦ ለመጠቀም መሞከርም ለጥሩ ውጤት ያበቃልና ችላ አትበሉት።
ሌላው ስታጠኑ ሌሎች ሰዎች እንዳይረብሿችሁ የተመረጠ ቦታ ከማዘጋጀትም በላይ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ሆናችሁ የራሳችሁን የጥናት ሕግ ማውጣት ይኖርባችኋል።
ልጆች ሀገራችን ለነገ ትልልቅ መሪዎች፤ ሣይንቲሰቶች፤ ሐኪሞች፤ ግንበኞች፤ በአጠቃላይ በሁሉም የሙያ ዘርፎች የላቀ ሙያ ባለቤት የሆኑ ትውልድ አባላት ያስፈልጋታል። ስለዚህም እናንተ ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች ቁልፉ ትምህርት መሆኑን ተረድታችሁ በመማር፣ በመጠየቅና በመመራመር ብቁ ትውልድ እንድትሆኑ እመክራችኋለሁ። እሺ ልጆች፤ በሉ ሣምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ሠላም ሁኑ፤ መልካም የትምህርት ሣምንት!!!
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2013 ዓ.ም