ኢትዮጵያ የዓለም ሆቴሎች ካውንስል በነበረችበት ወቅት አባል በመሆን ሰርተዋል:: የሆቴልና ቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ በአማካሪነትና በመሪነት ለብዙ ዓመታት በመስራት እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ትልልቅ ዝግጅቶችን በሆቴል መስተንግዶ መምራት የቻሉ ናቸው:: በተለይም ከኢትዮጵያ ይውጣ በሚባልበት ወቅት ዘርፉ የተሻለ እንደሆነና ኢትዮጵያ አፍሪካን አንድ ለማድረግ እንደምትችል ለማሳየት ባደረገችው ስምንት ተከታታይ ጉባኤ ላይ የእርሳቸው አሻራም ነበረበት::
ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ባለሀብቶች ጀርባ ያሉ፣ አዲስ ሀሳብ በመስጠት አሰራሮችን የቀየሩም ናቸው ይባልላቸዋል:: በተለይ በሆቴሎች ዘርፍና በንግዱ ዓለም እንደ እርሳቸው አሻራ ያሳረፈን ለመጥቀስ ቀላል አይሆንም:: ምክንያቱም ማንም የማይደርስበትንና የማያስበውን የሰሜን ተራራ ሎጂ እንዲኖረው ጥቂት ሼር ገዝተው ሙሉ እውቀታቸውን ተጠቅመው ከአንድ የውጭ ዜጋ ጋር እውን አድርገውታል:: አሁን ደግሞ የማማከር ሥራ የሚሰራ ድርጅትና ሁለት ሆቴሎች በመክፈት እየሰሩ ይገኛሉ::
በሪልስቴት ዘርፉም ቢሆን ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን እየተንቀሳቀሱ ነው:: ስለዚህም ሁልጊዜ ለአገሬ የሚሉ ሰው ናቸው አቶ ፋንቱ ጎላ:: እናም ይህ ሁሉ የህይወት ተሞክሯቸው ብዙ ትምህርት ይሰጠናልና ለዛሬ የ‹‹ ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸው:: ልምዳቸውን ትቋደሱ ዘንድም ጋበዝናችሁ::
ፋንታሁነኝ
በወቅቱ አጠራር በበጌ ምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት በወገራ አውራጃ በጠገዴ ወረዳ በቀራቅር አቅራቢያ በምትገኘው ልዩ ስሟ ጉልቋ ሚካኤል በምትባል ስፍራ ነው የተወለዱት:: በአሁኑ ሰሜን ጎንደር ውስጥ ማለት ነው:: አባታቸው አርበኛ ናቸው:: ብዙ ጀብዱ የፈጸሙና ጃንሆይ መጀመሪያ በደብዳቤ ግራዝማች የሚለውን ማዕረግ ከሰጧቸው መካከል አንዱ ናቸው:: የሊሻን ዲፕሎማ ሳይቀር ተበርክቶላቸዋል:: ይህም በእንግዳችን እጅ ይገኛል:: በተጨማሪ ዘመናዊ ትምህርት ባይማሩም የአንድ አውራጃ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ የነበሩም ናቸው:: ታዲያ ይህ ሁሉ መለያ ባህሪ የእንግዳችንም ከሆነ ውሎ ሰነባብቷል:: ምክንያቱም አባታቸውን ሙሉ ለሙሉ መስለዋቸዋል:: እንደእርሳቸው ቁጥር፣ አገር፣ ሰው ወዳድ ናቸው:: የአባቱ ልጅ የሚሏቸውም ብዙዎች እንደሆኑ ይናገራሉ:: ለዚህ ደግሞ መሰረቱ አባታቸው እርሳቸውን ትተው ምንም አለማድረጋቸው ነው:: በተለይ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ ያለእርሳቸው አይሆንላቸውም:: ጠመንጃቸውንና ዳዊታቸውን አሸክመው ያስከትሏቸዋል:: ሲያመሹም ቢሆን ዱላና ባትሪ ይዘው የሚያመጧቸው እርሳቸው ናቸው:: ስለዚህም አባትና ልጅ እጅና ጓንት በመሆናቸው ባህሪያቸውም ተመሳሳይ ሆኗል::
ባለታሪካችን ጎረቤትን ሳይቀር አጎቴና አክስቴ እንጂ ሌላ ብለው አያውቁም:: እንደዚያ ተሰምቷቸውም አድገዋል:: በእርግጥ በተወለዱበት ቦታ ብቻ አላደጉም:: አባታቸው በሥራ በተዘዋወሩባቸው ቦታዎች ሁሉ እድገታቸውን አድርገዋል:: ለአብነትም ትክል ድንጋይ፣ አምባ ጊወርጊስ፣ ዳባት፤ ደባርቅ ከብዙ ዓመታት በላይ አሳልፈውባቸዋል:: ልጅነታቸውም በስፋት ያለፈባቸው ቦታዎች እነዚህ ናቸው:: በተለይ ዳባትና ደባርቅ ላይ ብዙ የልጅነት ትዝታ አላቸው:: ታዛዥና ትሁት ስለነበሩ ከሁሉም ጋር በፍቅር ኖረውበታል:: በጨዋታም ቢሆን ለየት ያለ አቋም ያላቸው ልጅ ናቸው:: በቁመትም ሆነ በአቅም ያልጠነከሩ ቢሆኑም እጅ ኳስ ሳይቀር በጥበብ መጫወት የሚችሉ እንደነበሩ ያስታውሳሉ:: የእግር ኳስ ላይም ጥሩ ተጫዋች እንደነበሩ አይረሱትም::
እንግዳችን ባህርዛፍ በጣም የሚወዱና የአባታቸውን እግር ተከትለው የሚንከባከቡ ናቸው:: ምክንያቱም በዚያ ጊዜ የሀብት መለኪያ ዛፍ ነበርና ሁሉም ድሀ ላለመባል ያደርገዋል:: እርሳቸውም ይህንን በማድረግ የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል:: በተመሳሳይ በእርሻ ሥራም ከቤተሰቦቻቸው አልፈው ጎረቤቱን ያግዛሉ:: ይህ የሚሆነው ደግሞ በደቦ እንደነበርም ይናገራሉ:: በህብረት መስራትን አቶ ፋንቱ ሲያስታውሱ በህብረት መብላትን ሳያነሱ ማለፍን አይፈልጉም:: ምክንያቱም እነርሱ ቤት ቤተሰቡ ብዙ ቢሆንም ጎረቤት ተለይቶ የሚበላበት ሁኔታ የለም:: አንድ በግ ከታረደ በአንድ ቀን ማለቅ እንዳለበትም ግልጽ ነው::
እናታቸውም ቢሆኑ ሰው ወዳድ በመሆናቸው የሰፈሩ ሰው ሳይቀር የሚታረሰው በእርሳቸው እጅ ነውና ጎረቤት ዘመድ እንጂ ባዳ እንዳልሆነ አይተውበታል:: ይህ ሁኔታ ቤቱን በፍቅር፣ በደስታና በበረከት ሲሞላውም እያዩ ኖረውበታል:: ከዚያ በኋላ ላለው ህይወታቸው መሰረት አስቀምጠውበታልም::
አቶ ፋንቱን ቤተሰቦቻቸው በተለያየ ስም የሚጠሯቸው ሲሆን፤ እናትና አባታቸው ፋንታሁነኝ ይሏቸዋል:: ስሙ የወጣበት ምክንያትም ከእርሳቸው በፊት የተወለዱ ወንድ ልጆች በመሞታቸውነው:: ሌላው ከአደጉ በኋላ ቤተሰቡን በኃላፊነት ሲያስተዳድሩ የወጣላቸው ሲሆን፤ ይህም አባብዬ የሚለው ነው::
አቶ ፋንቱ ከልጅነታቸው አይረሳኝም የሚሉት ነገር የባንዲራ ክብር ነው:: ጠዋትና ማታ ማውረዱና መስቀሉ ከውብ ኢትዮጵያ መዝሙር ጋር ያለው ትውስታ ሁሌ እዚያ ላይ በሆንኩ ያሰኛቸዋል:: በዚያው ልክ መንግሥት ለትምህርትና ለተማሪዎች የሚሰጠውን ትኩረትም አይረሱትም:: ምክንያቱም እረፍት ላይ በትልቅ ኩባያ ወተት በግድ ጠጣ ይባላሉ:: ቤት የሚወስዱትም ይሰጣቸዋል:: ይህም ምናለ ግማሹ እንኳን በኖረ ያሰኛቸዋል::
ከዳባት እስከ ቺኮዝሎቫኪያ
እንግዳችን የ60ዎቹ ተማሪ በመሆናቸው ወቅቱ ትምህርት ሳይቆራረጥ ለመጨረስ ትልቅ ትግልን የሚጠይቅበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ነገር ግን እርሳቸው ትግሉን አልፈው አጠናቀውታል:: መጀመሪያ እንደማንኛውም ልጅ በቄስ ከትምህርት ጋር ተተዋወቁ:: ዳዊት እስከመድገም ደርሰዋልም:: ከዚያ ዘመናዊውን ትምህርት በዳባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቀላቀሉ:: ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍልም በትምህርት ቤቱ መከታተል ቻሉ:: እንደውም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ የመጀመሪያዎቹ ወሳጅ እንደነበሩ ያስታውሳሉ::
ስድስተኛ ክፍልን በጥሩ ውጤት በማለፍም ወደ ደባርቅ ከተማ ከአባታቸው ጋር በማምራት ደባርቅ መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰባትና ስምንተኛ ክፍልን ተምረዋል:: ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ ያለውን ግን ከቤተሰብ ተለይተው ከእህታቸው ጋር ብቻ በመሆን ነው የተከታተሉት:: ምክንያቱም በጊዜው በጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ያለው ሁለተኛ ደረጃ አንድ ብቻ ነው:: እናም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሁኑ ፋሲለደስ ገብተው ትምህርታቸውን እንዲማሩ ሆነዋል::
ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ሲማሩ የቀለሙን ሳይሆን የንግድ ሥራ ትምህርት ዘርፉን የመረጡት አቶ ፋንቱ፤ ከ12ኛ ክፍል 380 ተማሪዎች ውስጥ 17 ልጆች ብቻ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ነበሩም:: በዚህም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል:: የመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉም ሁሉንም ኮርሶች የወሰዱ ሲሆን፤ ብዙም እንዳልከበዳቸው ያስረዳሉ:: ወደተለየው ዘርፍ ሲገቡም ቢሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መሰረት በመያዝ ስለነበር ብዙ ጠቅሟቸዋል:: ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን በሚገባ በማታና በቀን መከታተልም ችለዋል:: ሥራቸውን አቁመውም ለወራት በቀን ገብተው ተምረዋል:: በተለይም ከ1964 እስከ 1969 ዓ.ም ኢኮኖሚክስን ጥሩ አቅም ፈጥረው ነው ሲከታተሉት የቆዩት:: ነገር ግን የ66ቱ አቢዮት ፈነዳና በዊዝድሮ ትምህርቱ ተቋረጠ ::
እንግዳችን ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ከኢኮኖሚክስ ውጪ በጣም የሚወዱትና ዛሬ ድረስ የማይረሱት የኢትዮጵያ ታሪክን የተማሩበት አካሂድ ነው:: በወቅቱ ልዩ ትኩረት ይሰጠው ነበርና አራት መምህራን ያስተምሯቸዋል:: እነዚህም በአገሪቱ አንቱታን ያተረፉ እንደ እነፕሮፌሰር ፓንክርያስት፣ ዶክተር መርድና በቅርቡ ያረፉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው:: በዚህም ዛሬ ድረስ አንባቢና አገር ወዳድ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ::
የትምህርት ጉዳይ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ ያቋረጡትን ትምህርት በውጭ የትምህርት እድል አጠናቀውታል:: ይህም በቱሪዝምና ሆቴል ኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ የውጭ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ቺኮዝሎቫኪያ በአሁኑ ቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ አቅንተው የተማሩት ነው:: የመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ከከተማዋ በ80 ኪሎሜትር ራቅ ብላ በምትገኘው ዛራርኪ አነስተኛ ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ ትምህርቱን ሲጨርሱ ዳግም ወደ ፕራግ ተመልሰው በፕራግ የኢኮኖሚክ ትምህርት ቤት በቀጥታ ሁለተኛ ዲግሪ የሚሰጥ ስለሆነ አምስት ዓመት በትምህርት አሳልፈው በቱሪዝምና አገልግሎት ኢኮኖሚክስ ወይም በእንግሊዝኛው ኢኮኖሚክስ ኦፍ ቱሪዝም ኤንድ ሰርቪስ ኢንዱስትሪ የማዕረግ ተሸላሚና ብቸኛ ጥቁር አፍሪካዊ ሆነው ተመርቀዋል::
ሌላው ኔዘርላንድ ሄደው የወሰዱት ትምህርት ሲሆን፤ በማርኬቲንግ ማኔጅመንትና ፊዚካል ዲስትሪቢውሽን ዲፕሎማቸውን ያገኙበት ነው:: ከዚያ ውጪ ያሉት ትምህርቶቻቸው በስልጠና ላይ ያተኩራሉ:: በርከት ያሉና የተለያዩ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥም በውጪም ወስደዋል:: ከእነዚህ መካከል ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ የወሰዱት ስልጠና አንዱ ነው:: ኢትዮጵያን በመወከል እንዲሁም ተቋማት ላይ በነበራቸው ኃላፊነት ምክንያት የተሳተፉባቸው መድረኮችና ስልጠናዎችም ብዙ ናቸው::
ይህ ደግሞ በሥራዎቻቸው ጭምር ሁልጊዜ ከትምህርት ያራቁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል:: እንደውም ሥራዬ የሁልጊዜ ትምህርቴ ነውም ይላሉ::
ከግል ወደመንግሥት ከመንግሥት ወደራስ
የሥራ ሀ ሁ የተጀመረው በ12ኛ ክፍልና በዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸው አማካኝነት ሲሆን፤ ይህም በውጭ ጉዳይ የ11 ኤምባሲዎች በጀትና ፋይናንስ ኦዲተር ሆነው ሲያገለግሉ ነው:: ከዚህ ለቀው ለመማር ዩኒቨርሲቲ ገቡ:: ግን ትምህርቱ በአቢዮቱ ምክንያት ተቋረጠ:: ስለዚህም ያለሥራ መቀመጥ የሚያማቸው ባለታሪካችን፤ ከቱሪዝሙ ዘርፍ ጋር የሚያገናኛቸውን ሥራ ጀመሩ:: ይህም አክሱም ትራቭል ኤጀንሲ የሚባል የግል ድርጅት ውስጥ ገብተው የሰሩት ነው:: ችፍ አካውንታንት ነበሩ::
ቀጣዩ የሥራ ጉዟቸው ከትምህርት መልስ የሰሩበት ሲሆን፤ ይህም የሆቴሎች ኮርፖሬሽን ነው:: በሆቴልና ቱሪዝም ኤክስፐርትነት ሥራ ጀምረውበታል:: ዓመት ሳይሞላቸውም ወደ ራስ ሆቴሎች አስተዳደር ተዛውረው የሽያጭ ክፍል ማናጀር ሆነው እንዲሰሩ ተደረጉ:: ለዓመት ያህልም ከአገለገሉ በኋላ ዳግም ወደ ኮርፖሬሽኑ ተመልሰው የፕላኒንግ ክፍሉ ዳይሬክተር አደረጓቸው:: በዚህ ሳይበቃም የኮርፖሬሽኑ የሽያጭ ማናጀር ሆነው ተሾሙ:: ሁለት ዓመት ከአገለገሉ በኋላ ደግሞ በኮርፖሬሽኑ የጠቅላላው ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ ሆኑ:: በዚህም ስድስት ክፍሎችን በሥራቸው በመያዝ በአገሪቱ ይተዳደሩ የነበሩትን 66ቱን ሆቴሎች በኦፕሬሽኑ ይመሩ ጀመር:: ለአምስት ዓመታትም በቦታው ላይ ቆይተዋል:: ለአገሬ አበረከትኩ የሚሏቸውንም ትልልቅ ሥራዎች የሰሩበት ጊዜ ይህ እንደነበር ያስታውሳሉ::
ኢህአዴግ ሲገባ ደግሞ ከደርግ ጋር የሚሰራ ሁሉ ጠላት ነው የሚባልበት ጊዜ ስለነበር ለሁለት ወር ያህል መገለል ደርሶባቸው እርሳቸውን ለማየት በሚል መሞከሪያ ሥራ ተሰጣቸው:: ይህም ከከተማ ወጥቶ መስራት እንደሚችሉ ለማረጋገጥ ላሊበላና አክሱም ላይ ያላለቁና በጦርነቱ ምክንያት የፈራረሱ የመንግስት ሆቴሎችን በማናጀርነት መርተው እንዲጨርሱ ተላኩ:: እርሳቸውም የተወለዱትም ያደጉትም በሥራና በሥራ ስለነበር ደስ እያላቸው ባልተጠበቀ ጊዜ ማለትም ሁለቱንም ፕሮጀክት በሁለት ዓመት ውስጥ አጠናቀው አስመረቁ:: ያንን ያየው መንግሥትም እንደሚያስፈልጉት አመነ:: በቶሎ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት እንዲመለሱም አደረገ::
የጊዮን ሆቴሎች የጠቅላላ ኦፕሬሽን ማናጀር ሆነው መስራት እንዲችሉም አስቀመጣቸው:: ሦስት ወር ሳይቆዩ ደግሞ ወደ ዋቢሸበሌ ሆቴሎች ድርጅት አዘዋወሯቸውና ጀነራል ማናጀር ሆነው እንዲሰሩ አደረጓቸው:: 11 ብራንቾችን በመያዝም ለሁለት ዓመታት በዚህ እንዲያገለግሉም ሆነዋል:: በዚህ ቆይታቸው ብዙ ለውጥ እንዲመጣ ቢያደርጉም እስካሁን የማይረሳቸው ግን የአፍሪካ ህብረት የስምንት ተከታታይ ጉባኤዎችን መስተንግዶ በመምራትና የህገመንግስት ለውጥና የመንግሥት ምስረታ ሲደረግ ዝግጅቱን በሆቴሉ ዘርፍ ለ45 ቀናት የሰጡት እነርሱ መሆናቸውና ውጤታማ ሥራ መስራታቸው አንዱ ነው::
በመንግሥት የሚከፈለው ደመወዝ ቤተሰቡን በሚፈልጉት ልክ ማስተዳደር አላስቻላቸውምና ሥራ ለመልቀቅ ተገደዱ:: በተለይም ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት ቤት እየተማሩ ስለነበር ያንን መሸፈን ግድ ስለሆነባቸው የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ ወደ ግሉ ዘርፍ ዳግም በ1988 ዓ.ም ገቡ:: ይህም መርካቶ ጣና ገበያ ሲሆን፤ ጀነራል ማናጀር በመሆን ለሦስት ዓመታት አገልግለውበታል:: መርካቶን ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉበትን ብዙ ነገርም አግኝተዋል:: ሥራን ፣ ሰውን፣ ሰራተኛና አሰሪን ፣ አብሮ የሚሰራ ኃይልን ከዚህ ውጪ የትም እንደማይገኝ አረጋግጠውበታል::
‹‹መርካቶ የራሴን ሥራ ያስጀመረችኝ መምህሬ ነች›› የሚሉት አቶ ፋንቱ፤ መርካቶ ውስጥ ያለው የሥራ ፈጣሪነት አቅም እርሳቸውን የማማከር ድርጅት እንዲከፍቱ ያስቻላቸው ነው:: ይህም ‹‹ፋን ኮንሰልታንሲ›› የሚል ሲሆን፤ የቱሪዝም ሥራ ጥናቶች፣ ቪዚብል ስተዲዎች፣ ቢዝነስ ፕላኖች፣ የአዳዲስ ሆቴሎች ዝግጅቶች፣ በሆቴል ውስጥ የሚያስፈልጉ የማኔጅመንት ጥናቶችን በማድረግ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው:: ከዚያ ጎን ለጎን ደግሞ ሌሎች ሥራዎችንም የሚያከናውኑበት ነው:: ለአብነት የደቡብ ክልል የቱሪዝም ዘርፉን ማስተርፕላን ያዘጋጁት አንዱ ነው:: ወደ 200 የሚደርሱ የፕሮጀክት ሀሳቦችን ቀርጸው 50 የሚሆኑትንም ከነ መጀመሪያ ዲዛይኑ ሰርተው ለባለሀብቱ ማስተላለፍ ችለዋልም::
የአዲስ አበባ የቱሪዝም እድገትና የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ምቹነት በሚልም ብዙ ጥናቶችን አድርገዋልም:: ይህ የሆነው ደግሞ በዓለም አማቀፉ ባንክ አማካኝነት ነበር:: እንደ እንጦጦ ፓርክ አይነት ሥራዎች በዚያ ጥናት ውስጥ ተካተዋል:: ያው እንደ ዶክተር አብይ ዓይኑ የተገለጠለት ኖሮ አልተሰራበትም እንጂ:: አሁንም ቢሆን ቢታይ ብዙ ነገሮች ይወጣሉ የሚል እምነት አላቸው:: ከዚህ በተጨማሪ ማንም ያልደፈረውን የሰሜን ተራራን ውብና ማራኪ ገጽታ ከአንድ የውጭ አገር ዜጋ ጋር በመሆን እርሱ በገንዘብ እርሳቸው በገንዘብም በእውቀትም ሎጅ በማለት እንዲከፈት አድርገዋል:: የራሳቸውን ባለአራት ኮኮብ ሔርፋይዚ ሪዞልትና በቅርቡ ደግሞ ቋራ ሆቴልን ከፍተው ጎንደር ውስጥ ሁለቱን በማስተዳደር ላይም ይገኛሉ::
በእያንዳንዱ መንግሥት የራሳቸውን አሻራ እንዳሳለፉም ይናገራሉ:: ለአብነትም የደርግ ጊዜ የነበረውን ሥራቸውን ያነሳሉ:: የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመውሰድ እንደ ሊቢያ ያሉ ብዙ የአፍሪካ አገራት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም:: ባለስልጣኑን ለማታለል ቤት እስከመስራት ደርሰዋል:: አፍሪካም ለሶስት ተከፍሎ ነበር:: ሆኖም ኢትዮጵያ ይህንን መፍትሄ ለማበጀት በተከታታይ ስምንት ዓመታት ጉባኤዎችን አድርጋለች:: ለዚህ ደግሞ የእኔ አሻራ ጥቂትም ቢሆን ነበረበት:: ምክንያቱም ለእነርሱ የሚደረግ የሆቴል መስተንግዶ ሙሉ ለሙሉ መጀመሪያ በምክትልነት ከዚያም በዋናነት የመስተንግዶ ኮሚቴው ፅ/ቤት እየመሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ያደረጉት አንዱ ነው::
ከእደ ጥበባት ጋር በተያያዘ በዓለም ባንክ ቅጥር ለሁለት ዓመታት የሰሩትም ሌላው ሥራቸው ነው:: ከምግብ ዋስትና ጋር በተገናኘም ሰርተዋል:: ክራውን ኤጀንት ከሚባል የእንግሊዝ አንጋፋ ድርጅት ጋር በመሆን 15 ዓመታት እስከ ካንትሪ ዳይሬክተር ደረጃዎች ላይ በመድረስ ለአገራቸውም ለራሳቸውም ተጠቃሚ ያደረጉበት ሥራም ሌላው ተጠቃሽ ተግባራቸው ነው:: በቦርድ አባልነትም እንዲሁ ብዙ ቦታዎች ላይ ሰርተዋል:: እንደ እነ አምባሳደር ሆቴልና ዘፍመሽ አይነት ድርጅቶችንም ቢሆን ከስሙ ጀምሮ የእርሳቸው አሻራ ያረፈበት እንደሆነና ከ150 በላይ ሆቴሎች ጥናት ሰርተው ለውጤት እንዳበቋቸው አጫውተውናል::
የአገር ፍቅር
እርሳቸው ከአባታቸው ብዙ የለመዷቸው ነገሮች አሉ:: ከእነዚህ መካከል የአገር ፍቅር፤አገር ወዳድ መሆን አንዱ ነው:: እንደውም በተረተረት ወይም በታሪክ ሳይሆን በተግባር መማራቸውን ያነሳሉ:: አባታቸው በጣሊያን በተወረርንበት ወቅት ተዋጊ ነበሩ:: ለአገራቸው ቆስለው ቁስላቸውን አሳይተዋቸዋል:: ሆነው እንዲሆኑም አስተምረዋቸዋል:: እርሳቸውም ይህንን ለማስተማር እየጣሩ ይገኛሉ:: ልጆች ከቤተሰባቸው የሚወርሱት ነገር ተረት ሳይሆን ተግባር መሆን አለበት ብለው ያምናሉ:: በዚህም ሰርተው እንዲሰሩ በማድረግ ነው ልጆቻቸውን እያሳደጓቸው ያሉት::
አሁን ያለው ትውልድን ቴክኖሎጂው እየፈተነው ነው:: በተግባር የሚነግረው ስለሌለም ከአገሩ ይልቅ የውጪውን ዓለም ጠንቅቆ ማወቅ ይፈልጋል፤ ያውቃልም:: ይህንን ግን ማጥፋት ይቻላል:: ደጋግሞ ማስተማር ብቻ ነው የሚጠይቀው:: ከቴክኖሎጂው እኩል እየተራመዱ፤ እያነበቡ አገርን ማስነበብና ልጆቻችን ላይ መስራት ቀላል ነው ባይ ናቸው:: ልክ አይደለህም ለዘመኑ አይመጥንም:: ያላወቀውን ማሳወቅ፤ እኛ እንደምንበልጥ ማሳየትና ማሳመን ያስፈልገናል:: ልጆች የሚያዩትን ነው የሚቀበሉት:: ለዚህ ደግሞ ብዙ የሚታይ ሀብትና ታሪክ አለን:: እናም ይህንን በማድረግ አገራችንን ልቡ ውስጥ ልንሰራለት ያስፈልጋል ይላሉ::
ልጆች ከሰፈራቸው በአገርህን እወቅ ክበባት አማካኝነት እንዲወጡ ማድረግና ታሪካቸውን እንዲረዱ መጋበዝ የወላጆች ግዴታ መሆን አለበት የሚሉት አቶ ፋንቱ፤ ቦታዎች በራሳቸው ብዙ የሚናገሩትና የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ:: በተለይም ቴክኖሎጂው የገዛውን ትውልድ ልቡን ቶሎ ይሰብረዋል:: ስለሆነም ተፈጥሮን እንዲያነቡ ማድረግ ይገባናል:: መመራመር እንዲችሉም የአገራቸውን ባህል፣ አኗኗር፣ እሴት በደንብ ማሳወቅና የሚያዩበትን ቦታ ማስጎብኘትም መፍትሄ ነው::
ትውልዱ እንዲያውቅም እንዲማርም ምንም እድል አልተሰጠውም:: ከአለበት ቦታ ወጥቶ ሌላ የተሻለ እንዲያይም አልተደረገም:: በዚያው ይማራል በዚያው ይሰራል:: ይህ ደግሞ ከሰፈር በላይ የለም እንጂ አገር የተለየች ነች እንዲል አያደርገውም:: ስለዚህም ማንም ሊፈርድበት አይችልም:: በመሆኑም ከመንግሥት እስከ ግለሰብ ድረስ የደረሰ ሥራ ያስፈልጋል:: የአገር ፍቅር በአገር ርብርብ የሚፈጠር ነውና ይህንን እናድርግ ይላሉ::
ለአንድ አገር ህልውና ሰፊ አገር መኖር ግድ ነው:: ለዚህ ደግሞ የተሻሉ ክልሎችን በስፋት መፍጠር ያስፈልጋል:: ምክንያቱም ውድድር ይኖርና አንድ ቦታ ላይ የሚከማች ሰው እንዳይኖር ያደርጋል:: ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የተለያዩና አዳዲስ ልምዶች ከቦታ ወደ ቦታ ይዘዋወራሉ:: በእውቀትና በእድገት ደረጃም የተመጣጠነ ዜጋ ይፈጠራል:: እንትናን ልምሰልም ይቀራል:: እኩል ነን ሲመጣ ደግሞ እያወቅንና እይታችን እየተስተካከለ ይሄዳል:: የሰው ፍቅር ዋጋ ያገኛል:: ሁሉ ነገር በፍቅር ልኬት ይኖረዋል:: አገር ወዳዶችም ይበራከታሉ:: ብዙ ነገሮች ፈውስ ያገኛሉም::
የህይወት ፍልስፍና
እውነት አምላክ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ:: ምክንያታቸውም ፍጹማዊ እውነት ከእርሱ ውጪ በማንም አይኖርም ነው:: በዚህም ዓለም ላይ ያለው እውነት አንጻራዊ እንጂ ፍጹማዊ አይደለም ይላሉ:: ነገር ግን ከአንጻራዊው ወጥቶ ወደ እውነት መቃረብ ይቻላል መርሀቸው ነው:: በሌላ በኩል እውነት ማለት ተጨባጭ ሁኔታን ማወቅ እንደሆነ ያስረዳሉ:: ተጨባጭ ሁኔታን አውቆ በተሰማሩበት ሙያ ወደ እውነት የሚጠጋ ሥራ መስራት ትክክለኛ መንገድ ያሳያል አቋማቸው ነው:: እውነትን ለማወቅ መጣር፣ ማንበብና ከሁሉም ፍጥረታት እውቀት ይገኛል ብሎ ማመን የህይወት ፍልስፍናቸው ሲሆን፤ ይህንን ማድረግ ያስደስታቸዋል::
የፍቅር ጥሪ
ታናሽ ሆነው ቤተሰቡን የሚሰበስቡ ናቸው:: በተለይ የተማረና መማር የሚፈልግ ሰው እስከመጨረሻው መደገፍ ልምዳቸው ነው:: የነብሳቸው ጥሪ እንደሆነም ይሰማቸዋል:: ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችሉና ከሁሉ ጋር በጋራ መኖር፤ በጋራ መስራትን ምርጫቸው የሚያደርጉም ናቸው:: ከባለቤታቸው ጋር ያገናኛቸውም ይህ ተግባቢነታቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ይናገራሉ:: በእርግጥ ጎንደር ሁለተኛ ደረጃ ሲማሩ ያውቋታል:: ግን ባለቤታቸው እንደምትሆን አስበውም አልመውም አያውቁም:: የውሃ አጣጭ ነገር ሆነና አስተሳሰራቸው እንጂ::
የፍቅር ሀ ሁ የተጀመረው አዲስ አበባ ከመጡ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ነው:: ለዚያውም መንገድ ላይ ተገናኝተው በተለዋወጡት ስልክ አማካኝነት:: ከዚያ በኋላ መግባባትና መገናኘታቸውም ጠነከረ:: ለትምህርት ሄደው እስኪመለሱ እንኳን ተጠባብቀው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል:: ብዙዎች አገራቸው ሳይመለሱ እርሳቸውን ለአገራቸው ያበቃቻቸው በፍቅር ጠርታቸው ነው:: የእርሷ የፍቅር ጥሪ አገራቸው ላይ እንዲኖሩና እንዲሰሩ አድርጓቸዋል:: ልጆቻቸው ሳይቀር ውጪ ቢማሩም ለአገራቸው እንዲኖሩ ያስተማረው ይህ የፍቅር ጥሪ ነውም::
ከሁሉ ነገር የሚያስገርመው የጋብቻቸው ሁኔታ ሲሆን፤ ምንም አይነት ድግስ ሳይኖር ሁለት ሁለት ሰው ከሁለቱም ወገን በመያዝ መዘጋጃ በመሄድ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል:: ይህም በአጋጣሚ የሆነ እንደነበር ያስታውሳሉ:: የሚኖሩት ዘመድ ቤት ሰጥቷቸው ሲሆን፤ የተሻለ ቦታ አግኝተው ቤት ለመስራት የባልና ሚስት ደመወዝን ማጋጨት ያግዛል መባሉን ሰሙ:: ከዚያም ማዘጋጃ ሄደው ተፈራረሙ:: ይሁን እንጂ የመጀመሪያ ልጃቸውን ልደት ለማክበር ሲሉ ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው ስለነበር ዳግም ደግሰው ድል ባለ ሰርግ ተጋብተዋል:: አሁን 35ተኛ የጋብቻ ዓመታቸው ላይ ደርሰዋል:: አራት ልጆችንም አፍርተዋል:: ሁሉም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል:: የአራቶች አያት አድርገዋቸዋልም::
መልዕክት
ማንም ሳይወድቅ አልተነሳም:: ማንም መጥፎ ታሪክ የሌለው አገርም የለም:: ነገር ግን ታሪካቸውን እንዴት ተቀብለው አስተናገዱት ዋናው ጉዳይ መሆን አለበት:: አውሮፓውያን የሚዘገንን ታሪክን አስተናግደዋል:: ሆኖም አንድም አካል ያንን ሲያነሳ አይታይም:: እንደውም መጥፎውን ጭምር መልካሙን ለማድረግ እንደተፈጸመ አድርገው ያስረዱበታል:: ይህ ደግሞ ለነገ መሰረታቸው ጠቅሟቸዋል:: በእነርሱ ዘንድ ብዙ ታሪክ የለም:: ግን አንድም ታሪክ አይጣልም:: የሚጎለብትና ትምህርት ሆኖ በጥበብ የሚረቅ ዘዴ ይፈየድለታል:: እኛ ደግሞ ብዙው የሚያፋቅር፣ ትንሽ ምልከታ ብንጨምርበት የሚያራቅቅና ብዙ ጥበብን የማይጠይቅ ታሪክ ያለን ነን:: ነገር ግን በትንሹ ልዩነት በማይባለው ነገር እንጋጫለን:: ይህ ነገራችን አሁን ማክተም አለበት:: ሀብታም መሆናችንን ማሳወቅ እንጂ ለጸብ መጋበዝ የለብንም:: ብዙ ለመጠቀም ብዙውን ሀብት ማብዛት ያስፈልገናል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው::
በየቀኑ ከእውቀት ጋር የተያያዘ ንባብና ወቅቱን የዋጀ ተግባር ላይ መሳተፍ ሁልጊዜ በአዲስ ፈጠራ መጎልበት ነው:: ምክንያቱም የድሮ አስተሳሰብን ከዘመኑ ጋር ማዛመድ ያስችላል:: አዲስ ምልከታንም ያላብሳል:: ማንነትንም ቢሆን ይገራል:: ስለሆነም ይህንን ማድረግ ልምዳችን መሆን አለበት:: የአገር ደስታ የቤተሰብም ነው:: የቤተሰብ ሥራም የአገር ነው:: ስለሆነም ለእኔ ብሎ መስራት ከምንም በላይ ዛሬ ያስፈልገናልና ይህንን ሲሉ ይመክራሉም::
ሁሌ አመስጋኝ፤ ሁሌ በተሰጠን ደስተኛ፣ ሁሌ ሌሎችን አድናቂ እንሁን:: ምክንያቱም በእነዚህ ማንነታችን ይገነባል:: በተጨማሪ ከቤተሰባችን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን መልካሙን አስተሳሰብም ለመውረስ እንጣር:: ይህም ነገን እንድናይ ያደርገናልና:: ሌላው የራዕይ ሰው መሆን ይገባናል:: ነገን ለማየት እንሰራለንና፤ ህልመኛም ብቻ ሳይሆን ውጤታማም ያደርገናልና ይላሉ:: እኛ እንግዳ ተቀባይምና ሰው ወዳድ እንጂ የተለየ ባህል ያለን አይደለንም:: ትልቅ ሰው ከተባልንም እኛ ብቻ ነን:: በብዙ ሀብት መካከል ያለን ባለጸጎች:: ስለሆነም ትልቅነታችንን እያሳየን ትልቅ መሆንን እናልም የማሳረጊያ መልዕክታቸው ነው:: ሰላም !!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም