“አስተዋይ ከሌላው ይማራል ሞኝ ደግሞ ከራሱ” ይላል አገርኛው ብሂላችን:: አዎ ትክክል ነው :: ምክንያቱም የህይወትንም ፤የሥራንም አልያም የትኛውንም መጥፎም ክስተት ይሁን ጥሩ አጋጣሚ ልንማር የሚገባን ከሌሎች ስኬትና ውድቀት ነው:: በተለይ ከመጥፎ ክስተቶች ለመማር እራሳችንን መሞከሪያ ማድረግ የለብንም:: ከዛ ይልቅ ተመሳሳይ ስህተት ፈጽመው ዋጋ የከፈሉትን በማየት በራሳችን ይህ አሳፋሪ ውድቀት እንዳይደገም ማድረጉ የብልህ ተግባር ነው::
ዛሬ አገራችን በውስጥም በውጭም ጠላት እየተዶለተባት ነው፤ እኛ ህዝቦቿ ደግሞ እርሷን ከዚህ ችግር ለማውጣት ከምን ጊዜውም በላይ አንድ የምንሆንበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንዳለን ይሰማኛል:: ነገር ግን ሥራችን ሃሳባችን በጠቅላላው እንቅስቃሴያችን አገራችንን ታሳቢ ያደረገ አይመስልም:: እንዲያውም የስልጣን ጥም ለሚያናውዛቸው ራስ ወዳዶች መጠቀሚያ ላለመሆንና የአገራችንን ሰላም ከማስጠበቅ ይልቅ እርስ በእርሳችን ጎራ ለይተን የጥላቻ ቃላት ሲለዋወጥ ነው የሚስተዋለው ::
ከዚህ ቀደም አሁን እኛ እንደሚያደርገን ያደረጋቸው አገራት ዛሬ ላይ ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ አይተን ብቻ ብልህ ሆነን ከነእርሱን መማር በቻልን ነበር:: በዓለም ላይ ከህዝባቸው ዘላቂ ጥቅም የግል ፍላጎታቸው የሚያይልባቸው ባለስልጣናትም ሆኑ አንጃዎች ለራሳችው ጥቅም ሲሉ ህዝባቸውን እርስ በእርስ እንዲሁም ከጎረቤት አገራት ጋር አባልተውና አጫርሰው የደም ጥማቸው ጋብ ሲልላቸው በቃ አሁን እንደራደራለን፤ አልያም ተስማምተናል ብለው የይስሙላ መስፈርቶቻቸውን አስቀምጠው የራሳቸውን ድል የሚያበስሩ በርካቶች ናቸው:: ታዲያ እኛ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ብልህ ለመማር ከዚህ ቀደም እያየን የመጣናቸው አካሄዶች አይበቁም ወይ እላለሁ::
ለአብነት ያህል ከሳምንታት በፊት እንኳን የሀማስ እና የእሥራል መሪዎች ያደረጉት ነገር እንደ ብለህ ለመማሪያ በቂ በእኔ እይታ ደግሞ ከበቂም በላይ ነው:: እነዚህ ሁለት መሪዎች ከሳምንት በፊት ክብሪቱን ራሳቸው ለኮሱት፤ ከአንደበታቸው በሚወጡ ጸብ አጫሪ ቃሎችም እሳቱ በደንብ እንዲቀጣጠል አደረጉት ፤ ይህንን ያዩ ዜጎቻቸው ደግሞ እኔ ለአገሬ ብለው ከቤታቸው ወጥተው ጎዳና ዋሉ:: በሁለቱም በኩል የሚወነጨፉት ሮኬቶችና የሚተኮሱት ከባድ መሳሪያዎችም የእነሱን ቃል ሰምተው ከቤት በወጡ እንዲሁም በቤታቸው ቁጭ ብለው ፈጣሪያቸውን በሚማጸኑ አረጋዊያን፣ወጣቶች፣ ሕፃናትና እናቶች ላይ ዘነቡ:: ግጭት ለኳሾቹ ቃጠሎውን ለሕዝቡ ሠጡት።
ሕዝብም ላለፉት ቀናት በተለኮሰው እሳትም እስኪበቃው ተለበለበ፤ ታዲያ ከዚህ ያተረፈ ማነው? ማንም::
በእነዚህ ቀናት የሁለት መሪዎች ክብሪት ጫሪነት በተለኮሰው እሳትም ባለኝ መረጃ ከ232 በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን ፣ 12 አይሁዳዊያን 244 ከምንም የሌሉ ቤታቸው የተቀመጡ ንፁሐን ሕፃናትና ሴቶች ህይወታቸው አለፈ:: በሺዎች የሚቆጠሩትም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት፣ ለንብረት ውድመት ተዳረጉ፤ እንደ አገርም በሁለቱም ወገን በቢሊዮን የሚቆጠር የንዋይ ውድመትም ደረሰ::
ታዲያ ከዚህ ምን እንማር? ለነገሩ ከዚህ ችግር መማር ካለብን እኛ ዜጎቹ ብቻ ሳንሆን የሚመሩን ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ነገ በምርጫ ተወዳድሬና አሸንፌ መንግሥት እሆናለሁ ብለው እየተዘጋጁ ያሉ ኃይሎች በሙሉ ልብ ሊሉት የሚገባ ይመስለኛል:: ምክንያቱም ግጭት ጉዳት እንጂ ጥቅም ኪሳራ እንጂ ትርፍ ስለማይኖረው:: ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲጫረስ ክብሪት መጫራቸው ዛሬም ባይሆን ነገ የእሳቱ ወላፈን እንደሚያገኛቸው ማሰብ ያስፈልጋል::
እንግዲህ እነ ሀማስና እሥራኤል ዛሬ ላይ ደግሞ ምን ላይ ናቸው ብንል እራሳቸው በለኮሱት እሳት አምነዋቸው ድጋፋቸውን ለመስጠት አደባባይ ወጥተውም ሆነ በቤታቸው ቁጭ ብለው ያለቁትና የተላለቁትን እረስተዋቸዋል፤ እነሱ የሚወዳቸውን ቤተሰብ ጥለው ለአገራችን ብለው ሞተዋል፤ አሁን ላይ እነሱ አጀንዳ አይደሉም ፤ይልቁንም ይደግፋቸው የነበሩት መሪዎቻቸው በእነሱ ደም ላይ ቆመው ለመስማማት ሽር ጉድ እያሉ ነው:: ታዲያ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ይህንን አይተህ ወደራስህ ቤትና አገር አትመለስም፤እኔ የምደግፈው ፓርቲ ካላሸነፈ ዘራፍ የምንል ደጋፊዎች ከዚህ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል::
እነዚህ ሁለት መሪዎች እሳቱን ጭረው የጠማቸውን ደም እስኪበቃቸው ከደፉ በኋላ ለሕዝባቸው “የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገናል፤ ቤታችሁ ግቡ!” ብለዋል። በቃ ይኸው ነው መጨረሻው:: እንድትሞትላቸው ይፈልጉ ይሆናል እንጂ እነሱ አይሞቱልህም:: ስልጣን ላይ መውጣታቸውን አልያም መቆየታቸውን እስኪያረጋግጡ ድረስ ተደፈርን ተደፈርክ በርታ እያሉ ያበረታቱሀል፤ በኋላስ በኋላማ እርግጠኝነቱ ላይ ሲደርሱ በቃ ቤትህ ግባ ይሉሀል:: እኔ ደግሞ የምለው መጀመሪያም ከቤት አትውጡ:: ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ነው:: ምርጫችሁን በትክክለኛው መንገድ ስጡ:: ተበደልኩ የሚልም አካል ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ይዳኝ እንጂ አደባባይ መውጣት መፍትሔ አያመጣም::
ከሁሉም ገራሚው ነገር ደግሞ ሁለቱም ወገኖች እስከአሁን ሚዲያዎችን ያጨናነቁት፤ እነሱን አምኖ ለተጎዳው ሕዝብ ኀዘናቸውን በመግለፅ ሳይሆን፤ ከሕዝቡ እልቂትና ከሐገር ውድመት ያተረፉትን የየራሳቸውን ድል በማብሰር መሆኑ ነው።
በጠቅላላው ህዝብ ዱሮም ነበረ ፤ ዛሬም አለ ፤ ነገም ይኖራል:: ኢትዮጵያም ትላንትም ዛሬም ነገም ከዛ በኋላም ትኖራለች። ነገ የማይኖሩት ዛሬ እኛን አባልተውና አጋጭተው ነገ የራሳቸውን ድል ፣ አሸናፊነት ለማወጅ የጓጉት ሴረኛ ፖለቲከኞቻችን ናቸው። ስለዚህ ሴረኞች ፖለቲከኞች በሚቀዱልን ቦይ አንፍሰስ:: የኢትዮጵያ ህዝብ ዘመናትን አብሮ የኖረ ወደፊትም አብሮ የሚኖር የተዋለደ፣የተጋመደና እርስ በእርሱ የተሳሰረ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጠላትን በጋራ አሳፍሮ የመለሰና ነፃነቱን ያስከበረ ነው:: ይህን መልካም እሴት ለልጆቻችን ማስተላለፍ ይኖርብናል::
ዛሬ የተደቀነብንን አደጋ ተሻግረን ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች አገር የምናደርገው በጋራና በአንድነት መቆም ስንችል ነው:: ግጭቶችንና ጥቃቶችን በጋራ መከላከልና መፍትሔ በመስጠት ነው:: ስለሆነም ከሴራ ፖለቲከኞች ነፃ መውጣት የምንችለው ምክንያታዊ ስንሆን ነው:: እነ ሶሪያ፣ሊቢያና የመን ያሉ አገራት ከአጋጠማቸው እልቂትና ውድመት እኛ ብዙ ትምህርት መውሰድ አለብን::
በእምነት
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም