በአሁኑ ወቅት የዓለም ህዝብ በጋራ እየተጋፈጣቸው ከሚገኙ ችግሮች ውስጥ አንዱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ነው:: እአአ ህዳር 2019 በቻይና እንደተከሰተ የሚነገርለት ኮቪድ 19 ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ጊዜም ሁሉንም የዓለም ሃገራት አንድ በአንድ በማዳረስ የሉላዊነት ዘመን ትልቅ ማሳያ መሆኑን አሳይቷል:: በዚህ ጊዜ ውስጥም ከ166 ሚሊየን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎችም በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል::
በሃገራችንም ቫይረሱ ለመጀመርያ ጊዜ ከተገኘበት መጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከ268 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ ከ4 ሺህ በላይ ዜጎችም ህይወት አልፏል::
ይህ ፈተና ታዲያ ለሃገራችንም “በቡሃ ላይ ቆሮቆር” እንደሚባለው ከወቅታዊው የሃገራችን የፖለቲካ ምስቅልቅል እና የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ የመንግሥትና የህዝቡ ተጨማሪ ራስ ምታት በመሆን ከአንድ ዓመት በላይ ዘልቋል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ የስርጭቱ መጠን እየሰፋ፣ በአንጻሩ ደግሞ የህብረተሰቡ ጥንቃቄ እየቀነሰ ሄዷል::
ይህ ደግሞ አደጋው እየከፋ እንዲሄድ የሚያደርግ በመሆኑ ዛሬም “ጥንቃቄ አድርጉ” የሚል መልዕክት ከጤና ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ይነገራል:: ነገር ግን ከሚነገሩ መልዕክቶች ውስጥ ተግባራዊነቱ እየቀነሰ ሲሄድ ይስተዋላል::
በአሁኑ ወቅት ኮቪድን በመገናኝ ብዙሃን ወይም በወሬ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ከአጠገባችን ያሉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው አልያም የምንወዳቸውን የቅርብ ሰዎች ህይወት ተነጥቀን ማየት እየተለመደ መጥቷል:: ለሃገር ትልቅ ውለታ የዋሉ ታዋቂ ሰዎችንም በቫይረሱ እያጣን እንገኛለን::
ትላንት ያየናቸውና በቅርብ የምናውቃቸው ወዳጆቻችን ዛሬ ከጎናችን ሲለዩ እንደዘበት እያየን ችግሩን መላመዳችን ሌላ ማህበራዊ ቀውስ በመሆኑ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው::
በተለይ አሁን አሁን የምናያቸው የሠርግ እና የቀብር ስነሥርዓቶች ላይ የሚታደሙ ሰዎችን ሁኔታ ስንመለከት ቫይረሱ ምን ያህል ቦታ እንደተነፈገው እንረዳለን:: በቴሌቪዥን መስኮቶችም ቢሆን አልፎ አልፎ አንዳንድ ትላልቅ የመንግሥት ባለስልጣናት ጭምር በዚህ መዘናጋት ውስጥ እንመለከታለን::
ምንም እንኳን የመንግሥት ባለስልጣናት የህብረተሰቡ አካል ቢሆኑም መሪዎች ናቸውና ለእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ትኩረት መስጠትና ለሌላውም አርአያ በመሆን የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል::
ከዚህም በተጨማሪ አሁን አሁን ቀደም ሲል ቀንሰው የነበሩ ስብሰባዎችም ወደቀደመው ሁኔታ የተመለሱበትና ያለጥንቃቄ የሚካዱበትን ሁነት አልፎ አልፎ እንመለከታለን:: በመሆኑም እነዚህና መሰል የመዘናጋት ጥጎችን ቆም ብለን ማሰብ ከሁላችንም ይጠበቃል::
ይህንን ፈተና መሻገር የምንችለው አንድ ሆነንና በአንድ ልብ ተሳስበን መንቀሳቀስ ከቻልን ብቻ ነው:: ለዚህ ቻይናን በምሳሌነት መውሰዱ በቂ ነው። በቻይና ሁዋን ግዛት ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ በተወሰደው ዕርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ችለዋል።
እነሱ የሄዱበት መንገድና የወሰዱት ዕርምጃ ዛሬ ከመንግሥትና ከጤና ባለሙያዎች ከሚሰጡን መመሪያዎች የተለዩ አልነበሩም:: ውጤታማ የሆኑት የመከላከያ መልዕክቶችን በትክክል መተግበርና የራሳቸውንም ኃላፊነቶች በተገቢው መንገድ መወጣት በመቻላቸው ነው። ዛሬ ተከርችመው የነበሩ ቤቶች ተከፍተዋል። የተቋረጡ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል። ከወረርሽኙ ስጋትም ወጥተው ወደመደበኛ ህይወታቸው እየተመለሱ ነው::
በመሆኑም እኛም ከበሽታው ስጋት ተላቀን ኢትዮጵያን ለማሻገር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የድርሻችንን ለመወጣት እንችል ዘንድ የሚሰጡንን ምክረ ሃሳቦች በትክክል ልንጠቀምበት ይገባል:: ይህ ሲሆን ከፊታችን የተደቀነውን የጽልመት አደጋ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን ልንሻገር እንችላለን፤ ካልተጠቀምንበት ግን የምንመኛቸው መልካም ቀናት ይርቃሉ፤ የምናጣቸው ዜጎች የሚሰቃዩ ወገኖቻችንም እንዲሁ የበዙ ይሆናሉ።
በየቀኑ የምንሰማቸውን መጥፎ ዜናዎች ወደ መልካም ለመቀየር የጥንቃቄ ምክሮችን በቁርጠኝነት መተግበር፤ የነገ ተስፋዎቻችንን በእጃችን ለማስገባት በአንድ ልብ ሆነን ለመንቀሳቀስ ቃል መግባት ያለብን አሁን ነው።
በተለይ ለሠርግና ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን:: ለአንድ ቀን ደስታ ብለን ጥንቃቄ የጎደላቸው ተግባራትን ማከናወን ነገ ከማንወጣው አዘቅት ውስጥ የሚከተን በመሆኑ ጥንቃቄ አይለየን:: ከዚህ በተጨማሪ በገበያ ስፍራዎችም ቢሆን ማስክ በማድረግና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ራሳችንን ከኮቪድ 19 እንጠብቅ::
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ባጋጠመበትና መንግሥት በዚህ ላይ ከፍተኛ መረባረብ እያደረገ ባለበት ሁኔታ የኮቪድ 19 መስፋፋት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም:: በቀላሉ መከላከል የምንችለውን ኮቪድ 19 በራሳችን እንዝላልነት መከላከል ካቃተን በራሳችን ላይ ተጨማሪ አደጋ ማምጣት በመሆኑ በጤና ባለሙያዎች ለሚሰጡ ምክሮች ጆሮ ልንሰጥ ይገባል::
ይህንን ወቅት በጥንቃቄ ማለፍ ከቻልንና ለራሳችን፣ ለቤተሰባችንና ለማህበረሰባችን ተገቢውን ዋጋ ከሰጠን ይህ ቀን አልፎ የደስታ ቀን ይመጣል:: ያ ጊዜ ደግሞ ለሁሉም ነገር በቂ ነውና ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ኮቪድ 19ን እየተከላከልን በብልሐት እንለፈው::
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም