በጎልማሳነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው ነው። ማለዳ ተነስቶ እግሩ ወደመራው አቅጣጫ ተጉዞ ማታ ወደቤቱ የሚመለስ በሰፈሩ ያሉሰዎች በእለታዊ ተግባሩ የሚገረሙበት በውስጡ ያለውን ጦርነት በተግባር እየኖረ የሚውል ግለሰብ። ግለሰቡ አግባብ ባልሆነ መንገድ ከሥራ የተሰናበተ፤ በሰዎች የተጎዳ፤ በምድር ላይ ነገን እንዲናፍቅ የሚያደርግ አንዳችም ተስፋ ያልቀረለት ሰው ነው።
በመሆኑ ጥቅል በሆነ የሀዘን ስሜት ውስጥ ገብቶ እቤቱ መቀመጥ ጀመረ። ወንድሞቹና እህቶቹ ለውሎው የሚያስፈልገውን ለወጪ የሚሆን ገንዘብ እየሰጡት ከገባበት ጥልቅ ሀዘን እንዲወጣ ቢመክሩትም እርሱ ግን ዓለም በቃኝ ወደማለቱ አዘነበለና የዘወትር ተግባሩ እግሩ ወደመራው ሲኳትን ውሎ መመለስ ሆነ። ገንዘብ በማይኖረው ጊዜ መንገደኛን መለመኑን ቀስ በቀስም የለመደውም ሆነና በማህበረሰቡ ድጋፍ ተስፋ የመቁረጥ ህይወትን በየቀኑ ይኖራል።
በተመሳሳይ የህይወት ዘይቤ ውስጥ የሚገኙ በተስፋ መቁረጥ ጉዞ ውስጥ የሚገኙ አያሌ ሰዎች አሉ። በተስፋ መቁረጥ ድባቴ ውስጥ ቀናቸው ነግቶ የሚመሽባቸውን ቤታቸው ይቁጠራቸው። የጽሁፉ መነሻ ያደረግነው ጎልማሳ ከገባበት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሊያወጣው የሚችል፤ ያጣውን የሥራ እድል ሊያገኝበት የሚችል እድል ከሰፈሩ ደርሷል። አንድ ቀን ከቤቱ ወጥቶ የተለመደውን ጉዞ ለማድረግ ከቤቱ እምብዛም ሳይርቅ ከቤቱ አቅራቢያ የተለጠፈ የሥራ ማስታወቂያን ይመለከታል። የሥራ ማስታወቂያውን መስፈርት ሲያነበው እርሱ በሚገባ ሊያሟላው የሚችል መሆኑን ያስባል።
ደጋግሞ ማስታወቂያውን እያየ ጭንቅላቱን እየወዘወዘ እኔ ይህን ሥራ በሚገባ መስራት የምችል ሰው ነኝ፤ ግን እንደለመዱት በሴራቸው ያባርሩኛል። ምክንያቱም እቺ ምድር ለእንደ እኔ አይነቱ ሰው አትሆንም። በማለት ከቤቱ በር ላይ የመጣውን እድል ወደ ጎን አድርጎ፤ እንደ ለመደው እግሩ ወደ መራው ይቀጥላል። ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ያለሰው መድረሻው የማይታወቅ ጉዞ። በተስፋ መቁረጥ ዛቢያ ውስጥ የሚመላለስ ህይወት። በዛሬው ጽሁፍ ተስፋ መቁረጥን እንመለከታለን። አምስት ጥያቄዎችን በመጠየቅ በምንሰጠው ምላሽ ውስጥ በተስፋ መቁረጥ ለተከበቡ ሰዎች ተስፋን እንዘራለን፤ እንዴት መውጣት እንዳለባቸውም እንመካከራለን።
ተስፋ መቁረጥ የተሸናፊነትና የደካማነት ስሜት ማሳያ ሆኖ በስፋት ይገለጻል። ሰው በተስፋ ውስጥ የሚኖር ፍጡር ስለሆነ ተስፋ የሚያደርገው ነገር ከሌለው ህይወቱ በፈተናና በመከራ የታጠረ ሆኖ በከፍተኛ ውስጣዊ ጦርነት ውስጥ ያልፋል። ተስፋ የቆረጠ ሰው እሳቤው ነገ ላይ መሆኑ ቀርቶ በዛሬ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ዛሬም በሙላት ሳይሆን በቅጽበታዊ ትርጉም ውስጥ የሚያልፍ ነው። ግዴለሽ መሆንና ራስን መጣል መገኛቸው የትነው ከተባለ ተስፋ በቆረጡ ሰዎች ከተማ ውስጥ ቢባል አሳማኝ ነው።
1. ተስፋ መቁረጥ ምን ማለት ነው?
ተስፋ መቁረጥ ማለት በእኛ እንደሚሆን ያሰብነው፤ ልንቆጣጠረው እንደሚገባ ይሰማን ያልነበረው፤ እንደምንጠብቀው በዘላቂነት እንደማይሆን ሲገባን ወይንም ስንቀበል በውስጣችን የሚፈጠር የሥነ-ልቦና መቃወስ ነው። ተስፋ የቆረጡ የሚባሉ ሰዎችን ለማየት ስንሞክር የተስፋ መቁረጥ ልካቸው የተለያየ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። ነገርግን ሁሉንም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ሦስት ነገሮች አሉ። እነርሱም፣
• ሁኔታውን መቆጣጠር አለመቻል – ተስፋ የቆረጡ የምንላቸው ሰዎች ከተስፋ መቁረጣቸው በፊት የነበረው እይታቸው ነገሮችን ራሳቸው መቆጣጠር እንደሚችሉ ያስቡ የነበሩ መሆናቸው ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል። ተማሪ ከመምህሩ ፍጥነት ጋር እኩል እንደሚሄድ አስቦ በመስከረም ወር ውስጥ በከፍተኛ መነሳሳት ወደ ት/ቤት ይሄዳል። ተማሪው ከመምህሩ ጋር አብሮ መሄድ እንዳልቻል በተረዳ ጊዜ ግን የመምህሩን ፍጥነት ከእርሱ ትምህርት የመቀበልና የማጥናት ጋር አብሮ ሄዶ መቆጣጠር አለመቻል እንደሆነ ሲሰማው የትምህርት መጀመሪያው ላይ የነበረው ዓመቱን በመሪነት የማጠናቀቅ ጥረቱ ተስፋ እያነሰው ይመጣል።
በሂደትም እስከወዲያኛው በትምህርት ተስፋን የሚቆርጥ ሊሆን ይችላል። ተማሪዎች በየዓመቱ መስከረም ወር ውስጥ የበዛ ተስፋ እንዲሁም ወራት ወደ ሰኔ በተጠጉ ቁጥር የተስፋ መውረድ የሚገጥማቸው በመሆኑ ጥሩ ምሳሌዎቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። በጥልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገለጹ ባይሆኑም በተማሪነት ህይወት ውስጥ የተስፋ መቁረጥ ስሜቶች በየዓመቱ ይስተዋላሉ። መነሻው ደግሞ መቆጣጠር እንደሚችሉ ያሰቡትን መቆጣጠር አለመቻልነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ በሥራ ህይወት ውስጥ፣ በትዳር ህይወት ከትዳር አጋር ጋር ባለ ግንኙነት፣ በልጆች አስተዳደግ፣ በጉርብትና እና በጥቅሉ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ወዘተ እንዲሁ ነገሮችን ባቀዱት መንገድ መቆጣጠር አለመቻል ወደ ተስፋ መቁረጥ ይገፋል። መዳረሻው በተስፋ መቁረጥ መከበብ።
• በዘላቂነት መረታት – ሰዎች በዘላቂነት አንድን ነገር መቆጣጠር እንደማይችሉ ሲረዱ የሚገቡበት የውስጥ ጦርነት እርሱ ተስፋ መቁረጥ ነው። አንዲት እናት ልጇ በአጉል ሱስ ውስጥ ገብቶ ስታይ ልቦ ማዘኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ልጇ ከገባበት እስራት ለማውጣት መቀነቷን ፈትታ ባለመድሃኒት ፍለጋ ማድረግ የምትችለውን በሙሉ ታደርጋለች። ልጇም የእናቱን ስሜት ለማከም በማሰብ ካለበት አጣብቂኝ ለመውጣት ብዙ ሊሞክር ይችላል። ሁለቱም ያደረጉት ጥረት ሁሉ አልሳካ ሲል ተስፋ ወደመቁረጥ ምእራፍ ላይ ይደርሳሉ። ተስፋ መቁረጥ ማለት በአንድ ነገር በዘላቂነት መረታትን ማሳያ ነው። በዘላቂነት መረታትን ማመን ትክክል የሚሆንበት ቦታ ቢኖርም የህይወትን ምልዑ አቅጣጫ በአሉታዊነት በሚቀይርበት ሁኔታ ግን መሆን የለበትም።
• የሥነ-ልቦና ቀውስ – ሥነ-ልቦና ማለት ሰፊ ጽንሰ-ሃሳብ ነው። በሥነ-ልቦናችን ጤናማነት ዙሪያ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ። ተስፋ መቁረጥ አንዱ የሥነ-ልቦናችንን ውቅር ከሚወስኑ፤ የአስተሳሰብ መንገዳችን ከሚቃኙት መካከል ነው። ተስፋ ማጣት የሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ የገቡ ሰዎች ላይ በስፋት የሚታይ ነው። የሥነ-ልቦና ቀውስ ግን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችል መገንዘብም ተገቢ ነው። የሥነ-ልቦና ጤናማነት ለሁሉም ሰው የሚገባ ነው። ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚያልፍ ማንኛውም ሰውም የሥነ-ልቦና ምክር የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው።
2. ተስፋ መቁረጥ ማንን ያጠቃል?
ተስፋ መቁረጥ የተማረውን፣ ያልተማረውን፣ ሃብታሙን፣ ደሃውን፣ ወጣቱን፣ አዛውንቱን፣ ወንዱን፣ ሴቷን፣ አፍሪካዊውን፣ አሜሪካዊውን በአጭሩ ሰውን ሁሉ የሚያጠቃነው። ዛሬ ላይ በጉብዝና ከፍታ ላይ ያገኘነው ሰው የሆነ ጊዜ ላይ ተስፋ በመቁረጥ ድባብ ውስጥ ልናገኘው እንችላለን። ተስፋ መቁረጡ ግን ያለምክንያት የሚከሰት አይደለም፤ መነሻ ምክንያት ይኖረዋል። መነሻ ምክንያቱም ተስፋ የቆረጠው ሰው ጥፋት ወይንም የሌሎች ተጽእኖ ሊሆን ይችላል።
የእለት ጉርሱን ጥሮ ግሮ የሚያገኘውም ሆነ ለዓመታት የሚሆነውን በጎተራው ያደረገ ሁሉም ሰው በመሆናቸው ተስፋ በመቁረጥ ከበባ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። በሃብት ከፍታ ውስጥ የናጠጡ የሚባሉቱ ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ገመድ ፈላጊ ሆነው ስናገኛቸው ልንገረም የማይገባው ተስፋ መቁረጥ ሰው የተባለውን በሙሉ የሚመለከት በመሆኑ ነው። በእውቀት ላይ እውቀትን ደራርበው በመያዝ ምሳሌ የሆኑ የምንላቸው አንቱታን ያተረፉ ግለሰቦች አንድ ቀን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስናገኛቸው ተዓምር የተፈጠረ ሊመስለንም አይገባም።
በሁሉም ዘንድ ሊደርስ የሚችል፤ ሰው በገዛ እጁ ህይወቱን እንዲያጠፋ እስኪሆን ድረስ ሊያደርስ የሚችል በውስጣችን የሚከናወን ታላቅ ጦርነት መጠሪያ ስሙ ተስፋ መቁረጥ ነው።
3. ተስፋ ማድረግ እና መስጋትን በሚዛን ማድረግ እንዴት ይቻላል?
ተስፋ በሰው ልጆች ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው የማይዳሰስ ሃብት ብንለው ማጋነን አይሆንም። በገንዘብ ሆነ በቁሳቁስ ደረጃ ከሚገለጽ ሃብት ይልቅ በውስጣችን የሚብላላ የማይዳሰስ ሃብት አለ፤ ተስፋ ከማይዳሰሱ ውስጣዊ ሀብቶቻችን መካከል ከግንባር ቀደምቶቹ መካከል አንዱ ነው። ተስፋ በሰው ልጆች ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ ሰው ሁሉ ታላቅ ሰራተኛ፣ የሥራውን ፍሬ ለሌሎች ለማካፈል የሚፈልግ፣ ከሰው ጋር በመኖር ውስጥ ያለውን ትርጉም የሚረዳ፣ የለውጥ ሃዋርያ ለመሆን መነሳሳት ያለበት ወዘተ ሊሆን ይችላል። ተስፋ የነገ ስንቅ ነውና ነገን እያዩ ዛሬን መኖር አስደሳች የሚያደርግም ነው። ተስፋ ዛሬ ላይ በመገኘታችን ውስጥ በትላንት ውስጥ የረዳን አቅምም ነው። ተስፋ ዛሬን በአግባቡ መኖር እንድንችል የሚረዳ አሁናዊውም ሃብት ነው። ተስፋ ከማድረግ ወደ ኋላ ማለት ባለንበት ላይ እየረገጥን ለመኖር መወሰን ወይንም የምድር ቆይታችን እንዲያጥር በመሻት ውስጥ የሚገለጽ ነው።
ተስፋ ማድረግ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነገር ነው። ነገ ውስጥ እንዲህና እንዲያ እሆናለሁ ወይንም አደርጋሁ ብሎ በማሰብ ተስፋ ማድረግ አስፈላጊነቱ በጉልህ ይታያል። ተስፋ ከማድረግ ባሻገር ተስፋ ያደረግነውን በምናጣበት ጊዜ የሚፈጠረው ድካም እርሱ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚያስገባን እንዳይሆን ተስፋ አደራረጋችን በልክ መሆን አለበት።
ከአንድ እርከን የትምህርት ደረጃ ወደ ሌላው በተሄደ ቁጥር ለውጥ ላይ እንደሚደረስ አስበው ነገርግን ህይወት እዚያው መርገጥ የሆነ ሲመስላቸው ተስፋ በመቁረጥ በር ውስጥ ዘው ብለው ገብተው ምሽታቸውን በመሸታ ቤት በማሳለፍ ህይወታቸውን ትርጉም አልባ የሚያደርጉት እንዲሁ ብዙ ናቸው።
ተስፋ ማድረግ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይደለም፤ ነገርግን ተስፋ ያደረግነውን ያጣን መሆኑን ሲሰማን የሚገጥመን ተስፋ መቁረጥ የህይወታችንን አቅጣጫ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በሚጎዳ መንገድ መሆን ስለሌለበት በሚዛን መሆን አለበት። ስለሆነም ተስፋ ማድረግንና ተስፋ ማጣትን እንዴት በሚዛን ማድረግ ይገባል ብሎ ማሰብ ተገቢነቱ ጉልህ ነው። ተስፋ መቁረጥ ወይንም ያሰብኩትን ከማጣት የሚያቆመኝ የለም፤ እኔ የሞከርኩትን በሙሉ አገኛለሁ ወዘተ ከሚባል ከቅዥት ጋር ከሚጠጋጋ አስተሳሰብ መውጣት ይገባል። ሰው ስለሆንን በውስንነት ውስጥ የምንንቀሳቀስ መሆኑን መረዳት ይገባል። በውስንነት የምንንቀሳቀስ ስለሆነ ተስፋ ያላደረግነው ነገር ሊገጥመን ይችላል።
እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2016 በአሜሪካ በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሒላሪ ክሊንተን እንደሚያሸንፉ ደጋፊዎቻቸው እርግጠኛ ስለነበሩ የድምጽ ቆጠራ ተጠናቆ ውጤቱ በይፋ ከመታወቁ በፊት ደስታቸውን ለማክበር ዝግጅት እያዘጋጁ ነበር። በሃርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው ላይ ጽሁፋቸውን ያስነበቡ ኪኒያስ የተሰኙ ጸሐፊ ሁኔታውን ተስፋ በማድረግና ያሰቡትን ተስፋ በማጣት መካከል ያለውን ሚዛናዊ ቦታ በመፈለግ ረገድ ተጠቅመውበታል።
አንድ ነገር እንዳሰብነው ይሆናል በሚል በልበ-ሙሉነት ከሚያዝ አቋም ይልቅ እንዳሰብኩት ባይሆንስ በሚል እሳቤ ተደግፎ ሲከናወን መልካም ይሆናል። ማንም ሰው መውደቅን ባይፈልግም ባይሳካልኝ ብሎ እያሰበ የሚሰራ ሰው በሥራው የበለጠ ጥረትን እንዲጨምር እድል እንደሚሰጠው በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ጽፈዋል።
4. በተስፋ መቁረጥ ጊዜ ምን እናድርግ?
የተስፋ መቁረጥ ስሜት በከበበን ጊዜ ፈጥነን እጅ ከመስጠት በአግባቡ መዋጋት አስፈላጊ ነው። ጠቢቡ ሰለሞን በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው (ምሳሌ 24፡10) በማለት በመከራ ወቅት ጠንካራ ጉልበት ይዞ የመገኘትን አስፈላጊነት ይገልጻል።
ተስፋ መቁረጥ ሁላችንም ጋር ሊደርስ የሚችል መሆኑን ከተረዳን ተስፋ በመቁረጥ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን ማንሳት አስፈላጊ ነው። ተስፋ መቁረጥ እንዳለ ሁሉ ተስፋ ማድረጋችንን በሚዛን ማድረጉ ዋነኛው ነው። ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ በምንገኝበት ጊዜ ግን ምን ማድረግ እንዳለብን አስቦ መተግበሩ አስፈላጊ ነው።
በዓለማችን በተለያዩ ዘርፎች እንቱታን ያተረፉ ሰዎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ አልፈው ያውቃሉ። በተስፋ መቁረጥ ጊዜ ውስጥ ግን የተማሩትን ነገር ሲያስቡ የሰው ልጅ ለመከራ እጅ አልሰጥም ካለ እስከምን ድረስ በመሄድ ለሌሎች የሚተርፍ ትምህርት ይዞ እንደሚወጣ የሚያስረዳ ነው። በፖለቲካ ምክንያት በእስር ያሳለፉ ሰዎች የሚፈቱበትን ቀን ሳያውቁ ለዓመታት በእስር/በግዞት በሚሆኑበት ጊዜ የሚያልፉበትን የውስጥ ትግል በመጽሐፎቻቸው መግለጽ የተለመደ ነው። መቼ ከእስር ሊፈቱ እንደሚችሉ ሳያውቁ በጠባብ ጨለማ ክፍል ውስጥ ዓመታትን ማሳለፍ የሚፈጥረውን ስሜት ማሰብ ነው። በጠባብና በጨለማው ክፍል ውስጥ መሆን ከባዱ ነገር
በተስፋ መቁረጥ ጊዜ ማሰብ ያለብንን ለማሰብ የተሻለ ምሳሌ የሚሆን ምሳሌ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም በግዞት በጠባብ ጨለማ ክፍል ውስጥ ዓመታትን የሚያሳልፈውን ሰው በምናባችን እንሳለው። በጨለማ ጠባብ ክፍል ውስጥ አንድ ዓመት፣ ሁለት ዓመት፣ አምስት ዓመት፣ አስር ዓመት ወዘተ በሆነው ሰው ውስጥ ምን የሚብላላ ይመስለናል? ቀኖች በጨመሩ ቁጥር ጠባቡ ክፍል የእሬሳ ክፍልም እንደሚሆንም በማሰብ ተስፋ በመቁረጥ ጥግ ላይ መድረስም ይገባል። እንዲህ ከመሰለው ተስፋ መቁረጥ ወጥተው የጽናት ምሳሌ የሆኑ ግለሰቦችን ምድራችን ተመልክታለች።
በተስፋ መቁረጥ ድባብ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ልናደርግ የሚገቡን ሦስት ቁልፍ ነገሮች አሉ፤ እነርሱም፣
• በእምነት ውስጥ ነገሮችን መመልከት መቻል – እምነት የሰው ልጆች የዛሬና ነገ መገናኛ ድልድይ የተስፋ መነሻ ነው። ሰው ሁሉ ከየሃይማኖት የሚቀዳው እምነት አለው። ከእምነቱ መካከል በአይኑ አይቶት የማያውቀው ሁሉን እንደሚችል የሚያምነው ፈጣሪ ያለው መሆኑ አንዱ ተጠቃሽ ነው። በጨለማው ክፍል ውስጥ ያለው በዓመታት እድሜ ውስጥ ሙሉ ተስፋውን የተነጠቀ ሰው በምን ጉዳይ ላይ ተስፋ ሊያደርግ ይችላል፤ ከፈጣሪው በስተቀር። በመሆኑም በፈጣሪ ላይ የሚኖር እምነት፣ ከሞት በኋላ የሚኖር ህይወት መኖሩን የመረዳት እምነት፣ በታሪክ አጋጣሚ አንድ ቀን ከዛሬው ተስፋ አስቆራጭ ድባብ መውጣት እችላለሁ የሚለው እምነት እጅግ ወሳኝ ነው።
• ላለንበት ህይወት ትርጉም መስጠት – ዛሬ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባነው በሰዎች አሻጥር ቢሆን ስለ እውነት ዋጋ እየከፈለን እንዳለን ትርጉም በመስጠት በጽናት የመቆም አቅም ሊሆነን ይገባል እንጂ በመነሻችን ላይ እንደገጠመን ጎልማሳ መሆን የለብንም። ዛሬ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባነው በራሳችን ጥፋት እንደሆነ የምናምን ከሆነ በይቅርታ መንፈሳችንን በማደስ ውስጥ ሌሎች በተመሳሳይ መንገድ ውስጥ እንዳይገቡ እገዛ በማድረግ ጉዞችንን ትርጉም መስጠት አለበት አሁንም ጎልማሳው በራሱ ምክንያት በሩ ድረስ እንደመጣለት የሥራ እድል።
• በተመሳሳይ መንገድ ውስጥ ካለፉት መማር – መጽሐፍት በማንበብ፣ ቪዲዮ በመመልከት፣ ወይንም በአካል ሊሆን ይችላል በተመሳሳይ የተስፋ መቁረጥ ድባብ ውስጥ ያለፉ ሰዎች የትላንት ጉዞ መማር ያስፈልጋል። የተስፋ መቁረጥ ድባብ ሁሉም ሰው የሚያልፍበት በመሆኑ እከሌ ብለን በዚህ ጉዳይ ላይ የምናማክረው ሰው ባይኖር እንኳን በዙሪያችን ካሉ ሰዎች መካከል ሊሰማን ይችላል ብለን ለምናስበው ሰው ያለንበትን ሁኔታ አስረድተን ከተስፋ መቁረጥ ድባቡ ለመውጣት ጥረት ማድረግ ይገባናል።
5. ተስፋ የቆረጠ ሰው ሲገጥመን ምን እናድርግ?
በሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት በርካታ ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። የፖለቲካ አለመረጋጋት ሞትን፣ ስደትን፣ ቤተሰብ መበተንን፣ በጥቅሉ ለሞቱት ህይወትን በቁማቸው ላሉት ተስፋቸውን ማጣት ምክንያት እንደሆነ እንረዳለን።
ሰዎች ምን ማድረግ እስከማይችሉ ድረስ ደርሰው እያንዳንዱን ቀን ጥልቅ በሆነ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚመለከቱ በርክተዋል። እንዲህ ያሉ በቀውስ ውስጥ ተስፋ ቆርጠው የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ በዙሪያችን በበዛ ተስፋ ማጣት ውስጥ የሚያልፉ ይኖራሉ።
በመሆኑም ተስፋ የቆረጠ ሰው ሲገጥመን ምን ማድረግ እንዳለብን ማሰብ ይኖርብናል። ተስፋ በመቁረጥ ድባብ ውስጥ ልናደርገው የምንችለው ብዙ ነገር ቢኖር ዋናዎች ግን ሁለት ናቸው።
– አንደኛው መስማት – በዙሪያችን ያለ ተስፋ የቆረጠ ሰው እያስተላለፈ ያለውን መልእክት ለመስማት ጆሮችንን መስጠት። ያለበትን ሁኔታ በአግባቡ መረዳት። እያለፈበት ያለውን ነገር በሚገባ እኔ ብሆን ብሎ በማሰብ መስማት። ስለ ሰማናቸው ብቻ ከተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሊወጡ የሚችሉ ሊኖሩ ይችላሉና መስማትን አቅልለን አለማየት። በመስማት ውስጥ የምናሳርፋቸውን ብዙ ናቸውና በአቅማችን ማድረግ የምንችለውን ማድረግ እንድንችል በሚረዳ መንገድ እንስማቸው።
– ሁለተኛው ማድመጥ – በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ወደ ትኩረታችን የሚመጡ የበረከቱ ጉዳዮች አሉ። ከነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ትኩረት የምንሰጣቸው ጉዳዮች ማለት የምናደምጣቸው ጉዳዮች ማለት ናቸው። የምናደምጣቸው ጉዳዮች ላይ ማድመጣችን በተግባር የሚረጋገጠው ለጉዳዮች በምንሰጠው የተግባር ምላሽ ነው። ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሲገጥሙን ልናደርገው የሚገባው ነገር መስማት ብቻ ሳይሆን ማድመጥም ተገቢ ነው። በተግባር በምክር፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በጊዜ ወዘተ አብረናቸው በመቆም ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲወጡ ማድረግ ይገባል።
በጽሁፋችን መነሻ ላይ የገለጽነው ጎልማሳ የሚሰሙት እና የሚያደምጡት እንዲያገኝ መሻታችን ከሆነ በዙሪያችን ያሉትን ለመስማትና ለማድመጥ በመፍቀድ ለተግባር እርምጃው አንድ ወደፊት እንበል። ሰላም።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013