ስልጠና፣ ስብሰባ ወይም ለየግል ጉዳይ ሲባል ከከተሞች መውጣት የተለመደ ነው። እግረ መንገድ ጉብኝት ይኖራል። ወጣ ማለት ከዋና አላማው በተጨማሪ የሚሄዱበትን አካባቢ ለመጎብኘት፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመጠቀም ወይም ለመመልከት እድል ይፈጥራል። ያው የአገር ውስጥ ቱሪስት እንደ ማለት ነው። በነዚህ ከተሞች እንደደረሱ ታዲያ መጀመሪያ መቀመጫዬን እንደሚባለው ለማረፊያ የሚሆነውን ሆቴል ማጠያየቅ አይቀርም። የሚችሉትን ያህል የተሻለ በሚባለው ሆቴል ለማረፍ መረጃ ያጠያይቃሉ። በኋላ አልጋ ቶሎ ካልያዙ ያልቅና ፍለጋው አድካሚ ይሆናል። ከጎን ማረፊያ ሌላ ጥሩ ምግብ የት እንደሚገኝም እንዲሁ መጠየቆት አይቀርም።
በከተሞቹ የሆቴል አገልግሎት ችግር የለም። አቅም የፈቀደውን መጠቀም ይቻላል። በየከተሞቹ የሆቴል አገልግሎት ተስፋፍቷል። አዳማ፣ ሀዋሳ የመሳሰሉት ከተሞች ልክ እንደ አዲስ አበባ ሽቅብ በማደግ ላይ ናቸው። በርካታ ባለወለል ህንጻዎችን በብዛት መመልከት ይቻላል። ከእነዚህ ህንጻዎች መካከል አብዛኞቹ የሆቴልና ሆስቴል አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። ህንጻዎቹ የከተሞቹን ለውጥ የሚናገሩ ብቻ ሳይሆኑ በሆቴል አገልግሎት በኩል ያለውን ክፍተት የቦታ ውስንነት ሳይገድባቸው ለመሙላት የቻሉ ናቸው ማለትም ያስደፍራል። አብዛኞቹ ባለአራት ወለል ናቸው። ከሩቅም ከቅርብም ሲታዩ ያምራሉ። ግቢያቸውም ጽድት ያለ ነው።
በአልጋው ዋጋ ላይ ለውጥ የሚያመጡ የተለያዩ አገልግሎቶች አሉ። ቴሌቪዥን ካለው ዋጋው ይጨምራል። ዋይፋይ ሌላው ዋጋ ከፍ የሚያደርግ አገልግሎት። ወደ ሆቴል ቤቶቹ ወይም ሆስቴሎቹ ሲሄዱ በቅድሚያ አልጋ ስንት ብር እንደሆነ ይጠይቃሉ። ቀጥሎ የሚያነሱት ትልቁ ጥያቄ ስለ “ዋይፋይ” መኖር አለመኖር ነው፤ ካለም ስለፍጥነቱ ማንሳቶ አይቀርም። በዚህ ዘመን ዋይ ፋይ ወሳኝ ነገር ነዋ! መኖሩን ሲያረጋግጡ “አንድ እዳ ቀለለ” ብለው የአልጋ ይከፍሉና ይወጣሉ። ውሃ ፣ አጎቨርና የመሳሰሉት አይኖሩም ብለው አያስቡም። ውሃውም ከጠፋ በባሊ ይቀርባል፤ ሀገራዊ ችግር ነዋ! ስለዚህ አልጋዎትን ይዘው እፎይ እንዳሉ ወደ ጉዳይዎ ይሄዳሉ።
የሄዱበትን ከተማ ዞር ዞር ብለው ጎብኝተው አሊያም ጉዳዮትን ሲጨርሱ ወደ ሆቴሉ የመመለሻ ጊዜ ይደርሳል። ያን ግዜ ነው አልጋ ክፍል ገብተው አንዳንድ ነገሮችን ሲፈትሹ በመጸዳጃ ቤት ጠረን የሚቸገሩት። ይሁን እንጂ የዚህ ችግሩ ውሃ እንደልብ አለመኖር ነው ብለው ይገምታሉ። እሱ ብቻ ግን ችግር አይደለም የመጸዳጃ ቤቶቹ እቃዎች በእብዛኛው የወላለቁ ናቸው። አንዳንዶቹ ግድግዳዎች በፍሳሽ የወየቡ ሆነው ያገኙዋቸዋል። ይህም ሁኔታ የክፍሎቹን ማራኪነት ይቀንሰዋል። በውሳኔዎ ሊፀፀቱም ይችላሉ።
ክፍሎቹ ቶሎ ቶሎ እድሳት የሚደረግላቸው አይመስሉም፤ በግድግዳዎቹ ላይ ከሚታዩት ነገሮች መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። ይቀፋል። ቢቻል ቶሎ ቶሎ ማደስ አለባቸው፣ ቢያንስ ግድግዳው በውሃ እንዲጸዳ ቢደረግ ችግሩ ሊታይ አይችልም። ለነገሩ ገበያው ካለ ችግር የለባቸውም። የንግድ ስፍራው ባለቤቶች “ዋይ ፋይ” ስላለ እሱ ላይ ተተክለው ሁሉንም እንደሚረሱዋቸው ያስባሉ።
አንዳንዴ የሚያጋጥመው ደግሞ ይገርማል። እስቲ ሀዋሳ በአንድ ወቅት የሆነው ላጫውታችሁ። ከአመታት በፊት አምስት መቶ ብር ከፍዬ የያዝኩት አልጋ ቴሌቪዥኑ አልሰራ ብሎ ቡና ቤት ተከታትዬ ተመልሼ ተኛሁ። ይህ ትንሽ ነው። ሶኬቶች ፣ የቧንቧ እቃዎች የፊት መታጠቢያ መስታወት የአጎበር ችግር በስፋት ይታያል።
አጎበር በተለይ ለወባማ አካባቢዎች ወሳኝ ነው። ምን ለወባ ብቻ ቢንቢ ለሚባዛባቸውም ጭምር ወሳኝ ነው። አሁን አሁን ግን አጎቨር ብሎ ነገር በየሆቱሉ አታዩም። ካለም ተቋጥሮ የከረመ ነው፤ ስትፈቱት የተቀዳደ ጠረኑም የሚገፋተር ሊሆን ይችላል። ዋይፋይ ካለ ሌላው ምን ይሰራል! ይገርማል።
ቢንቢ ሲያናፋቦት ያድራል። በተለይ በወባ ተይዘው የሚያውቁ ከሆነ እነሱን ሲያባርሩ እንቅልፍ የሚባል በቅጡ ሳያዩ ያድራሉ። አልያ ደግሞ ሲጠበጠቡ ማደር ነው፤ ቲማቲም መምሰል አለ። ይሄ ሁሉ ችግር እያለ አጎበር ማስቀረትን ምን አመጣው? ተቆጣጣሪው አካልስ ይህን ለምን አይከታተልም?እርግጥ ነው ሀገራችን ወባን ጨምሮ በተላላፊ በሽታዎች መከላከል ተጠቃሽ ሀገር ለመሆን በቅታለች። ተጠቃሽ ትሁን እንጂ በሽታዎቹን አጥፍታለች ማለት ግን አይደለም። ወባ ከሀገሪቱ ጠፋ ተብሎ በይፋ አልተነገረ፤ መጥፋቱ በይፋ የተነገረው ፈንጣጣ መሰለኝ።
ሌላው የዚህ ዘመን የአልጋ ክፍል ወሳኝ አገልግሎት ዋይ ፋይ ነው። ቴሌቪዥን ችግር የለውም። ሁሉም ተገልጋይ ዋይ ፋይ ይፈልጋል። በዚህ መረጃ ዘመን በከተሞች ከማህበራዊ ሚዲያ ተለያይቶ የሚኖር ሰው የለም። ገንዘብ ካላጠረው በቀር በሞባይል ዳታ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉትን አገልግሎቶች ሁሉም ይሞካክራል።
ዜናው፣ ሙዚቃው፣ ከስራ ጋር የተያያዙ መረጃዎች መለዋወጡ የሚካሄደው በሞባይ ስልኮች ነው። በማህበራዊ ሚዲያ፣ ኢ-ሜይል እና በመሳሰሉት አማካይነት ነው፤ ሞባይል ስልኮች በዳታ ቢሰሩም ዋጋው ውድ ስለሆነ ሁሉም ዋይፋይ ያሳድዳል። በሞባይል ዳታ ወጪው አይችልም “ ይህ አገልግሎት ካለ የአልጋው ችግር የለውም” ብለው ነው አንድም ሰዎች በአልጋ ዋጋ ብዙም ሳይደራደሩ የሚይዙት። እነ “ፌስ ቡክ፣ ዩ ቲዩብ” ላይ በርካቶች ተጥደው ይውላሉ፤ ያድራሉ። እሱን ሳይፈታትሽ የሚውል የሚያድር የለማ።
ዋይፋይ ይህን ያህል ቢፈለግም የሆቴል ቤቶቹ ዋይ ፋይ ግን የልብ የማያደርሱ ወይም ጨርሶም የማይሰሩ የሚባሉ አይነት ናቸው። ሌሊት ተነስተው ወይም ማለዳ ላይ ካልሆነ በቀር ኔትወርክ አይኖርም። ይገባል፤ ይወጣል። እነዚህ ሆቴሎች “ዋይ ፋይ አላቸው” ብለው በጊዜ ገብተው ሲሞክሩ ቢያመሹና ቢያድሩ ኔት ወርክ ላያገኙ ይችላሉ። ብለው ብለው ሲያጡ ይተኛሉ፤ ይነጋል፤ ከሆቴሉ ጋር ይፋታሉ።
የሆቴሎች ዋይ ፋይ አልጋ ማሻሻጫ እንጂ ደንበኞችን መጥቀሚያ አይደለም። ለዚያውም እኮ ደንበኛው ለስብሰባ ለስልጠና ወዘተ የሄደ ሊሆን ይችላል። ቀን ላይ ዋይ ፋይ የሚጠቀመው በስብሰባው ቦታ ነው። ከዚያም ሲወጣ ከተማ ለማየት ዞር ዞር ይላል። ከሁለት ሰአት በፊት ወደ ሆቴሉ አይመለስም። የጸጥታና ደህንነት ጉዳይ እያሳሰበው ካልሆነ በቀር አምሽቶ ቢገባ ይመርጣል። እንደገባም ተጣጥቦ አረፍ እስከሚል ድረስ ዋይፋዩን አይፈልገውም። ከዚያም አብዛኛውን ሰአት በመኝታ ያጠፋል። በቀረችው ጊዜ ነው ከዋይ ፋይ ጋር የሚፋጠጠው። ቢሉት ቢሉት ዋይ ፋይ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ ነው የሚለው።ችግሩ የሆቱሉን ተገልጋይ ታሳቢ ያደረገ አቅም ያለው ዋይፋይ አለማዘርጋት ነው። የይስሙላ አግለግሎት ነው ያለው። የከፈልክበትን እኮ ነው የሚከለክሉህ።
ሆቴሎቹ ግንባራቸው ያምራል፤ ግቢያቸውም ችግር የለበትም። አገልግሎታቸው በተለይ የይስሙላው የዋይፋይ አገልግሎት ጉዳይ ግን መፍትሄ ይፈልጋል። ዘመኑ የመረጃ ነው። ማህበራዊ ሚዲያው አንዳንዶች ላልተገባ ነገር ስላዋሉት አይጠላም። ይህን አገልግሎት ማስገኘት የሚችለውን የዋይ ፋይ መስመር ከሆቴሉ ቁመና ጋር የሚመጥን ማድረግ ያስፈልጋል። ህንጻ ቢቆልሉት ብቻውን ትርጉም የለውም። ህንጻው ተገልጋይ የሚፈልገውን የዋይፋይ አገልግሎት ይዞ መገኘት አለበት። አለበለዚያ ሰዎች በድጋሚ የሚይዙት ሆቴል ሊሆን አይችልም። ዋይፋይ አልጋ ማሻሻጫ መሆኑ መቅረት አለበት።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013