ክፍል ሁለት
በክፍል አንድ ጽሑፌ ከፍል ውኃ እስከ እንጦጦ በተዘረጋው ታሪካዊ ጎዳና ግራና ቀኝ የተከማቹትን በርካታ ተቋማት በመቃኘት ታሪካዊ ፋይዳቸውን ለማሳየት ተሞክሯል። ተቋማቱ የተሸከሙትን የታሪክ አሻራ በተመለከተ “በነበር” ማጉላቱና መዘከሩ ባይከፋም ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው ግን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ከተደረጉት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች ጋር ተቋማቱ በየግላቸው ግቢ ውስጥ ታሪካቸውን በቋሚ መዘክርነት እያደራጁ የማስተሳሰሩን ሥራ ቢተጉበት ሊኖረው የሚችለውን ሀገራዊ ጠቀሜታ በተመለከተ በጥቂቱም ቢሆን ለመጠቆም ተሞክሯል።
በዚህ በሁለተኛው ክፍል ለማሳየት የሚሞከረው ከክፍል አንድ ቀጣይ የሆነውን የጎዳና ዳርቻ ተቋማት ታሪካዊ ዳሰሳ ነው። መነሻችን የለገሃር ባቡር ጣቢያ ሆኖ ሽቅብ በቸርችል ጎዳና ወደ ላይ በመውጣት ማረፊያችን መሃል አራዳ ከሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ይሆናል። የለገሃር (ላጋር) ባቡር ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1894 ዓ.ም ሲሆን አጀማመሩንም በተመለከተ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የስዊስ ዜጋ ለነበረው አልፍሬድ ኢልግ እና ለፈረንሳዊው የንጉሡ አማካሪ ለሊዮን ሸፈኔ “የኢትዮጵያ መንግሥት ምድር ባቡር ኩባንያ” በሚል ስያሜ ለ99 ዓመት የሚቆይ ኮንሴሽን ከሰጡ በኋላ ነበር። በዚህም ታሪካዊ ምክንያት የተነሳ ይህ ኩባንያ የመጀመሪያው የሀገሪቱ የግል ኩባንያ ሊሆን ችሏል።
ኩባንያው ሥራ ከጀመረ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የአድዋ ጦርነት በመጀመሩ እንቅስቃሴው ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በፈረንሳይ መንግሥት ውሳኔ እንደገና እ.ኤ.አ በ1897 ዓ.ም የመጀመሪያው የሐዲድ መንገድ ዝርጋታ ሥራ ከጅቡቲ ተጀምሮ ድሬዳዋ የደረሰው እ.ኤ.አ በ1900 ዓ.ም ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ጋር የተያያዘና በዘመኑ የፖለቲካ አካሄድ ጥርጣሬ ስለነበራት እ.ኤ.አ በ1908 ዓ.ም ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ተጨማሪ ስምምነት በመደረጉ የቀድሞ ስሙ ተቀይሮ “የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ምድር ባቡር ኩባንያ” ተብሎ በመሰየም ሥራው ሊቀጥል ችሏል። በዚህ ስምምነት መሠረትም የሐዲድ ሥራው በ1917 ዓ.ም አዲስ አበባ ደርሶ በመጠናቀቁ መደበኛ የጭነትና የመንገደኞች ማጓጓዝ ተግባሩን በስፋት ማካሄድ ጀመረ። እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም እንደገና ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ስምምነቱ ታድሶ ሁለቱ መንግሥታት እኩል የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው በመደረጉ ጽህፈት ቤቱ ከፓሪስ ወደ አዲስ አበባ ሊዛወር ችሏል።
ጅቡቲ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ ከመውጣቷ ጋር ተያይዞም በኩባንያው ስም ላይ መሻሻል ተደርጎበት እ.ኤ.አ በ1981 “የጅቡቲና የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ድርጅት” በመባል ሥራውን ቀጥሏል። ይህ ኩባንያ ግዙፍ ታሪካዊ ፋይዳ ተሸክሞ ሕዝብ የሚማርበትና ተመራማሪዎች ሊጎበኙት የሚገባ የረባ ቋሚ ኤግዚቢሽን ባለማደራጀቱ ግን ለብዙ ዜጎቻችን ዛሬም ድረስ ኩባንያው “ባዕድ” ባለሀገር በመሆን ባቡርን በሚያሞግሱ ዘፈኖች ብቻ እየማለልን ለመኖር ግድ ሆኗል። ከመሸ በኋላም ቢሆን የከተማው አስተዳደርና አዲሱን የባቡር ፕሮጀክት የተረከበው ተቋም ተነጋግረው ኩባንያው ደረጃውን የሚመጥን ቤተ መዘክር ማቋቋም ቢችል ለከተማችን አንዳች የታሪክ ከፍታ ሊፈጥር እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ከለገሃር ፊት ለፊት የቆመው የይሁዳ አንበሳ ሐውልትም የሚያኮራ ታሪክ ስላለው እንዲሁ ልዩ ትኩረት ቢሰጠው አይከፋም። ጉዟችንን ሽቅብ በመቀጠል በእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር በሰር ዊንስተን ቸርቸል ስም በተሰየመው ዋና አውራ ጎዳና ግራና ቀኝ በሚገኙት ታሪካዊ ተቋማት ላይ እንደተለመደው የወፍ በረር ቅኝት እናድርግ። ይህ ታላቅ የከተማችን ጎዳና ሌጋሲው የተሸረበው ከተጠቃሽ በርካታ ታሪኮች ጋር ብቻም ሳይሆን የባህላዊ ይዘት ካላቸው ቅርሶችም ጋር ጭምር ተሸምኖ ስለሆነ በተለየ ሁኔታ ሊታይ ይገባዋል። ብዙ ቀደምት እናቶች የማይዘነጉትና ወጣቱ ትውልድ ምናልባትም አልሰማ ከሆነ “ቸርችር ጎዳና” በሚል ስያሜ የጋሞ ጠቢባን ያስተዋወቁት ዝነኛና ተወዳጅ የሴቶች የሀገር ጥበብ ዲዛይን ብዙ እናቶቻችን የተማርኩበት የወቅቱ መዋቢያ ነበር።
በቸርችል ጎዳና በአንቺ አረማመድ፣
እንዴት ይዘለቃል ይህ ሁሉ መንገድ።
ተብሎ በግጥም መወደሱም ይህንኑ እውነታ ለማመላከት ይመስላል። አንድም የመንገዱን ውበት፤ አንድም የጥበቡን ማራኪነት ለማድነቅ።
በቸርችል ጎዳና ግራና ቀኝ የተሰደሩት ታሪካዊ ተቋማት በቁጥር በርከት ስለሚሉ ለመጠቃቀስ የሚሞከረው ዋና ዋናዎቹን ብቻ ይሆናል። ፋሽስቶች ለራሳቸው ጉዳይ ይገለገሉበት የነበረው የዛሬው ራስ ሆቴልና መደዳውን የተደረደሩት ግንብ ቤቶች ልብ ተቀልብ ሆኖ በእዝነ ልቦና ላደመጣቸው የሚመሰክሩት ብዙ ቀደምት ትዝታ አላቸው። ሆቴሉ ከመጠጥ፣ ከምግብና ከመኝታ አገልግሎት ውጭ ማሰብ ባለመቻሉ ግን በታሪክ የአደራ ሸክም እንደቃተተ ዕድሜውን ይገፋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በ“ጦቢያ” ስም ለተሰየመ የኪነ ጥበባት ትዕይንት፣ የመጻሕፍት ምርቃና ለመሰል ዝግጅቶች በሩን ከፍቶ በማስተናገዱ በእጅጉ ሊመሰገን ይገባል።
ሆቴሉን ተጎራብቶ ያለውና በተሸከመው የጥበብ አደራ ግዝፈቱ ከፍ ብሎ የሚታየው የብሔራዊ ቴያትር ቤትና ከፊት ለፊቱ የቆመው የአንበሳ ሐውልት ለከተማችን እንደ መሪ መልካ ምድራዊ ምልክት (Laned Mark) የሚታዩ ቅርሶች ናቸው። ይህ አንጋፋ ቴያትር ቤት የዕድሜውን ያህል ታሪኩን በቋሚ መዘክርነት አደራጅቶ ለሕዝብ ክፍት ቢያደርግ የከተማችን ተወዳጅ ሙዚዬም የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። ቴያትር ቤቱ አዲስ በሚያስገነባው ሕንጻ ውስጥ ይህ የመዘክር ማደረጃ ክፍል ሳይታሰብበት እንደማይቀር ተስፋ በማድረግ ነገን በትዕግስትና በትዝብት እንጠብቃለን።
በኃላፊነት ከሚያስተዳድረው ከብሔራዊ ቴያትር ጋር “የቡና አጣጭ” ያህል ቅርበት ያለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በግቢው ውስጥ ያለው የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ድርጅትም ለቸርችል ጎዳና በቅርበት ከሚጠቀሱት ታሪካዊ ተቋማት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ከቤተ መጻሕፍቱ ውጭ” ከዘፍጥረቱ ጀምሮ ታሪኩን በወጉና የማዕረጉን ልክ ያህል አደራጅቶ አለመያዙ ብቻም ሳይሆን ለብዙ ዓመታት የኖረው አንዴ “ስፖርት” አንዴ “ማስታወቂያ” አንዴ “ወጣቶች” በአሁኑ ወቅት ደግሞ “ቱሪዝም” የሚሉ መጣያ ስሞች እየተለጠፉለት ፍዝዝና ድንግዝ ብሎ እንዳንጎላጀጀ ነበር።
ዛሬም ድረስ ከፍዘቱ ነፃ ስለመውጣቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እርግጥ ነው የሀገሪቱ ቅርሶች የተከማቹበት የብሔራዊ ሙዚዬም ተቋም የሚገኘው በዚሁ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሥር መሆኑ አልጠፋንም። በዚህ ዐውድ ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ግን በራሱ ግቢ ውስጥ የሚኒስቴሩን ክብር በሚመጥን መልኩ ታሪኩን የሚያስተዋውቅ ቋሚ መዘክር ቢያደራጅ አይጠቅመውም፤ አይጠቅመንም ወይ? ለማለት ነው።
በዚሁ ታሪካዊ የቸርችል ጎዳና ጠርዝ ላይ ከሚገኙት ተቋማት መካከል አንዱ የብሔራዊ ቴሌቪዥንና ሬዲዮኑን የሚመራው ተቋም ሕንጻ ነው። ሰማኒያ አምስት ዓመት እድሜ ያስቆጠረው (መስከረም 1928 ዓ.ም ተመሠረተ) የብሔራዊው ሬዲዮና በ1957 ዓ.ም የቋቋመው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ታሪክና የዓመታት ጉዞ በአግባቡ ተደራጅቶ ለጎብኚዎች ተደራሽ ቢሆን ፋይዳውና ጠቀሜታው በእጅጉ አስፈላጊ በሆነ ነበር። በተለይም ኃይሉን አጠናክሮና በወረራ አቅሙ የሙጥኝ ብለን ለተጣበቅንበት የማሕበራዊ ሚዲያ ምርኮኝነት ጥሩ ማለዘቢያ ዕውቀትና ማንቂያ ሊሆን ስለሚችል ሳይውል ሳያድር ቢታሰብበት አይከፋም።
በነሐሴ ወር 1934 ዓ.ም ልደቱ የተበሰረለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ወርቅ የተጎናጸፈው የብሔራዊ ባንክ ለሌሎች ተቋማት የተላለፈው መልእክት ቢደርሰው መልካም እንደሆነ እናስባለን። ከቸርችል ጎዳና በስተቀኝ ስላሉት የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የፖስታና የቴሌኮሚዩኒኬሽን መስሪያ ቤቶች በቀዳሚው ጽሑፌ ላይ ስለጠቀስኳቸው ደግሜ አልከልስም። ጥቂት ወደ ላይ ከፍ ስንል የምናገኘው የዘመነ ደርግ ዘካሪ የ“ትግላችን ሐውልትም” እንደ እንጀራ ልጅ ገፋ ገፋ ተደርጎ ትኩረት ባይነፈገው መልካም ነው። የቀድሞው ልዑል መኮንን የዛሬው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልም በሕዝብ መዋጮ ከመገንባቱ ጋር ተያይዞ ታሪካዊ አሻራው ደማቅ እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም።
ወደ ላይ ከፍ ስንል የምናገኘው የቴዎድሮስ አደባባዩ ሴባስቶፖል ሐውልትና “በሰይጣን ቤት” የተሰየመው የመጀመሪያው ሲኒማ ቤትም እጅግ ከፍ ያል ታሪክ እንዳላቸው ለማናችንም እንግዳ አይደለም። በተለይም በሁለት የእንግሊዝ ጄኔራሎች ስም በተሰየመበት መስቀልያ መንገድ ላይ የሚገኘውና በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ደራስያን ማሕበር ፕሬዚዳንት በክቡር ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ግፊት ስያሜውን ያገኘው የቴዎድሮስ አደባባይ ብዙ ታሪኮችን አምቆ የያዘ ስለሆነ ታስቦበት ቢጠና ብዙ እውቀት ባጋራን ነበር።
አሁን መዳረሻችን ወደ ሆነው አራዳ እየተቃረብን ነው። አራዳ ማለት ወጣ ገባ የሆነ ጉብታማ ሥፍራ ማለት ነው። ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዝቅ ብሎ ዛሬ ማዘጋጃ ቤቱ ካረፈበት ቦታ ጀምሮ ወደ ደቡብ (አሮጌው ፖስታ ቤትን ጨምሮ) የተዘረጋውን ሰፊ ሥፍራ የሚያካልለው የጥንቱ የአራዳ ገበያ ለአዲስ አበባ ከተማ በንግድና በባህል ማእከልነት ማገልገሉን ታሪክ ይነግረናል።
በአራዳ ገበያ ውስጥ ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በሜዳ ላይ ተዘርግተው ሸማችና ሻጭ የሚራኮትበት የደራ የገበያ ማዕከልም ነበር። በዳሶች ሥር እየተጠለሉ መሥራት ከጀመሩ የሀገርኛ ነጋዴዎች ጎን ለጎን የውጭ ዜግነት የነበራቸው፤ በተለይም የግሪክ፣ የዐረብ፣ የአርመንና የህንድ ዜግነት የነበራቸው ነጋዴዎች ሱቅ እየሠሩ ዘመናዊ የንግድ ሥራ ማካሄድ የጀመሩትም በዚሁ አካባቢ ነበር። በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ የመጀመሪያ ዓመታት የንግዱ እንቅስቃሴ ወደ መርካቶ እንዲዛወር ቢደረግም ሱቆቹ ግን የአራዳ (የፒያሳ) መለዮዎች ሆነው ዘልቀዋል። ሲኒማ ቤቶችም ተከፍተው አራዳ የንግድ ብቻ ሳይሆን “የባህል ማእከልነቱንም” ድርሻ ይዞ ሊቆይ ችሏል።
በወቅቱ አራዳ ገበያን የማይጎበኝና በአራዳ ውስጥ የማይሸጥ የሸቀጥ ዓይነት አልነበረም። ለአልባሳት የሚውሉት፤ አቡጀዲ፣ መብሩቅ፣ መርዶፋና ካኪ ሜዳ ላይ ተዘርግተው ይሸጣሉ። የዕጣኑ፣ የሉባንጃው፣ የከርቤውና የአርቲው መዓዛማ ጠረን ገበያተኛውን እንዲጠራ ተደርጎ ይደረደራል። ቃጭሉ፣ ጨሌው፣ ዶቃው፣ ወለባው፣ ጉትቻውና የእግር አልቦው ቆነጃጅትን እንዲማርክ ተደርጎ ይሠደራል። ዘይቱ፣ ሽቶውና ላምባው የሰውን አቅም ባገናዘበ ሁኔታ በመስፈሪያ እየተቀዳ በሩብም በአላዳም ይቸረቸራል።
የበርኖስ፣ የቡልኮና የሸማ ተራውም በተመደበለት ቦታ ገዥን ይጣራል። ዛሬ የኢየሩሣሌም መታሰቢያ ህንፃ ከቆመበት ቦታ ጀምሮ ወደ ታች ያለው ሥፍራ እህል፣ ሣርና፣ ጭድን የመሣሰሉት የሚሸጡበት ክልል ነበር። ዝቅ ብሎም የሙዝ፣ የሎሚ፣ የትርንጎና የሸንኮራ አገዳ መሸጫ ቦታዎች ይገኙ ነበር። ማዘጋጃ ቤቱ ከሚገኝበት ሥፍራ ይካሄድ የነበረው የገንዘብ ለገንዘብ መንዛሪዎች ጨርቅ አንጥፈው አላዱን፣ ሩቡን፣ መሀለቁን፣ በዓይነት በዓይነቱ ደልድለው ቅንስናሽ ገንዘብ ይመነዝሩ የነበረ መሆኑንም ታሪክ ያጫውተናል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ትዕዛዝ ታህሣሥ 26 ቀን 1899 ዓ.ም. ፓኖያሊያስ ሜሪያሊስ ከተባለ መሀንዲስ ጋር የስምምነት ውል ተፈርሞ ሥራው ተጀምሮ በኋላም ካስቴኛ በተባለ ኢጣሊያዊ ኢንጂነርና ኦርፋንዲያስ በተባለ ግሪካዊ አርክቴክት አማካይነት በዘመነ ንግሥት ዘውዲቱ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ዜና መዋዕሉ ይተርካል። ከፍ ባለ ግርማ ሞገስ የቆመው የምኒልክ ሐውልትም በራሱ ዳጎስ ካለ መጻሕፍት የበለጠ ታሪክ ያስነብባል።
የሀገር ፍቅር ቴያትር ቤትን፣ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራን ተከትሎ በፒያሳ አካባቢ የተስፋፉትን የሲኒማ ቤቶች፣ ሆቴል ቤቶችንና (ጣይቱ ሆቴል ሳይዘነጋ) ሌሎች በርካታ ታሪካዊ ምስክሮችን ብናስታውስ ባልከፋ ነበር። ችግሩ የጋዜጣው አርብ ጥበትና የርእሱ ስፋት ልናስታውስ የፈቀደልን ይህን ያህል ብቻ ነው። በእነፃ ላይ ያለው የአድዋ ሙዚዬም ሥራ ከግብ ሲደርስ መዘክሮችን አጠቃሎ ለትውልድ በማቆየቱ ረገድ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል በማመን ቅኝታችንን እዚሁ ላይ እንገታለን። ሰላም ይሁን!
ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013