ክፍል አንድ
“ነበር ለካንስ እንዲህ ቅርብ ኖሯል?”
“የእንጦጦ ከተማ ቤቱም ዕድሞውም ስላማረ ብርዱ እጅግ የበረታ ነው:: ነገር ግን ከእንጦጦ በታች ካለው ፍል ውሃ ለመታጠብ አጼ ምኒልክም ወይዘሮ ጣይቱም ወርደው ነበር::” (ታሪከ ነገሥት ዘ ዳግማዊ ምኒሊክ – ገጽ 138::”
“…እቴጌ ጣይቱ ፍል ውሃ አካባቢ ቤት ለመሥራት ለንጉሡ ጥያቄ አቅርበው ስለተፈቀዳላቸው ከፍል ውሃ ከፍ ብሎ በሚገኘው ጉብታ ላይ ቤተ መንግሥት አሠሩ:: በኅዳር ወር 1889 ዓ.ም እንጦጦን ለቀው ወደ ፍል ውሃ ወርደው በመቀመጥ አካባቢውን ለመኳንንቱ ከፋፍለው በመስጠት ቤት እንዲሰሩ አደረጉ:: ይህ የእቴጌ ጣይቱ የሠፈራ ዕቅድ የመጀመሪያው የከተማው መሪ ፕላን ተደርጎ የሚቆጠረው ስለዚሁ ነው::” (አዲስ አበባ ባለፈውና በአዲሱ ሚሌኒየም – ገጽ 6::)
“እቴጌ ጣይቱ ለመጨረሻ ጊዜ…በኢያሱ ትዕዛዝ በሰኔ ወር 1908 ዓ.ም ከጊቢ (ቤተ መንግሥት) እንዲወጡና እንጦጦ ወደሚገኘው የቀድሞ መኖሪያቸው እንዲሄዱ ተደረገ::” (ሀብቴ አባ መላ ከጦር ምርኮኝነት እስከ አገር መሪነት – ገጽ 173::)
እቴጌ ጣይቱ በፍል ውሃው ጠበል ተማርከው አዲስ አበባ ብለው በሰየሟት ከተማቸው ውስጥ ታላቁን ቤተ መንግሥት በአስደማሚ ውበትና ፕላን በማሳነጽ ለ19 ዓመታት ያህል በተድላና በደስታ ከባለቤታቸው ከአጤ ምኒልክ ጋር ኖረውበታል:: ከንጉሡ ህልፈት በኋላም በወራሴ ዙፋን ተፋላሚ ኃይሎች መካከል በተጎነጎነ ሤራና ተንኮል ተጠርጥረው በግዞት ወደ መጀመሪያው የእንጦጦ ቤታቸው ተግዘው እንዲዘጋባቸው ተደርጓል::
በዚህን መሰሉ ዝግ ሕይወት ውስጥ በግዞት ላይ በነበሩበት አንድ ዕለት በጊቢያቸው ውስጥ ነፋስ ለመቀበል ወዲያ ወዲህ ሲሉ ከእንጦጦ ወደ ፍል ውሃ የተዘረጋው ዋና አውራ ጎዳና ወለል ብሎ በዕይታቸው ውስጥ ይገባል:: ግር እንዳላቸውም በቅርባቸው የነበረችውን ደንገጡራቸውን ጠርተው “እቴዋ ይህ ጎዳና ወዴት የሚያደርስ ኖሯል?” በማለት ይጠይቋታል:: ምስኪኗ ተጠያቂም ግር እንደተሰኘች “እመቤቴ ሆይ ይህ ጎዳና እኮ እርስዎ ራስዎ ቆመው ያሰሩትና ከእንጦጦ ወደ ፍል ውሃ የሚያጋጥመው ታላቁ አውራ መንገድ ነው፤ እንዴት ዘነጉት?” ብላ ብትመልስላቸው እቴጌይቱ በትዝታ ቅዝዝ እንዳሉ “አዬ ነበር ለካንስ እንዲህ ቅርብ ነው” በማለት መለሱላት ይባላል::
“ይወስዳል መንገድ፤ ያመጣል መንገድ”
የጣይቱ ርዕይ የወለዳት አዲስ አበባ ዕድሜዋ ከመቶም ዘሎ ሦስት ዐሠርት ተኩል ታክሎበታል:: ስሟ ገንኖ የእድሜዋን ልክ ያህል ወግ ርቋት የኖረችው ይህቺ አዲስ አበባችን ፀዳሏ እየፈካ መድመቅን የተያያዘችው ከሦስት ዓመታት ወዲህ ነው ቢባል ለሙግት አይዳርግም:: ቢያሟግትም መብት ነው::
በተለይም ከፍል ውሃ ወደ እንጦጦ በተዘረጋውና “በነበር” የተገለጸው ነባር ጎዳና ዛሬ ወግ ደርሶት እኛም የትናንቱ መልኳ ትውስ ሲለን “ለካስ ነበር እንዲህ ቅርብ ነው” እያልን ለመገረም አብቅቶናል:: ለመሆኑ እስከ ዛሬ እንጦጦና ፍል ውሃ የዐይንና የቅንድብ ያህል ተጎራብተው እየኖሩ እንዴት እርስ በእርስ ለመናበብና ለመተሳሰር ተሳናቸው? ይህ እንዳይሆንስ ሀገራዊ አዚም የጣለብን ምን ይሉት የሥርዓት ክፋት ነበር? ብለን ብንጠይቅ ተገቢ ይመስለናል::
ልክ እንደ ጣይቱ ሁሉ የዘመናችን ባለ ርዕይ ለሆኑት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምሥጋና ይሁንና የጎዳናውና የአካባቢው ታሪክ በእጅጉ እየገዘፈና እየተለወጠ በመሄድ ላይ ነው:: ስለዚህ ታሪካዊ ጎዳና መለስተኛ የወፍ በረር ቅኝት በማድረግ አንዳንድ እውነታዎችን ለመዳሰስ እንሞክራለን::
መነሻችን የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች ይሁኑ እንጂ ዙሪያቸውን የከበቧቸው ታሪካዊ ተቋማትም በቅኝቱ ውስጥ ተካተዋል:: የፍል ውሃ አካባቢ በራሱ አንድ ታላቅ የታሪክ ሙዚዬም ነው:: የተከበበውም በአንጋፋዎቹ የመከላከያ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቶችና በፖስታና በቴሌኮሚዩኒኬሽን ተቋማት ነው:: እነዚህ ተቋማት ከ1900 ዓ.ም በፊትና በኋላ መቋቋማቸውን ልብ ይሏል:: በፍል ውሃው ራስጌና ግርጌ የኢዮቤልዩ፣ የታላቁ ቤተ መንግሥታትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የክብር ጥላቸውን አርበበው ለአካባቢው ትልቅ ሞገስ እንዲሰፍንበት ምክንያት ሆነዋል:: የአንጋፋዎቹ የፊንፊኔ፣ የሂልተንና የሸራተን ሆቴሎችም የአካባቢው የማዕድ ቤት መሆናቸውን ጠቁሞ ማለፉ አይከፋም::
ጉዟችንን ቀጥለን ወደ ላይ ከፍ በማለት በአውራ ጎዳናው ግራና ቀኝ የምናገኛቸውን ዋና ዋና ሞገሳማ ታሪካዊ ተቋማት በንስር ዐይን እንፈትሻቸው:: የፓርላማውና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሕንጻዎችና የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልን በቀኛችን እያስተዋልን፣ በግራችን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ግንብን እየታከክን ጥቂት እርምጃዎችን ተራምደን በሚያዝያ 27 የድል አደባባይ ላይ ቆመን ዙሪያ ገባውን ስንቃኝ እንደመማለን::
በእግራችን የትምህርት ሚኒስቴር መስሪያቤት እና በድንጋይ ውርወራ ርቀት የሚገኙት የመቶ ዓመት ባለዕድሜው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትና የ80 ዓመት አዛውንቱ የፕሬስ ድርጅት የታሪካችን ካዝናዎች መሆናቸው ይታወሰናል:: በስተቀኝ የሚገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲና አንጋፋው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤቶች ለሀገራችን ሥልጣኔ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በመዘከር ኮፍያችንን ዝቅ አድርግን በማመስገን ሽቅብ ጉዟችንን እንቀጥላለን:: በቅርብ ርቀት የሚገኘው የጥንቱ የአራት ኪሎው የወወክማ አሻራም የሚደበዝዝ አይደልም::
በስተግራ የመንፈሳዊ ሞገስ ተደርቦለት የቆመው የቤተክህነቱ ሕንጻና ተጎራባቹ ብሔራዊ ሙዚዬም የሺህ ዘመናት ቅርሶችና ታሪክ ባለቤቶች መሆናቸውን ጠረናቸው ይመሰክርልናል:: በስተግራ የቴክኖሎጂው ፋኩልቲ ግዘፍ ነስቶ ቆሟል:: ጥቂት እልፍ ስንልም አብሮ አደጎቹ የገንዘብና የፍትሕ ሚኒስቴር (ዛሬ ጠቅላይ ፍርድ ቤት) መስሪያ ቤቶች የመቶ አሥራ ሦስት ዓመት ጓደኝነታቸው እንዳስቀና ዛሬም ድረስ እንደተፋቀሩ ተጎራብተው ይገኛሉ:: ከፍ ስንል የየካቲት 12 የሰማእታት ሐውልት ስሜታችንን እያነዘረ ዝቅ በማለት ለሰማእቱ ክብር ሰጥተን እንድናልፍ ግድ ይለናል:: ተጎራባቹና ተመሳሳይ ስም የሚጋሩት የየካቲት 12 (በቀድሞ ስሙ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ሆስፒታልም የአደባባዩ ተጨማሪ ሞገስ እንደሆነ እናስተውላለን:: አልፍ ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ደጃፍ ላይ እንደርሳለን:: በትውልዶች መካከል የነውጥና የለውጥ እሳተ ገሞራ መፍለቂያ ምንጭ የሆነው ይህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጠረኑ ብዙ የታሪክ ሁኔታዎችን ያስታውሰናል:: ከጀርባው ያለው የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ትዝታም እንዲሁ በራሱ የታሪክ መዓዛ ሲያውደን ይታወቀናል::
ከዩኒቨርሲቲው ፊት ለፊት ጺሙን እንደተንዠረገገ የቆመው የማርክስ ሐውልት “ዐይናችሁን ላፈር ተብለው ጥንብ እርኩሳቸው እንደወጣው” እንደ ቀደምት ጓደኞቹ ተሰባብሮ ከመወገድ ተርፎ የዘመነ ሶሻሊዝምን ወቅት ፍንትው አድርጎ ያሳየናል:: ከጀርባው ያለው የቀድሞው የየካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት የዛሬው የኢኮኖሚና ቢዝነስ ፋኩልቲም የዘመነ ደርግን ወታደራዊ መንግሥት በህሊናችን እንድንስል ቅሪት ሆነው መቆማቸው ይታወሰናል::
ከፍ እያልን ስንሄድ ዝነኛው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሳንወድ በግድ “ነዎሩ!” ብለን እጅ እንድንነሳው ያስገድደናል:: ከበላዩ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም “ለምን በሙሉ ዐይን ትመለከቱታላችሁ” በሚሉ የሴኪዩሪቲ ዘቦች ቢታጠርም ዐይናችንን አንሸዋረን ገርምመነው ማለፋችንን የተረዱት አይመስልም:: ትንሽ ራመድ ስንል ታሪካዊውና ብዙ ያልተዘመረለትን የስዊዲሽ ሚሲዮን (የዛሬውን እንጦጦ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን) ታክከን እናልፍና የጋሞ ጠቢባን በተራቀቁበት የሀገር ባህል አልባሳት መሸጫ ውቂያኖስ ውስጥ ተዘፍቀን ስንደነቅ ራሳችንን እናገኛለን:: በዚያ የደራ ገበያ መካከል የሚገኘውና በ1924 ዓ.ም ማስተማር የጀመረው የቁስቋም ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት ለስንቱ የሀገሪቱ ምሁራን መፍለቂያ እንደሆነ ከቀድሞ ተማሪዎቹ መካከል ዶ/ር ንጉሤ ተፈራና በቅርቡ በህልፈተ ሕይወት የተለዩት የደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ሻለቃ ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ቢመሰክሩ ኖሮ ብዙ እውቀት ባስጨበጡን ነበር ያሰኛል::
ፈውስ ፍለጋ ለጠበል ከሚተሙት ምእመናን ጋር እየተጋፋን የእንጦጦ አቀበትን ስንያያዝ በስተ ግራ የምናገኘው የራስ አበበ አረጋይ መኖሪያ ቤት የነበረውንና በአሁኑ ወቅት የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል በመባል የሚታወቀውን የጤና ተቋም እየታከክን ሽቅብ ገስግሰን የምናርፈው ባለ ርዕዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ባስዋቡት የእንጦጦ መናፈሻ ውስጥ ይሆናል::
የእንጦጦ መናፈሻ እንዲህ በቀላሉ በወሽመጥ ትረካ ተጠቅሶ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን ብዙ የሚጻፍለት ስለሆነ ወደፊት ጊዜው ፈቅዶ ከጊዜ ላይ ቆርሶ ሲያድለን የምንለውን እንላለን:: እንዲያው በደምሳሳው ግን ከፍል ውሃ (የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች መነሻችንን አድርገን) እንጦጦ መናፈሻ እስክንደርስ ድረስ እቴጌ ጣይቱ ቆመው ባሰሩት አውራ ጎዳና ግራና ቀኝ የምናስተውላቸው ታሪካዊ ተቋማት በሙሉ ከግዝፈታቸውና ከተሸከሙት ትርጉም አንጻር ስንመረምራቸው የተመሠረቱት በአጋጣሚ ወይንስ ሆን ተብሎ ታቅዶ? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን::
“ታሪክ ለዕውቀት ይሆናል መሠረት”
ለሦስተኛ ጊዜ አንድነትን፣ የወዳጅነትንና የእንጦጦን ፓርኮች አሳምረው ለሰጡን ባለ ርዕዮችና አሻራቸውን በተለያዩ ሙያቸው ላኖሩት የሀገራችን ባለውለታዎች ኮፍያችንን ዝቅ አድረገንና ከወገባችን ጎንበስ ብለን ምሥጋና በመቸር በራስ ሙግት ጥቂት የሃሳብ ጉዞ እናድርግ::
አንድ ሀገር ጎብኚ ባዕድ ባለሀገር (ቱሪስት) ወይንም ተወላጁ ባለሀገር የታችኞቹን የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች ጎብኝቶ ብቻ ሽቅብ ወደ እንጦጦ ፓርክ እንዲገሰግስ ታቅዶ ከሆነ ብንሟገትበት አይከፋም:: ለምንስ ከላይ ከዘረዘርናቸው ባለ ታሪክ ተቋማት ጋር አይጋመድም ወይንም በዘመናዊው የሀገራችን የፖለቲካ አገላለጽ አይደመሩም ብለን መጠየቅ የምንችል ይመስለኛል:: ለምን ቢሉ ፋይዳው ከፍ ያለ ስለሆነ::
እርግጥ ነው አብያተ መንግሥታቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሕዝብ መዝናኛነትና መናፈሻነት እየተለወጡ መሆናቸውን እያስተዋልን ነው:: በቅርቡ እንኳን በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ እንዳሉ ደርሰንበታል፤ በደጃፉም ስናልፍ ተንጠራርተን ያየናቸው ጅምሮች የሚያጓጉ እንደሆኑ ተገንዝበናል:: ይህ ጥረት ብቻ ሳይሆን ለባለ ርዕዩ ተጨማሪ አንድ ከፍታ የሚጨምር አሻራ ነው:: ሌሎቹ ተቋማትስ? በተለያዩ የዓለም ሀገራት እንዳሉቱ በየፊናቸው ታሪካዊ ሙዚየም ወይንም የሚጎበኙ ታሪካዊ እሴቶችን አደራጅተው ለሕዝብ ክፍት ቢያደረጉ አይጠቅም ይሆን?
ለምሳሌ የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤቶች (ፓርላማውና ፌዴሬሽኑ) የራሳቸውን አጥር በማይደፈር በሚመስል የብረት አጥር ከርችመው ብቻ እንደተፈሩ ከሚኖሩ ይልቅ ለባለቤቱ ለሕዝቡ ታሪካዊ ሙዚየዬም ወይንም የኤግዚቢሽን ማሳያ ቦታ አደራጅተው ታሪካቸውን ለዜጎችና ለባዕዳን ቢያስጎበኙ አይበጅም ትላላችሁ? ይህ ጸሐፊ በአንድ ወቅት ለምርምር ሥራው ጥቂት ሰነዶችን ማመሳከር ፈልጎ የፓርላማውን ቤተ መጻሕፍት ለመጠቀም ይቻል እንደሆን ሲጠይቅ የደረሰበትን ግልምጫና ዘለፋ በተመለከተ ከአሁን ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ትዝብቱን አስፍሮ ማስነበቡ አይዘነጋም:: በአንጻሩ የአሜሪካውን የነጩን ቤተ መንግሥት ለመጎብኘት በተገኘበት አጋጣሚ የተደረገለትን ሸብ ረብ ማስታወሱም አይረሳም:: እነዚህ ሁለት “የሕዝብ ቤቶች” ወደ እውነተኛ “የሕዝብ ባለቤትነት” ተመልሰው ሙዚዬም ቢያደራጁ ጠቀሜታው የትየለሌ እንደሆነ መገመቱ አይከብድም::
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ሆኑ በ1900 ዓ.ም የተቋቋሙት አንጋፋዎቹ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የሺህ ዘመናት ባለታሪኳ ቤተክህነት (ለ2000 ዓ.ም የሚሌኒየም በዓል እንደተደረገው)፣ ባለ መቶ የዕድሜ ባለፀጋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትም ሆነ ፕሬስ ድርጅቱ የየራሳቸውን ታሪክና የረጅም ዘመናት ጉዞ በቋሚ ኤግዚቢሽን መልክ ቢያደራጁና ከአዳዲሶቹ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር ለታሪካዊው ጎዳና ተጨማሪ ታሪክ ቢያክሉ ፋይዳው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም:: በተለይም አንድ የሀገር ጎብኚ በአንድ ቀን ብቻ መዲናዋን ጎብኝቶ ከመሄድ ይልቅ ለቀናት ያህል በየተቋማቱ ጉብኝት በማድረግ ለቱሪዝም እንፉቅቃችን መፍትሔ ሊሆን ስለሚችል የሰማ ላልሰማ ሃሳቡን አጋርቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፈጠራ ዱካ ቢከተል በእጅጉ ሊጠቅም ይችላል:: ለዜችጎም ቢሆን በታሪክ የመናቆሩን አባዜ አለዝቦ በራስ ታሪክ የመኩራትን ጸጋ ሊያጎናጽፍ ይችላል:: ሰላም ይሁን!
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013