የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቁልቁል ሲምዘገዘግ ቆይቶ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ጀምሯል:: የሀገሪቱ የወጪ ንግድ ከአምስት ዓመታት ቁልቁል ጉዞ በኋላ ባለፈው በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘት ተችሏል:: በዚህ ዓመት ደግሞ ከ2012 ዓ.ም የተሻለ የወጪ ንግድ አፈጻጸም እየተመዘገበ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ::
ትናንት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 29 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች:: በዚህም የእቅዱን 85 በመቶ ማሳካት ችላለች:: በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር በ380 ሚሊዮን ዶላር ወይም 16 በመቶ ብልጫ እንዳለው የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል::
ከ2012 ወዲህ በዘርፉ መታየት የጀመረው መነቃቃት በዚህ ዓመትም መቀጠሉን ከሪፖርቱ መረዳት ይቻላል:: ሀገሪቱ ከፍተኛ አለመረጋጋት እና የኮሮና ወረርሽን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት የወጪ ንግድ ላይ ስኬት ማስመዝገብ መቻሏ የራሱ አንድምታ እንዳለው እና በቀጣይም የእድገቱን ዘላቂነት ለማስቀጠል የተለያዩ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያብራራሉ::
የምጣኔ ሀብት አማካሪው አቶ አብስ ጌታቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መጠነኛ መሻሻል መታየት ጀምሯል:: በዚህ ዓመት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የወጪ ንግድ ገቢ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ዘላቂነት ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ ሰጪ ነው:: ሀገሪቱ ብዙ ችግሮች ውስጥ ሆና በዘርፉ ውጤት እንድታስመዘግብ ያስቻላት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ የሚሉት አቶ አብስ፤ በተለይም ባለፉት ዓመታት የተገነቡና ወደ ስራ የገቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጪ ንግዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ እንዲቀጥል የራሱን ሚና ተጫውቷል ይላሉ::
ሀገሪቱ ከባድ የጸጥታ አለመረጋጋት ውስጥ ብትሆንም አብዛኞቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥበቃ እየተደረገላቸው ስራ መስራታቸውን ቀጥለዋል:: በመሆኑም ለወጪ ንግድ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እያመረቱ ናቸው:: ይህም የወጪ ንግድ ገቢ እንዳይቀዛቀዝ ብሎም መሻሻል እንዲያሳይ ሚና ተጫውቷል የሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል::
እንደ አቶ አብስ ማብራሪያ፤ የአንድ ሀገር የወጪ ንግድ አፈጻጸም በራሱ ብቃት ላይ ብቻ የሚመሰረት አይደለም:: የሌሎች ተወዳዳሪ ሀገራት ሁኔታም ወሳኝነት አለው:: ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የወጪ ንግድ ምርት የሚያመርቱ እና ከኢትዮጵያ ጋር የሚወዳደሩ ሀገራት ላይ ኮሮና ጫና ውስጥ መግባታቸው እና ወረርሽኙ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ አነስተኛ መሆኑ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ መሻሻል እያሳየ እንዲቀጥል የራሱን ሚና ተጫውቷል::
የወጪ ንግድና አየር መንገድ ቁርኝት እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ አብስ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ በዓመቱ ያሳየው ጥሩ አፈጻጻም በወጪ ንግድ ዘርፍ ለታየው መልካም አፈጻጸም አስተዋጽኦ ነበረው የሚል እምነትም እንዳላቸው ይናገራሉ:: በዘርፉ የተመዘገበው ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አብስ ሌላው ቢቀር እንኳን ተቋሙ አሳካለሁ ብሎ ያስቀመጠውን ውጥን አለማሳካቱ መሰራት ያለበትን ያህል እንዳልተሰራም አመላካች ነው:: አሳካለው ካለው ውስጥ 15 በመቶውን ማሳካት አልቻለም::
እንደ አቶ አብስ ገለጻ፤ እቅዱ እንዳይሳካ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፤ ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ ያስከፈላት ጦርነት መካሄዱ እና የወጪ ንግድ ምንጭ የሆኑት አንዳንድ ምርቶች ጦርነቱ ከሚካሄድበት አካባቢ የሚገኝ መሆኑ በዘርፉ ለማሳካት የታቀደው ግብ እንዳይሳካ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል:: ሰላምና መረጋጋት የወጪ ንግድን ጨምሮ ለሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስኬት ወሳኝ ነው ፤ በቀጣይ ጊዜያት በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሀገሪቱ ወደ ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስ ማድረግ ያስፈልጋል:: የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል:: ከዚያ ባሻገር ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ መቀየስም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: ሰላምና ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ማቀናጀት ከተቻለ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገቡ ይቻላል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013