ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል። አሳሳቢ፣ አስደንጋጭ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ የሚመስሉ ችግሮች ከውስጥም ከውጪም ይታያሉ። ሀገሪቱ ወደፊት ስትስፈነጠር ወደ ኋላ ለመጎተት የሚሞክሩ ገመዶችም ብዙ ናቸው። በሀገር ውስጥ ልዩነትን ከማክረር፣ ከስልጣን ሽኩቻ እና ጥቅመኝነት ጀምሮ እስከ ውጪዎቹ ጣልቃ ገብነት ድረስ ጋሬጣዎቹ በርካታ ናቸው። እስኪያልፍ ቢያለፋም እያንዳንዱ ፈተና በጥበብ፣ በአመራር ብቃት ፣ በትዕግስት እና በመስዋዕትነት መታለፉ ግን አይቀሬ ነው።
ይህ በውስጥም በውጪም የሚታየው የጠላት መብዛትና ማንዣበብ ደግሞ የኢትዮጵያ መጻኢ ጊዜ ብሩህ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ጨለማው አልፎ ብርሃኑን ለማየት ደግሞ ጨለማውን በብርሃን መተኪያውን መንገድ መሥራትና ምሰሶ ማቆም ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል። ኢትዮጵያውያን የውስጥ ልዩነቶቻችንን አሳድረን አንደ ቀደሙት አያት ቅድመ አያቶቻችን በአንድነት ከተነሳን ጨለማው በብርሃን፤ ስጋቱ በተስፋ፤ ድክመቱ በጥንካሬ አንደሚለወጥ ጥርጥር የለም።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ነች። በቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች። የራሷ አኩሪ ታሪክ ባለቤት። ይሄ ታሪኳና ጀግንነቷ ግን በልጆቿ ጽናት የተገኘና ማንም ሰጥቶ የሚነጥቃት አይደለም። ኩሩዎቹ ልጆቿ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ዳር ድንበሯን አስጠብቀው ያስረከቡን ሀገር ናት።
አባት እናቶቻችን የሀገራችን ሉአላዊነቷ ሳይደፈር ሊወሯትና ቅኝ ሊገዟት የመጡትን ሁሉ የሽንፈት ካባ እያከናነቡ ታሪክንም ሀገርንም ለዛሬው ትውልድ አስረክበዋል። እኛም የተረከብናትን ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ከነችግሩ ሳይሆን ችግሩን ተጋፍጠን ፤ልማቱን አፋጥነን የተሻለች ሀገር አድርገን ሊሆን ይገባል። አባት እናቶቻችን ያቆዩልንን ታሪክ አድሰን ልማቱን አሳድገን ስምና ዝናዋን አስጠብቀን መሆን አለበት። ለዚህም ከልመና ነፃ የሚያወጣንን ልማት በተጠናከረ መልኩ በህብረት እየሠራን እንገኛለን።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ዕድገት ጥንካሬና መጪ ተስፋ ያስደነገጣቸው ጠላቶች ለማደናቀፍ ሩጫ ቀጥለዋል። መስኮቱን ከፍቶ ለተኛ ሰው በቤቱ ሌባ አይገባበትም ብሎ ማሰብ አይቻልም ፤ አሁን በሀገራችን ያለው ግጭት ለሌባ መስኮት ከፍቶ እንደመተኛት ነው። አሁን ገርበብ ብሎ የተከፈተውን መስኮት ተጠቅሞ የውጪው ኃይል
ወደቤታችን ሊገቡና ተነስ ተቀመጥ ሊሉን ማሰባቸውን በሚያወጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች እየታዘብን ነውና። የሃይማኖት፣ የብሄር ፣ የፖለቲካ ልዩነት ያለን ብንሆንም በሀገራችን ጉዳይ እንዲሁም ክብሯን ለመንካትና ሉአላዊነቷን ለመገዳደር ለሚመጣብን ግን ዳር ድንበሯን የማናስደፍር ህብረ ብሄራዊ አንድነት ያለን ዜጎችም ነን።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ናት። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ሁሉም ወገን እንደ ዓይኑ ብሌን የሚጠብቀው የህዳሴው ግድብ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ጥቂት ወራት ናቸው የቀሩት። ይሄ ዕረፍት የነሳቸው የውጪና የውስጥ ጠላቶቻችን ደግሞ ስኬቱን ለማደናቀፍ አቅደውና ሳይታክቱ እየሠሩ ናቸው። ታሪካችንን ያልተገነዘቡ አንዳንዶችም በሀገር ውስጥ ጉዳዮቻችን ገብተው አለቃና መሪ ለመሆንም ከጅለዋል። ይሄን አድርጉ ይሄን አታድርጉ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጪዎች እስከመሆን ደርሰዋል። ይሄ በየትኛውም ሉአላዊት ሀገር ላይ የማይሞከር ፤ሀገርንም ዜጋውንም የናቀና የደፈረ ተግባር ነው።
ስለሆነም ‹‹እኛ እናውቅላችኋለን ስናሞኛችሁ ዝም ብላችሁ ተቀበሉ›› ዓይነት በልጅነት ጊዜ ያለፈ ጨዋታ በሀገር ላይ ለመጫወት የሚሞክሩ ኃይሎችን አንድ ሆነን ከሀገራችን ላይ ዓይናችሁን ንቀሉ ልንላቸው ይገባል። በውጪም በውስጥም ያለን ዜጎች ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ለአገራችን ሉዓላዊነትና ክብር ድምፃችንን ከፍ አድርገን ልናሰማም ይገባል።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ወሳኙ ህዝብ እንጂ ጣልቃ ገብና ተላላኪዎች ሊሆኑ ከቶ አይገባም። የውጪ ኃይሎች የኢትዮጵያ ጉዳይ በዚህ ደረጃ ያሳሰባቸው እውነት ለሀገራችንና ለህዝባችን አስበው ነውን? ብሎ መጠየቅም ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ነው። አንዴ በብሄር ሌላ ጊዜ ደግሞ በሃይማኖት ለማናከስና ለማባላት ያልተሞከሩ ያልተጠነሰሱ አጀንዳዎች አልነበሩም። ሆኖም ግን አስተዋዩ ህዝብ ዓይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ የተወረወሩ ወቅታዊ ቦንቦችን ሁሉ በጥንቃቄና በዘዴ አልፏቸዋል። አሁንም በየአቅጣጫው ሀገር ለማፍረስ ህዝብን ለማጫረስ የሚለቀቁ የግጭት መንገዶችን መዝጋት፤ ለሀገራችን ሉአላዊነት አንድ ሆኖ መቆምና እጅ ለመጠምዘዝ የሚከጅሉትን ጉልበት አለን ባዮች ሁሉ በአንድነት ማውገዝ ይገባል። ኢትዮጵያ ሉአላዊት ሀገር እንደመሆኗ የማንንም ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ድምፃችንን ደግመን ደጋግመን ማሰማት ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2013