ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የኦሮምኛ ሙዚቃን በመሰንቆ ተጠብበውበታል። የሙዚቃ ስራዎቻቸው ከኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አልፈው በሌሎች ሰዎችም ዘንድ ተወዳጅ ናቸው። ከዘፋኝነታቸውና ከመሰንቆ ተጫዋችነታቸው በተጨማሪ ተወዳጅ የግጥምና ዜማ ስራዎችንም ለአንጋፋ ድምፃውያን ሰጥተዋል።
የእርሳቸውን ግጥምና ዜማ ተቀብለው ካዜሙት ድምፃውያን መካከል ዝነኛው ድምፃዊ የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሰሰ አንዱ ነው። በዘፋኝነታቸውም ሆነ በግጥምና ዜማ ደራሲነታቸው ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ማደግ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክተዋል … አንጋፋው የመሰንቆ ተጫዋች አርቲስት ለገሰ አብዲ!
ለገሰ የተወለደው በ1931 ዓ.ም፣ በሰላሌ አውራጃ፣ ያያ ቀጨማ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ነው። አባቱ አቶ አብዲ ዳዲ፤ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ፎሌ ጉደታ ይባላሉ። ለአባትና ለእናቱ ብቸኛ ልጅ የነበረው ለገሰ፤ እናቱን በሞት የተነጠቀው ገና ሕፃን ሳለ ነበር። የአባቱ የአቶ አብዲ ዳዲ ወዳጅ የነበሩት ባለመሰንቆው ወሰኑ ዲዶ፣ ለገሰ ገና በልጅነቱ በመሰንቆ ፍቅር እንዲወድቅ ምክንያት ሳይሆኑ አይቀሩም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮም መሰንቆ የለገሰ መለያ/ መታወቂያው ሆነ። በሠርግና በሌሎች ዝግጅቶች ላይ እየተገኘ መሰንቆ መጫወት ጀመረ።
ከትውልድ አካባቢው ከሰላሌ ተነስቶ ወደ ወሊሶ፣ ጅማ፣ ወለጋ፣ ኢሉባቦርና ሌሎች አካባቢዎች ድረስ በመሄድም መሰንቆን ይጫወት ነበር። በዚህም የመሰንቆ ልዩ ችሎታና ተሰጥዖ እንዳለው ማስመስከር ቻለ። ለገሰ በየሰርግ ቤቱ የሚጫወተው የመሰንቆ ጨዋታ ለገቢ ማግኛም ጭምር መሆኑን የተረዱትና ያለእናት ያሳደጉት አባቱ አቶ አብዲ ዳዲ፤ የልጃቸውን ሙያ አናንቀውበት አያውቁም ነበር። ይልቁንም በልጃቸው ችሎታ ደስተኛ ስለነበሩ ለወጣቱ ተጫዋች የሞራል ስንቅ በመሆን ያበረታቱት ነበር።
በሙዚቃ ችሎታውና ተሰጥዖው ስሙ እየታወቀ የመጣው ለገሰ፣ የመሰንቆ ፍቅር እንዲያድርበት ምክንያት በሆኑትና የአባቱ ወዳጅ በነበሩት ወሰኑ ዲዶ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሄደ። አዲስ አበባ ገብቶም የክብር ዘበኛ ጦር ወታደር ሆኖ ለመቀጠር ተመዘገበ።
በ17 ዓመት የወጣትነት እድሜው በውትድርና የተጀመረው የክብር ዘበኛ ቆይታው ግን ከወታደርነት ይልቅ ወደ ሙዚቀኛነት ወሰደው። ለገሰ የሙዚቃ ተሰጥዖ ስለነበረው ችሎታው ታይቶ ወደ ክብር ዘበኛ ጦር የሙዚቃ ክፍል ተዛወረ። በጊዜው በወር 13 ብር ይከፈለው ነበር። በወቅቱ ወጣቱ ለገሰ ካሳ ተሰማንና ጥላሁን ገሰሰን ጨምሮ ከሌሎች አንጋፋ ድምፃውያን ጋር የመስራት እድል ማግኘት ችሏል። ከጥላሁን ገሰሰ ጋር ከክብር ዘበኛ በፊት ለገሰ ወደ ወሊሶ ተጉዞ በነበረበት ወቅት ተገናኝተው ተዋውቀዋል።
ለገሰ ለሰባት ዓመት ያህል በክብር ዘበኛ የሙዚቃ ክፍል ውስጥ ካገለገለ በኋላ ክብር ዘበኛን ለቆ ያቀናው ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትያትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ቤት) ነበር። በትያትር ቤቱ በሙያው ሲያገለግል በወር 70 ብር ደመወዝ ይከፈለው ነበር።
በትያትር ቤቶች ውድድር በነበረበት ወቅትም ለገሰ በመሰንቆ ችሎታው ሌሎች ተወዳዳሪዎችን በልጦ በመገኘት ይሸለም ነበር። በተለይ ለአዲስ ዓመት ጠንካራ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። ለገሰ ኦሮምኛ ሙዚቃዎችን ለጆሮ በሚጥም መልኩ በመሰንቆ አጅቦ በማቅረብ ውድድሮቹን በአሸናፊነት ያጠናቅቅ ነበር። በሙዚቃ መሳሪያ አጨዋወት ችሎታውም «መሰንቆን እንደ ሰው ማነጋገር ይችላል» እስኪባል ድረስ ታዳሚውን የማስደመም ብቃት ነበረው።
አርቲስት ለገሰ ከብሔራዊ ትያትር ቤት ከለቀቁ በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች እየተዘዋወሩ መስራታቸውን ቀጠሉ። ባለቤታቸውን ያገኙትም በዚሁ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በሚሰሩበት አጋጣሚ ነበር። አርቲስት ለገሰ የሰባት ልጆች (አራት ወንዶችና ሶስት ሴቶች) አባት ካደረጓቸው ከወይዘሮ እጅጌ አበበ ጋር የተዋወቁትአርቲስቱ ሙዚቃ ሊጫወቱ ወደ ደብረ ብርሃን በሄዱበት ወቅት ነበር።
በዚያ አጋጣሚ የተጀመረው ትውውቅም ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀ የትዳር ሕይወትን መገንባት ችሏል። በግላቸው ማሲንቋቸውን አንግተው ቦረናና አዶላ ድረስ እየተዘዋወሩ በመስራት ማህበረሰቡን ያዝናኑ፣ ሕይወታቸውን ይመሩና ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩም ነበር።
አርቲስት ለገሰ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሱ በነፃነት መዝፈንም ሆነ ሃሳብን መግለፅ በማይቻልበት በዚያ ወቅት በኦሮምኛ ቋንቋ በሚደረድሯቸው ስንኞቻቸው በማሲንቆ ታጅበው በድፍረት ስለሚዘፍኑ ከማህበረሰቡ ታላቅ ፍቅርና አክብሮትን አትርፈው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም አርቲስት ለገሰ ለቋንቋው እድገትና ዕውቅና ታላቅ ተጋድሎን ካደረጉ አንጋፋ የመድረክ ፈርጦች መካከል አንዱ እንደነበሩ ለሙያውም ሆነ ለእርሳቸው ቅርብ በሆኑ አጋሮቻቸው ተመስክሮላቸዋል።
ከክብር ዘበኛ እና ከብሔራዊ ትያትር በተጨማሪ በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት እና በፖሊስ ኦርኬስትራ ያገለገሉት አርቲስት ለገሰ፤ ከሌሎች ድምፃውያንና የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋቾች ጋር ሆነውም በብዙ ስፍራዎች በርካታ ሙዚቃዎችን ተጫውተዋል።
አርቲስት ለገሰ የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን በባህላዊ ዜማ አቀራረብ ለረጅም ዓመታት በመላ አገሪቱ እና በጎረቤት አገራት ስላስተዋወቁ ‹‹የኦሮምኛ የባሕላዊ ሙዚቃ አምባሳደር›› እየተባሉ በብዙዎች ዘንድ ይወደሳሉ። ከድምጻዊነታቸው በተጨማሪ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ግጥምና ዜማዎችን በመድረስ ይታወቃሉ።
አርቲስት ለገሰ ከድምጻዊነታቸው በተጨማሪ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ግጥምና ዜማዎችን በመድረስም ይታወቃሉ። ለራሳቸው ሙዚቃዎች ግጥምና ዜማ ከማዘጋጀት በተጨማሪ ለሌሎች አንጋፋ ባለሙያዎችም ግጥምና የዜማ ስራዎቻቸውን ሰጥተዋል። ለአብነት ያህል «አማ ስኳሬ» እና «አወይ የገላ ሳሙና» የተሰኙትን የጥላሁን ገሰሰ ታዋቂ የዘፈን ግጥሞችን የደረሱት አርቲስት ለገሰ አብዲ ናቸው።
ከሙዚቃ ችሎታቸው ባሻገር በተለይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የሕጻናት ፕሮግራም የኦሮምኛ ቋንቋ ዝግጅት ፕላይ መሰንቆ በማናገር ልዩ ችሎታ እንዳላቸው አስመስክረዋል። እርሳቸው በቃላት የሚያወጡትን «አካም ጅርታ» እና ሌሎች የኦሮምኛ የሰላምታ ልውውጦችን ከመሰንቋቸው ጋር በማዋሃድ ሕጻናትን ያዝናኑ ነበር። ይህም የሆነው እያንዳንዱን የመሰንቆ ድምጽ አቅጥነው እና አወፍረው ከሰው ልጅ ንግግር ጋር እንዲመሳሰል አድርጎ መሰንቆ የመጫወት ጥበብን ስላዳበሩ ነው። መሰንቆ አናጋሪው አርቲስት ለገሰ ‹‹የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበብ የሚገኘው ከባህላዊ ሙዚቃ ነው›› የሚል እምነት ነበራቸው።
ሱዳን አገር ከክብር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ጋር ሄደው በመሰንቆ ሲጫወቱ የመሰንቆው ድምጽ እና የአርቲስቱ የአዘፋፈን ስልት የማረካቸው የሱዳን ሙዚቀኞች አብረዋቸው እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርበውላቸው እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸው ይናገራሉ። እርሳቸው ግን አገራቸው ላይ መስራት በመፈለጋቸው ግብዣውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል። ለታሪክ የሚተላለፉ የኪነ ጥበብ ስራዎቻቸውን እያፈለቁ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በሙያው ላይ ቆይተዋል።
ምንም ዓይነት ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርትን ሳይማሩ አራቱንም የሙዚቃ ቅኝቶች በመጫወት የሚታወቁት አርቲሰት ለገሰ አብዲ፤ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በሚያሳዩት የመሰንቆ ጨዋታ ጥበብ ለበርካታ የሙዚቃ ሰዎችና ቡድኖች እንደ አርአያ መሆን የቻሉ አንጋፋ ባለሙያ ነበሩ።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በቆየው የሙዚቃ ሕይወታቸው በተለያዩ ጊዜያት በመድረክ ላይ ካቀረቧቸው ዘፈኖች በተጨማሪ አንድ የሸክላ፣ አስራ አንድ የካሴት እንዲሁም አንድ ሲዲ (CD) እና ቪሲዲ (VCD) በማሳተም ሙዚቃዎቻቸውን ለአድማጭ አድርሰዋል።
«መሰንቆን እንደ ሰው ማነጋገር ይችላሉ» የሚባልላቸው አንጋፋው የጥበብ ሰው በስራዎቻቸው የሚገባቸውን ጥቅም እና ክብር እንዳላገኙ ብዙ አድናቂዎቻቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በመድረክ ዝግጅታቸው ወቅት እስከ 15ሺህ ብር ድረስ ከታዳሚው ተሸልመው የሚያውቁ፣ በመሰንቆ አጨዋወት ችሎታቸው ታዳሚን ቁጭ ብድግ የሚያስብሉ ጥበበኛ ነበሩ።
በኦሮምኛ ቋንቋ በነፃነት መዝፈንም ሆነ ሃሳብን መግለፅ በማይቻልበት ወቅት፤ ችግሮችን ተቋቁመው በመዝፈን ለቋንቋው እድገትና ዕውቅና ታላቅ ተጋድሎን ካደረጉ አንጋፋ የመድረክ ፈርጦች መካከል አንዱ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።
አርቲስት ለገሰ ‹‹ብቻቸውን የመሰንቆ ትምህርት ቤት ናቸው›› እያሉ የሚያወድሷቸው ሙያተኞች በርካታ ናቸው። ከ60 ዓመታት በላይ የኦሮምኛን ሙዚቃ በመሰንቆ በመጫወት ለሙዚቃው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ጥበብን፣ ፍቅርን፣ ውበትን፣ አካባቢን፣ ባህልን፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን እያነሱ በመሰንቋቸው ተጫውተዋል፤ አጫውተዋል፤ በጥበብ ማኅበረሰቡን አገልግለዋል።
ከትዳራቸው ሰባት ልጆችን (ሦስት ሴቶችና አራት ወንዶች) ያፈሩት አርቲስት ለገሰ፤ የእሳቸውን ሙያ የያዘና ፈለጋቸውን የተከተለ ልጅ ግን የላቸውም። ልጆቻቸው ከሙዚቃ ይልቅ በሌሎች የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው በአንድ ወቅት «የእኔ ድምጽ ወደ ቤተሰቤ አልተላለፈም» ሲሉ ተናግረው ነበር።
አርቲስት ለገሰ የሰሯቸውንና የአበረክቷቸውን ያህል ባይሆንም ሽልማቶችን አግኝተዋል። ለአብነት ያህል በ2010 ዓ.ም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ማዕከል ጋር በመተባበር በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ደዴሳ ከተማ ባዘጋጁት መርሐ ግብር ላይ አርቲስት ለገሰ ከሰዓሊ ለማ ጉያ ጋር የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑበት እውቅና ተጠቃሽ ነው።
የአርቲስት ለገሰ አብዲን ሙዚቃ ሲሰሙ ልዩ ስሜት የሚሰማቸው ቋንቋውን የሚሰሙና የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ቋንቋውን የማያውቁትንም ጭምር መሆኑ የአርቲስቱን የጥበብ ክህሎት በተለየ መልኩ እንዲደነቅ ያደርገዋል። በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው፣ ወለል ካለው መስክ ላይ ነጭ የአገር ባህል ልብሳቸውን እንደለበሱ፤ መሰንቋቸውን አንግተው በአይረሴ ድምጻቸው የሚያዜሙበት ልዩ ስልታቸው ዛሬም ድረስ በብዙዎች ትዝታ ውስጥ ይገኛል።
አርቲስት ለገሰ በአንድ ወቅት ወድቀው ባጋጠማቸው ስብራት ምክንያት ለዓመታት ከሙዚቃ ርቀው ቆይተዋል። ይኸው አደጋ ለበርካታ ጊዜያት ወደ ሆስፒታል አመላልሷቸዋል። በመጨረሻም አንጋፋው የመሰንቆ ጠቢብ አርቲስት ለገሰ አብዲ በተወለዱ በ80 ዓመታቸው፣ ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም፣ አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በማግሥቱ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013