ሌት ተቀን ያለዕረፍት የሠሩ ሀገራት የእድገትና ብልፅግና ማማ ላይ መውጣት ችለዋል። ሥራ ወዳድና ትጉህ ህዝብ ያላቸው ሀገራትም የዓለም ኢኮኖሚ ቁንጮ ለመሆን በቅተዋል። እነዚህ ሀገራት ለሥራ ከፍተኛ ትርጉም በመስጠታቸውም ህዝባቸውን ከድህነት አላቀው ወደ ሀብት አሻግረዋል። ለዚህም አሜሪካንን፣ ቻይናን፣ ጃፓንን፣ጀርመንን፣ እንግሊዝንና ፈረንሳይን በምሳሌነት ማንሳቱ ብቻ በቂ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ረጅም ሰዓታትን በሥራ ማሳለፍ በጤና ላይ ጉዳት ከማስከተሉም በላይ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል የጤና ባለሞያዎች የሚስማሙ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚሁ ምክንያት የበርካታ ዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ እንደሚገኝ ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ በዓለም ጤና ድርጅትና በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ጥምረት የተሠራን አንድ ጥናት ዋቢ በማድረግ ከሰሞኑ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ በዓለም ጤና ድርጅትና በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የተሠራው የጥናት ግኝት የረጅም ሰዓታት ሥራ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ አሳይቷል። በዓለም ጤና ድርጅትና በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የዓለምአቀፍ ህብረተሰብ ጤናና ሠራተኞች ክፍል በጋራ በተሠራው በዚሁ ጥናት በዓለም አቀፍ ዙሪያ 745 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ከስትሮክና ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ በ2016 ህይወታቸው ማለፉንና ይህም ከ2000 ጀምሮ የ29 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ዘገባው አመልክቷል።
በኢንቫርዩሜንታል ኢንተርናሽናል ጆርናል የታተመው ይህ ጥናት ረጅም ሰዓታትን ከመሥራት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን ሞት በሚመለከት የመጀመሪያውን ትንታኔ ይዞ ብቅ ያለ ስለመሆኑም ተነግሮለታል። በጥናቱም የዓለም ጤና ድርጅትና ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት በ2016 በዓለም አቀፍ ዙሪያ በትንሹ በሳምንት 55 ሰዓታትን በመሥራታቸው 398 ሺ የሚገመቱ ሰዎች በስትሮክ እንዲሁም 347 ሺ ያህሉ ደግሞ ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ማለፉን ተጠቁሟል።
ከ2000 እስከ 2016 ባሉት ዓመታትም በረጅም ሰዓታት ሥራ ምክንያት በልብ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ42 ከመቶ እንዲሁም በስትሮክ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ19 ከመቶ መጨመሩን ጥናቱ አስታውቋል። ጥናቱ በሳምንተ ከ35 አስከ 40 ሰዓታት ከመሥራት ጋር ሲወዳደር በሳምንት ከ55 እና ከዚያ በላይ ሰዓታትን በሥራ ማሳለፍ በስትሮክ የመሞትን ዕድል በ35 ከመቶ እንደሚጨመርና በልብ በሽታ የመሞትን ዕድል ደግሞ 17 ከመቶ ከፍ እንደሚያደርግ ደምድሟል።
በ2016፤ በዓለም አቀፍ ዙሪያ 488 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በሳምንት ከ55 ሰዓት በላይ ለሚሆን የረጅም ሰዓታት ሥራ መጋለጣቸውንም የዓለም ጤና ድርጅትና ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት በጥናቱ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ከዚሁ የረጅም ሰዓታት ሥራ ጋር በተገናኘ የሚሞቱ ሰዎችን ከፍተኛውን ቁጥር ወይም 72 ከመቶ ያህሉን የሚሸፍኑት ወንዶች መሆናቸውንና በምዕራብ ፓስፊካ አካባቢ በሚገኙ ሀገራት ማለትም በቻይና፣ በደቡብ ኮርያ፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓንና በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚኖሩ በመካከለኛና ጠና ባለ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች መሆናቸውም በጥናቱ ተረጋግጧል። ከተመዘገቡ ሞቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከ60 አስከ 79 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉና ከ45 አስከ 74 ዓመት ባለው ዕድሚያቸው በሳምንት ከ55 እና ከዚያ በላይ ሰዓታት የሠሩ መሆናቸውም በጥናቱ ተጠቁሟል። የረጅም ሰዓታት ሥራ አንድ ሦስተኛ ለሚሆነው ከአጠቃላይ ከሥራ ጋር በተያያዘ ለሚከሰት ሞት ምክንያት ስለመሆኑም ጥናቱ አሳይቷል።
የዓለም ጤና ድርጅትና ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ጥናት 37 የልብ በሽታ እና 22 የስትሮክ ትንታኔ ጥናቶችን እንዲሁም ከ1970 እስከ 2018 ከ 154 ሀገራት ከ 2 ሺ 300 በላይ የሚሆኑ ሰርቬይ ዳታዎችን ማካተቱም ተጠቁሟል። ምንም እንኳን ጥናቱ የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተበትን ጊዜ ባይሸፍንም የጥናቱ ግኝት የመጣው በረጅም የሥራ ሰዓታት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመጣበት ጊዜ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜም ይህ ሞት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጠቅላላው ህዝብ ቁጥር 9 ከመቶ ያህሉ እንደሆነም የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ይህ ሁኔታ ከሥራ ጋር በተገናኘ ለሚከሰት የአካል ጉዳትና ያለዕድሜ ሞት ሰዎችን አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል።
የኮሮና ወረርሽኝ ለሥራ ስርዓቶች የበለጠ ትኩረት የሰጠ መሆኑንና በተለይ ወረርሽኙ ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ እድገትን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ተጨማሪ የሥራ ሰዓቶችን እንደሚጠይቅ የዓለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል። የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ወረርሽኙ የሰዎችን የሥራ ሁኔታ በእጅጉ መቀየሩን አስምረዋል።
ሥራዎችን በስልክ ማከናወን በአብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ባህል መሆኑንና ይህ ሁኔታ በቤትና በሥራ ቦታ ያለውን ድንበር መከፍቱን ገልጸዋል። ለስትሮክም ሆነ ለልብ በሽታ ዋጋ የሚሰጥ ምንም ዓይነት ሥራ እንደሌለም ገልጸው፤ የሠራተኞችን ጤንነት ለመጠበቅ መንግሥት፣ ተቀጣሪዎችና ሠራተኞች በጋራ ለመሥራት መስማማት እንዳለባቸው ጌኔራል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትም መንግሥታት አስገዳጅ የትርፍ ሰዓት ሥራን የሚከለክሉ እና በሥራ ሰዓት ላይ ከፍተኛ ገደቦችን የሚጥሉ ህጎችንና መመሪያዎችን እንዲያስተዋውቁ ፣ እንዲተገበሩ እና እንዲያስፈፅሙ የሚመከር ሲሆን፤ ሠራተኞቹ የሚሠሩበት ሰዓት በሳምንት ከ55 ወይም ከዚያ በላይ እንደማይበልጥ ለማረጋገጥ የሥራ ሰዓትን መጋራት እንደሚችሉ ይጠቁማል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013