(ክፍል አንድ)
በድፍረት የዛሬዋ ዓለማችን “ጥቁር ሞት”የተሰኘ ገዳይ ወረርሽኝ የእጅ ሥራ ናት ይሉናል ፤ የ”WHY NATIONS FAIL” ተጣማጅ ጸሐፊያን ዳረን አኬሞግሉና ጀምስ ሮቢንሰን ከእግዜሩ ሊያጣሉን። ደግነቱ ይህን አያዎ ይትበሀላቸውን ተከትለን ስንመረምር እግዜሩ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረበት የዘፍጥረት Genesis እውነትና ቀኖና አውድ ጋር ፍጹም የማይገናኝ ከመሆኑ ባሻገር አይጣረስም። ነገሩ ወዲህ ነው። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1346 ዓ.ም የሐር ንግዱን መስመር ተከትሎ በነጋዴዎች አማካኝነት በአይጥ ቁንጫ የሚተላለፈው “ጥቁር ሞት” በጥቁር ባህሯ የወደብ ከተማ ታና ገባ።
ወረርሽኙ ፈጥኖ ሜዲትራኒያንን አዳረሰ። በዓመት ውስጥ የዛን ጊዜዋ የቤዛንታይን መዲና ኮንስታንቲኖፕልን የዛሬዋን የቱርክ መዲና ኢስታንበሉ ደረሰ። በ1348 ዓ.ም የሰውን ልጅ እንደ ቅጠል እያረገፈ ፈረንሳይን ፣ ሰሜን አፍሪካንና ጣሊያንን አካለለ። ከግማሽ በላይ የዓለምን ሕዝብ ፈጀ። በዚሁ ዓመት በወርሀ ነሐሴ እንግሊዝ ገብቶ ከግማሽ በላይ ሕዝብ ጨረሰ። በዚህ የተነሳ የመካከለኛው ዘመን የአውሮፓ ሕዝብን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሠረት አናጋ። ስሪቱን ፐወዘ።
በቤዛንታይኑ የሮማ ኢምፓየር እግር የተተካው የፊውዳል ስርዓት ክፉኛ በጭሰኛና በገበሬ ጉልበት እጥረት ተሽመደመደ። ምርት ቀነሰ። ይህን መልካም አጋጣሚ የተገነዘቡ ብልህ ገበሬዎች መብታቸውና ጥቅማቸው እንዲከበር ማንጎራጎርና ማመጽ ጀመሩ። ቀደም ባሉ ዓመታት የተጣሉባቸው ቅጣት እንዲነሳ ያለክፍያ የሚያገለግሉበት ስዓት እንዲቀነስ ጫና ማድረግ ቀጠሉ። በተለይ በኤይንሻም አካባቢ የሚገኝ ገዥ መደብ በአመጹ መፈናፈኛ ስላጣ የጭሰኞችንና የገበሬዎቹን ጥያቄ ያለአንዳንች ማቅማማት ለመቀበል ተገደደ።
ይህ ታሪካዊ ክስተት እንደ ሰደድ እሳት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ተዛመተ። እየዋል እያደር አዝማሚያው ያላማራቸው የገዥው መደብ አባላት ለውጡን ከወረርሽኙ በፊት ወደነበረበት ለመቀልበስ ሲንቀሳቀሱ መንግሥት አቋማቸውን ደግፎ ከጎናቸው ቆመ። በዚህ የተበሳጩት ገበሬዎች በዋት ታይለር መሪነት በ1381 ዓ.ም የእንግሊዝንም ሆነ የዓለምን ታሪክ እንደ አዲስ የበየነ አመጽና እንቢታን ቀሰቀሱ።
ለንደንን ተቆጣጠሩ። የማታማታ አመጹ ቢጨናገፍ መሪያቸው ታይለር በሞት ቢቀጣም መብታቸው ግን እንደተከበረ ዘለቀ። ይህ የጭሰኞችና የገበሬዎች አመጽ ወይም ግሎሪየስ አብዮት በኋላ ላይ ለተቀጣጠለው የኢንዱስትሪ አብዮትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥንስስ ሆኖ በታሪክ ተመዘገቦ ይገኛል። “ጥቁር ሞት”ም የሰው ልጅ በታሪኩ ካጋጠሙት ወሳኝ መታጠፊያዎች critical juncture ተራ ተሰለፈ። ለመሆኑ ወሳኝ መታጠፊያ ማለት ምንማለት ነው !?
ከፍ ብሎ በጠቀስሁት ግሩም ድንቅ መጽሐፍ ገጽ 101 ላይ ወሳኝ መታጠፊያን እንዲህ ይበይነዋል ፤”…ጥቁሩ ሞት የወሳኝ መታጠፊያ ጉልህ ማሳያ ነው። ወሳኝ መታጠፊያ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እንደ አዲስ የሚበይኑና የሚጠረምሱ ዓበይት ሁነቶች ናቸው። የማህበረሰብን ፈለግ በአዎንታ ወይም በአሉታ የሚያስቀይር ባለሁለት አፍ ስለት ሰይፍም ነው። በአንድ በኩል ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን የብዝበዛና የጭቆና ቀለበት በመስበር እንደ እንግሊዝ ነፃና አሳታፊ ስርዓት ለመገንባት መሠረት ሲሆን፤ በሌላ በኩል በምሥራቅ አውሮፓ በታሪክ እንደተመዘገበው ወሳኝ መታጠፊያ የከፋ አምባገነን አገዛዝንና ብዝበዛን ሊያሰፍን ይችላል ። …”
የፈረንሳይ አብዮት እንደ እንግሊዙ ግሎሪየስ አብዮት አነሳሱ ስር ነቀልና አደገኛ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ በአውሮፓ ለተለኮሰው የኢንዱስትሪ አብዮት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ነበረው ። በሒደት ፖለቲካው አሳታፊ ፤ ኢኮኖሚው አካታች እየሆነ በመምጣቱ በእንግሊዝ፣ በአውስትራሊያ ፣ በአሜሪካና በካናዳ ብልጽግና ማበብ ዴሞክራሲ መጎልበት ጀመረ። የግሎሪየስና የፈረንሳይ አብዮቶች ተንሰላስለው በምዕራብ አውሮፓ ሰማይ የዕድገት ጎህ እንዲቀድ ምክንያት ሆኑ። የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መሠረት ጣሉ። በእነዚህ ስኬታማ አብዮቶች የተነሳ አብዮት ሁሉ አጥፊና አፍራሽ ተደርጎ መወገዙ ቀረ። በተቃራኒው ከስንት አንድ የለውጥ መነሻና መስፈንጠሪያ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ ምሳሌ ሆኑ።
አብዮቶች ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ አገዛዝ የሚጎነቁሉ ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ተቋማት የሚጎለብቱበት እና የበለጸገ ሀገር መገንባት የሚችሉበት አጋጣሚም እንዳለ አብነት ሆኑ። በአንጻሩ አብዛኛዎቹ አብዮቶች የራሽያን የጥቅምት አብዮት ጨምሮ ሁሉም አካታች የኢኮኖሚና አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት ባለማቆማቸው ዛሬ ድረስ ባሉበት ይረግጣሉ። በነገራችን ላይ ወሳኝ መታጠፊያነት ከአብዮት ከፍ ሲልም ከፖለቲካ ጋር ብቻ የተዋደደ ጽንሰ ሃሳብ አይደለም ።
በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ታሪክ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ሳይንሳዊ ፣ ቴክኖሎጂያዊ ፣ ወዘተረፈ ውስጥ ወሳኝ መታጠፊያዎች አሉ። የኮምፒውተርንና የኢንተርኔት መፈጠር ለኢንፎርሜሽን ኮሙንኬሽን ቴክኖሎጂ መበልጸግ ወሳኝ መታጠፊያዎች እንደሆኑ። ወደ ሀገራችን ጥቂት ፖለቲካዊና ታሪካዊ መታጠፊያዎች ሽንቁር ትላንትን እናጮልቅ ዛሬንና ነገን እንመልከት። እንርእይ።
በወታደራዊ ደርግ የተቀማው የኢትዮጵያ ተማሪዎች፣ ገበሬዎች ፣ ላብ አደሮችና ከተሜዎች የ1966 ዓ.ም አብዮት በሀገራችን ታሪክ በወሳኝ መታጠፊያነት/critical juncture /ከሚጠቀሱ የታሪክ ገጾች ቀዳሚ ነው። ዛሬ ሀገራችን ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ስካርም ሆነ እራሷን ፈጥርቆ ለያዛት ሀንጎቨር የዳረጋት ጌሾው የበዛበት የ66ቱ የአብዮት ጥንስስ ነው። አዎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ወዘተረፈ ስካር ያ አላዋቂ የጠነሰሰው የዳጉሳ ጠላ ተወቃሽ ነው።
ደርግ ይህን ታሪካዊ መታጠፊያ አሳታፊ ፖለቲካዊ ምህዳር እና አካታች ኢኮኖሚያዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል በአዎንታዊ መበየን ይችል ነበር። ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም በቀጣይ ነፃ ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ማካሄድ ይችል ነበር። ደርግ ግን እንደነ ሌኒን ለስልጣኔ ያሰጉኛል ያላቸውን የአጼ ኃየለሥላሴ ባለስልጣናትን እና የደርግ አባላት ሳይቀር መግደል ጀመረ። እነ አጥናፉ አባተንና ተፈሪ በንቲ በመንግሥቱ የሚመራዊ የደርግ ክንፍ ገና በማለዳው በግፍ በመግደል ስልጣኑን ካደላደለ በኋላ መጀመሪያ ወደ ኢህአፓ በኋላ ፊቱን ወደ መኢሶን በማዞር መተኪያ የሌለውን የተማረ አንድ ትውልድ ጨረሰ።
ለዛውም ባለብሩህ አዕምሮ ሙሁራንና በትምህ ርታቸው ጎበዝ የነበሩ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን። በነገራችን ላይ በዛን ጊዜ የተፈጠረ ክፍተት ዛሬ ድረስ ሊሞላ ባለመቻሉ ዳፋው እንደ ጥላ ይከተለናል። የአጼውን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ገርሶሶ የባሰ አምባገነናዊ ሆኖ አረፈው። መሬት ለአራሹን አውጆ ብዙም ሳይቆይ የገበሬውን ምርት በርካሽ በኮታ መሰብሰብን ተያያዘው። መሬቱን በእጅ አዙር ተቆጣጠረው። ንጉሳዊ አገዛዙ እንዳሻው ያዝዝበት የነበረውን ኢኮኖሚ በሶሻሊዝም ስም ተቆጣጠረው ። አፈናውን አባብሶ ቀጠለበት።
የደርግን አዝማሚያ ገና በውል ሳያጤን ትህነግ/ ህወሓት የሸዓብያን የትጥቅ ትግል መንገድ መከተል መረጠ። እነዚህ ኃይሎች እየተጋገዙ በደርግ ላይ የሚሰነዝሩት ወታደራዊ ጥቃት እየተጠናከረ ሄደ። ከዓመት ዓመት እየተጠናከሩ ፤ የሚቆጣጠሩት ነፃ መሬት እየሰፋ ፤ ትግሉን የሚቀላቀል ወጣት ቁጥር እየጨመረ ፤ በጦር መሳሪያና በትጥቅ እየደረጁ መጡ። በመጨረሻም ትህነግ ከ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ በ1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ፤ ሸዓብያ ከ30 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ በዚሁ ዓመት አሥመራን ተቆጣጠሩ። ትህነግም ሆነ ሸዓብያ እንደ ደርግ ሁሉ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ መንገድ በመትለም ከአዙሪቱ ሰብረው የመውጣት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀሩ። የደርግ አምባገነናዊ አገዛዝ በሌላ ለዛውም ሀገርን አምርሮ በሚጠላ ዘረኛ፣ ከፋፋይና ዘራፊ አገዛዝ ተተካ።
ባለፉት 30 ዓመታት በፌዴራልና በኋላ በትግራይ አገዛዝ ላይ የነበረው “ነፃነትን የማያውቀው ነፃ አውጪ !” ትህነግ ለዜጎች ነፃነትና እኩልነት ታገልሁ ቢልም በተግባር ግን ከደርግ የባሰ አምባገነን ፣ ዘራፊና ቀውስ ቀፍቃፊ ሆነ። እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራል ስርዓት የማቆም ዕድል ቢያገኝም እሱ ግን አስመሳይ ዴሞክራሲን እንዲሁም ከፋፍሎ ለመግዛት የሚያመቸውን እና በዜጎች መካከል መጠራጠርን ፣ ልዩነትንና ጥላቻን የሚጎነቁል አገዛዝ ተከለ። የማንነትና የጥላቻ ፖለቲካ በተለይ ለ30 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሌት ተቀን በመሰበኩ ምክንያት ኢትዮጵያዊ ማንነት እየኮሰመነ አክራሪ ብሔርተኝነት እየገነገነ መጣ። በዚህም የሀገር ህልውናና የግዛት አንድነት ፈተና ላይ ወደቀ። በዜጎች መካከል ጥላቻ ፣ ልዩነትና መጠራጠር ሰፈነ። የአንድ ቡድን የበላይነት ገነነ። ኢኮኖሚውን ከሽንኩርት ችርቻሮ እስከ ጅምላ ንግድ ተቆጣጠረው። ፖለቲካዊ ስልጣኑን ጠቅልሎ በመዳፉ አስገባ። የዜጎች ነፃነትና ዴሞክራሲ ባዶ ተስፋ ሆኖ ቀረ።
ደርግ በአዲስ ዓይነት ማፊያ ቡድን ተተካ። ጭቆናው ከዓመት ዓመት እየተባባሰ ሄደ። ዘረፋ የአገዛዙ መለያ ሆነ። የስብሀታዊ ስረወ መንግሥት ሀገሪቱን በአጥንት አስቀራት። ዜጎችን ሁለተኛ ዜጋ አደረጋቸው። በዚህ የተማረረው ሕዝብ በተደጋጋሚ በተለያየ መንገድ ለውጥን ቢጠይቅም መልሱ ማብቂያ የሌለው ግድያ ፣ ስቃይ ፣ አፈናና እስር ሆነ። በመጨረሻ ሕዝባዊ ተቃውሞው እየተጠናከር በትህነግ/ኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ኃይል ከሕዛባዊ ተቃውሞው ጋር እየተናበበና እየተንሰላሰለ ከሦስት ዓመታት በፊት ለውጡ እውን ሊሆን ቻለ።
ይህ ለውጥ ግን ከደርግም ሆነ ከትህነግ/ኢህአዴግ በመሠረቱ ፍጹም የተለየ ነው ማለት ይቻላል። እንደ ቀደሙት አንድን አምባገነን በሌላ የተካ ሳይሆን ምን አልባት የለውጥ ኃይሉ እንደ ሀገር እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የመጨረሻው ዕድል እንደወጣለት ፤ ኃላፊነት እንደወደቀበት በውል የተገነዘበና ወሳኝ መታጠፊያ እጁ ላይ እንደገባ በማጤን ፖለቲካውን አሳታፊ ፤ ኢኮኖሚውን አካታች ለማድረግ አበክሮ እየጣረ ይገኛል።
የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት ፤ አላሠራ ብለው የነበሩ ሕጎችን ለማሻሻል የሄደበት ርቀት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። እነዚህ የተቋማት ግንባታዎች ፤ የአሠራርና የአደረጃጀት መሻሻያዎች ግብ ቀጣዩን ምርጫ ነፃ ፣ ተአማኒ ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቀ እና ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ማስቻል ነው። እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ፤ በክፍል ሁለት መጣጥፌ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሁና እንድትወጣ ግብ የተጣለለት ቀጣዩ ምርጫ ለሀገራችን እንደ ዓድዋ ድል ወሳኝ መታጠፊያ መሆኑን አጽንኦት እሰጣለሁ እሞግታለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2013