ዛሬ ስለ ተስፋ እነግራችኋለው። ተስፋ ስላችሁ ግን በምንምነት ውስጥ ያለውን ህልም አይነቱን ተስፋ እያልኳችሁ አይደለም። በራዕይ ውስጥ ስላለው፣ ለለውጥ በተነሱ ልቦች ውስጥ ያለውን እሱን ማለቴ ነው። የቆማችሁት በምን ይመስላችኋል? ወጥታችሁ የምትገቡት በምን ሀይል በምን ብርታት ቢሆን ነው? እዚህ ዓለም ላይ በህይወት ለመኖር እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ኃይሎች ውስጥ አንዱ የተስፋ ኃይል ነው፡፡
ህይወት ከተሰራችባቸው ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ አምላካዊ ቀመሮች ውስጥ ተስፋ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በሀይማኖት አስተምህሮት ላይ እንኳን ተስፋ ለህይወት ያለውን የላቀ ዋጋ ማየት እንችላለን። ተስፋውን የገደለ፣ ተስፋውን ያጣ ሰውነት ለመኖር አቅም አያገኝም። ትልቁ መኖራችን ያለው በትልቁ ተስፋችን ውስጥ ነው። ወደ ፊት እንድንሄድ፣ ወደ ፊት እንድናይ ልባዊ ተስፋ ያስፈልገናል። ያለ ሙልዕተ ተስፋ ምንም ነን።
ተስፋ በራዕይ ውስጥ ያለ ለለውጥና ለአዲስ ነገር በሚጓጓ መንፈስ ውስጥ የሚፈጠር የመልካም ነገሮች ፍኖት ነው። ከግለሰባዊነት ባለፈ ለአንድ ሀገርና ህዝብ ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ እንዳለ ሆኖ እድገትና ስልጣኔ ከሚፈበረኩባቸው አእምሮአዊ የልማት ሀይል አንዱና ዋነኛው ነው ባይ ነኝ። መኖር መተንፈስ ብቻ አይደለም፣ መኖር መተንፈስ ብቻ ነው ብንል እንኳን እንድንተነፍስ የሚያበረቱን ኃይሎች እንዳሉ መርሳት የለብንም። እንድንኖር፣ እንድንተነፍስ አቅምን ከሚፈጥሩልን ኃይሎች ውስጥ አንዱ ጸዐዳ ተስፋ ነው። ተስፋ ከስኬትና የምንፈልገውን እንድናገኝ ከማድረግ ባለፈ እንዳንሞት የሚያደርግ ታላቅ ሰውነታዊ ኃይል አለው።
ሰዎች ሁሉ የሚወድቁት፣ ሰዎች ሁሉ የሚሞቱት ተስፋ ሲያጡ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። በህክምናው ዓለም ብናይ እንኳን የአንድ ህመምተኛ የመዳንና የመሞት ልኬት የሚወሰነው በተስፋ ነው። ተስፋ አለው..ተስፋ የለውም ሲባል ሰምታችኋል ብዬ አስባለው። ተስፋ በመኖርና በመሞት መካከል የተሰመረ የህላዊ ድንበር ነው። በተስፋ ማጣት ውስጥ ሆነን የምናሳካው ህልም፣ የምናሳካው ራዕይ የለም። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነን የምንማረው ትምህርት፣ የምንይዘው ትዳር በአጠቃላይ የምንኖረው ህይወት ዋጋ ቢስ ነው።
ለምንም ነገር በተስፋ የተሞላ ልብና መንፈስ ያስፈልገናል። ለምንም ነገር ወደፊት ሊያስኬደን የሚችል ብርቱ መነቃቃት ግድ ይለናል። በህይወት ውስጥ በእያንዳንዱ ነገራችን ላይ ጋፍና ጸዐዳ መልኩን ይዞ ተስፋ አብሮን አለ። ዛሬ ላይ በብዙ ችግርና ማጣት የምንሰቃየው ውስጣችን ተስፋ ባለመኖሩ ነው። ወይም ደግሞ ሳንሰራና ሳንለፋ በአጉል ተስፋ በመጠበቅ ውስጥ ስለቆምን ነው እላለው።
በነገራችን ሁለት አይነት ተስፋዎች አሉ። አንደኛው የበረከት..የልዕልና ተስፋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የማጣት..የድህነትና የእኩይ ነገሮች ተስፋ ነው። አሁን ላይ ብዙዎቻችን በሁለተኛው የተስፋ ጎዳና ላይ የቆምን ነን። ሁለተኛው ተስፋ ማለትም የድህነትና የማጣት ተስፋ ያልኳችሁ ውስጣችን ምንም አይነት ራዕይና መነሳሳት ሳይኖር በስሜት..በደመነፍስ እንዲያው ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን በብዙ ልፋት የሚገኝን አንድን ነገር የእኛ እንዲሆን መጠበቅ ማለት ነው። ይሄ የተስፋ አይነት ሰዎችን ከመጉዳትና እኔ ከንቱና የማረባ ነኝ፣ ለመልካም ነገር አልተፈጠርኩም ብለን ራሳችንን እንድንጠላ ከማድረግ ባለፈ የሚጠቅመን አንዳች ነገር የለም። በዚህ የተስፋ አይነት ውስጥ መኖር ጉዳቱ ይሄ ብቻ አይደለም በህይወት ውስጥ ለብዙ ግራ መጋባትና ለብዙ ያልተገቡ እኩይ አመለካከቶች በመዳረግ አቅማችንን በመግደል ለሱስና ለመሰል አላስፈላጊ ድርጊቶች እንድንጋለጥ በር ይከፍትብናል።
ዛሬ ላይ ብዙ ህልማችን ብዙ ራዕዮቻችን የመከኑብን በዚህ የሞት ተስፋ ላይ ስለቆምን ነው። እውቀትና ጉልበት ይዘን ከንቱ ሆነን የምንኖረው በዚህ የውሸት ተስፋ ላይ ስለተደገፍን ነው። ሀገርና ህዝብ ከመጥቀም ይልቅ የወጣት ጡረተኛ ሆነን ከአያቶቻችን እጅ ላይ የምንበላው በዚህ የተነሳ ነው እላለው። በተስፋ ለመኖር እንዴት ተስፋ ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል። በነገራችን ላይ ይህ የተስፋ አይነት የሞት ተስፋም ሊባል ይችላል። በህይወታችን የመጨረሻው ክፉ ነገር ላይ የምንደርሰው በዚህ ተስፋ ውስጥ አልፈን ነው። በዚህ ተስፋ ውስጥ ለውጥ የለም፣ በዚህ ተስፋ ውስጥ ደስታ የለም። እርሱ ህይወታችን የሚባክንበት፣ ህልም ራዕያችን የሚመክንበት የውድቀት ጥግ ነው።
ብዙዎች ባለመንቃት ባለማሰብና ባለማወቅ ምርጡን የተስፋ አይነት ትተው በዚህ የሞት ተስፋ ውስጥ ይኖራሉ። አሁኑኑ ያላችሁበትን የተስፋ ሁኔታ ዞር ብላችሁ ብታዩ ጥሩ ነው እላላው። ያለዛ እየባከናችሁ ነው። ምንም ጥሩ ነገር ላትፈጥሩ የማይመጣን..የማይሆንን ነገር እየጠበቃችሁ ነው።
ሁለተኛው የተስፋ አይነት የምርጦች ተስፋ ይባላል። ምክንያቱም ምርጥ ነገር ሁሉ ለምርጥ ጭንቅላት የተቀመጠ ስለሆነ ነው የምርጦች ተስፋ ያልኩት። በዚህ የተስፋ አይነት ውስጥ ሞትና ርኩሰት የለም። በዚህ የተስፋ አይነት ውስጥ መውደቅ የለም። ብንወድቅ እንኳን እንድንነሳ የሚያስችል ኃይል ይኖረናል። በዚህ የተስፋ አይነት ውስጥ አሁን ላይ ብዙ ነገራችን ልክ እየመጣ ነው እላለሁ፡፡
ደስታችን፣ ሰላማችን እንዲሆንልን የምንፈልገው ነገር ሁሉ በዚህ የተስፋ ስርዓት ውስጥ ያለፈ ነው። በወጣትነታችን በጎ ሥራ እየሠራን ያለን ሁሉ፣ በሥራችን ስኬታማ የሆንን ሁሉ፣ በምንፈልገው ነገር ላይ ውጤታማ የሆንን ሁሉ ውስጣችን በገነባነው የለውጥ ተስፋ ላይ ስለቆምን ነው እላለው። ምርጥነት ከማሰብ ይጀምራል። የሚያስብ ጭንቅላት ተስፋ የሚያደርገው ነገር ይኖራል። በማሰብና ተስፋ በማድረግ ውስጥ ደግሞ ራዕይና ህልም እውን ይሆናል ማለት ነው።
ብዙዎቻችን ሳናስብ ተስፋ የምናደርግ ነን..ሳናስብ ተስፋ ያደረግንው ነገር ደግሞ ከመሆን ይልቅ ላለመሆን የቀረበ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ነገር ማሰብን ስለሚፈልግ ነው። ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት ማሰብ ይቀድማል። እስካሁን ድረስ የተበላሹ ህይወታዊ አጋጣሚዎች ሁሉ ካለማሰብ በቀቢጸ ተስፋ የተከወኑ ስለሆኑ ነው። ሁሌም ወደ ትልቅ ነጋችሁ..ወደምትፈልጉት የከፍታ ምዕራፍ ለመሸጋገር በማሰብ የታገዘውን ብሩሁን ተስፋ የእናንተ አድርጉ። እግር የሚራመደው በማሰብ ነው። እጅ የሚሰራው፣ አይን የሚያየው፣ ጆሮ የሚሰማው ሁሉ ነገራችን ጥቅም እየሰጠን የሚገኘው ከማሰብ ቀጥሎ ነው።
አንዳንድ ሰዎች አሉ ከቤት ይወጡና ወዴት እንደሚሄዱ የማያውቁ። የት ነው የምትሄዱት ተብለው ሲጠየቁ ወዴት እንደምሄድ አላውቀውም ዝም ብዬ ነው የምራመደው የሚሉ። ካለማሰብ ገበያ ስለሆነ ብቻ ገበያ የምንሄድ እኮ አለን። ካለማስተዋል በለው ሲባል ሰምተን በለው እያልን የምንጮኸም ሞልተናል። ካለመረዳት ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያየነውን ውሸት እውነት ነው ብለን ለሌሎች አጋርተን እናውቃለን። ህይወት ማሰብ ናት…ካለማሰብ የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ጉዳት ነው ይዘውብን የሚመጡት።
ወዴት እንደምትሄዱ ካላወቃችሁ ትልቁ ተስፋ ከእናተ ጋር አይደለም ማለት ነው ወይም ደግሞ በህይወት ውስጥ የምትለፉለት፣ ማለዳ..በየቀኑ አብዝታችሁ የምታስቡት የስኬት ጫፍ የላችሁም ማለት ነው። ትልቅ ተስፋ ውስጣቸው ያለ ሰዎች ወዴት እንደሚሄዱ የሚያውቁ ናቸው። ውሳኔያችሁን ለእግሮቻችሁ ሳይሆን ለአእምሯችሁ ተዉለት። አይኖቻችሁ መልካም እንዲያዩ፣ ጆሮዎቻችሁ መልካም እንዲሰሙ ራሳችሁን በመልካምና በሚገባ ቦታ ላይ አቁሙት። ምርጥ ነገሮች ሁሉ በምርጥ ተስፋዎች ውስጥ የተቀመጡ ናቸው። አሁን ላይ በእውቀታቸው፣ በጉልበታቸው በገንዘብና በጊዜአቸው ሀገርና ህዝብ እያገለገሉ ያሉ እነሱ በምርጥ ተስፋ ውስጥ የሚኖሩ የምርጥ ተስፋ ውጤቶች ናቸው። ትልቅነታችን ያለው በዚህ ትልቅ ተስፋ ውስጥ ነው።
ተስፋ የሌለው ትውልድ ተስፋ የሌለው ሀገርና ህዝብ የመፍጠር ኃይል አለው። ተስፋችሁ ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ከእናንተ ቀጥሎ ለሚመጣው አዲሱ ትውልድም የላቀ ዋጋ አለውና ሀገርና ህዝብን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችልን ትልቅ በጣም ትልቅ ተስፋን የእናንተ አድርጉ። በህይወት ውስጥ የብዙ ነገር መጨረሻዎች ከተስፋ ብዛትና ከተስፋ ማጣት የሚመጡ ናቸው። እንዳልኳችሁ ትላልቅ ተስፋዎች ትላልቅ ሰዎችን የመፍጠር ኃይል አለው። በትላልቅ ተስፋ የተፈጠሩ ትላልቅ ሰዎች ደግሞ በአካል በአእምሮ በስነ ልቦናና በኢኮኖሚ አቅማቸው የተገነቡ ናቸው። እኚህ ግለሰቦች ለሀገር የሚሆን ብዙ ነገር ይኖራቸዋል። በእነዚህ ግለሰቦች የተፈጠረች ሀገር ደግሞ ምን አይነት ገጽታ እንደሚኖራት ለሁላችንም ግልጽ ነገር ነው።
በትልቅ ተስፋ ውስጥ መኖር ራስን በትልቅ ሀገራዊ እውነት ውስጥ ማስቀመጥ ነው። አሁን ላይ ሀገራችን ላለችበት ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቀውሶች በእውቀትና በተስፋ የተካኑ ችግር ፈጣሪዎች ሳይሆኑ ችግር ፈቺ ዜጎች ያስፈልጋሉ። በእውቀት በስልጣኔ የሚበልጡን ሰዎች በዙሪያችን መኖራቸው የላቀ ዋጋ አለው። ከሚበልጡን ጋ ስንሆን እነሱን ለመሆን፣ የደረሱበት ለመድረስ እንበረታለን። ትንሹን ተስፋችንን ገለን ትልቁን ተስፋ ውስጣችን እንገነባለን። በዚህም ብርቱና ታታሪ በመሆን ሀገር አሻጋሪ ከሆኑት ውስጥ እንመደባለን ማለት ነው።
በእወቀትም ሆነ ተስፋ በማድረግ ከእኛ ካነሱት ጋር ስንሆን ግን ራሳችንን ከማሻሻልና ከማበርታት ይልቅ በነበርንበት እንድንቆይ እንገደዳለን። ስለዚህም በዙሪያችን በተስፋ የተለቁ በእውቀትና በጥበብ የተሻሉ ሰዎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ መሆን ይጠበቅብናል። ከሚበልጡን ሰዎች ጋር ወዳጅነትን ስንፈጥር ከነበርንበት አስተሳሰብ፣ ከነበርንበት ኋላ ቀር ህይወት የመውጣት እድሎች ይኖሩናል። ሁሌም ቢሆን ትንሹን ተስፋችንን ገለን ወደ ትልቁ ለመሄድ ጉልበትና ኃይልን የሚፈጥሩልን ሰዎች ያስፈልጉናል። ከተኛንበት የሚያነቃን ውስጣችን ትልቅ ተስፋ የለም ማለት ራሳችንን እያጣነው ነው ማለት ነው።
አሁን ካላችሁበት የህይወት ምስቅልቅል የምትወጡት በትልቅ ተስፋ ትልቅ ነገር ስትጀምሩ ነው። ከምኞት ወጥታችሁ ወደ ተጨበጠ ገሀዳዊ እውነት እንድትሸጋገሩ ልዕለ ሀያል ተስፋ ያስፈልጋችኋል። ልዕለ ሀያል ተስፋ የሚገነባው በጠንካራ የሥራ ልምድ ምንም ነገር እንደምንችልና እንደምናሳካ በማመን ስንጀምር ነው። ከሁሉም በፊት ግን ከገደላችሁና እየገደላችሁ ካለው ቀቢጸ ተስፋ ውጡ..። አንድ አይነት ሰው አትሁኑ..በመሞከርና በመለማመድ አዲስ ነገር መፍጠር እንደምትችሉም እመኑ። ብሩህ ነጋችሁ ያለው በትልቁ ተስፋችሁ ውስጥ ነው። አሁኑኑ ራሳችሁን ከነሙሉ ቀልባችሁ አግኙት። ከነሙሉ ቀልብ መገኘት ራስን በትክክለኛ ቦታ ላይ ትክክል ሆኖ ማግኘት ማለት ነው። ከነሙሉ ቀልባችን ስንገኝ ትናንሽና ውዳቂ ሀሳቦች አይፈነጩብንም። ኧረ እንዲያውም አጠገባችንም አይደርሱም።
ትልቁ ተስፋችን በህይወት ውስጥ የማይጠቅሙንን ሞታዊ መከራችንን የሚዋጋልን ጋሻና ጦራችን ነው። ከነሙሉ ቀልብ መገኘታችን ይሄን ትልቅ ተስፋችንን ወደ ውጤት ለመቀየር በምናደርገው ትግል ውስጥ ቀዳሚው መስፈርት ነው። ትልቁን ተስፋ የእኛ ስናደርግ በህይወታችን ውስጥ የተበላሹን ብዙ ነገሮች መስተካከል ይጀምራሉ። ምን ሆኜ ነው እንዲህ የኖርኩት ብለን በትላንት እስክንቆጭ ድረስ ብዙ ተዓምራቶች ይከሰቱልናል። ከመባከን ወጥተን ህይወት ምን ያክል ውብ እንደሆነች የምንረዳበት ጊዜ ይሆናል። ሀገር ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት ወደሚል ዘመነኛ እሳቤ እንሸጋገራለን። አበቃሁ። ቸር ሰንብቱ፡፡
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013