የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ከሁለት ወራት በኋላ ዘግይቶ ነው:: መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ግንቦት አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት በተወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ቀስ በቀስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥሩ እያሻቀበ ሊሄድ ችሏል:: በዚህም በሰኔ ወር ብቻ አራት ሺ 674 አዳዲስ ሰዎችን በማጥቃት አጠቃላይ በወረርሽኙ የተያዙት ሰዎች ቁጥር በአራት እጥፍ አድጎ አምስት ሺ 876 ደረሰ:: ከዚያም በአደገኛ ሁኔታ ወደፊት መገስገሱን ቀጠለና በአጭር ጊዜ ውስጥ የስርጭት አድማሱን በማስፋፋት ሐምሌ አጋማሽ ላይ ከ19 ሺህ 280 ሰዎችን በላይ ሊጨምር ችሏል::
ከሰኔ ወር በፊት በኮሮና ቫይረስ በቀን ይያዝ የነበረው የሰው ብዛት ከመቶ በታች የነበረው ከሰኔ ማለቂያና ከሐምሌ ጀምሮ ግን በአንድ ቀን ብቻ 915 ሰዎችን በመያዝ ከባዱን ዱላውን ማሳረፉን ቀጠለ:: የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ የነበረ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሐምሌ አጋማሽ ላይ 336 ደረሰ:: በአንድ ቀን የሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከአንድ ወደ ሃያ ስድስት ከፍ ብሎ ተመዘገበ::
እንዲህ እንዲህ እያለ በሚያስፈራ ሁኔታ ቫይረሱ ስርጭቱን በመቀጠል እስከ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 266 ሺህ 264 ደርሷል:: ሶስት ሺህ 996 ሰዎችንም በሞት አጥተናል:: ከአሁኑ የሆስፒታሎች አልጋ እየሞላ መሆኑም ተሰምቷል:: የችግሩን አስፈሪነት በሚሊኒየም የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሸምሰዲን ሰኢድ ከስድስት ወራት በፊት “እስካሁን ድረስ ብዙም ፍርሃት አይሰማኝም ነበር:: አሁን ግን አስፈሪው ጊዜ እየመጣ መስላል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈራሁ፤ ምክንያቱም በህክምና ማዕከላችን ውስጥ ያሉት አልጋዎች በታካሚዎች ሞልተውብናል፤ ተጨማሪ ህሙማን ለመቀበል ተቸግረናል፣ አንዳንድ ህሙማኖቻችንም ከዚህ ቀደም አይተነው በማናውቀው መልኩ በፍጥነት እየሞቱብን ነው” በማለት ገልጸዋል:: ያም ሆኖ ወረርሽኙ እንደ ሃገር በርካታ ነገሮችን እያመሰቃቀለ አስፈሪ ችግር ሆኖ ቀጥሏል::
ታዲያ በዚህ ሁሉ የጭንቅ ጉዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባቱን መጠን ለመጨመር የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ እዚሁ ከጓዳችንም የተሰማ መልካምና ተስፋ ሰጪ ዜና አለ:: ይህም ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ በተመለከተ በሳይንሳዊ ምርምር በተደገፈ መንገድ የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ቫይረሱን ለማከም የሚያስችል መድሃኒት በዝግጅት ሂደት ላይ መሆኑ በኦፊሼላዊ ደረጃ መገለጹ ነበር:: ምርምሩ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ተደጋጋሚ የምርምር ሂደት አልፎ ወደ ምርት እና ቀጣይ የእንስሳት ፍተሻ እና ክሊኒካል ፍተሻ ስራዎች እንዲሸጋገር መደረጉንም ሰምተን እጅጉን ተደስተን ነበር:: በዚህ መንገድ እየተዘጋጁ የሚገኙት ሃገር በቀል መድሃኒቶችም መሰረታዊ የምርምር ሂደት በማለፍ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግ ሂደቶችን በስኬት ማለፋቸው መገለጹም አይዘነጋም::
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያውያን የባህል ሃኪሞች ጋር እና የህክምና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን የሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንሳዊ ሂደቶች በማሳለፍ ለዘመን አመጣሹ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ወረርሽኝ ህክምና የተዘጋጀውን መድሃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላቸውን ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር:: መድሃኒቱ የመከላከል አቅም የሚጨምር፣ መርዛማነት የሌለው እና አዋጭነቱ የተረጋገጠ ነው መሆኑንም የጤና ባለሙያዎቹ አረጋግጠዋል:: የምርምር ሂደቱ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም በጉዳዩ ላይ ተሰጥቶ የነበረው መግለጫ ያመላክታል::
የምርምር ሥራው ቀጥሎ ወረርሽኙም የስርጭት አድማሱን ማስፋት በጀመረበት ወር ላይ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም “በኮሮና ቫይረስና በሌሎች ወረርሽኞች ዙሪያ አገር በቀል የባህል መድሃኒቶች ህክምና ዕውቀቶች ሊያመጡ የሚችሏቸው መፍትሔዎች” በሚል ርዕስ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ ሚኒስትሮችና የዘርፉ ምሁራን ውይይት ማካሄዳቸው ተሰማ:: በዚህም ሃምሳ ስምንት የሚሆኑ የባህል መድሃኒት ህክምና ናሙናዎች ተለይተው በቅደም ተከተል እየተሰራባቸው መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከነገረን እነሆ ወራትን አልፈን ዓመት አስቆጠርን:: በውይይቱ ወቅት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ወደ ምርምር ሂደት እንደገቡ የተገለጹት ሃምሳ ስምንት የባህል ህክምና ናሙናዎች በቅደም ተከተል ወደ ተግባር እንዲገቡ ሥራ እየተሰራባቸው ቆይቷል:: የባህል መድሃኒት ናሙናዎቹ የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ እና ሰዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ ለማከም የሚያስችሉ ተብለው በባለሙያዎች እስከመለየት ደረጃ መድረሳቸውንም ሰምተን ነበር::
የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና የሚያደርሰውንም ጉዳት ለመቀነስ የአገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም ግዴታ መሆኑንም ከተወያዮቹ መካከል አንዷ የሆኑት ዶክተር ሂሩት ካሳው አስታውቀው ነበር:: የራሷን አገር በቀል ዕውቀቶች በመጠቀም አሳሳቢውን የኮሮና ወረርሽኝ ከማከም በተጨማሪም አገሪቱ በቀጣይ በባህል መድሃኒት ህክምናዎቿ በዓለም ዙሪያ ለመታወቅ የሚያስችል ይህንንም ማድረግ እንደሚገባ ሚኒስትሯ አመላክተው ነበር:: የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት፤ በወቅቱ “በዘርፉ በቂ ዕውቀትና ሃብት እያለን አዕምሯችን በምዕራባዊ ዕውቀት ጥገኛ ማድረግ የለብንም” የሚል ጠቃሚ መልዕክት አስተላልፈው ነበር::
ይህ በእጅጉ ህዝብን የሚጠቅምና ሃገርንም ከችግር የሚታደግ ታላቅና መልካም ጅምር ነበር:: ምን ያደርጋል ነበር ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ:: ከተባለ በመቆየቱ “ነበር” ሆነ እንጂ:: ሆኖም በፍጹም በነበር ሊቀር አይገባውም:: ታዲያ እስከ መቼ ነው በእጃችን ላይ ያሉትን ሃገር በቀል መድሃኒቶቻችን ለመጠቀም የምንጠብቀው? ወይንስ ማንን ነው የምንጠብቀው? የማንንስ ይሁንታ ነው የምንፈልገው? የመከላከል አቅም የሚጨምሩ፣ መርዛማነት የሌላቸው እና አዋጭነታቸው በባለሙያ የተረጋገጡት እንኳንስ የእኛዎቹ ተፈጥሯዊ መድሃኒቶች በራሳቸው የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ጉዳት እንዳላቸው የሚገለጹት የሌሎች አገራት ክትባቶችስ ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ባለበት በእንዲህ ዓይነቱ የጭንቅ ሰዓት በ “ኢመርጀንሲ ኬዝ” ጥቅም ላይ ሲያውሉ የማንን ይሁንታ ጠየቁ? የሕዝብን ህይወት ለመታደግ ፈቃዱ የራስ ነውና! ነው ወይስ በእጃችን ላይ የራሳችን መዳኛ መንገድ እያለ በፈረንጅ ሳይንስ የተቀመመ መድሃኒት ካላገኘን በቀር እናልቃለን ማለት ነው? ደግሞም እኮ “መድሃኒቱ ላይሳካ ይችላል:: በእጃችሁ ላይ ያለውን ተጠቀሙ” ብሎናል የዓለም የጤና ድርጅት:: በእጃችን ላይ ያለው አማራጭ ደግሞ እነርሱ እንደሚሉን “እጅን መታጠብ” ብቻ አይደለም፤ አባቶቻችን ያወረሱን ከሳይንስ ያልሆነ ነገር ግን ከሳይንስም በላይ የሚበጅ፣ ከጥበብ የሆነ መድሃኒትም በእጃችን ላይ አለና እንጠቀምበት:: መድሃኒቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወይም የዓለም የጤና ድርጅት ሳይሆን የራሳችን መንግስት ፈቃድ ይስጥ፤ ልክ እንደ ዓባይ ውሃ በራስ ሃብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግምና!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2013