የታላቁን የረመዳን ወርን መጠናቀቅን ተከትሎ 1442ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ተከብሯል። ከበዓሉ ቀደም ብሎ ደግሞ በርካታ የጎዳና ላይ የአፍጥር መርሃ ግብሮች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተካሂደዋል። ለአብነት ያህል በደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባህር ዳር፣ መርሣ፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተሞች የተካሄዱት የአፍጥር መርሀ ግብሮች ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ የአፍጥር ዝግጅቶች ሕዝበ ሙስሊሙ በጋራ ዱአ (ፀሎት) ያደረገባቸውና ማዕድ የተጋራባቸው አስደናቂ መርሃ ግብሮች ከመሆናቸው ባሻገር ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞቹ / እህቶቹ ጋር ያለውን ፍቅርና ትስስር ይበልጥ ያጠናከረባቸው መድረኮች ሆነው አልፈዋል። የአፍጥር መርሃ ግብሮች ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድረስ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተሣትፎና ሚና ከፍተኛ ነበር። ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን መርሃ ግብሮቹ የሚከናወኑባቸውን ሥፍራዎች ከማጽዳት ጀምሮ ዝግጅቶቹን በማስተባበርና ጥበቃ በማድረግ አኩሪ የፍቅርና የአንድነት ተግባራትን አከናውነዋል።
ይህ የክርስቲያን ኢትዮጵያውያን አኩሪ ተግባር በመተጋገዝና በመከባበር መኖር መለያው ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨማሪ ደስታና የኩራት ምንጭ ይሆናል። በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን የቆየና ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርም ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል።
በእርግጥ በክልሎች የተከናወኑት የአፍጥር መርሃ ግብሮች የብዙ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አለማግኘታቸው የሚያስተዛዝብ ጉዳይ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ተግባራት ትርጉማቸውና ጠቀሜታቸው መልከ ብዙ በመሆኑ ሊበረታቱና የመገናኛ ብዙኃን ሽፋንም ሊያገኙም ይገባል።
መሠል ተግባራት የሕዝቡን ትስስር ከማጎልበት ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከውስጥ ከውጭም ብዙ ፈተናዎች ለተደቀኑባት ኢትዮጵያ እጅግ ትልቅ አዎንታዊ ትርጉም አላቸው። የውስጥ ኃይሎችን ተጠቅመው አገሪቱን እረፍት የነሷት የውጭ ኃይሎች የእኩይ ድርጊታቸው ዋነኛ ምክንያት / ሥሌት የኢትዮጵያውያንን ልዩነት መጠቀም ነው። ‹‹ኢትዮጵያውያን የተለያዩ፣ የማይስማሙና የተከፋፈሉ ናቸው›› በሚል ስሁት ግምት የዓላማቸው ተጋሪ የሆኑ የውስጥ ኃይሎችን በማሰለፍ አገሪቱን መበጥበጥን እንደዋነኛ አማራጭ አድርገው የሚጠቀሙበት እነዚህ ኃይሎች መሠል የአንድነት መርሃ ግብሮች (የጎዳና ላይ ኢፍጣር) ምቾት ይነሣቸዋል። እነዚህ መርሃ ግብሮች ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ለሙስሊም ወገኖቻቸው ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር የሚያሳዩባቸው ስለሆኑ ይህ የኢትዮጵያውያን ትብብርና መከባበር ጠላቶች ያሰቡትን እኩይ ተግባር ለማስፈፀም አቅም እንዲያንሳቸው ያደርጋል።
ከጎዳና ላይ የአፍጥር መርሃ ግብሮቹ መካከል የብዙዎችን ቀልብ የሣበው ማክሰኞ ዕለት፣ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍጥር ሥነ ሥርዓት ነበር። በረመዳን ፆም ማጠናቀቂያ እና በኢድ አል-ፈጥር በዓል ዋዜማ ላይ የተከናወነው ይህ የአፍጥር መርሃ ግብር፤ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና ከ15 ሺህ በላይ ሕዝብ የተሣተፈበት ሲሆን፤ የተሣታፊው ቁጥር አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። በመርሃ ግብሩ ላይ ‹‹ለሀገሬ ዘብ ነኝ…የህዳሴው ግድብ የአንድነታችን ዓርማ ነው…ያለችን ሀገር አንድ ኢትዮጵያ ነችና እንጠብቃታለን›› የሚሉ መፈክሮች ተስተጋብተውበታል።
በተግባር የታየው አንድነትና መከባበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክቶች ተላልፈውበታል። የኢትዮጵያ እሥልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ዒድሪስ በአፍጥር ዝግጅቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹… ይህ የዛሬው ተግባር ከዚህ ቀደም በአገራችን ያልተከሰተና ያልታሰበ ነገር ስለሆነ በጣም ደስ የሚል፤ መልካም የሆነ አገራዊ፣ ሕዝባዊ ዝግጅት ነው። ለአዘጋጆቹ በሕዝቡ ሥም ከፍ ያለ ምሥጋና ላቀርብላችሁ እወዳለሁ። ለመንግሥታችን፤ ለመሪዎቻችን በተለይም ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ፣
ለደህንነቶቻችን፣ ለፖሊሶቻችንና ለመከላከያዎቻችን በእናንተ ሥም ከፍ ያለ ምሥጋና ላቀርብላቸው ይገባል። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ላዘጋጁ መሪዎቻችን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ከፍ ያለ ምሥጋና አቀርባለሁ…አላህ መጨረሻውን ኸይር ያድርገው። አላህ ለአገር የሚጠቅም ያድርገው፤ አላህ ለሕዝብ የሚጠቅም ያድርገው፤ አላህ ለመንግሥት የሚጠቅም ያድርገው…
ለአንድነት፣ ለሠላም፣ ለልማት እንድንዘጋጅ አደራ እላለሁ። ከመሪዎቻችን በጎናቸው ቆመን ‹አይዟችሁ፤ በርቱ› እንድንላቸው አደራ እላለሁ…አገራዊ ምርጫውን በሠላም እንድናሣልፍ፣ እንድንከባበር፣ የበላያችንን እንድናከብርና ለበታቻችንም እንድናዝን እንድንተባበር አደራዬን አስተላልፋለሁ። አገራችን አማን፣ ሠላም ትሁልንልን…አላህ አንድነትን ይስጠን፤ እንከባበር፤ እንተባበር፤ እንመካከር፤ አላህ ወደ ልማት የምንጓዝ ያድርገን፤ አገራችን ከፍ ብላ የምትታይ ያድርግልን፤ ሕዝባችን መብቱ የተከበረ፣ የጠናና የጎለበተ ያድርግልን…›› ብለዋል።
በዕለቱ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ዝግጅቱ ያማረና የተሣካ እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ የአደባባይ ላይ የአፍጥር ሥነ ሥርዓት እንዲያከናውን ከመጀመሪያው ጀምሮ አጋርነታቸውን አሣይተዋል። ይህ የኢትዮጵያውያን ትብብር ወዳጅን አስደስቷል፤ ጠላትንም አስከፍቷል። በተለይም ‹‹ኢትዮጵያውያንን በሃይማኖት ከፋፍለን የሕዳሴውን ግድብ ሥኬት እንደናቅፋለን›› ብለው ያሰቡ አካላት እጅግ ደንግጠዋል።
እዚህ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በአፍጥር መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የተናገሩትን መጥቀስ ተገቢ ይሆናል። አቶ ጃንጥራር የአፍጥር መርሃ ግብሩ እጅግ ያማረ፣ ለሌላው ዓለም አስተማሪ የሆነና ክብረ ወሰን የሰበረ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው፤ መርሃ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን በጎ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች ምሥጋናና አድናቆት ሊቸራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ‹‹ … አገራችን ኢትዮጵያ እና መዲናችን አዲስ አበባ የብዙ እምነቶችና ብሔሮች መገኛ በመሆናቸው በቀላሉ እሣት መጫር ይቻላል ብለው የሚታትሩ ግብዞች ቢኖሩም ዓላማቸው እንደማይሳካ ግን የእምነት አባቶቻችን አሣይተዋልና ለዚህ ተግባራቸው ክብርና ምሥጋና ይገባቸዋል። የመላው ኢትዮጵያውያን ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ሁሉም እምነቶች በነፃነት የሚራመዱባት ከተማ ናት። ከተማችንን በጋራ ማበልፀግ የምንችለው ስንተሳሰብና ስንከከባበር ነው። ይህ መተሳሰባችንና መከባበራችን የሚያስቀናቸው አካላት ሀልጊዜም ይነሱብናል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብርሃን ምንጭ የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይሳካ በብሔርና በሐይማኖት ሊለያዩን ለሚፈልጉ እኩያን እኛ ኢትዮጵያውያን ሀቀኛ ወንድማማቾች መሆናችንን ልናሳያቸውና የተጀመረውን ፕሮጀክታችንን በሥኬት ልናጠናቅቅ ይገባል። በቅርቡ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት መርሃ ግብር በጋራ ስናሳካ ሐፍረታቸውን ይከናነባሉ… ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቻችን የሁላችንም ሀብቶች ናቸው፤ የሁላችንም ሐብቶች በመሆናቸው ጠብቀናቸውና አክብረናቸው ለዓለም ምሣሌነታችንን እንድናሳይ አደራ እላለሁ…›› ብለዋል።
የአፍጥር መርሃ ግብሩ ተሣታፊዎችም ኢትዮጵያውያን ሊከፋፍሏቸው ለሚመጡ አጥፊዎች ሁሉ ቦታ እንደሌላቸው በተግባር ያሳዩ በመሆናቸው ይህንን ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም ኢትዮጵያውያን፣ ሐይማኖትን ተገን አድርገው የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳዎች ለማስፈፀም የሚጥሩ አካላትን እንዲጠነቀቁና እንዲታገሉም አደራ ብለዋል። በቀጣይም ሕዝቡ አንድነቱን እና አብሮነቱን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የአገሩን ሠላምና አንድነት ሊያስጠብቅ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የአዲስ አበባውን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተከናወኑ የጎዳና ላይ የአፍጥር መርሃ ግብሮች በሠላም መጠናቀቃቸው የእሥልምና እምነትና የእምነቱ ተከታዮች ሠላምን የሚሹ መሆናቸውንና የሌሎች እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ትብብርና ሚና ምን ያህል ወሣኝ እንደነበር አሣይተዋል።
ከጎዳና ላይ የአፍጥር መርሃ ግብሮች በተጨማሪ ሐሙስ ዕለት፣ ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም፣ የተከበረው የኢድ አል-ፈጥር በዓል ይኸው የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት ሆኖ አልፏል። በተለይም በዕለቱ በአዲስ አበባ ስቴዲየም የተከናወነው የኢድ ሶላት ስግደት ሥነ ስርዓት ደማቅና ያማረ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሌሎች እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ትብብር እንደተለመደው በአርዓያነት የሚጠቀስ ነበር።
ወትሮውንም ቢሆን የረመዳን ወር በሙስሊም ኢትዮጵያውያን በጉጉት ከሚጠበቀው ባልተናነሰ መልኩ በክርስቲያን ኢትዮጵያውያንም የሚናፈቅ ታላቅ ወር እንደሆነ ምሥክር መቁጠር አያሻም። በታላቁ ወር ዕለታዊ የአፍጥር መርሃ ግብሮች ላይ ለመታደም ሰዓት የሚቆጥሩ ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ትዝታዎቻቸውንና ገጠመኞቻቸውን ሲያወሩ መስማት እጅግ ያስገርማል፤ ያስደስታልም። የፆሙ ጊዜ አልቆ የኢድ አል-ፈጥር በዓል ሲከበርም ይኸው አብሮነት ይበልጥ ጠንክሮ ይታያል።
እንግዲህ የኢትዮጵያ ጠላቶች መስበር የሚፈልጉትን ይህን አብሮነትና አንድነት ነው። አልተሳካላቸውም እንጂ ብዙ ጊዜ ሞክረውታል። ዘንድሮ አገሪቱ በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ተይዛ መገኘቷን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው የውስጥ ሠላሟን ይበልጥ በማናጋት የሕዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማደናቀፍ ታትረው እየሰሩ በሚገኙበት ወቅት የታየው የኢትዮጵያውያን አንድነት ጨርሶ ተሥፋ ያስቆርጣቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም ክፉኛ እንዳስደነገጣቸው ግን አይካድም።
በዕለቱ መላው የበዓሉ ተሳታፊዎች በአንድ ድምጽ ‹‹ግድቡ የእኔ ነው›› በማለት ኢትዮጵያውያን የህዳሴው ግድብ ባለቤት መሆናቸውን አስተጋብተዋል፤ በየትኛውም መልኩ የግድቡን ግንባታ የሚያደናቅፉ አካላትን በጽናት እንደሚታገሉም አስጠንቅቀዋል። ይህ እጅግ ትልቅ ትርጉም ያለው መልዕክት ነው! የግድቡን ሙሌት በማዘግየት ግንባታውን ለማሰናከል ላይ ታች ለሚሉ አካላት ትልቅ ዱብ’ዳ ነው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ዋናው ቁም ነገር የኢትዮጵያውያን መተባበር እንጂ ሌላው የጠላት ድንፋታና ሴራ ሁሉ እዳው ገብስ እንደሆነ ነው።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በበዓሉ ዋዜማ እና በኢድ ሶላት ስግደት ላይ ሲናገሩ ‹‹ … እኛ ማንም ሰው እንዲበደል፤ ማንም ሰው እንዲከፋ እንደማንፈልግ ሁሉ ሕዝባችንን የሚያስከፋ፤ ሠላማችንን የሚያደፈርስብን አንቀበልም…ሀብት የሌለው ሰው፤ ያላደገ አገር፤ ያላደገ ሕዝብ፤ ራሱንና አገሩን ማስከበር አይችልምና እባካችሁ አንድ ሆነን አገራችንን አንድ እናደርግ…አገር መብቷ እንዲከበር አንድነትና ሕብረት ወሣኝ ነው…የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሠርተን እናስጠነቅቃለን፤ ጠላቶቻችንን እናንበረክካለን…እኛ ሁላችንም የዓባይን ጉዳይ በአግባቡ ይዘን ልናስብበት፣ ልንጨነቅበትና ልንነጋገርበት ይገባል… እኛ ስንከባበርና ስንዋደድ አንድነታችንን ከመጠበቅ ባለፈ ጠላታችንን አሳፍረን ልማታችንን ማስቀጠል እንችላለን…›› ያሉትም ለዚሁ ነው።
ታላቁ የረመዳን ፆም ሕዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው የሚታረቅበት፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነቱንና አንድነቱን የሚያጎለብትበት እንዲሁም ከየትኛውም መጥፎ እሳቤ የሚርቅበት ታላቅ የፆም ወቅት ነው። የረመዳን ወር ከሶላት ስግደትና ከፆም ተግባራት በተጨማሪ መልካም ሥራዎች የሚፈፀሙበት ታላቅ ወር እንደሆነ የእሥልምና አሥተምህሮ ያስገነዝባል። በዘንድሮው የረመዳን ፆም እና የኢድ አል-ፈጥር በዓል ወቅት የታየው ተግባርም ይኸው አስተምህሮው የሚያዘው ታላቅ ተግባር ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጠናክሩና ጠላትን ተሥፋ የሚያስቆርጡ ጠንካራ መልዕክቶች የሚተላለፉባቸውና በጎ ተግባራት የሚታዩባቸው መሠል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።